Thursday, December 1, 2011

መጨረሻህ አይደለም


    አንድ ዕለት ትንሸ ጉድጓድ ቆፈርኩና ጉዳቴን ከዚያ አስቀመጥኩት፡፡ ስደብቀው ልረሳው እንደምችል አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ትንሽ ጉድጓድ ማደግ ጀመረ፡፡ በየእለቱ እሸፍነዋለሁ እንጂ ትቼው ልሄድ አልቻልኩም፡፡ መክፈል ያለብኝ ዋጋም እንደሆነ ታየኝ፡፡ ደስታዬ ከእኔ ርቋል ልቤም ክፉኛ አዝኗል፡፡ የማውቀው ሁሉ ሕመሜን ነው፡፡ የቆሰለው እኔነቴ ደስታን የዘበት አድርጎ ጠፈረብኝ፡፡
    በሌላ ጊዜ በጉድጓዴ ላይ ቆሜ ሳለ ወደ ሰማዩ አባቴ አለቅስ ጀመር፡፡ እንዲህም አልኩ "የፍቅር አምላክ ነህ ይሉሃል በእውነት አንተ በዚያ ካለህ ..." በእውነትም እርሱ በዚያ ስለነበር እጆቹን በዙሪያዬ ዘረጋ፡፡ ለተጎዳው ልጁ የእንባውን ጅረት በፍቅር መዳፍ አበሰ፡፡ ከዚህ ይልቅ የሚመች ምቹ ቦታ የለም፡፡ የልቤን በር ከፍቼ ጉዳቴን ሁሉ ነገርኩት፡፡ እያንዳንዱን አስነዋሪ ሥራዬን ሁሉንም እያንዳንዱን ቃል አደመጠኝ፡፡ ጥልቁን ቆፈርኩና ጉዳቴን አገኘሁት፡፡ ቆሻሻውንም ጠርጌ አስለቀኩት፡፡ ከዚያም በንጉሡ እጅ ላይ ኖረው በዚያች እለት መዳን ሆነ፡፡ የነፍሴን ጽልመት ገፎ መንፈሴን ነፃ አደረገው፤ አርነትም ወጣሁ፡፡ ጉዳቴ በነበረበት ቦታ የሆነ ደስ የሚል ነገር ማበብ ጀመረ፡፡ ከእንባዎቼና ከሕመሜ ያደረገውን ነገር ሳየው ጉዳቴን ሁሉ ለሚችለው ጌታ እርግፍ አድርጎ መተውንና መቼም ቢሆን ዳግም ችግሮቼን አለመቅበርን አስባለሁ፡፡
    በፈጸምከው ስህተት አልያም ባጋጠመህ ውድቀት መነሣት የማትችል መስሎ ተሰምቶህ ያውቃል? ዋጋ የሌለህ ተስፋህ የተሟጠጠ እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ ያልተስተካከልክስ መስሎ ተሰምቶሃል ስህተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ሕይወት ሁልጊዜም ፍትሐዊ አይደለችም፡፡ እየወቀስናቸው ባይሆንም ጥሩ ያልሆነ ሁኔታዎች ግን ይከሰታሉ፡፡ በዚህ ውስጥ መቆየትህ ደግሞ አንተን የበለጠ ሊጎዳህ ይችላል፡፡ ስህተት ከሠራህ፣ ውድቀት ካጋጠመህ ሁልጊዜም ለአንተ እንደገና እድል አለ መጨረሻህም አይደለም፡፡
    በመረጥከውም በማንኛውም ቅጽበት አዲስ ጅማሬ ሊኖርህ ይችላል፡፡ ለዚህ ነገር ውድቀት ብለን የምንጠራው መውደቅን ሳይሆን ወድቆ መቅረትን ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ችግሮች ይኖሩበታል፡፡ ግን ሰው ችግሮቹን ለመወጣት ፈጣን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ያለማቋረጥ በሕይወቱ ውስጥ በተፈጠሩት ስህተቶች ላይ ቢያተኩር እርሱ ችግር ውስጥ ነው፡፡ ረጅም ጊዜ የሚወስዱ አንዳንድ ውሳኔዎች ቢኖሩም እስከተቻለህ ድረስ ግን በስህተት ላይ ቁርጠኛ አሳብ አለመያዝን አስወግድ፡፡
