Monday, November 16, 2015

የሕይወት አቅርቦት

(ካለፈው የቀጠለ)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


                                              ሰኞ ህዳር 6 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

       ስለ ሕይወት ስናስብ መለኮታዊነት እና ዘላለማዊነት የብቻው የሆነውን እግዚአብሔርን ልብ እንላለን፡፡ ሕይወት እግዚአብሔር ብቻና ከእርሱ ብቻ ነው፡፡ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር የገባቸውን፤ በተረዱት መጠን ቢናገሩ እርሱ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ያነሰ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን ልዩ የሚያደርገው ነገር ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት አስገኝ የለበትም፡፡ ስለ እርሱ ሕልውና ስናወራ እርሱ ራሱ ብቻ መሰረትና ፍጻሜ ነው፡፡

       ዘላለማዊነት ከእግዚአብሔር አንጻር የነገሮች ረጅም ጊዜ መቆየት አይደለም፡፡ መለኮታዊነትም በበላይነት እያስተዳደሩ መዝለቅ አይደለም፡፡ እርሱ ብቻ ዳርቻ በሌለው፤ ስፍራም በማይወሰንለት ልዩነት ከ እና እስከ መቼም ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ‹‹ፊተኛ እና ኋለኛው›› (ኢሳ. 44፡6) የእርሱ በቂ ማብራሪያ አይደለም፡፡

       ይህ ከእውቀት ከፍለን እንድናውቅ የተገለጠልን እውነት ነው (1 ቆሮ. 13፡9)፡፡ ይህ አርነት እንድንወጣ በቂ ቢሆንም የምናጣጥመው መንፈሳዊ ነጻነት የመጨረሻ ማብራሪያ ግን አይደለም፡፡ ራሱን እግዚአብሔርን ለምንወርስ (ሮሜ 8፡16) ለእኛ ከመታወቅ የሚያልፍ ነገር ከእርሱ እንደተደረገልን ማመን የሐሴታችን ጥግ ነው፡፡ ገና ከዚህ ሕይወት ጋር ለማይቆጠር ጊዜ፤ በማይወሰን ስፍራ እንኖራለን፡፡ እግዚአብሔር ብቻ ያልተፈጠረ ሕይወት ነው!

       ቅዱሱ መጽሐፍ ሕይወት መገኛዋ ሕይወት የሆነው እግዚአብሔር እንደሆነ ያስረዳናል፤ ‹‹በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ።›› (ራእ. 22፡1)፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ የእኛም ሕይወት እርሱ ሕይወት የሆነው እግዚአብሔር ነው፡፡ ብቻውን ጸንቶ የሚኖር ሕይወት፤ ባህርዩ ሊቀየር የማይችል ሕይወት እግዚአብሔር አምላካችንና አባታችን ነው፡፡

       ተወዳጆች ሆይ፤ የእግዚአብሔር ሕይወት ለሞት የሚገዛ ሕይወት አይደለም፡፡ ከሕልውና በቀር መጥፋት አያብራራውም፡፡ ሽንፈት ድካም፤ መለወጥ መናወጥ አይገልጸውም፡፡ ይህ ሕይወት ከራሱ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር መልአክ ቢሆን አይሰጠንም፡፡ የሥጋ ለባሽ የጥረቱ ውጤት ሊሆንም አይችልም፡፡ በምንኖርበት ዓለም እንኳ ሕይወት ከእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

       ከእርሱ ዙፋን ካልወጣ፤ ከፈቃዱ ካልፈሰሰ ከየትም አይገኝም፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት ከእርሱ ብቻ የሆነ ውድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት ይዘቱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ጥልቀቱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ወርድ ስፋቱ የዘላለም አምላክ እርሱ ነው፡፡ የዚህ ሕይወት መልካምነቱ ከእግዚአብሔር ያነሰ አይደለም፡፡

