ማክሰኞ ታህሳስ
30/2005 የምሕረት ዓመት
አንድ
ቂመኛ ሰው “ክፉውን በመልካም እንጂ በክፉ አትቃወም” የሚለውን የፍቅር ትምህርት በመቃወም “እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል?” በማለት
ቡዳሃን (የቡድሂዝም እምነት መስራች) ጠየቀው፡፡ እርሱም ካደመጠው በኋላ “አንድ ሰው ለጓደኛው ስጦታ አዘጋጅቶ ወሰደ፡፡ ነገር
ግን ጓደኛው ስጦታውን አልቀበልህም አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ይህ ስጦታ ለማን የሚሆን ይመስልሃል?” አለው፡፡ ወጣቱም “ለዚያው ለራሱ
ነዋ!” ሲል መለሰ፡፡ ቡዳሃም “መጥፎና ጠማማ ሰው ሰማይን በምራቁ ለማበላሸት ተንጋሎ እንደሚተፋ ሰው ነው፡፡ የጠማማው ሰው ምራቅ
ተመልሶ ራሱን ያረክሰዋል እንጂ ሰማይን ማርጠብ አይችልም፡፡ ክፉም እንዲሁ በክፋቱ ሌላውን ከሚጎዳ ይልቅ ራሱን በይበልጥ ሲጎዳ
ይኖራል” በማለት ቂመኛውን ሰው አስተማረው፡፡
ከቡድሂዝም
ትምህርት መካከል የማስታውሰውንና ከክርስትና አስተምህሮ ጋር በእጅጉ አንድ የሆነውን ክፍል እንዳስታውስ ያደረገኝ በአገራችን የተለመደ
አንድ አባባል ወደ አእምሮዬ ስለመጣ ነው፡፡
“አንተም ክፉ ነበርክ ክፉ አዘዘብህ
እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ፡፡”
ይሰኛል፡፡
ሰውየው “የእጅህን ይስጥህ” የሚለው
ርግማን እንደተፈፀመበትና ተመጣጣኝ ዋጋ እንደተከፈለው ሌላኛው ወገን “እሰይ” በሚሰኝ እርካታ ውስጥ ሆኖ የተናገረው ቃል እንደሆነ
የኃይለ መለኮት ሹም ለነበሩት በዛብህ የተገጠመው ይህ ግጥም ያስረዳናል፡፡
በሰው ታሪክ ውስጥ ብርቱ ከሆኑት መሻቶች መካከል አንዱ የጣለን ተጥሎ፣
የገፋን ተገፍቶ፣ የናቀን ተንቆ፣ ያቆሰለን ቆስሎ፣ የቀማን ተነፍጎ በቁም ሳለን መመልከት ነው፡፡ ለዚህ ነው “የእገሌን ነገር ካላሳየኸኝማ
እውነት የለህማ!” በማለት ሰዎች ደፍረው እግዚአብሔርን የሚናገሩት፡፡ እግዚአብሔር ካልፈረደ ብለው እንዳሰቡ የሚያደርጉም ብዙ ናቸው፡፡
ለአንዳንዶች በዚህ ምድር ላይ የመቆየት ፍላጎት የተመሰረተው የከፋባቸው ላይ እንደ ገና ዳቦ እሳት ሲነድበት ለማየት ጭምር ነው፡፡
ወገኔ ግን ልብ ያላለው ነገር ቢኖር በሌላው ላይ እንዲሆንና እንድናየው የምንፈልገውን ፍርድ ጌታ በዛው በደል ውስጥ ሆነን ሳለ
በእኛ ላይ አለማድረጉን ነው፡፡ በከፋ ላይ ክፉ ይዘዝበት ብንል በክፋት ውስጥ ከተገኘሁ ክፉ ይዘዝብኝ እንደ ማለትም አይደል? ጌታ
ግን ይህንን አላደረገብንምና ክብር ይግባው!
አውግስጢኖስ
“ክፉ ነገር ሁሉ የደግ ነገር ጉስቁልና ነው፡፡ አንድን ነገር ክፉ ብለን የምንጠራው በውስጡ ሊኖረው የሚገባው ደግነት ስለጎደለውና
መልካሙን መሆን ስለተሳነው ነው” እንዳለ መጠኑ ይለያይ እንጂ የሰው ታሪክ በክፋት የተሞላ ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሱ
ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ዋናውና ብቸኛው ግን ሰው የእግዚአብሔር ክብር ስለጎደለው ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር የሚወደውን አንድያ ልጅ
የመላኩም ምስጢር ይኸው ነው፡፡ ኢየሱስ በሰውና በእግዚአብሔር፣ በሰውና በሰው መካከል የነበረውን የጠብ ግድግዳ እንዲሁም በሰውና
በዲያቢሎስ መካከል የነበረውን የፍቅር ጥምረት ያፈርስ ዘንድ ደግሞም ለእውነት ሊመሰክር ተወለደ (ዮሐ. 18÷37)፡፡
ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ መድኃኒት የመወለዱ ምክንያት ሕዝቡ ሁሉ በሽተኛ
(ኃጢአተኛ) መሆኑ ነው፡፡ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ ወደዚህ ዓለም የመምጣቱ ምስጢር ሕዝቡ ሁሉ ሀዘንተኛ መሆኑ ነው፡፡
ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን የምስራች የመነገሩ ዋና ነገርም ሁሉ መፍትሔ ፈላጊ መሆኑ ነው፡፡ በእርሱ የሥጋ ልደት እኛ ለመንፈስ ልደት
በቅተናል፡፡ በእርሱ ግርግም ላይ መተኛት እኛ በሰማያዊ ስፍራ ላይ ተባርከናል፡፡ በእንጀራ ቤት የሕይወት እንጀራ ተወለደ፡፡ እረኛና
የእግዚአብሔር በግ የሆነው ጌታ በእረኞችና በበጎች መሐል ተገኘ፡፡
“ቃልም ሥጋ ሆነ (ዮሐ. 1÷14)፡፡ ቤተልሔም የሰማይና የምድር
መገናኛ ሆነ፣ እግዚአብሔርና ሰው በቤተልሔም ተገናኙና ፊት ለፊት ተያዩ፡፡ ከድንግል የተወለደው ኢየሱስ በሰው ታሪክ ገብቶ አምላካዊ
ሥራውን ጀመረ፣ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ልጅ በጊዜ ውስጥ ተወለደ፡፡ በቤተልሔም የተወለደው በሰው ልብ ውስጥ ሊወለድ መጣ፣ ለተቀበሉት
ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው (ዮሐ. 1÷12)፡፡ አሁን ሰው አዳም እንዳደረገ (ዘፍ. 3÷8) ከእግዚአብሔር
ሊደበቅ አይችልም፡፡በክርስቶስ ሰብአዊ ባሕሪ በግልጥ ይታያል፡፡ ክርስቶስ ሰው በመሆኑ ምንም ተጨማሪ ክብር አላገኘም፣ በአምላክነቱ
ከነበረውም ምንም አልጠፋበትም፡፡ በእጆቹ መንቀሳቀስ የአምላክ የአምላክ ሁሉን ቻይነት፣ በሰብአዊ ልቡ ትርታ ወሰን የሌለው የእግዚአብሔር
ፍቅር፣ በዓይኖቹ ለኃጢአተኞች የማይገመተው የእግዚአብሔር ምሕረት ነበረ፡፡ እግዚአብሔር አሁን በሥጋ ተገልጦአል፣ ምስጢረ ሥጋዌ
ማለትም ይህ ነው፡፡ ጌታችን በሠራበትና በተናገረበት ጊዜ እርሱን ላዩት ለሰሙትና ለነኩት እግዚአብሔር በቅድስናው ተገለጠ (ዮሐ.
14÷9፣ 12÷45)፡፡ እግዚአብሔር ሕፃን ሆኖ ተጠቅልሎ በግርግም በተኛ ጊዜ (ሉቃ. 1÷12) ሰዎች ይህ አማኑኤል ነው፣ ይህም
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው (ማቴ. 1÷23፣ ኢሳ. 7÷14) ለማለት ቻሉ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ በመልበሱ በራሱ ላይ የወሰደው
ውርደት ምን ያህል እንደሆነ ልንገምት አንችልም፡፡ መስቀልና ግርግም ተያይዘው ይሄዳሉ” (በአባ ወ/ጊዮርጊስ ማቴዎስ፣ የጌታችን
የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ ሚያዚያ 5/1986 ዓ.ም)፡፡
የታላቋ ሮም የጠነከረ ሕግ፣ የግሪካውያን ጥበብና ፍልስፍና፣ የአይሁድ
ሃይማኖትና የሰዎች የግል ጥረት ሰውን ከክፋቱና ከጠማማ ልቡ ሊታደገው አልቻለም፡፡ ሰው ከእግዘዚአብሔር መመዘኛዎች አንፃር በአግባቡ
ሊኖር ባለመቻሉ የዘላለም አምላክ የዘላለም ልጁን ላከ፡፡ የመለኮትን የመከበር ፍላጎትና የእኛ መዳን የሚጠይቀውን ዋጋ ልክ በማሟላት
ከውርደት ጥልቀት ወደ ክብር ከፍታ ተሸጋገርን፡፡ ክፉውን በመልካም የምንቃወምበት ኃይል ያለው እንግዲህ እዚህ ውስጥ ነው፡፡ ኃጢአታችን
ለገና ዳቦ ከሚውለው የማገዶ ፍጆታ የከፋ ቅጣትን የሚያስከትል ሆኖ ሳለ ኢየሱስ የእኛን ፍርድ ተቀብሎ በጸጋው የማይገባንን አደረገልን፡፡
በክርስቶስ መወለድ ያገኘነውን በረከት ከተረዳን ልክ እንደ እናቱ ድንግል ማርያም “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ
በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች” (ሉቃ. 1÷47) ልንል አግባብ ነው፡፡
በሰው ታሪክ ውስጥ ብርቱ ከሆኑት መሻቶች መካከል አንዱ የጣለን ተጥሎ፣ የገፋን ተገፍቶ፣ የናቀን ተንቆ፣ ያቆሰለን ቆስሎ፣ የቀማን ተነፍጎ በቁም ሳለን መመልከት ነው፡፡ ለዚህ ነው “የእገሌን ነገር ካላሳየኸኝማ እውነት የለህማ!” በማለት ሰዎች ደፍረው እግዚአብሔርን የሚናገሩት፡፡ እግዚአብሔር ካልፈረደ ብለው እንዳሰቡ የሚያደርጉም ብዙ ናቸው፡፡ ለአንዳንዶች በዚህ ምድር ላይ የመቆየት ፍላጎት የተመሰረተው የከፋባቸው ላይ እንደ ገና ዳቦ እሳት ሲነድበት ለማየት ጭምር ነው፡፡
ReplyDelete