    እያንዳንዱ ሰው ስህተት መሥራቱ ዓለም አቀፋዊ ሐቅ ነው፤ ማንም ፍፁም አይደለምና፡፡ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው የሚለው ደግሞ በምድር በሰማይ የታመነ ነው፡፡ ስለዚህ ስህተትህን ሊያስተካክል እና ከውድቀትህ ሊያነሣህ የሚችል የሆነ ነገር ካለ ግፋበት፡፡ እናም አስፈላጊ የሆነውን አድርግ፡፡ ሊተገበር የማይቻል ነገር ቢሆን ግን እርሳው፡፡ በአዲስ ሁኔታም ጀምር፡፡ ከሆነ ብቻ ብለህ አታስብ፡፡ ይህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት እርግጠኛው መንገድ ነውና፡፡ አሁን ልታደርግ ስለሚገባህ ነገር በርትተህ አስብ፡፡ ራስህን መቀበልና የተቀበልከውንም ማንነት ማፍቀርን ተማር፡፡ ሕይወት በመንገድህ በምታመጣቸው በእያንዳንዱ ልምድ ውስጥ ራስህን የተሻለ ለማድረግ መጣርህን አታቋርጥ፡፡   
    እጅግ የበራ የወደፊት ዘመን የተመሠረተው የትላንቱን በመርሳት ላይ ነው፡፡ ያለፉ ውድቀቶችህንና የልብ ስብራቶችህን እስካላስወገድካቸው ድረስ በሕይወት ውስጥ ወደፊት መራመድ አይቻልህም፡፡ ስለዚህ በተደናቀፍክበት ጊዜ ቶሎ ለመነሣት፣ እንደገናም ብርሃኑን ለማየት አንዲት ቅጽበት እንኳን በጸጸት ሳታባክን ወደፊት ተጓዝ፡፡ ለመጣው ሁሉ ጠንካራ፣ ለቀጣዩ ደግሞ ዝግጁ ሁን፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዳቸው ከዚህ በኋላ ለሚመጣው እንደ መሪ የተላኩ ናቸው፡፡ ያለ ዕለት ከዕለት ግጥሚያዎቻችን እና ፈተናዎቻችን ሕይወት ባዶና አንድ ዓይነት ትሆናለች፡፡ ችግሮች አብዛኛውን ጊዜ ልንማራቸው ግድ የሚሉን እውቀቶች ናቸው፡፡
    ስለዚህ ሁሉንም የሕይወት ተሞክሮዎች ደስተኝነት ከሰፈነበት አቀባበልና ከእምነት ጋር ተግባባቸው፡፡ በሚያጋጥምህ በእያንዳንዱ ችግር ውስጥ የተደበቁትን ስጦታዎች በማስተዋል ሆነህ መርምር፡፡ ሰው መሆን እንደ እንግዳ ቤት ነው፡፡ እያንዳንዱ ማለዳ አዲስ አዳራሽ ነው፡፡ ደስታ፣ ሐዘን እና ጊዜያዊ ግንዛቤዎች እንደ አልተጠበቀ ጎብኚ ሆነው ይመጣሉ፡፡ ሁሉንም በጸጋ ተቀበላቸውና ተደሰትባቸው፡፡
ከሁሉም በላይ ይህንን እውነት አክብር፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ይህን የሕይወት አስደናቂ ሥጦታ እና ዳግመኛ እድል ሰጥቶሃል፡፡ ማንም ሰው የሚናገረው ወይም የሚያደርገው ምንም ነገር አንተን የማትረባ አያደርግህም፡፡ ጌታ እንደ ማለዳ ሣር ያድስሃል፣ ምህረቱንም ትጠግባለህ፡፡ አንተ ብትደክም የወደደህ ብርቱ ነው፡፡ አንተ ብታሸልብ የሚጠብቅህ ንቁ ነው፡፡