       ብርቱካን ብንጨምቅ የሎሚ ውኃ እንደማይፈሰው ሁሉ ከእርሱ የሚፈሰው ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ሁሉ የያዘ ነው (ማቴ. 7፡17-19)፡፡ የሕይወት ማብራሪያ የሰዎች ልምምድና የማወቅ ደረጃ አልያም የኑሮ ተሞክሮ ሳይሆን ራሱ ሕያው እግዚአብሔር ነው፡፡ ከሕይወት ውጪ መኖር ማለት ከእግዚአብሔር ውጪ መኖር ነው፡፡ የሕይወት ክልል የእግዚአብሔር ክልል ነው፡፡ ከእርሱ ጋር መሆናችንን የማይገልጡ ግን መልካም ነገሮች አሉ፡፡ በእኛ የሚሠራው መልካሙ ሕይወት ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነውና (ፊል. 2፡13)፡፡

       ሕይወት ማለት እግዚአብሔር አለኝ ማለት ነው፡፡ ልምምዶቻችን ሕይወት አይሆኑም፡፡ ሕይወት እግዚአብሔር ነውና፡፡ ከዚህች ዓለም የሰበሰብነው ሁሉ ሕይወት አይሆንም፡፡ ወደ እርሱ መቅረብ ብቻ የእርሱን ሕይወት መኖር ነው፡፡ እውነተኛውን ሕይወት መለማመድም ነው፡፡ ሰዎች በእግዚአብሔር ውስጥ ሲያልፉ ብቻ እንጂ በራሳቸው አልፈው ወደ እግዚአብሔር ሕይወት አይደርሱም፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ በሥጋ ለባሽ ውስጥ ያለው ‹‹የእኔነት›› ሕይወት እንጂ የእግዚአብሔር ሕይወት አይደለም፡፡ ትክክለኛ ሕይወት እኛ በእግዚአብሔር እርሱም በእኛ ሲያልፍ የሚሆነው ነው፡፡ ቅዱሱ ሕያው እግዚአብሔር የእኛና የዚህ ዓለም ክፍተት አይደለም፡፡ ደግሞ የፍላጎቶቻችን ሎሌም አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር የሆነው ከትክክለኛ አስተሳሰብ፤ ከሰዎች መልካም የጋራ ስምምነትም በእጅጉ ይበልጣል፡፡

       የመረረ ነገር ሳለ የጣፈጠ፤ የደፈረሰ ነገር ሳለም የጠራ አይኖርም፡፡ ክርስቲያን አንዱን የእግዚአብሔር ሕይወት የሚለማመድ ነው፡፡ እርሱ ያለው እጅግ ጣፋጭ የሆነው አለው፤ እርሱ ያለው እጅግ የጠራው አለው፡፡ እርሱ ያለው የማይጨረሰው አለው፡፡ እርሱ ያለው የማይጣሰው አለው፡፡ እርሱ ያለው የማይገመተው አለው፡፡ እርሱ ያለው ሁሉም አለው (2 ቆሮ. 6፡10)፡፡

       በዚህም ክርስቲያን ልክና ልክ ያልሆነውን የሚያሳይ መንገድ፤ ጨለማውን የሚያጋልጥ ብርሃን፤ አልጫውን የሚያጣፍጥ ጨው ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነውን ሕይወት የሚለየው ራሱ ምንጩ ነውና፡፡ የሕይወት መገኛ ደግሞ ሕይወት የሆነው እግዚአብሔር ነው፡፡ እኛና እግዚአብሔር ጎን ለጎን ብንሆን እንኳን ተለያይተናል ማለት ነው፡፡ የቱንም ያህል መልካምና ፍጹም ብንሆን ‹‹እኔነት›› የእግዚአብሔርን ሕይወት ሊገናኝ፤ ተካክሎትም ሊዘልቅ አይችልም፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ በቅዱሱ መጽሐፋችን ውስጥ ከሕይወት ያነሰ ነገር አናስተውልም (ዮሐ. 20፡31)፡፡ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር ለሰዎች ያለው ትልቁ ነገር ‹‹ሕይወት›› ነው፡፡ ሥጋ ለባሽ መንፈስ የሆነውን የዘላለም አምላክ ከሕይወት ላነሰ ነገር ተስፋ ያደርገው ይሆናል፤ እርሱ ግን ለሰዎች ሁሉ ሕይወቱን ሰጥቶአል፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት የእኛ እንዲሆን የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ መገለጥ ነበረበት (ዮሐ. 1፡14፤ 1 ጢሞ. 3፡16)፡፡ እግዚአብሔር ከኃጢአት በታች ተዘግቶ ሞት ለተፈረደበት የዓለም ሕዝብ የላከው ሕይወት ልጁ ኢየሱስ ክርቶስ ነው(1 ዮሐ. 5፡12)፡፡

