ቅዳሜ ጥር
11/2005 የምሕረት ዓመት
ከእያንዳንዱ ሰው ጥረት ጀርባ ያለው ጥልቅ መሻት ደስታ እንደሆነ
ሁሉ በእግዚአብሔር አሳብ ውስጥ ያለው ከፍታም ደስታ ነው፡፡ እርሱ በሰው ታሪክ ውስጥ ያዘጋጀው ትልቁ ነገር ደስታ ነው፡፡ እግዚአብሔር
ማንንም ለሀዘን፣ ለሮሮረ፣ ለመከራና ስቃይ አልፈጠረም፡፡ ዛሬ የምናልፍበት የተበላሸ ነገር ሁሉ የሰው መበላሸት ውጤት ነው፡፡ ነገር
ግን ሰው በየዘመናቱ በራሱ መንገድ ደስታን ሲያስስ ኖሮአል፡፡ የደስታ መገኛ ሀብት እንደሆነ ያሰቡ ሰዎች ለዚህ እስከ መጋደል ኖረዋል፣
የሰላም ምንጩ እውቀት እንደሆነ ያሰቡ ወገኖችም የቻሉትን ያህል ለመጠበብ ሞክረዋል፣ ደስታ የሚገኘው ሥልጣን በመያዝ እንደሆነ የተሰማቸው
ሰዎችም ለዚህ ታምነው ኖረው አልፈዋል፡፡ ሁሉም በየተሰማራበት ተግባር ለመደሰት ዘወትር ይሻል፡፡
ደስታን ስለ መፈለግ ስናስብ የጠቢቡ ሰሎሞንን ፍለጋ እናስታውሳለን፡፡
ብዙ ሰው ዝና ቢኖረው የማይቸገር፣ ሀብት ቢኖረው የማይርበው፣ ሥልጣን ቢኖረው የማያዝን ይመስለዋል፡፡ ከእነዚህ አንዱ እንኳ ቢኖረን
እንባዎች ሁሉ ከአይኖቻችን እንደሚታበሱ እናስባለን፡፡ ዳሩ ግን ጠቢቡ ሰሎሞን እነዚህን ሁሉ ነገሮች በአንድነት ጠቅልሎ የያዘ ንጉሥ
ነበር፡፡
ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ ዝናና ጥበቡን ሰምታ፣ ብዙ ጓዝና እጅ መንሻ
ይዛ፣ ቀይ ባህርን አቋርጣ ነፍስ እስከማይቀርላት ድረስ የልቧን ሁሉ የገለጠችለት የእስራኤል ገዥ ነበር(1ነገ. 10÷1-10)፡፡
ለክብሩ የማይንበረከክና በጥበቡ የማይደመም ያልነበረለት ሰሎሞን የሕይወት ትርጉም የጠፋበት የደስታ አድራሻ ግር ያለው ሰው ነበር፡፡
መጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ ሁለትን በመንፈስ ሆነን ስናጠና ጥበበኛው እንዴት ባለ ድካምና ጥረት ውስጥ እንዳለፈ የፍለጋውንም ከንቱነት
እናስተውላለን፡፡