Tuesday, January 1, 2013

የእድሜ በረከት




                                                                                                                              

                                 ማክሰኞ ታህሳስ 23/2005 የምሕረት ዓመት


        እግዚአብሔርን እናመሰግነው ዘንድ ካሉን ምክንያቶች ሁሉ የላቀው ምክንያት ይመስለኛል፡፡ መቼም ሰው ነንና ስለ በላነው ምግብ እንጂ ስላላመጥንበትና ስለዋጥንበት እድሜ ለማመስገን ግንዛቤውም ሆነ ፍላጎቱ የለንም፡፡ እረ እንደውም! ለምንበላውና ለበላነው ለማመስገንም እንፈተናለን፡፡ ማን ነበሩ “ማምሻም እድሜ ነው” ያሉት፡፡ እውነታቸውን ነው ሰው ጥርሱ ያኘከውን፣ አፉ ያመላለሰውን፣ ምላሱ ያጣጣመውን በጉሮሮው የሚያወርደው እድሜው ካለው ነው፡፡ ብዙዎች በአፍና በጉሮሮ ድንበር ላይ በተፈጠረ ፍጥጫ በአይን ተሰናብተውን መቃብር ወርደዋል፡፡ አደራ! የምለውን ከምግብ አንፃር ብቻ እንዳታዩብኝ፡፡ ምክንያቱም ወሬም ያንቃል፡፡ በዚህ የተጎዱ ብዙ ናቸው፡፡ ጌታ ከዚህ ውርደት ይጠብቃችሁ፡፡
         አሁን ምን እያሰብኩ መሰላችሁ የምጽፈው ጣቶቼ በአድማ እንቢ ቢሉ (ባረገው ለምትሉ ይቅር ይበላችሁ)፣ አንደበት ለመናገር ባይታዘዝ፣ ጆሮም ቢተባበራቸው በየትኛው መንገድ እንገናኝ ነበር? መቼም የአይን ጥቅሻ ወረቀት ላይ አይሰፍር? ግን ከዚህ ሁሉ ሥጋት በላይ እድሜው ባይኖርስ? እንኳን ማውራት መሰማማት፣ እንኳን መተያየት መደባበስ፤ መተሳሰብም ሲዳላ ይሆን ነበር (እየዬ ሲዳላ ነው እንዲሉ)፡፡
         ገንዘብና ቁሳቁስ እንደ ትልቅ በረከት በሚቆጠሩበት ማኅበረሰብ መካከል እድሜን እንደ በረከት ማውራት “ከሌለህ የለህም” በሚለው አሳብ ላይ ጅሐድ እንደማወጅ ነው፡፡ መቼም ይህ ብሒል ምንጩ ስለደረቀ በዚህ አንጣላም፡፡ እስቲ አንድ ጊዜ ወንዶች ብቻ “እድሜያችሁ ስንት ነው?” . . . እሺ ጥግ ላይ ያለኸው . . . “ሴቶችን ለምን አትጠይቅም?”፡፡ እሺ እህቶችስ “እድሜያችሁ ስንት ነው?” . . . እሺ መሐል ያለሽው . . . “የእኛ እድሜና ደመወዝ አይጠየቅም”፡፡ የተቀበልነውን መካድ ሰጪውን አያሳስተውም፡፡ የሆነልንን አለመመስከራችን አድራጊውን ከክብር አያሳንሰውም፡፡ ብዙ ከተቀበለ ግን ብዙ ይጠበቅበታልና ስለ እድሜያችሁ ጌታን አክብሩት፡፡