       ከእግዚአብሔር ያገኘነው ሕይወት ከእርሱ ብቻ የፈሰሰ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት የእኛ እንዲሆን መፍሰስ ነበረበት፡፡ በኮሬብ ከዓለቱ ውኃ እንዲፈልቅ ዓለቱ መመታት ነበረበት (ዘጸ. 17፡6፤ 1 ቆሮ. 10፡4)፡፡ ሕይወት ወደ እኛ እንዲደርስ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን መቀበል አስፈለገው (1 ጴጥ. 2፡24)፡፡ በእርሱ ያገኘነው ሕይወት ከእግዚአብሔር የመጣ (የፈሰሰ) ነው፡፡ ከእግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እኛ የፈሰሰ የዘላለም ሕይወት (ዮሐ. 7፡37፤ 4፡13-14)፤ በየዘመናቱ በሚነሡ ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ያለ ገደብ የሚፈስ ሕይወት ክርስቶስ ነው (1 ዮሐ. 5፡12)፡፡ እርሱ የሚፈስ ብቻ ሳይሆን የማይቋረጥም ሕይወት ነው፡፡

        በእግዚአብሔር ማንነት ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ ሕይወት ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት ራሱን የገለጠበት ብቸኛው መንገድ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ዮሐ. 1፡17፤ 14፡6)፡፡ ኢየሱስን መረዳት እግዚአብሔር ለእኛ እንዴት ሕይወት እንደሆነልን መረዳት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ የመለኮት ሙላት ነው (ቆላ. 2፡9)፡፡ በሰው ወግና ዓለማዊ በሆነ በከንቱ ፍልስፍና መታለል ያልተማረኩ ሁሉ እያንዳንዱ ነገራቸውን በዚህ ሕይወት ተጽእኖ ስር ያደርጋሉ፡፡

         ተወዳጆች ሆይ፤ ሰው ወደ ሰማይ የሚደርሰው ከሰማይ በመጣው ሕይወት ብቻ ነው (ዮሐ. 3፡12-13)፡፡ እግዚአብሔር በሞት ጥላ ወዳለው የሰው ዘር የመጣው ነገሮችን ከሕይወት ጋር በማስተሳሰር ነው (ኤፌ. 2፡5)፡፡ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ‹‹ . . እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ›› (ዮሐ. 10፡10) ብሎናል፡፡ ከሰማይ የመጣው ምድሪቱ ላይ ካልሠራ የሰማይን መኖር አይቻልም፡፡ በሰማያት ወዳለውም መድረስ ከቶ አይሆንም፡፡ እግዚአብሔር አለኝ የማለት መሠረቱ ደግሞ ኢየሱስ ነው፡፡

         በእርግጥ እኛ እግዚአብሔር አለኝ ማለታችን ሳይሆን እርሱ በእኛ አለሁ ማለቱ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ‹‹የሚሆንና የሚበዛ›› ሕይወት በእኛ ውስጥ መሆኑ ምንኛ ታላቅ ነገር እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ በእኛና በዚህ ዓለም ደግሞም ሊመጣ ባለው ዓለም ክርስቶስ ይለያል፡፡ በዚህ ሕይወት ለዘላለም መተያየትም አለመተያየትም አለ (ሉቃ. 23፡39-43)፡፡ እኛ ልክ እንደ ሔኖክ ‹‹ግፍ ተሞልታለች›› ከተባለችው ዓለም ‹‹እግዚአብሔር ወሰደው/ ወሰዳት›› የሚባልልን የእግዚአብሔር ሕይወት በእኛ ውስጥ ያለ የእግዚአብሔር ልጆች ነን (ዘፍ. 5፡24፤ 1 ተሰ. 4፡17)፡፡

