Sunday, February 9, 2014

ምክር፡

                                   Please Read in PDF: Miker 2                                 
                                 
                           እሁድ የካቲት 2 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት


       ልጄ ሆይ፤ ይህ ዓለም ቀድሞ ከወዴት መጣ ኋላስ ወዴት ይሄዳል ብለህ ለመመርመር አትጨነቅ፡፡ እንኳን የዓለምን ነገር የራስህንም ነገር መርምረህ ለማወቅ አትችልም፡፡ አሳብህም ሁሉ ለዛሬ ብቻ ይሁን እንጂ ላለፈው ቀን ለትናቱ፤ ወይም ለሚመጣው ቀን ለነገ አታስብ፡፡

      ልጄ ሆይ፤ ወዳጅ ማለት ሰው አይምሰልህ፡፡ ነገር ግን ወዳጅ ማለት ጊዜ ነውና በጊዜህ ሁሉ ይወድሃል፤ አለጊዜህ ግን ወዳጅህ እንኳ ይጠላሃል፡፡ ጊዜ ማለትም ቀንና ሌሊት አይምሰልህ፡፡ ነገር ግን ጊዜ ማለት የእግዚአብሔር አሳብ የሚፈጸምበት ነው፡፡ ስለዚህ በሆነውም በሚሆነውም ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን እያልህ ተቀመጥ፡፡

      ልጄ ሆይ፤ ብዙ ተድላና ደስታ ለማድረግ አትጨነቅ፤ ይህንን ለማድረግ የፈለግህ እንደ ሆነ ግን ለሰው መራራትና ደግነትን አታገኛቸውም፡፡ ስለዚህ ተድላና ደስታህ በልክ ይሁን፤ እድሜህንም ያለ ሀዘንና ያለ መከራ በደስታ ብቻ ለመጨረስ አይሆንልህም፡፡ ነገር ግን ሀዘንና ደስታ ከባሕርይህ ጋር ባንድነት ተዋህደው የሚኖሩ ናቸውና በእድሜህ ሙሉ ሁለቱንም በየተራ ታገኛቸዋለህ፤ ካልሞትህም በቀር ከኀዘንና ኃጢአት ከመሥራት አትድንም፡፡

      ልጄ ሆይ፤ መቅሰፍት ይመጣብኛል ብለህ አትጨነቅ፡፡ ትልቅ መቅሠፍት ማለት አሳብ ማብዛት ነው፡፡ ልጄ ሆይ፤ የሰውን ነገር ችሎ ለማይኖርና አሳብ ለሚያበዛ ከኃጢአቱም ለማይመለስ ሰው ቶሎ መሞት ይሻለዋል፡፡

      ልጄ ሆይ፤ ደጉን ሰው ለማጥፋት አታስብ፤ ደጉን ሰው ለማጥፋት ብታስብ ግን ራስህን ጨምረህ ታጠፋለህ፡፡ ለሌላ ሰውም የክፋትን መንገድ አታስተምር፡፡ ፈጣሪህም እግዚአብሔር እንደ ሆነ እመን፡፡ ነገር ግን የእርሱን መጀመሪያና መጨረሻ መርምሬ አገኘዋለሁ ብለህ አትጨነቅ፡፡

      ልጄ ሆይ፤ ሰው ባጭሩም ቢሆን በረጅሙም ቢሆን፤ በዚያው በዘመኑ ለራሱ ደስ ብሎት ካልኖረ፤ ከእርሱ በኋላ ለሚነሡት ለልጆቹ ወይም ለዘመዶቹ ገንዘብ ቢሰበስብ ምንም ትርፍ የለውም፡፡ ሰው ሁሉ እርሱ ከሞተ በኋላ በሰማይ በሚያገኘው ነገር ደስ ይለዋል እንጂ ደክሞ ሰብስቦ በዚህ ዓለም በተወው ገንዘብ ደስታ የለውም፡፡

