Tuesday, February 18, 2014

ምክር፡

                                    Please Read in PDF: Miker 4

                                       
                    ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

        ልጄ ሆይ፤ ክፉ ሕልም አለምሁ ብለህ አትደንግጥ፡፡ ደግ ሕልምም አየሁ ብለህ ደስ አይበልህ፡፡ ሕልም ማለት የሰው አሳብ እንደ ሆነ እወቅ፡፡ እንኳን ሌሊት በሕልም ቀንም ባይን የታየ ነገር ሳይደረግ ይቀራል፡፡ ደግሞ ሌሊት በሕልም፤ ቀንም ባይን ያልታየ ነገር እንዲያው በድንገት ይደረጋል፡፡ እግዚአብሔር ይሁን ያለው ነገር ጊዜውን ይጠብቃል እንጂ ምንም ቢሆን ሳይሆን አይቀርም፡፡

         ልጄ ሆይ፤ አካልህና ልብስህ ዘወትር ንጹሕ ይሁን፡፡ እጅህን ለሥራ፤ ዓይንህን ለማየት፤ ጆሮህን ለመስማት ፈጣኖች አድርግ፡፡ አፍህን ግን በጠንካራ ልጓም ለጉመህ ያዝ፡፡ አረጋገጥህ በዝግታ፤ አነጋገርህ በለዘብታ ይሁን፡፡ ያልነገሩህን አትስማ፤ ያልሰጡህን አትቀበል፡፡ ያልጠየቁህን አትመልስ፡፡ ሽቅርቅር አትሁን፤ ንብረትህ ጠቅላላ ይሁን፤ ምግብህና መጠጥህ በልክ ሆኖ ያው የጠዳና የጣፈጠ ይሁን፡፡ ምግብህና መጠጥህም የሚቀርብበት ዕቃ ሁሉ ንጹሕ ይሁን፡፡ የምትተኛበት አልጋና የምትቀመጥበት ስፍራ ከእድፍና ከጉድፍ ንጹሕ ይሁን፡፡ በእውነትና በሚገባ ነገር ሁሉ ይሉኝታ አትፍራ፡፡ የምትሠራው ሥራ ሁሉ የመንግሥት ሥራ ካልሆነ በቀር ፖለቲከኛ አትሁን፡፡


         ልጄ ሆይ፤ በዚህ ዓለም ነግሦ በሥጋትና በአሳብ ከሚኖር ንጉሥ ይልቅ እግዚአብሔር የሰጠውን ዘመን ያለ ሥጋትና ያለ አሳብ የሚጨርስ ድኃ ይበልጣል፡፡

ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር የሚቀየምበት፤ ንጉሥ የሚቆጣበት፤ ሰው የሚጠፋበት ነገር ካልሆነ በቀር ያሰብኸውን ከማድረግ አትመለስ፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓለም ለሥጋህ ጥቅም፤ በወዲያኛው ዓለም ለነፍስህ ጥቅም የሚሆን ነገር ካልሆነ በቀር ለስሜ መጠሪያ ይሆናል ብለህ ሰውነትህን እጅግ አታድክም፡፡

        ልጄ ሆይ፤ ወደቅሁ ብለህ እጅግ አትዘን፤ ደግ ሰው የሆንህ እንደ ሆነ፤ ከወደቅህ በኋላ ትነሣለህና፡፡ ደግሞ ተነሣሁ ብለህ በጣም ደስ አይበልህ፡፡ ክፉ ሰው የሆንህ እንደ ሆነ ከተነሣህ በኋላ፤ ትወድቃለህና፡፡
ልጄ ሆይ፤ በሚስትህና በልጆችህ፤ በቤተሰቦችህም ላይ ጨካኝና ቁጡ አትሁን፡፡ ያለ ስርዓትም ሲኖሩ ዝም አትበላቸው፡፡ ግን አንተም ሰነፍ ትባላለህ፡፡ እነዚያም ላይ ቅጣትን ታመጣባቸዋለህ፡፡ ወረተኛም አትሁን፤ የሠራተኛም ደመወዝ አታስቀር፤ የንጉሥንም ትእዛዝ ጠብቅ፤ በቆላ አገር አትኑር፡፡ ብዙ ሥራም አትጀምር፤ ነገር ግን ልብህ የወደደውን አንዱን ብቻ አጠንክረህ ሥራ፡፡