        ሕይወት መንፈሳዊና ዓለማዊ ብለን የምንከፍለው አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው አሳብ የአመንዝራነት ምቹ በር ነው፡፡ ክርስቲያን የሚለማመደው አንዱን መለኮታዊ ሕይወት ነው (ፊል. 1፡21)፡፡ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ‹‹በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር›› (ሉቃ. 2፡52) እንተባለ፤ በሰው ፊት ያደገው ያው በእግዚአብሔር ፊት ያደገው ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ሥራው ድንኳን መስፋት እንደ ነበረ እናውቃለን (ሐዋ. 18፡2)፤ ዳሩ ግን ዓለማዊና መንፈሳዊ የሚባል ሕይወት አልነበረውም፡፡ ክርስቲያን ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር የሚያደርግበት አንድ ሕይወት አለው (1 ቆሮ. 10፡31)፡፡

       ሰማይ የትም እንዳለ ሁሉ የእግዚአብሔር ሕይወትም የትም ቢሆን ይገዛል፡፡ እግዚአብሔር የላይኛውን መሻት በእኛ ውስጥ አድርጎአል፡፡ ልጁን ሕይወት አድርጎ ለሞትነው ለእኛ አቅርቦአል፡፡ ያለ ክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔር የእኛ ሕይወት ሊሆን አይችልም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በእርሱ እንደ ቃሉ የማያምን ሁሉ ስለ ሰማይ ቢያወራም እንኳ በዚያ ውስጥ ያለው ምድራዊ ነው፡፡ ስለ መንፈሳዊ ነገር በብዙ ቢገልጥ ውስጡ ያለው ግን ሥጋ ነው፡፡

      ለሚያምኑ የእግዚአብሔርን ሕይወት እንዲኖሩ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች ተደርገዋል (2 ጴጥ. 1፡4)፤ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚያስፈልገን ሁሉ በአባታችን በእርሱ ዘንድ አለ፡፡ የዚህ ሁሉ መሰረቱ ግን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (1 ቆሮ. 3፡11)፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን ማስተዋል የኢየሱስን ሕይወት ለመኖር ትልቅ እርምጃ ነው፡፡

       እውነተኛው የሕይወት ልምድ ክርስቶስ ነው፡፡ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በክርስቶስ የሕይወት ልምምዳቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ የሸሸገው ለጨለማው ዓለም የተሰወረበት ሕይወታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የእኛ ዋጋ እኛ ለእኛ ያለን ግምት ሳይሆን እግዚአብሔር ያለው ሁሉ ነው (ዘፍ. 15፡1)፡፡ ከክርስቶስ ጋር በመሞት የጀመርነው፤ እግዚአብሔር የሸሸገው፤ ደግሞ በክብር የሚገለጥ ሕይወት አለን (ቆላ. 3፡3-4)፡፡ ክርስቶስ ሕይወት ነው!

