Wednesday, February 5, 2014

ከዛፉ ውረዱ (ካለፈው የቀጠለ)


                                 Please Read in PDF: Kezafu Weredu 2
                                                                     
                           እሮብ ጥር 28 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

            ሱሰኛ መሆን ማለት፡

1. በአንድ ነገር ተጽእኖ (ባሪያ) ስር ማደር ነው፡ ሰዉ በቤተሰቡ አልያም ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ አሳዳሪዎችም አሉት፡፡ ከአንዳንዶቹ ለመፈታት ጥቂት አቅም የሚጠይቅ ሲሆን ሌሎቹ ግን በአብዛኛው ያታግላሉ፡፡ ሱስ ባሪያ ላደረገን ነገር መኖር ነው፡፡ በማያቋርጥ ድግምግሞሽ ከተሸነፍንለት ሱስ ጋር መታየት ነው፡፡ አንድ ሰው ያለ ተጨማሪ ነገር ሊከውን የሚችለውን ያለ ሱሳችን ማድረግ አለመቻልም ነው፡፡ ተጽእኖው ያየለ እንደ መሆኑ ሕይወትን እስከ መክሰር ወዳሉ ውሳኔዎች ያደርሳል፡፡ ለአመጽ ያስጨክናል፣ ለጭብጥ እፍኝ  የማይሞላውን ያደፋፍራል፡፡ ከእውነታው ጋር ሳይሆን ከምናባችን ጋር ነዋሪ ያደርገናል፡፡ ማኅበረሰቡ ትልቅ ግምት ለሚሰጣቸው ነገሮች ትኩረት ነፋጊ መሆንን ያስከትላል፡፡ በጋራ እንድንኖርባት በተሰጠችን ዓለም የራሳችንን ሌላ ዓለም እንድንፈጥርና ራሳችንን እንድናገልል እንሆናለን፡፡ ‹‹አላስችልህ አለኝ›› የምንልበት ጎጂ ነገር ካለ በእርግጥም ሱሰኛ ሆነናል ማለት ነው፡፡

        አብዛኛውን ጊዜ ሱስን ከጫት፣ ከሲጋራ፣ ከሀሺሽ፣ ከአልኮል . . ጋር ብቻ ማያያዝ የተለመደ ነው፡፡ በእርግጥ እንደነዚህ ያሉ ነገሮች በግልጥ የምናስተውላቸውና ማኅበረሰቡ ችግሩ መሐል ሆኖ ሲቃወማቸው የቆዩ ጎጂ ልምምዶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ጠንከር ያለና ቁርጥ ተቃውሞ ታይቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ እኔ እንደማስበው ለዚህ ምክንያቱ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሰዎች ራሳቸው ሱሰኛ መሆናቸው ይመስለኛል፡፡

       በሱሰኝነት ላይ የተደረጉ ጥናቶችን በተወሰነ መልኩ ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ዳሩ ግን ተግባራዊ ለመሆንና ለውጥ ለማምጣት አልታደሉም፡፡ ምናልባትም ጥናቶቹ ራሳቸው በሱሰኞች የተሠሩ ይመስሉኛል፡፡ ያልተለወጠ አይለውጥምና ቤተ መፃሕፍት ከማሞቅ ያለፈ ወደ ሞት እሳት እየተማገደ ያለውን ትውልድ ሊታደጉት አልቻሉም፡፡ ሱሰኝነት ከተለያዩ አመሎች ጋር ይዛመዳል፡፡ ጫት ማላመጥ ብቻ ሳይሆን ክፋት ማመንዠግም ሱስ ሆኖ ይታያል፡፡ ሲጋራ ማጨስ ብቻ ሳይሆን ሰው ማጨስም ከባድና ጎጂ ሱስ ነው፡፡ ‹‹አመሏ ነው›› እንደ ልባቸው እንዲኖሩ ፈቃድ የሆናቸው ብዙ ሱሰኞች አሉ፡፡ የተላመድነው ክፉ ጠባይ ካላስገበረ ያስፋሽካል፡፡   

       ሐሜት የሚያዛጋቸው፣ በወሬ የሚውጡትን ፈልገው በሰው ዙሪያ የሚያደቡ፣ እውነትን ካልሸቃቀጡ፣ ሽንገላን አላምጠው ካልዋጡ ዓይን ቦግ የማይልላቸው፣ እግር የማይራመድላቸው፣ እጅ የማይዘረጋላቸው በውስጥ መስመር ሱሰኞች ናቸው፡፡ እንደነዚህ ያሉትን መንፈስ ካልሆነ ሥጋ ልብ አይላቸውም፡፡ ሰላም ቆይተው የደንቡን ካላደረስን ሞቼ እገኛለሁ የሚሉ፣ ልብ መንሻቸውን ጎዝጉዘው፣ ወሬ አጫጭሰው፣ ክፉ ብልሃት አንጥፈው ነፍስ አጋድመው የሚተራረዱ ሱሰኞች ብዙ ናቸው፡፡ እንደ ልማዱ የጫት፣ የሲጋራ፣ የሀሺሽ፣ የአልኮል ሱስ አይሆንላቸውም፡፡ ዳሩ ግን ሕሊናቸው ብዙ ክፉ ልምምድ ያስተናግዳል፡፡ ትንኝ አጥርቶ ግመል ይውጣል፡፡ ምሰሶው ተጋድሞ ጉድፍ ይወነጅላል፡፡ እንዲህ ካለው ሱስ መንፈስ ቅዱስ ያሳርፋል፡፡  

2. በእውነታው ሳይሆን በስሜት መኖር ነው፡ ክፉ ልማድ ባሪያ ያደረገው ሰው አእምሮውን ሳይሆን ስሜቱን፤ በመንፈስ ሳይሆን ሥጋውን ለማርካት ትጉ ነው፡፡ እውነታዎችን ለመጋፈጥና የሚጠይቁትን መፍትሔ ለመከወን ከመቁረጥ ይልቅ ማፈግፈግን እንለማመዳለን፡፡ በነገሮች ላይ የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች የትክክለኛ አስተሳሰባችን ውጤት ሳይሆኑ የሱሳችን ፈርጣማ ጡንቻዎች ግፊት ውላጅ ይሆናሉ፡፡ ግብዝነትን እንለማመዳለን፡፡ ለሁኔታዎቻችን ማስመሰል የመፍትሔ አማራጭ ይሆናል፡፡

       ቃልም ተግባርም በስሜታችን የሚዘወር ሽመናን ይመስላል፡፡ ይህም እንደ ሱሳችን ዓይነት ይለያያል፡፡ ቻርልስ ባውዲሌር የተባለ ጸሐፊ ሱሰኝነትን ‹‹በምናባዊ ገነት ውስጥ መትመም ነው›› ይለዋል፡፡ ውሸት የሆነውን ነገር የእውነት ያህል ተቀብሎ ለመደሰት ራስን መስጠት፡፡ የሰው ነፍስ እውቀት፣ ስሜትና ፈቃድን በጋራ የሰለጠኑባት ዓለም ናት፡፡ እነዚህ ክፍሎች በእግዚአብሔር መንፈስ ጥላ ስር ካልሆኑ ለጥፋት ከፍተኛ ግብዓት ይሆናሉ፡፡ በተለይ ሰው በስሜት ሲሆን እውነት ያልሆነ የሚመስል፣ ኃይል የሌለው መልክ ብቻ፣ ማስተዋል የጎደለው ትጋት ስለያሚበዛ ውድቀት በደጅ ያደባል፡፡

       ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ሕብረት ማድረግ የምንችለው በመንፈስ በእውነት ስንሆን ነው፡፡ ከዚህ የሚያለፈው ግን ስሜት ነው፡፡ በነፍሳችን ውስጥ ስሜት ያለው ድርሻ ባይካድም ስሜትን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ የመንፈስ ቅዱስን መገኘት መናፈቅ መዘባበት ነው፡፡ ስሜታዊ ሰው እውነታውን ለማድረግ ይፈተናል፡፡ ምክንያቱም ስሜቱ አዚም ይሆንበታል፡፡ ከዚህ የተነሣ ከላቂውን ችላ ብሎ የጊዜው ላይ ደፋ ቀና ይላል፡፡ ሱሶች ስሜትን የማስቆጣት፣ ሚዛንን የማሳት፣ እይታን ድንግዝግዝ የማድረግ አቅም ስላላቸው ኑሮን ግብዝነት ይጠናወተዋል፡፡  

