Tuesday, February 11, 2014

ምክር፡



                         ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

       ልጄ ሆይ፤ በነገርህ ሁሉ የታመንህ ሁሉ፡፡ በአነጋገርህም ደማም ሁን፡፡ ሰውን የሚያስፈራና የሚያሳዝን ነገር ለመናገር አትድፈር፡፡ በልዝብ ምላስ ሰውን አታታል፡፡ ሰውንም ከሚያሙ ሰዎች ጋር አትደባለቅ፡፡ ልጄ ሆይ፤ ንብረትህ በልክ ይሁን፡፡ ቤተ ሰዎችም አታብዛ የቀንድ ከብትና የጋማ ከብትም በብዙ አታርባ፡፡ ላንተ የማይገባውን ነገር ከማንም ቢሆን አትቀበል፡፡ አንተም ለማንም ቢሆን የማይገባውን ነገር አትስጥ፡፡ የማታገኘውንም ነገር አትመኝ፡፡ በዓይንህ ካላየህና እርግጥ መሆኑን ካልተረዳኸው በቀር በማንም ሰው ላይ የሚወራውን ወሬ እውነት ነው ብለህ አትቀበል፡፡ ለሰውነትህ የሚያስፈልገውን ነገር ለማግኘት አስብ እንጂ ሰው የሚጠፋበትን ሰው የሚጨነቅበትን ነገር አታስብ፡፡

       ልጄ ሆይ፤ ሮጠህ ለማታመልጠው ነገር አትሽሽ፡፡ እርሱም ሞት ነው፡፡ ደጋ ብትወጣ፤ ቆላ ብትወርድ፤ ወንዝ ተሻግረህ ብትሔድ፤ በዋሻ ብትደበቅ፤ ጠመንጃና መድፍ ይዘህ ብትሰለፍ ምንም ቢሆን ከሞት ለማምለጥ አትችልም፡፡ እግዚአብሔርንም ፍራ በሥጋና በነፍስ ላይ ሥልጣን አለውና፡፡ ንጉሥንም አክብር እግዚአብሔር ሠይፍን አስታጥቆታልና፡፡ በአንተም ላይ የሹመት ሥልጣን ያላቸውን አገረ ገዢዎችን ሁሉ አክብራቸው፤ ታዘዝላቸው፡፡ አባትና እናትህን፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያስተምሩህን መምህሮችህን፤ የሀገር ሽማግሌዎችንና ባልቴቶችን ሁሉ በሚቻልህ ነገር እርዳቸው፡፡

       ልጄ ሆይ፤ ካረጀህ በኋላ እንደ ገና ተመልሼ ምነው ልጅ በሆንኩ ብለህ አትመኝ፡፡ ምንም ቢሆን አታገኘውምና፡፡ ወደፊትም ምነው በሞትኩ ብለህ አትመኝ፤ ምንም ቢሆን አይቀርልህምና፡፡
        ልጄ ሆይ፤ እገሌ ቸር ነው ይበሉኝ ብለህ ገንዘብህን ለማንም አትስጥ፡፡ ለወዳጅ ከመስጠት ለዘመድ መስጠት ይሻላል፡፡ ለጠላት ከመስጠት ለወዳጅ መስጠት ይሻላል፡፡ ከሁሉ ይልቅ ለተቸገሩ ድሆች መስጠት ይበልጣል፡፡ ለድሆች የሰጠ ሰው ብድሩን በሰማይ ያገኛል፡፡

       ልጄ ሆይ፤ ማናቸውንም ነገር ቢሆን ለመስማት እንጂ ለመናገር አትቸኩል፡፡ ከወዳጅህም ጋር በተጣላህ ጊዜ ቀድሞ በወዳጅነታችሁ ጊዜ የነገረህን ምስጢር አታውጣበት፡፡ ከወዳጅህም ጋራ አንድ ጊዜ ጠብ ከጀመርክ በኋላ፤ ምንም ብትታረቅ ሁለተኛ ምስጢርህን ለእርሱ ለመናገር አትድፈር፡፡ ቂምህንም አትርሳ፡፡ ቂምህን አትርሳ ማለቴ ከታረቅህ በኋላ ክፉ አድርግበት ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን እርሱ ሞትንና ኩነኔን የማያስብ ክፉ ሰው የሆነ እንደ ሆነ እርቅ አፍርሶ እንዳያጠፋህ ሳትዘናጋ ተጠንቅቀህ ተቀመጥ ማለቴ ነው፡፡

       ልጄ ሆይ፤ ከሚያሸንፍህ ሰው ጋር አትጣላ፡፡ ሐሰት ነገርም ይዘህ በዳኛ ፊት አትቅረብ፡፡
       ልጄ ሆይ፤ ሰው አንድ ጊዜ ከሞተ በኋላ፤ ሁለተኛ አይገኝምና ምንም ቢሆን ሰውን ለማጥፋት አታስብ፡፡ አካሉም ከተቆረጠ በኋላ ሁለተኛ እንደ ዛፍ አያቆጠቁጥምና የሰውን አካል ለማበላሸት አታስብ፡፡ በማንም ሰው ላይ አትቆጣ፡፡ ስለ ሃይማኖቱና ስለ ምግባሩም ቢሆን፤ ስለ ምግቡና ስለ ልብሱ ልዩነትም ቢሆን በማናቸውም ምክንያት ቢሆን አትቆጣ፡፡ እግዚአብሔር ለሁሉም ፀሐይን አውጥቶ፤ ዝናሙን አዝንሞ፤ ሁሉንም እንደ ጠባያቸው ያኖራቸዋልና አንተም የእግዚአብሔር ልጅ እንድትባል ሁሉንም እንደ ጠባዩ ውደደው እንጂ አትጥላው፡፡   

      ልጄ ሆይ፤ ማንም ሰው ቢሆን ባንተ ላይ የሐሰት ወሬ ሲያወራብህ የሰማህ እንደ ሆነ ታገሠው፡፡ መታገሥ ባትችል ግን ጠብህን በግልጥ አድርገውና ሰው ሁሉ ይወቀው፡፡ ጠብህን ካስታወቅህ በኋላ፤ ምንም ክፉ ወሬ ቢያስወራብህ እውነት ነው ብሎ የሚቀበለው ሰው አይገኝም፡፡ ማንንም ሰው ቢሆን በአግቦና በሽሙጥ አትናገረው፡፡ አንተንም በአግቦና በሽሙጥ ቢናገርህ ወደ ዳኛ ሔደህ አትክሰስ፡፡ ርስትና ጉልትህን የሚነቅል፤ ገንዘብህን የሚቀማ፤ ሰውነትህን የሚያጠፋ ነገር ካልመጣብህ በቀር በማናቸውም ባሉባልታ ነገር ወደ ዳኛ አትሒድ፡፡ በወዳጅህም ላይ በቶሎ አትቆጣ፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እያሳለፍህ መጨረሻውን ተመልከተው፡፡  

      ልጄ ሆይ፤ ነገርህ እረጅም አይሁን፡፡ ለማድረግም የማትችለውን ነገር አደርጋለሁ አትበል፡፡ ከጎረቤቶችህ ጋር ተስማምተህ ኑር፡፡ ልጄ ሆይ፤ ሰልፍ ለኃይለኞች፤ ሩጫም ለፈጣኖች፤ ባለጠግነትም ለሠራተኞች አይደለም፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ጊዜ ያጋጥማቸዋል፡፡ ስለዚህ ሰውን ከመመልከትና ሰውን ከመጠበቅ ጊዜን መመልከትና ጊዜን መጠበቅ ይሻላል፡፡

       ልጄ ሆይ፤ የአንበሳና የነብር የሌሎቹንም አራዊት ግርማ ከመፍራት ይልቅ፤ እግዚአብሔርን የማይፈሩ የክፉ ሰዎችን ፊት ፍራ፡፡ የዱር አራዊት ለመግደል ካልፈለጓቸው እነርሱ ፈልገው አይመጡም፡፡ ክፉ ሰዎች ግን ሰውን ፈልገው ካላጠፉ እንቅልፍ አይወስዳቸውም፡፡ ከተሳለ ጦር ይልቅ የክፉ ሰዎች ምላስ ጠልቆ ይዋጋል፡፡