      ተወዳጆች ሆይ፤ እውነተኛ ክርስቲያን አሁን በዚህ ዓለም ላይ የሚኖረው ኑሮ በወደደውና ስለ እርሱ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለው እምነት የሚኖረው ነው (ገላ. 2፡20)፡፡ በወደደን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ደካሞች፣ ገና ኃጢአተኞች፣ ገና ጠላቶቹ ሳለን ስለ እኛ ሞቶአል (ሮሜ 5፡6-10)፡፡ እግዚአብሔር ‹‹ዓለሙን ወዷል›› ከመባሉ አስቀድሞ ‹‹አንድያ ልጁን እስኪሰጥ›› (ዮሐ. 3፡16) ተብሎአል፡፡ እግዚአብሔር እኛን ለመውደድ ዋጋ ከፍሎአል፡፡ ለኃጢአት ዋጋ ሳይከፈል የእግዚአብሔር ጽድቅ ኃጢአተኛውን በፍቅር ሊገናኘው አይችልም (ሮሜ 6፡23)፡፡         
  
      ስለ እኛ ራሱን የሰጠ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነፍሱን ስለ እኛ አሳልፎ ለሞት ሰጥቶአል (ዮሐ. 15፡13፤ 2 ቆሮ. 5፡14)፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅርም በዚህ አውቀናል (ኤፌ. 3፡19)፡፡ እርሱ ኢየሱስ ‹‹ከኃጢአታችን በደሙ ያጠበን›› ነው (ራእ. 1፡6)፡፡ ራሱን በሰጠው በእርሱ እኛ የእግዚአብሔርን ሕይወት ተቀብለናል፡፡ በወደደውና ስለ እርሱ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለው እምነት የሚኖር ክርስቲያን፡-

1. ክርስቶስ በእርሱ ሁኔታ ይገለጣል (ገላ. 1፡15)፡- ከሥጋና ከደም ጋር የማንማከርበት የክርስትናው መሰረት ‹‹ኢየሱስ›› ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት ካለን በየትኛውም ሁኔታችን ልጁ ኢየሱስ በእኛ ሁኔታ ውስጥ ይገለጣል፡፡ እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ኑሮ ልጁን መግለጥ ይወዳል፡፡ ለዚህ የመለኮት መሻት የሚታዘዝ ሕይወት የጥረት ውጤት ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ የሚሆንልን ነው፡፡

2. ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሕይወት በውስጡ ይኖራል (ዮሐ. 15፡5)፡- ከእግዚአብሔር ያገኘነው ሕይወት ሁሉንም በራሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ያለዚህ ሕይወት ክርስቲያን ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ አንድ ፍሬ በቅርንጫፉ ላይ ከመሆኑ፤ ቅርንጫፉ ደግሞ በዛፉ ላይ ከመሆኑ የተነሣ ሕይወት አለው፡፡ በውስጣችን ያለው ነገር ፍሬውን መራራ አልያም ጣፋጭ ሊያደርገው ይቻለዋል፡፡ በውጪው ኑሮአችን እለት እለት የምንለማመደው በውስጣችን ያለውን የክርስቶስ ሕይወት ይሆናል፡፡

3. ኢየሱስ ክርስቶስ ይሳልበታል (ገላ. 4፡19)፡- በክርስቲያን ሕይወት እድገት የሚጠበቅ ነው፡፡ እናት ከምጧ በኋላ እንደምትደሰት ሐዋርያው ስለ ገላትያ ሰዎች ምጥ ይዞት ነበር፡፡ ርዕሱ ደግሞ ክርስቶስ እንዲሳል ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ እግዚአብሔር እናንተ ላይ መሳል ቢፈልግ ምን የሚስል ይመስላችኋል? አዎ! ልጁን ኢየሱስን ነው፡፡ ሐዋርያው እያለ ያለውም እንዲሁ ነው፡፡ ክርስቶስ በቬሮኒካ ጨርቅ ላይ ሳይሆን በእኛ ማንነት ላይ መሳል ይፈልጋል፡፡ ቆዳችን ላይ እንድንነቀሰው ሳይሆን ልባችን ስፍራ እንዲለቅለት ይፈልጋል፡፡   

4. ጌታ በሥጋው ይከብራል (ፊል. 1፡20-21)፡- ክርስቶስ በውስጣችን ብቻ ሳይሆን ከውስጣችን ወደ ውጪም መታየት አለበት፡፡ ሥጋ ውጫዊውን ማንነታችንን ያሳያል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ውጫዊ በሆነው ማንነታችን በግልጥነት ሊከብር ያስፈልጋል፡፡ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለን እምነት በመኖራችን እግዚአብሔር ክብር ሆኖ ይገለጣል፡፡