         እየተማርን፣ እየለበስን፣ እየሠራን፣ እየበላን፣ እየወጣን እየገባን፣ በጎ ብቻ ሳይሆን ክፉም እያቀድን ያልከፈልንበት ትልቅ ሀብት እድሜ ነው፡፡ ትላንት አጥታችሁ ዛሬ ያገኛችሁ፣ ትላንት አግኝታችሁ ዛሬ ያጣችሁ፤ ትላንት ተወዳችሁ ዛሬ የተተዋችሁ፣ ትላንት ተጠልታችሁ ዛሬ የተፈቀራችሁ፣ ትላንት ተገፍታችሁ ዛሬ የተከበራችሁ፣ ትላንት ታቅፋችሁ ዛሬ የተዋረዳችሁ እድሜ ባይኖራችሁ ይህንን ፈረቃ እንዴት ታዩት ነበር? እንኳንም ኖረን ከፋን፣ እንኳንም ኖረን ተጠላን፣ እንኳንም ኖረን አጣን፣ እንኳንም ኖረን ታማን፣ እንኳንም ኖረን ተንገዳገድን፤ እንኳንም ኖራችሁ ተሰደዳችሁ፣ እንኳንም ኖራችሁ አለቀሳችሁ፣ እንኳንም ኖራችሁ ሁሉ ሆነ፡፡ “. . . . ሞቴን እመርጣለሁ” ለማን ብላችሁ? እድሜ ውድ ነው! እስኪንጠፈጠፍ ትጉ፣ እስኪሟጠጥ በርቱ፡፡ ታዲያ አደራ ሰጪውን እያመሰገናችሁ!
         አንድ ሰው ሞቶ ቀብር ሄደን መቃብሩ ሥፋራ ስንደርስ አንድ ሰው አለፍ ብሎ ቆሞ ሲቃ እየተናነቀው፣ ጎንበስ ቀና እያለ፣ እንደ መቀነት እጁን ወገቡ ላይ ጠምጥሞ ያለቅሳል፡፡ እኔም ምናልባት በሰው ሀዘን ላይ የራሱን እያዘነ ይሆን በማለት የጆሮዬን ኃይል ጨመርኩ፡፡ ብዙ ጊዜ ሀዘን ላይ ምን ይገርመኛል መሰላችሁ አባታችሁ ሞቶ ለእናታቻው የሚያለቅሱ፣ እህታችሁ ሞታ ለወንድማቸው የሚያነቡ ሰዎች (እነዚህ ሁሉ የሌሏቸውስ? ለምትሉኝ ለቅም አያታቸው)፡፡ ታዲያ እንዲህ ያሉ ሰዎች ሀዘን ቤቱን የለቅሶ ቢፌ (እንደ ምግቡ ያለ) ያስመስሉታል፡፡ አንድ ሞቶባችሁ ምን አልባት ለማረጋገጥ ቀሪዎቹን መቁጠር ይጠበቅባችኋል፡፡ ወደ ወጣቱ ስንመለስ አብዝቶ እያለቀሰ አንድ ነገር ይላል፡ -“ምን አለ ጥቂት ብትታገሽኝ፣ ምን አለ ኖረሽ በተበሳጨሁ፣ ምን አለ ቆመሽ ሳስታምምሽ በኖርኩ . . . .” ወጣቱ ከነባልንጀሮቼ አስለቀሰን፡፡ ለካ የወዳጅ ጭቅጭቁም ይናፍቃል፣ ለካ የአፍቃሪ ቁጣውም ያሳርፋል፣ ለካ የባልንጀራ ተግሳጹም አምሮት ነው . . . . በእርግጥም ያ ቀን ብዙ አስተማረን፡፡
1. እድሜ ዕድል ነው፡-  እያንዳንዱ ቀን ወደ ግባችን፣ ወደ ስኬታችን፣ ወደ መሻታችን እንደርስበት ዘንድ ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ የስጦታው ሕልውና ደግሞ በሰጭው እግዚአብሔር እጅ ላይ ነው፡፡ የእኛ ድርሻ በተሰጠን እድሜ በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡ ሞትን የሚፈራ በእድሜው ያልተጠቀመ ብቻ ነው፡፡ እድሉን ያላባከነ ሞትን በደስታ ይጋፈጣል፡፡ ሰዎች እድል እንዲሰጡን ብዙ ጊዜ ደክመናል፡፡ ብዙዎች ከስህተታቸው ለመማር፣ የበደሉትን ለመካስ እድሉን ሳያገኙ በምኞት አልፈዋል፡፡ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ነገር እንዳደረገልን ልብ በሉ! በእድሜ ባርኮናል፡፡ ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡
2. ኃላፊነት ነው፡- ኃላፊነትን ከቁሳቁስ ጋር ያያዙ እድሜያቸውን ከስረው የማይከተላቸውን ሰብስበው ያልፋሉ፡፡ በእድሜአቸው አመሻሽ ላይ ጸጸት እንደ እግር እሳት ያንገበግባቸዋል፡፡ በማይመልሱት ትላንት ይቆዝማሉ፡፡ የማይለውጡትን ያመነዥጋሉ፡፡ ዛሬ በዋዛ ላለፋቸው ነገ ኪሳራ ነው! ጌታ ለተፈጠርንለት ነገር ኖረን እንድናልፍ ይርዳን፡፡  
3. ሀብት ነው፡- በዓለም ላይ ትልቁ የሀብት ስፍራ መቃብር ነው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ሰዎች እውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ፍቅራቸውን፣ መፍትሔያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ቃላቸውንና ተግባራቸውን ሁሉንም ይዘው ከአፈር ጋር ኑሮ ይመሰርታሉ፡፡ ውጤቱ ሞት ቢሆንም ምክንያቱ ግን የእድሜ ማብቃት ነው፡፡ እድሜ ሲያበቃ ምክር የለውም፡፡ ጅምሩ እንደተጀመረ፣ ዝርክርኩ እንደተዝረከረከ፣ የጎደለው እንደጎደለ ብቻ ሁሉም ባለበት ነው፡፡ እድሜ ሀብት ነውና የሥጋቸውን እየሰጡ በነፍሳችሁ ለመጫወት ከሚከጅሉ ተጠበቁ፡፡ ኢየሩሳሌም ውስጥ የአይሁድ ሰንበት ከመግባቱ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ረቢው (መምህሩ) በከተማውና በየገበያው እየዞረ መለከት ከነፋ ገዥ ለሰጠው ብር መልስ እንኳ ሳይቀበል እየሮጠ ይሄዳል፡፡ ሻጭም እየሸጠ መለከት ከተነፋ ዕቃውን አይቀበልም፡፡ ተወዳጆች ሆይ እድሜያችሁን ዘርዝሩት!  
ከልቤ ምስጋና፡-
           አባት ሆይ እንኳንም አሰብከን፣ እንኳንም ፈጠርከን፣ እንኳንም በሰው መሐል ሰው ሆነን ተገኘን፡፡ ስምህ ይባረክ! ይህንን ቢጤያችን ሰው ሥልጣን ቢኖረው ኖሮ እንደማያደርገው እናውቃለን፡፡ ወላጅ እንኳ ልጁን የሚወልደው ነገን ስለማያውቅ ነው፡፡ አንተ ግን የዛሬ ማንነታችንን ቀድመህ እያወከው ፈጥረኸናል፡፡ የሥጋ ወላጆች በባለገ ልጃቸው ተጸጽተው በማኅፀን ሳለህ በሟሟህ ብለው ይቆጫሉ፡፡ አንተ ግን የመንፈስ አባት (አበ ነፍስ) ሁሉን ችለህ ሁሉን ተሸክመህ አለህ፡፡ ጌታ ሆይ መኖራችን በሰዎች አለመቻል ነው፡፡ ዛሬ ቢችሉ የሚጠሉን፣ ዛሬ ቢችሉ ኖሮ የሚያጠፉን፣ ዛሬ ቢችሉ ታሪካችንን የሚያበላሹ፣ ዛሬ ቢችሉ ኖሮ ካንተ የሚለዩን አድፋጮች ብዙ ናቸው፡፡ አንተ ግን መቻልህን ለማዳን አድርገኸዋል፡፡ ሰውን ወዳጅ ሆይ ጸጋህ አቁሞናልና ምሕረትህ እድሜ ሰጥቶናልና ስምህ ይቀደስ፡፡ 