    ምን ይሰማሃል? በሆነ በሞከርከው ነገር የተሸነፍክ እንዲሁም ዓለም በዙሪያህ እንደተናደችብህ ተሰምቶህ ያውቃል? ተመልከት፤ ይህ መጨረሻህ አይደለም፡፡ የጉዞህን መሪ፣ የዙሪያህን አጥር፣ የበላይና የበታችህ ጥላ የሆነውን ጌታ አስብ፡፡ እርሱ በዚህ ዓለም ሲመላለስ ስለ ሁላችንም የተቀበለውን መከራ እናውቃለን፡፡ እርግጠኛ ነኝ በጊዜው የደረሰበት ውርደት፣ ነቀፋ፣ ስድብና ስቅላት የመጨረሻው ነበር ብለህ እንደማታስብ፡፡ እንግዲያውስ ልንገርህ ሞቱ እንኳን መጨረሻ አልነበረም፡፡ ተነሥቷል!
   በሕይወት የሚያጋጥመን ማንኛውም ውድቀት የመጨረሻችን ለመሆኑ ማረጋገጫ አይደለም፡፡ ልብ በል ወደ መቃብር ብንወርድ እንኩን ወደ ንጉሡ ሠርግ በክብር እንነሣን፡፡ አሜን!
ስለዚህ ከተሳሳትክ አርም፣ ከወደቅክ ተነሣ እንጂ ፈጽሞ አታጉረምርም፡፡ ከተስፋ መቁረጥ ክፉ ጠላት ጠንቀቅ፡፡ ከሐቁ አትሽሽ፣ ጥፋተኛ ስትሆነ ጥፋተኝነትህን ተቀበል፡፡ ነገሮች ሲበላሹም ስህተት መቀነስ ላይ አተኩር፣ ከጥፋትህ ተምረህ ወደ ቀጣዩ ተግባር ተሻገር፣ ምክንያቱም የሕይወት ግብ ወደ ፊት መገስገስ እንጂ ክስና ሰበብ አልያም ጸጸት ላይ መቆዘም አይደለም፡፡ ያለፉ ስህተቶችህንና ውድቀቶችህን እዚያው ተዋቸው፡፡ አንድ ሕፃን ለመራመድ ሲፍጨረጨር ብናስተውል ማብቂያ የሌላቸውን ውድቀቶች እናያለን፡፡ ስኬቶቹ ግን በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ ውድቀቶቹ እንዳሉ ሆነው የማይቻል የሚመስለውን ነገር ማድረግ የቻለው ሕጻን በኃይለኛ ደስታ ውስጥ ይዋጣል፡፡ በጊዜው አቋሙን ስለ መጠበቁ እንጂ ስለ ወደቀባቸው ጊዜያት ያን ያህል ሳይጨነቅ ከደስታ ወደ ደስታ ይሸጋገራል፡፡
አንተም አታማር፣ ጊዜም አታጥፋ፡፡ ተስፋ በማድረግና ጠንክረህ በመሥራት ሕይወትህን በደስታ ሞልተሃት ኑር፡፡ እርግጥ ነው አስቸጋሪ ይሆንብናል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜም ቢሆን ሕይወትህን ስኬታማ የምታደርግበት፣ ራስህን በውብ ልጅነት የምትቀርጽበትና በውስጣዊ ሕይወትህ ያለህን ብልጽግና የምትጨምርበት መንገድ አለ፡፡ ስለዚህ ሙሉ ዓለም ቢታሰብ ለአንተ የተሻለ ቦታና ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል ማሰብህን አቁም፡፡ ስኬት የምታመራው ፈጽሞ ተስፋ ወደማይቆርጡ ሰዎች ነው፡፡ ምንም እንኳን ያልተሳኩ ነገሮችን፣ የውደቀት መጠናችንና የስህተታችን ብዛት ቢያይልም ተስፋ አትቁረጥ፡፡ “ተስፋችንን ታግሎ የሚጥል፤ መድኃኒታችንንም ረግጦ የሚሻገር ክፉ የለም፡፡”  / ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ/

2 comments:

  1. በጣም ተስፋ በቆረጥኩበት ሰአት ብሎጋችሁን ተመልክቼ
    በቃሉ ስለተጽናናሁ ደስ ብሎኛል በርቱ፡፡እግዚአብሄር ይባርካችሁ…

    ReplyDelete
  2. your blog is helpful to hopeless people. please aware it.

    ReplyDelete