(ካለፈው የቀጠለ)
በስመ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ሰኞ ህዳር 6 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
ስለ ሕይወት ስናስብ መለኮታዊነት እና ዘላለማዊነት የብቻው የሆነውን እግዚአብሔርን ልብ እንላለን፡፡ ሕይወት እግዚአብሔር
ብቻና ከእርሱ ብቻ ነው፡፡ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር የገባቸውን፤ በተረዱት መጠን ቢናገሩ እርሱ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ያነሰ አይደለም፡፡
እግዚአብሔርን ልዩ የሚያደርገው ነገር ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት አስገኝ የለበትም፡፡ ስለ እርሱ ሕልውና
ስናወራ እርሱ ራሱ ብቻ መሰረትና ፍጻሜ ነው፡፡
ዘላለማዊነት ከእግዚአብሔር አንጻር የነገሮች ረጅም ጊዜ መቆየት አይደለም፡፡ መለኮታዊነትም በበላይነት እያስተዳደሩ መዝለቅ
አይደለም፡፡ እርሱ ብቻ ዳርቻ በሌለው፤ ስፍራም በማይወሰንለት ልዩነት ከ እና እስከ መቼም ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ‹‹ፊተኛ እና
ኋለኛው›› (ኢሳ. 44፡6) የእርሱ በቂ ማብራሪያ አይደለም፡፡
ይህ ከእውቀት ከፍለን እንድናውቅ የተገለጠልን እውነት ነው (1 ቆሮ. 13፡9)፡፡ ይህ አርነት እንድንወጣ በቂ ቢሆንም
የምናጣጥመው መንፈሳዊ ነጻነት የመጨረሻ ማብራሪያ ግን አይደለም፡፡ ራሱን እግዚአብሔርን ለምንወርስ (ሮሜ 8፡16) ለእኛ ከመታወቅ
የሚያልፍ ነገር ከእርሱ እንደተደረገልን ማመን የሐሴታችን ጥግ ነው፡፡ ገና ከዚህ ሕይወት ጋር ለማይቆጠር ጊዜ፤ በማይወሰን ስፍራ
እንኖራለን፡፡ እግዚአብሔር ብቻ ያልተፈጠረ ሕይወት ነው!
ቅዱሱ መጽሐፍ ሕይወት መገኛዋ ሕይወት የሆነው እግዚአብሔር እንደሆነ ያስረዳናል፤ ‹‹በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና
ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ።›› (ራእ. 22፡1)፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ የእኛም
ሕይወት እርሱ ሕይወት የሆነው እግዚአብሔር ነው፡፡ ብቻውን ጸንቶ የሚኖር ሕይወት፤ ባህርዩ ሊቀየር የማይችል ሕይወት እግዚአብሔር
አምላካችንና አባታችን ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፤ የእግዚአብሔር ሕይወት ለሞት የሚገዛ ሕይወት አይደለም፡፡ ከሕልውና
በቀር መጥፋት አያብራራውም፡፡ ሽንፈት ድካም፤ መለወጥ መናወጥ አይገልጸውም፡፡ ይህ ሕይወት ከራሱ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር መልአክ
ቢሆን አይሰጠንም፡፡ የሥጋ ለባሽ የጥረቱ ውጤት ሊሆንም አይችልም፡፡ በምንኖርበት ዓለም እንኳ ሕይወት ከእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