Friday, February 7, 2014

ምክር፡

                         አርብ ጥር 30 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

       ‹‹የተወደድህ ልጄ ሆይ፤ ሰው ሁሉ በዚህ ዓለም የሚኖርበት ዘመኑ እጅግ አጭር ነው፡፡ ከዚያም የሚበዛው በመከራና በሀዘን ይፈጸማል፡፡ ይህንንም መከራና ሀዘን አንዳንድ ሰዎች በገዛ እጃቸው ፈልገው ያመጡታል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ሳያስቡት በድንገት ይመጣባቸዋል፡፡ መከራና ሀዘን በገዛ እጃቸው ፈልገው የሚያመጡ እንዴት ያሉ ሰዎች ናቸው ትለኝ እንደ ሆነ ስማኝ ልንገርህ፡፡

       አንዳንድ ሰዎች የሰው ገንዘብ ሊሰርቁ ሄደው እዚያው ይሞታሉ ወይም ተይዘው ይቀጣሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሰው ሚስት ለመቀማት ሄደው እዚያው ላይ ይሞታሉ ወይም ይቆስላሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሰውን ለማጥፋት የሐሰት ነገር ይዘው ይነሡና ባወጡት ዳኛ በቆጠሩት ምስክር ተረተው ይቀጣሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሰው ማኅተም አስመስለው ቀርጸው አትመው በውስጡም የሐሰት ቃል ጽፈው ይገኙና ይቀጣሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች አይታወቅብንም አይሰማብንም ብለው ንጉሥ ለመግደል  መንግሥት ለማጥፋት ሲመክሩ ይገኛሉና ብርቱ ቅጣት ይቀጣሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለኩራትና ለትእቢት ብለው አንበሳና ዝሆን ለመግደል በረሃ ይወርዱና በበረሃ በሽታ ይሞታሉ ወይም ያው ለመግደል የፈለጉት አውሬ ይገድላቸዋል፡፡

       እነዚህን የመሰሉ በገዛ እጃቸው መከራንና ኀዘንን በራሳቸው የሚያመጡ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ደግሞ ሳያስቡት በድንገት መከራና ኀዘን የሚመጣባቸው እንዴት ያሉ ሰዎች ናቸው ትለኝ እንደ ሆነ ስማኝ ልንገርህ፡፡


       አንዳንድ ሰዎች መሬታቸውን ሲያርሱ ሲዘሩ ከርመው አዝመራቸውን በረዶ የሚመታባቸው፤ አንበጣ የሚበላባቸው ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሲነግዱ ከርመው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በበረሃ ወምበዴ የሚነሣባቸው፤ በባህር መርከብ የሚሰበርባቸው ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በንግድም በእርሻም ቢሆን ወይም በማናቸውም ሥራ ቢሆን የሰበሰቡትን ገንዘብ እሳት የሚያቃጥልባቸው፤ ሌባ የሚሰርቅባቸው፤ ዘራፊ የሚዘርፍባቸው ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ባልሠሩት ሥራ ይከሰሱና ቆሞ የሚሟገት ጠበቃ፣ ተቀምጦ የሚፈርድ ዳኛ ያጡና የሚታሠሩ ወይም ገንዘብ የሚከፍሉ ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የወለዱት የማያድግ፤ የዘሩት የማይበቅል፤ ያረቡት የማይረባ የሆነባቸው ናቸው፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሳያስቡት በድንገት መከራና ኀዘን የሚመጣባቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡

       ልጄ ሆይ ፈቃደ ሥላሴ፤ አሳብ አታብዛ፤ ወደ ፊትም ምን ነገር ይመጣ ይሆን ብለህ አትጨነቅ፤ ምንም አሳብና ጭንቀት ብታበዛ የሚሆን ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወደ ፊትም እሾማለሁ፤ እሸለማለሁ፤ ብለህ በአሳብህ ደስ አይበልህ፡፡ ለሰውም አትናገር፤ ምናልባት ከተናገርህ በኋላ ሳታገኘው የቀረህ እንደ ሆነ ታላቅ ኀፍረት ይሆንብሃልና፡፡ ወደ ፊት የሚያናድድ ሥራ አትሥራ፡፡ በገዛ እጅህ በሠራኸውና ባለፈው ሥራ አትናደድ፡፡ ልጄ ሆይ፤ ጌታ ለመሆን ትፈልግ እንደ ሆነ ጌትነት ማለት ያለ አሳብና ያለ ጭንቀት መኖር ነው፡፡ አሳብህም ሁሉ ከሞትህ በኋላ ወዲያኛው ዓለም ስለሚሆነው ስለ ነፍስህ ነገር ይሁን እንጂ በዚህ ዓለም በሥጋህ ስለሚሆነው ነገር እጅግ አትጨነቅ፡፡

       ልጄ ሆይ፤ የሆነውን ነገር ተናገር እንጂ ገና የሚሆነውን ነገር አትናገር፡፡ ሌሎችም ሰዎች ገና የሚሆነውን ነገር ቢነግሩህ አትመናቸው፡፡ ክፉ የሚሠራ እንዲጎዳ ደግ የሚሠራ ግን እንዲጠቀም የታወቀ ነውና፤ ደግ ሥራ እየሠራህ ብቻ ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ጠብቅ፡፡ ነገር ሁሉ ጊዜው ሲደርስ በግድ ይፈጸማል እንጂ ጊዜው ሳይደርስ አይፈጸምምና ለማናቸውም ነገር ቢሆን አትቸኩል፡፡

       ልጄ ሆይ፤ ወደ ፊት እንደዚህ ያለ መከራ ያገኘኛል ብለህ አትጨነቅ፤ ነገር ሁሉ የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና እርሱ በፈቃዱ ያመጣው አይቀርልህም፤ ያለ እርሱ ፈቃድ የሚመጣው አያገኝህም፤ እነሆ ይህንንም በምሳሌ አስረዳሃለሁ፡፡ ከገደል አፋፍ በሚወጣ ምንጭ ላይ አፈር ወይም ጉድፍ ቢጨምሩበት ምንጩ በውስጥ እየገፋ ውኃው እየጠራ ይወርዳል እንጂ አይደፈርስም፡፡ እንደዚሁ ሁሉ የውስጥህን የሚያውቅ እግዚአብሔር ካልፈረደብህ ንብረትህ እየሰፋ፤ ጠላትህ እየጠፋ ይሔዳል እንጂ፤ ምንም ክፉ ነገር አይመጣብህምና አትጨነቅ፡፡

        ደግሞ በኩሬ ውኃ ወይም በጉድጓድ ውኃ ውስጥ አፈር ወይም ጉድፍ ቢጨምሩበት የውኃው ሽታ እየተለወጠ ውኃው እየደረቀ ይሄዳል እንጂ ውኃው ጥሩ አይሆንም፡፡ እንደዚሁ ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ የመጣውን መከራ በጉልበቴ ወይም በእውቀቴ አስቀረዋለሁ ብሎ መጣጣር በመከራ ላይ መከራ ለመጨመር ነው እንጂ፤ ሌላ ትርፍ ነገር አይገኝበትም . . . . ይቀጥላል!


           /ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ለልጃቸው ለፈቃደ ሥላሴ የፃፉት ምክር/

No comments:

Post a Comment