3. ብዙ ጉዳቱን ሳይሆን ጥቂት ልማቱን ማጉላት ነው፡ በሱሳቸው ስለ መጣው ትርፍ የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ በአንድ አጋጣሚ ‹‹የአበሻ አረቄ የጠጣሁ ቀን ፈተና ደፈንኩ›› ብላ የተናገረች ልጅ አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ ያ አጋጣሚ ለተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች እንድትጋለጥና ወደበለጠ ምስቅልቅል ሕይወት እንድትገባ ምክንያት ሆናት፡፡ እንደዚች ልጅ አመለካከት በጊዜው የጠጣችው መጠጥ ለውጤቷ እንደ ግፊት ኃይል  ሆኗል፡፡ የኋላ ኪሳራዋ ግን ውጤትም ሀብትም ሊመልሰው አልቻለም፡፡ በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ብዙ ጉዳቱ ሳይሆን እንደ እነርሱ አገላለጽ ጥቅም የሚሉትን ትንሽ ነገር እያዩ በተመሳሳይ አድራሻ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለተያዝንበት ነገር በጎነት በመሰከርን ቁጥር ከአስቸጋሪው ነገር ጋር የመኖር እድሜያችን እረዥም ይሆናል፡፡

        መጥፎው በአእምሮአችን ውስጥ ያለው ገጽታ አዎንታዊ ከሆነ በሱስ ተጽእኖ ስር ወድቀናል ማለት ነው፡፡  አንዳንዶች ጉዳቱን ባልተረዱበት ሁኔታ ሌሎች ደግሞ ‹‹አውቆ አበድ›› በሚያሰኝ መልኩ በሱስ ተጠምደዋል፡፡ ማደፋፈሪያና ማነቃቂያ በሚል ሰበብ ብዙ ሰብእናዎች ተበላሽተዋል፡፡ ሱስን በተመለከተ የአንዳንድ ሰዎች አመለካከት ‹‹በጎ›› ብለን የምንጠራቸውንም ነገሮች ያካትታል፡፡ እንደዚህ ያለው አተያየት ‹‹መልካሙንም ቢሆን በሱስ ልማድ አናድርገው›› የሚል ሙግት የያዘ ነው፡፡

        መጽሐፍ ቅዱስ በኃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ ይላል (2ቆሮ. 13÷5)፡፡ በሃይማኖት መኖር ክፋት የለውም፡፡ ዳሩ ግን በዚህ መልካም ውስጥም ሰው ራሱን እንዲመረምር ታዟል፡፡ ሰው መልካምነቱም ፍጹም አይደለም፡፡ ያ ቀን ደስ ስለሚላቸው ብቻ በዚያ ተመሳሳይ ቀን የሚቸሩ በሌላው ቀን ግን የማይደማቸው አሉ፡፡ ፀሐይ ለመጥለቅ ስታምጥ ልባቸውም እጃቸውም የሚፈታላቸው ከዚያች ሰዓት ውጪ ግን ጭንቅ ጭንቅ የሚላቸው አሉ፡፡ በጎውን በመንፈስ እንጂ በልማድ ስናደርገው በረከቱ አይረዳንም፡፡ ሱስ ሆኖባቸው የሚሰብኩ፣ የሚዘምሩ፣ ማህሌት የሚቆሙ . . ራሳቸውን አዝዘው ለእግዚአብሔር የሚያስገዙ አይደሉም፡፡ ቅር ቅር ስለሚላቸው፣ ቁሳዊ ትርፍን አስበው፣ የታይታ ጥማት ሰቅዞ ይዟቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ባለ አእምሮ ከልባችን ሆነን መንፈስና ኃይልን በመግለጥ ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት ያፈለሰንን አምላክ ልናገለግለው ይገባል፡፡

         መፍትሔ፡

1. ሱሰኛነትን አምኖ መቀበል፡ የችግራችን ማደፋፈሪያው ችግርነቱን አለመረዳት ነው፡፡ ብዙ ሱሰኞች እንደዚያ እንደ ሆኑ መቀበል ይቸግራቸዋል፡፡ ከእለት ተዕለት መሰረታዊ ተግባር እንደ አንዱ ስለሚቆጥሩት ልዩነቱና ጉዳቱን ልብ አይሉትም፡፡ ነገር ግን ሱስ የሆነብንን ነገር ካልሆኑት መለየትና አምኖ መቀበል ሊቀርብ ላለው መፍትሔ መታዘዝን ማሳየት ነው፡፡ በሽታውን ያልተናገረ መድኃኒት የለውም እንዲሉ ሱሰኝነት ችግር መሆኑን መቀበልና መመስከር ያሻል፡፡