        ልጄ ሆይ፤ ጨቅጫቃና እልከኛ ሚስት፤ ትእቢተኛና ልግመኛ አሽከር በቤትህ አታኑር፡፡ የእለት ምግብና ልብስ ካልቸገረህ በቀር ሥጋና ቅቤ ለመብላት፤ ጠጅና ጠላ ለመጠጣት፤ ጌጥ ለማጌጥ፤ ገንዘብ አትበደር፡፡ በኋለኛውም ወዳጅህ ፊት የቀድሞውን ወዳጅህን አትማው፡፡ በእኔም ጊዜ ይኸው ነው ብሎ ይታዘብሃልና፡፡

        ልጄ ሆይ፤ የዚህን ዓለም ብልጥግና ወይም ክብረት ለማግኘት እጅግ አትድከም፡፡ ይህንንም ለማግኘት እጅግ አትሩጥ፡፡ እንኳን የዚህ ዓለም ክብር የወዲያኛውም ቢሆን እግዚአብሔር ለመረጠውና ለታደለ ነው እንጂ ለሮጠ አይሆንምና፡፡

         ልጄ ሆይ፤ ክፉ ሰው ሳለ ደግ ሰው በመሞቱ፤ ሥራ የሚሠራ ሳለ ሰነፍ በመከበሩ፤ እግዚአብሔር አድሎአዊ ነው ብለህ አትናገር፡፡ በዚህም ነገር የጠለቀውን የእግዚአብሔርን ፍርድ ለመመመርመር አታስብ፡፡ ነገር ግን በማናቸውም ምክንያት ቢሆን የተሰወረውን ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ብቻ ተውለት፡፡
        ልጄ ሆይ፤ ከጌታ ጋር ሳለህ በፍጹም ልብህ አገልግለው፡፡ ትእዛዙንም ጠብቅ፡፡ በፍጹም ልብህ ለማገልገልና ትእዛዙን ለመጠበቅ የማትችል የሆንክ እንደ ሆነ ግን ተሰናብተህ ሂድ እንጂ ጌታን አታስቀይመው፡፡ ያለዚያ ጌታ ይቆጣና ይቀጣሃል፡፡ ወይም ደመወዝህን ቆርጦ ያስቀርብሃል፡፡

        ልጄ ሆይ፤ በቤተ ክህነት ለመኖር የወደድህ እንደ ሆነ መልካም ወደድህ፤ ነገር ግን ቄስ ወይም ዲያቆን ለመሆን አስብ እንጂ፤ ደብተራ ለመሆን አታስብ፡፡ ጠንቋይና አስማተኛ አትሁን፡፡ ምንም ጥንቆላ ብታበዛ፤ እግዚአብሔር ይሁን ብሎ የፈቀደውን ነገር ለማስቀረት ወይም አይሁን ብሎ የተናገረውን ነገር ለማድረግ አትችልም፡፡ ወደ ጠንቋይ ወደ አስማተኛም አትሂድ፡፡ እግዚአብሔር መልካምም ያደርግልህ እንደ ሆነ ክፉም ያደርግልህ እንደ ሆነ ጊዜው ሲደርስ ሁሉም አይቀርም፡፡

         ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር በምድር ላይ የፈጠረውን ፍጥረት በሙሉ ባይሆንም እንደተቻለህ መጠን በጥቂቱ መርምር፡፡ ፍጥረትንም በመመርመር ብዙ እውቀት ታገኛለህ፡፡ እነሆ መልካምና መጥፎ መሬት አለ፤ ከመልካምም መሬት ወርቅ፣ እንቁ፣ ብር፣ ነሐስ፣ ብረት፣ ሌላም ይህን የመሰለው ሁሉ ይገኝበታል፡፡ ደግሞ ለልብስና ለቤት ጌጥ የሚሆን ቀይና ጥቁር፣ አረንጓዴና ቢጫ፣ ነጭና ሰማያዊ፣ ቀለም ሁሉ ይገኝበታል፡፡ ቢዘሩበት ያበቅላል፤ ቢተክሉበትም ያለመልማል፡፡