      ልጄ ሆይ፤ ለንስሐ ዕድሜ ስጠኝ ብሎ መለመን ደግነት ወይም ክርስቲያንነት አይምሰልህ፡፡ ነገር ግን ለንስሐ እድሜ ስጠኝ ብሎ መለመን በሕፃንነቴ ወራት እንደ ልቤ ኃጢአትን ሁሉ ስሠራ ኖሬ ስሸመግልና ኃጢአትን ለመሥራት ጉልበቴ ሲደክም ያን ጊዜ ንስሐ እገባለሁ ማለት ነው፡፡ ትርጓሜውንም ገልጬ ብነግርህ ለንስሐ እድሜ ስጠኝ ብሎ መለመን የዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ፍትወትንም ሁሉ ሳልጠግበው አትግደለኝ ማለት ነው፡፡

      ልጄ ሆይ፤ አንተ ግን ከሚስትህና ከልጆችህ፤ ከዘመዶችህና ከወዳጆችህ ጋር በዚህ ዓለም ደስ ብሎህ እንድትኖር ዕድሜ ስጠኝ ብለህ ለምን እንጂ፤ ለንስሐ እድሜ ስጠኝ ብለህ አትለምን፡፡ ሲሸመግሉና ሲደክሙም ኃጢአት መሥራትን መተው የሚያጸድቅ አይምሰልህ፡፡ ሰውም ተወልዶ እስኪሞት ድረስ ምንም ቢሆን ከኃጢአት ንጹሕ ሆኖ አይገኝምና በየጊዜው ንስሐ ግባ እንጂ፤ ለንስሐ የሽምግልና ጊዜ ብቻ አትጠብቅ፡፡

      ልጄ ሆይ፤ ጠላትህ ሲሞት ወይም ሌላ መከራና ጭንቀት ሲያገኘው ደስ አይበልህ፡፡ እርሱ ሞቶ አንተ በዚህ ዓለም አትቀርምና አንተ ደግሞ በሠራኸው ሥራ እንደ እርሱ መከራና ጭንቀት ሳያገኝህ አይቀርም፤ በመከራና በሞትም የሰው ሁሉ ድርሻው ትክክል እንደ ሆነ እወቅ፡፡

      ልጄ ሆይ፤ ነውርህን ለብቻህ የሚነግርህ ሰውን አትጥላው፤ አንተም በወዳጅህ ላይ ነውር የሚሆን ነገር ያየህበት እንደ ሆነ ለብቻው አድርገህ ንገረው፡፡ ለሌላ ሰው ግን አትንገርበት፡፡

      ልጄ ሆይ፤ በየጊዜው በሰውነትህ ውስጥ የሚነሣውን አሳብ ደግና ክፉ መሆኑን ሳትመረምር ያሰብኸውን ሁሉ ለመፈጸም አትቸኩል፡፡ በዚህም ዓለም እግዚአብሔር የሚሰጠን በረከት ሁሉ እጅግ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከስጦታው ሁሉ ሚስትና ልጆች መስጠቱ እንዲበልጥ እወቅ፡፡

      ልጄ ሆይ፤ አንተ ራስህ የምትጠቀምበት ወይም ወዳጅህ የሚጠቀምበት ነገር ካልሆነ በቀር ሰው እንዲያመሰግንህ ብለህ ሰውነትህን አታድክም፡፡ ሰውም በከንቱ ቢያመሰግንህ ደስ አይበልህ፡፡ አመስጋኙም ተመስጋኙም ሁለቱም ይሞታሉና ደስ አይበልህ . . . ይቀጥላል!


     /ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ለልጃቸው ለፈቃደ ሥላሴ የፃፉት ምክር/

1 comment:

  1. How he was blessed,he was a light in
    that darkness,how he became that kind of person in that century,I am
    speechless and un thinkable for his age and his century,even it's hard to
    find this kind of person in our generation it's amazing.be blessed.

    ReplyDelete