2 comments:

  1. amen bechernetu yetebeken geta simu yikedes!

    ReplyDelete
  2. አንዳንድ ጊዜ ለወራት የተዘጋጀሁባቸው ልዩ ዝግጅቶች ላይ በህልሜ ሰዓት አልፎብኝ ሲዘጋ ስደርስ ነቅቼ እንኳ የቁጭት ስሜቱ ቶሎ አይበርድልኝም፡፡ ብዙ የማይደገሙ ቀናት በህይወቴ አልፈዋል፡፡ ያልተገኘሁባቸው የቅርብ ወዳጆቼ ሰርጎች ምናለ በተደገሙ አሰኝተውኛል፡፡ ያለፉ ጊዜያት እየቆጩኝም ያሉትን በአግባቡ አልጠቀምም፡፡ የጊዜያት ባለቤትንም እንደሚገባው አላመሰግንም፡፡
    ነፍስ ካወኩበት ጊዜ አንስቶ ‘‘ጊዜ ወርቅ ነው’’ ሲባል እሰማለሁ፡፡ ‘‘ጊዜ ታክሲ አይደለም’’ ብዬም አንጎራጉሬ አውቃለሁ፡፡ ግን ነገን ማየት የምችለው በርሱ ፈቃድ ብቻ መሆኑን የተረዳሁት አሁን አሁን ነው፡፡ ሌላ የበደል ቀን የሚጨምርልኝ ብሩክ አባት ስላለኝ እንደሆነ የገባኝም በቅርቡ ነው፡፡ የዛሬ ምሽት ከዋክብት በነገ ፀሐይ ተተክተው ማየት የሚቻለው በቸርነቱ ብቻ መሆኑን ያወኩት ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ነው፡፡ መኖር መብት ይመስለኝ ነበር፡፡
    ጋሽ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር በእድሜ ዘመኑ መገባደጃ ማስተላለፍ የሚፈልገው መልዕክት እንዳለ በአንድ ጋዜጠኛ ተጠይቆ እንዲህ ብሎ ነበር… “በረከታችሁን ቁጠሩ… ‘ማለዳ ከእንቅልፋችሁ ስትነቁ ተመስገን በሉ፡፡ ሞታችሁ ልታድሩ ትችሉ ነበራ’ ፤ ‘ከአልጋ ተነስታችሁ ስትቆሙ ተመስገን በሉ፡፡ በሆነ ምክንያት የአልጋ ቁራኛ ሆናችሁ ልትቀሩ ትችሉ ነበራ’……’’ እያለ ብዙ ልብ የማንላቸውን የምስጋና ርዕሶችን ዘርዝሮ ነበር፡፡ እውነት ነው እግሮቻችንም የሚታዘዙልን በሱ ፈቃድ እኮ ነው፡፡
    ብዙዎቻችን እኮ ‘‘ደግሞ ነጋ…’’ የምንል ነን፡፡ ንጋት ከሸሸው ሌሊት ጋር ሲታገሉ ስንቶች በዚያው ፀጥ እንዳሉ አናስተውልም፡፡
    ልዑል አምላክ ሆይ፡- አጥንቶቼ ሳይዋደዱ አንተን የሚያሳዝኑ ብዙ ዘግናኝ ቀናት በፊትህ እንደማሳልፍ እያወቅክ ግሩምና ድንቅ አድርገህ ፈጥረኸኛልና አመሰግንሃለሁ:: ድርጊቴም ምህረትህን አልከለከላትም፡፡ በቁጣህ ልትቀስፈኝ ይገባኝ የነበሩባቸው በርካታ ቀናት በፊትህ አልፈዋል:: ግን በእሳት ስጫወት የእሳት ቅጥር እየሆንክ በፍቅርህ ሳብከኝ፣ አባበልከኝ፤ ብዙ ዓመታትንም በእድሜዬ ላይ ጨመርክልኝ፡፡ አሁን ግን አባዬ ከዚህ በኋላ የሚኖረኝ ቀሪ እድሜዬ በፊትህ ያማረ ይሁንልኝ፡፡ ማለዳ ማለዳ በአዲስ ምስጋና፣ በአዲስ አምልኮ፣ በአዲስ ዝማሬ፣ በአዲስ ሽብሸባ፣ በአዲስ ቅኔ፣ በአዲስ ጭብጨባና በአዲስ እልልታ አዲሷን ምህረትህ ላግኛት፡፡
    ይህ በረከት የሆነው እድሜ ዘመኔ በቤትህ ይለቅ፡፡ አምላኬ ሆይ ሳላመሰግንህ ላለፉት የምህረት አመታት ሁሉ ዛሬ ይቅር በለኝ፡፡
    ለታደለማ ይህን ፅሑፍ ጀምሬ እስከምጨርስ ያለችው ጊዜም የምትታለፈው እኮ ካንተ ምህረት የተነሳ እንደሆነ ያስተውልና ያመሰግናል፡፡ ተመስገንንንንንንንንንንን

    ReplyDelete