        መጥፎ መሬት ግን ቢዘሩበት አያበቅልም፡፡ ቢተክሉበትም አያለመልምም፡፡ በላዩም ከሾህና ከመጥፎ ደንጊያ በቀር አይገኝበትም፡፡ ከደንጊያም ወገን ለጌጥ የሚሆን ክቡር ደንጊያ ይገኛል፡፡ ደግሞ ለግንብ ወይም ለቅጥር የሚሆን ደንጊያ አለ፡፡ ደግሞ ለማናቸውም ጉዳይ የማይሆን ደንጊያ አለ፡፡ ከሣርም ወገን ለሽቱ፣ ለጉዝጓዝም፣ ለከብት ምግብም፣ ለቤት ክዳንም የሚሆን መልካም ሣር አለ፡፡ ደግሞ ቢያሸቱት የሚገማ፤ ቢጎዘጉዙት የሚዋጋ፤ ለከብት ምግብም ቢያቀርቡት የሚረክስ፤ ለቤት ክዳንም ቢያደርጉት የሚያፈስ መጥፎ ሣር አለ፡፡

         ከወፎችም ወገን ድምጣቸው ያማረ ጠጉራቸው የለሰለሰ ይገኛል፡፡ ደግሞ ሲጮሁ እለቁ እለቁ ያሉ የሚመስሉ ጠጉራቸውም ለማየት የሚያስጠይፍ ወፎች አሉ፡፡ ከእንስሳም ወገን የኋላ እግሩን እንኳ ቢይዙት የማይራገጥ ወይም የማይዋጋ ገራም እንስሳ አለ፡፡ ደግሞ በአጠገቡ ሰው የማያስቀርብ ተራጋጭና ተዋጊ እንስሳ አለ፡፡ ከአራዊትም ወገን እንዲሁ ደግና ክፉ አይታጣም፡፡ ከመልአክትም ወገን ደግሞ ክፉ አለ፡፡ ደጉ እንደ ሚካኤል እንደ ገብርኤል፤ ክፉው እንደ ዲያቢሎስና እንደ ጭፍሮቹ፡፡ ከሰውም ወገን ደግሞ ክፉ አለ፡፡ ደጉ እንደ ኖህ፣ እንደ ኤርሚያስ፣ እንደ ዮሐንስ መጥምቅ፣ እንደ ድንግል ማርያም፣ ክፉው እንደ ቃየል፣ እንደ ዔሳው፣ እንደ ይሁዳ አስቆሮታዊ፡፡

         ከመሬትና ከደንጊያ፣ ከወፍም፣ ከእንስሳም፣ ከአራዊትም፣ ከመልአክትና ከሰውም ወገን ደግና ክፉ መኖሩ እግዚአብሔር ደግና ክፉ እያደረገ ፈጥሮት ነውን፤ ወይስ ከተፈጠረ በኋላ ከአንዱ ይልቅ ለአንዱ እያዳላ ነውን፤ ወይስ ፍጥረት ሁሉ በገዛ ራሱ ደግና ክፉ ለመሆን ይችላልን ትለኝ እንደ ሆነ፤ ይህ እጅግ የጠለቀ ጉድጓድና የረቀቀ ምስጢር ነውና እኔ መርምሬ ላውቀው አልችልም፡፡ አንተም ይህን መርምሬ አውቃለሁ ብለህ አትድከም፡፡

         ልጄ ሆይ፤ ዘመዶችህና ወዳጆችህ ጎረቤቶችህና አሽከሮችህ በጠላትነት በተነሡብህ ጊዜ በራስህና በጊዜው እዘን እንጂ በእነዚያ አትዘን፡፡ ኃጢአትህ ካልበዛ ጊዜው ካልደረሰ እንኳን ወዳጆችህ ጠላቶችህም ቢነሡ አይጎዱህም፡፡

        ልጄ ሆይ፤ ሰው ምንም ብልህና አዋቂ ቢሆን በራሱ ሥራ ብቻ ራሱን ችሎ እንዳይኖር እወቅ፡፡ ነገር ግን ሁሉም በየሥራው ጸንቶ እርስ በርሱ በሥራ ይፈላለጋል፡፡ ስለዚህ ሰውን ሁሉ አክብረህ ኑር እንጂ ሰውን አትናቅ፡፡ ሥራውንም አትንቀፍ፡፡ ገበሬውን አትንቀፍ፤ ከነቀፍኸውም እህሉንና አታክልቱን ከእርሱ አትፈልግ፡፡ ነጋዴውን አትንቀፍ፤ ከነቀፍኸውም ሐሩን፣ ምንጣፉን ሌላውንም የንግድ እቃ ከእርሱ አትፈልግ፡፡ . . . ይቀጥላል!


            /ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ለልጃቸው ለፈቃደ ሥላሴ የፃፉት ምክር/

No comments:

Post a Comment