2. ችግሩን እንጂ ራስን አለመውቀስ፡ በማኅበረሰባችን ዘንድ ሰው የሚጥላላውን ያህል ችግር አይጣጣልም፡፡ ሰብእና ጥንብ እርኩሱ እየወጣ ጎጂ ልምምዶች ግን የብዕር ስም ሁሉ አላቸው፡፡ ሰዎችን ማንኳሰስ ከችግሩ አይለያቸውም፡፡ እንዲያውም መደበቂያ ይሆናቸዋል፡፡ ሱሰኛ የሆኑበት ነገር ልክ አለ መሆኑን አውጁ፡፡ ለራስ ያለን ግምት ከማጣጣል አብሮዎት ያለው ክፉ ልማድ ምን ያህል የተዋረደና ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ መሆኑን መውቀሱ ማለፊያ ነው፡፡

3. በትክክል ሊረዳዎ ለሚችል ሰው ስለ ችግርዎ ያወያዩ፡ ‹‹ችግር ነው አይረባም›› ብለው የውስጥዎን ላገኙት አያባክኑ፡፡ አንዳንድ ማካፈሎች ለተጨማሪ ጉዳት ራስን ማጋለጥ፣ በየት ባገኘሁት? ለሚለን ደግሞ መረጃ ማቀበል ነው፡፡ ስለራስዎ መረጃ ሳይሆኑ የውስጥዎን ኑሮ ለትክክለኛው ሰው ያጋሩ፡፡ የእምነት አባት፣ የስነ ልቦና ባለሙያ፣ ጥብቅ ወዳጅ . . ብቻ ሳይሰስቱ ያካፍሉ፡፡ ከዚህ ችግር መውጣት ለእርስዎ ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታና ሁለንተናዊ ትርፍ በነጥብ ይዘርዝሩ፡፡ በተለይ ከዚህ በፊት እርስዎን በገጠምዎ የሱስ ችግር ውስጥ ተፈትነው ያለፉ ሰዎች ቢሆኑ ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ አቅም ይፈጥሩልዎታል፡፡

4. ለውጥ ሂደታዊ መሆኑን አይዘንጉ፡ ልተውህ ያልነውን በአሳባችን ቅጽበት ብንተወው የሁላችንም ደስታ ነው፡፡ ግን እንደ መግባቱ መውጣቱ አይቀልም፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ ለመተው መሞከር በስነ ልቦና እንደ አንድ የመፍትሔ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ኪሎ ይቅሙ ከነበረ ወደ ግማሽ ከዚያም ወደ ሩብ . . አሥር ሲጋራ ያጨሱ ከነበረ ወደ ስድስት ከዚያም ወደ ሦስት . . ከክብደት ወደ ቅለት በማምጣት ለለውጡ ተገዢ መሆን ይረዳል፡፡   

5. ባልንጀሮችን መምረጥ፡ ከሰው ልጆች ኃላፊነት አንዱ መምረጥ ነው፡፡ በፊታችን እያንዳንዱ ቀን ውሳኔያችንን በሚፈልግ መልኩ አማራጭ ይዞ ይመጣል፡፡ ክፉ ባልንጀርነቶችን ነፍሳችን አጥብቃ ልትጸየፍ ይገባታል፡፡ በእኩዮቻችን ተጽእኖ አላስፈላጊ ውሳኔዎችን ልንወስን እንችላለን፡፡ ዳሩ ግን ይህንን አላግባብነት በተረዳንበት ቅጽበት ከባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ልናጠራው ግድ ይለናል፡፡ የሰው ክፉ አሳብ አሳባችሁ፣ ጠማማ መንገድ መንገዳችሁ እንዲሆን አትፍቀዱ፡፡ እውነትን መሰረት አድርጋችሁ በትክክለኛው ሰዓትና ቦታ ‹‹እምቢ›› ማለትን ተለማመዱ፡፡ በሚያስጨክነው አለመጨከን ለጉዳት ይዳርጋል፡፡ እኛ የምናስበውን ነን እንደተባለ የአመለካከት ሚዛናችሁን ጠብቁ፡፡    

6. ተግባራዊ ሁኑ፡ ቤንጃሚን ፍራንክሊን ‹‹ብዙ ከመናገር ጥቂት ማድረግ የተሻለ ነው›› ይላል፡፡ ለሚሠራው እንጂ ለሚወራው ጊዜ አታጥፉ፡፡ በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ፣ ጉዳያችሁን በጸሎትና በምልጃ ፊቱ ማቅረብ፣ ከሸክም ሊያሳርፍ በሚችል ጌታ ፊት ራስን መጣል ይገባናል፡፡ ጆን ኦርትበርግ ‹‹The Me I Want to be›› በሚለው መጽሐፉ ‹‹The most important task of your life is not what you do, but who you become›› /በሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊው ነገር፤ የምታደርገው ሳይሆን የሆንከው አልያም ሆነህ የተገኘኸው ነው/ ይላል፡፡ ተግባርን በተመለከተ መጨከን ይጠይቃል፡፡ እንደዚህ ካለው ልምምድ ለመውጣት ብርቱ ፈቃደኝነት ማሳየትና የሚረዱንን ሰዎች መተባበር ያሻል፡፡ ክርስቲያን ሆናችሁ እንደዚህ ባሉ ሱሶች ውስጥ የሆናችሁ ወገኖቼ የመንፈሳዊ ስነ ልቦና እርዳታ ያስፈልጋችኋል፡፡  

       እንደ ማጠቃለያ፡

      አገልግሎት ምክንያት ሆኖኝ በተንቀሳቀስኩባቸው ክ/ሀገራት ከንፈራቸውን አረንጓዴ የተቀቡ፣ ድዳቸውን በአረንጓዴ የተነቀሱ፣ እግረዘቸውን ዘርግተው በማላመጥ ሥራ ላይ የተጠመዱ፣ በእጃቸው ሲጋራ ጨብጠው የጪስ አክሮባት የሚሰሩ፣ እንደ ሕፃን ልጅ በገዛ ነውራቸው የሚጫወቱ ብዙ ወጣቶችን አይቻለሁ፡፡ በተለይ አንዳንድ ቦታ ኑሮአቸውም ባህላቸውም ነው፡፡ ያንን መቃወም የእለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ እንደ መንፈግ ተቆጥሮ በእነርሱ ሕሊና ውስጥ ያስኮንናል፡፡ በዚያው ልክ ጨርቁን ጥሎ ያበደ፣ በሰንሰለት የሚውል፣ የችግረኛ ቤተ ሰዎቹ ጡረተኛ የሆነ ብዙ ወጣት ታስተውላላችሁ፡፡

       ጫትን በተመለከተ የምጣኔ ሀብት አንድ ፈርጣማ ክንድ ተደርጎ በመወሰዱ ትውልዱ የማያገናዝብ፣ ቅጠሉን ጎዝጉዞ ከተቀመጠ መድፍ ቢተኮስ የማይሞቀው እየሆነ መጥቷል፡፡ ዓለም ላይ በሲጋራ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ እንደሚሞት እየተወራ ባለበት በዚህ ሰዓት የወጣት አጫሾች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ከዚህ ችግር አንፃር የክርስትናው መፍትሔ አሁንም ደብዛዛ እንደ ሆነ ይሰማኛል፡፡ በዚህ ልምምድ ውስጥ የምናያቸው አብዛኛዎቹ ያመኑ የምንላቸው ናቸው፡፡ አገልግሎቱ ‹‹የሚወደኝ ቢኖር መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ›› የሚለው ቢቀር እንኳን ‹‹ጫቱን ጥሎ›› ጌታውን እንዲያመልክ የማድረግ ጉልበት ማጣቱ ኃይልን በሚያስታጥቅ እግዚአብሔር ፊት ያንበረክካል፡፡

       ቤተ ፍቅርን በተመለከተ ‹‹የጉብዝና ወራት›› በሚል ርእስ በቅርቡ በዚህ ድረ ገጽና በመጽሔታችን ላይ ተከታታይ ትምህርት የምንጀምር መሆኑን በትህትና እንገልፃለን፡፡ ለዚህም አመች ይሆን ዘንድ ወጣት ወገኖቻችን ፈተና የሆኑባችሁን ነገሮች በፖስታ ሳጥን ቁጥራችን 31106 አዲስ አበባ ብላችሁ ብትጽፉልን ለመፍትሔያችሁ እንተጋለን፡፡ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡


2 comments:

  1. amen kale hiwot yasemalen!

    ReplyDelete
  2. amen! Egziabher tsegawn abzito yabzalachehu!

    ReplyDelete