       ልጄ ሆይ፤ ለሁሉ ጊዜ አለው ብሎ ሰሎሞን የተናገረውን አትርሳ፡፡ ይህንም ነገር ለማስረዳት ሌላውን ነገር ሁሉ ትቼ የጌታችንን ነገር እጽፍልሃለሁ፡፡ አይሁድ በጌታችን ላይ በቅናት የተነሡበት ገና ሲጸነስ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ እስከ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ድረስ ጌታችንን ለመግደል ያስቡና ይመክሩ ነበር፡፡ ጌታችንም በየምኩራባቸውና በቤተ መቅደሳቸው በግልጥ ሲያስተምር ነበር፡፡ ግን ጊዜው እስኪደርስ በእርሱ ላይ እጁን ያነሣበት ሰው አልነበረም፡፡

       ጊዜው በደረሰ ጊዜ ግን እውነቱን ሐሰት፤ ጽድቁን ኃጢአት፤ ብርሃኑን ጨለማ አድርገው ቢነሡ ነገሩ በቶሎ ተፈጸመላቸው፡፡ ይህም ጊዜው ስለደረሰ ነው፡፡ ጌታችንም አይሁድ ሊይዙት በመጡ ጊዜ እንደዚህ ብሎ መለሰላቸው፤ ሁል ጊዜ በመቅደስ ከእናንተ ጋር ነበርሁ፡፡ እጃችሁንም አልዘረጋችሁብኝም፡፡ ነገር ግን ይህች ጊዜያችሁ ናት፤ የጨለማውም ሥልጣን (ሉቃ. 22÷53)፡፡

      ጌታችን እንዲህ ማለቱ ማናቸውም ነገር ቢሆን በጊዜው ይፈጸማል እንጂ ከጊዜው አያልፍም ሲል ነው፡፡ ስለዚህ ጊዜን አልፋለሁ ብለህ አታስብ፤ ግን በኃጢአት የመጣውን ክፉ ጊዜ በንስሐ ለማሳለፍ ይቻላል፡፡ ልጄ ሆይ፤ እኔ ደግ ሰው ነኝና ጠላት የለብኝም ብለህ አትናገር፡፡ ጠላቶችም የሚነሡ በክፉ ሰው ላይ ብቻ አይመስልህ፡፡ ግን አንተ ደግ ሰው ሆነህ ጠላቶች ቢነሡብህ እግዚአብሔር ይረዳሃልና ምንም አትፍራ፡፡ ለጊዜው እንኳ ባይረዳህ ሊፈትንህ ነውና እግዚአብሔርን አትጠራጠር፡፡

      እግዚአብሔርን ከማይፈሩ ሰዎች ጋር ባልንጀርነት አታድርግ፡፡ በክፉ ምክራቸውም አትደባለቅ፡፡ ምንም ብትጨነቅ ሀገርህ የሚጠፋበትን ምክር አትምከር፡፡ ልጄ ሆይ፤ በሠራሁት ሥራ ትርፍ ነገር አላገኘሁም ብለህ ሥራህን አትተው፡፡ ነገር ግን ባንዱ ወገን እንቢ ቢልህ በሌላው ወገን ፈትን፡፡ ለሥራው ሁሉ ዕድል አለውና፤ እግዚአብሔር ድካምህን አይቶ ባንዱ ወገን ሳይረዳህ አይቀርም፡፡

       ልጄ ሆይ፤ ጦርነት ይመጣብኛል ብለህ አትፍራ፡፡ ጦርነት በሰው ሁሉ ላይ ይመጣል እንጂ ባንተ ብቻ አይመጣብህም፡፡ ነገር ግን ዋና ጦርነት ማለት እግዚአብሔርን በማይፈሩ፤ ንጉሥን በማያከብሩ፤ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ በሚፈልጉ ሰዎች መካከል መኖር ነውና እንደዚያ ያለውን ጦርነት ፍራ . . . ይቀጥላል!  


      /ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ለልጃቸው ለፈቃደ ሥላሴ የፃፉት ምክር/

No comments:

Post a Comment