5. የጌታን ክብር እንደ መስተዋት ያብለጨልጫል (2 ቆሮ. 3፡18)፡- እግዚአብሔር መሻቱ የልጁን ክብር በእኛ ላይ ማንጸባረቅ ነው፡፡ እግዚአብሔርን መምሰል የእግዚአብሔር ሕይወት ከፍተኛው ነው፡፡ ለክርስቲያን ክርስቶስን መምሰል የተመደበለት ነው (ሮሜ 8፡29)፡፡ እግዚአብሔር አብ የልጁን መልክ በእያንዳንዳችን ላይ ሲያብለጨልጭ ማየት ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ›› (ማቴ. 3፡17) እንዳለው ይሆንለታል፡፡

         ሰው ያለ ክርስቶስ ከምድር ወደ ሰማይ፤ ጽድቁ እንኳ የመርገም ጨርቅ የሆነ ነው (ኢሳ. 64፡6)፡፡ መልካምነቱ ውስጥ መልካም ያልሆነ ብዙ ነገር የያዘ የተበላሸ ሕይወት ነው (ሮሜ 7፡18)፡፡ ከሰማይ ወደ ምድር፤ ሰው ኃጢአት አልባ ቢሆን እንኳ ሕይወቱ የተፈጠረ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ያልተፈጠረ ሕይወቱን እንዲካፈል ፍቅሩን ገልጧል፡፡ እንዲህ ላለው ምስኪን ሰው እግዚአብሔር ያለው መፍትሔ ‹‹ማሻሻል›› አይደለም፤ ዳግም መወለድ እንጂ (2 ቆሮ. 5፡17)፡፡

       በመጀመሪያው ልደት የሰው ሕይወት፤ በዳግም ልደት ደግሞ የእግዚአብሔርን ሕይወት አግኝተናል (ዮሐ. 1፡12-13)፡፡ እግዚአብሔር ፍላጎቱ መልካም ሰው ማግኘት ሳይሆን የልጁን መልክ የያዙ የእርሱን ሕይወት የተካፈሉ እውነተኛ ልጆችን ወደ ክብሩ ማምጣት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የእግዚአብሔር ሕይወት ያለው ነው፡፡

       ተወዳጆች ሆይ፤ ወደ ልጁ መልክ መምጣት የእግዚአብሔርን ባሕርይ በተግባር መኖር ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ማቋረጥ የሕይወት ግንኙነት መመስረት ሕይወትን በሚሰጥ በመንፈስ ቅዱስ መመራት ነው (ሮሜ 8፡14)፡፡ በውስጣችንና በዘንዳችን የሚኖረው (ዮሐ. 14፡17) የእውነት መንፈስ የእግዚአብሔርን ሕይወት እለት እለት በኑሮአችን ተግባራዊ እንድናደርገው ያስችለናል፡፡

       እንግዲህ እናንተ ለእውነት የምትቀኑ ሁላችሁ፤ በእኛ ያለው ሕይወት ውድ እንዲሆን አውቃችሁ፤ በምትቀበሉት መከራ ሁሉ በጌታ ታገሱ፡፡ መቼም ቢሆን ውድ ነገር ዘመቻ አለበት፡፡ ወንጌላችን ወጥመድ የሚሰብር፣ ጨለማን የሚገፍ፣ ሸክም የሚጥል፣ ቀንበርን የሚሰብር፣ ታሪክ የሚለውጥ፣ ሞትን የሚያሻግር እስከሆነ ድረስ ሐሰተኛው የሐሰት አባት ከነልጆቹ (ዮሐ. 8፡44) ቢፍጨረጨር ይህ የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ እናንተ ግን ‹‹የሕይወት አቅርቦት›› እንዳታጓድሉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ!
                                                                                           ተፈጸመ//  
                                                      ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment