በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
እሮብ ነሐሴ 18 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
ማንኛውም እውነተኛ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ትክክለኛ ኅብረት ከእርሱ ዘንድ የተደረገለትን በማወቅና በማመን ይጀምራል፡፡ እንዲህ የማይጀመር መንፈሳዊ ኑሮ እግዚአብሔርን ተቀባይ ራሱን ደግሞ ሰጪ አድርጎ ይሰይማል፡፡ እግዚአብሔር በፊቱ ከምናሳያቸው ትጋቶች ሁሉ በላይ ከእርሱ ለእኛ ያደረገውን ማወቃችን በእጅጉ ደስ ያሰኘዋል፤ ክብርና ምስጋናንም ያመጣለታል፡፡ ‹‹ነገር ግን፡- የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ፤ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው፡፡›› (1 ቆሮ. 1፡30) ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ በእርሱ እንመካበት ዘንድ የተደረገ ነው፡፡
የቆሮንቶስ መልእክት መጀመሪያይቱ በቤተ፡ ክርስቲያኒቱ (ማኅበረ ምእመናን) የነበረውን መንፈሳዊ ችግር ለመፍታት እንደ መጻፉ፤ በመልእክቱ መጀመሪያ ምእራፍ መንፈስ ቅዱስ ይህንን አሳብ ማጻፉ የቀጣይ መፍትሔ አሳቦች ትልቅ መሠረት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ላይ የማይደገፍ ሰው፤ ቢያንስ አንድ ሌላ የሚደገፍበት አለው፡፡ ሰው ከምንም ነገር ነጻ ቢሆን እንኳ፤ ከራሱ ግን ነጻ አይደለም፡፡ ሕያው የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ደግሞ በሌላው
ቀርቶ በራሳችንም እንድንመካ አይፈቅድልንም፡፡ ‹‹ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም›› (ኤፌ. 2፡8) ተብሎ ተጽፎአልና፡፡
ምእራፍ አንድ፡ - በአሁኑ ዓለም የቤተ፡ ክርስቲያን መለየትና ምስክርነት፡፡
አከፋፈል፡ -
1. በጸጋው የተደረገልን፤ እንዲሁም የተሰጠን ዋስትና (1፡1-9)
2. ክርክርና መለያየት (1፡10-16)
3. የክርስቶስ መስቀልና የእግዚአብሔር ኃይል (1፡17-31)