Friday, November 20, 2015

ድልና ምክር (1)

                                                                      

‹‹ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው›› /ምሳ. 24፡6/፤ ‹‹እርስ በርሳችን እንመካከል›› /ዕብ. 10፡25/!
                            
   አርብ ህዳር 10 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

         ምክክር ወደ መፍትሔ የሚያደርስ የጋራ ችግር ፈቺ ሂደት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን በጽድቅ ላለው ምክር እንደሚጠቅም ተጽፎአል (2 ጢሞ. 3፡16-17)፡፡ በክርስትናው መሰረት ላይ ሆኖ በእለት ከእለት ችግሮቻችን ላይ በጋራ ዝርዝር መፍትሔዎችን ማስቀመጥ፤ መመካከር፤ መጠያየቅ፤ መረዳዳት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ የመፍትሔ ሰዎች መሆን ይብዛላችሁ! 

·        በረከቶቻችሁን ቁጠሩ፡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስትሆኑ በኑሮአችሁ ያገኛችኋቸውን በጎ ነገሮች መመልከትን አትዘንጉ፡፡ የፈተና አንዱ መልክ ያላችሁን ሳይሆን የሌላችሁን እንድታስቡ መፈተኑ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በዚህ መንገድ ይቸገራሉ፡፡ እግዚአብሔር ያደረገላችሁ ይታያችሁ፡፡ በትንሹ እየተቸገራችሁያላችሁት እንኳ በመኖራችሁ እንደሆነ ይታወሳችሁ፡፡ የመኖርን ሌላኛውን ገጽታ መመልከት የምንችለው በሕይወት ስላለን ነው፡፡

        ፈቃዳችሁ ቢሆን እየጻፋችሁ ልትዘረዝሯቸው ሞክር፡፡ በእርግጠኝነት የምትጽፉበት ቀለሙ ያልቃል፤ ግን በረከቶቻችሁ ተጽፈው አልቀው አይደለም፡፡ የሆነላችሁ ብዙ ነው፡፡ ሩቅ ካለው ቅርብ ያለው ውብ ነው፡፡ ከተሸሸገባችሁ የተገለጠው አቅም ነው፡፡ ካልጨበጣችሁት የያዛችሁት ትርፍ ነው፡፡ በእናንተና በዙሪያችሁ ካለው ድካም አንዱ ከሌላችሁ የሚካፈለው ብርታት ትልቅ ነገር ነው፡፡

         በእለት ጸሎታችሁ ምስጋናን መናገር ቸል አትበሉ፡፡ የሚያለቅስም የሚስቅም የቆመ ብቻ ነው፡፡ የሚሰደድ የሚያሳድድ፤ የሚነቀፍ የሚነቅፍ፤ የወደቀ የተደላደለ . . ሁሉም መኖርን መሰረት አድርገው ነው፡፡ ለራሳችሁም ሆነ ለሌሎች ብርታት ዋጋ ስጡ፡፡ መልካሙን ነገራቸውን በድምቀት አስተውሉ፡፡ ይህንንም ከመንገር ፈጽሞ አትደብቁ!

·        ፍጹም እንዳልሆናችሁ አስተውሉ፡ መሳሳት ደስ የሚያሰኝ ነገር ባይሆንም፤ ስህተት ግን የሚኖር ሰው ገጠመኝ ነው፡፡ እናንተ በፍጹምነት መስፈርት የምትዳኙት እንደሌለ፤ እናንተንም በዚህ መንገድ ሊዳኛችሁ የሚችል የለም፡፡ ለራሳችሁ ይቅርታ ማድረግን ተለማመዱ፡፡ እግዚአብሔር ትቶላቸው በራሳቸው ሸንጎ ሲከሰሱ የሚኖሩ ብዙ ናቸው፡፡
       
       ችግርን ነቅሶ ማውጣት በጣም ቀላል ነው፡፡ በተለይ የሌሎች ድካም ላይ ጣት መቀሰር፤ እጅ ማስረዘም፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ድካም አለባችሁ? አጥርታችሁ ተመልከቱ፡፡ ውጪ ውጪ ከማለታችሁ አስቀድሞ ወደ ራሳችሁ እዩ፡፡ በራሳችሁም ሆነ በሌሎች የምትወቀሱበትን ነገር ለመለየት ሞክሩ፡፡ በቀጣይ ያንን ላለመድገምና ራሳችሁን ለማሳደግ ተማሩ፡፡

         በምሕረት ባለ ጠጋ የሆነውን ጌታ ይቅርታ ለመጠየቅ አትሸማቀቁ፡፡ በቀጥታ ድካማችሁ የሚያገኛቸውን ሰዎችም መበደላችሁን ተዉልኝ ለማለት አትፍሩ፡፡ ራሳችሁን ራሳችሁ እንዳታሳድዱት ግን ተጠንቀቁ፡፡ እናንተ ያልተዋችሁለትን እናንተን መርዳት ከባድ ነው፡፡ ከራሳችሁ አብዝታችሁ ተጠበቁ፡፡

·        በትሁት መንፈስ ራሳችሁን ገምግሙ፡ ግምገማ በብዙ ድርጅቶች ዘንድ የምንሰማው ቃል ነው፡፡ ሰዎች እርስ በርስ ይገማገማሉ፤ ራሳቸውን እንዲገመግሙም ይበረታታሉ፡፡ ራስን እንዲሁም በዙሪያችን ያለውን መመርመር የዓለም ቋንቋና መንገድ ብቻ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ‹‹በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ›› (2 ቆሮ. 13፡5) ይለናል፡፡ የመጣችሁበትን መንገድ ፈትሹ፤ ልትሄዱ ያለበትንም አጥርታችሁ ለመረዳት ሞክሩ፡፡

       እናንተንና የእናንተን በመመርመር ሂደቱ ይጠቅሙናል የምትሏቸውን ሰዎች ለማግኘት ተንቀሳቀሱ፤ አስፈላጊ ጥያቄዎችንም በትህትና አቅርቡ፡፡ የምትሰሙት እናንተ የሚነግራችሁም ያ ሰው እንዳትሸዋወዱ ይልቁንም እንድትደማመጡ ጸልዩ፡፡ አካላዊ ከሆኑ ነገሮች በበለጠ አመለካከታችሁን ማዕከል የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ አተኩሩ፡፡ ለአሳባችሁ ሰፊ የአሳብ ሽፋን ስጡ፡፡

        በገባችሁ ነገራችሁ ላይ ትክክለኛውን ውሳኔ ለማሳለፍ አታመንቱ፤ ተግባራዊ ለማድረግም ቁረጡ፡፡ ‹‹እንቢ›› ለሚያስፈልገው ከዚህ ያነሰ መልስ በመፈለግ አትድከሙ፡፡ ‹‹ሽሽት›› ለሚገባው እስኪሸሻችሁ ጊዜ አትስጡ፡፡ የግምገማችሁን ውጤት ግልጽ አድርጉ፡፡ የችኩል አትሥሩ፤ ጊዜ ውሰዱ፡፡ ከፈጸማችሁ አትመለሱ፤ የጨበጣችሁትን አታፍሱ፡፡ ትግበራ ላይ ልባችሁን ጠበቅ አድርጉ፡፡
-      ይቀጥላል -

v ችግርዎን እንካፈልዎ፡- ፖ.ሳ.ቁ፡ 31106 አ.አ፤ ኢሜል፡ bfb.tube@gmail.com ወይም የእርስዎን አድራሻ ይላኩልን፡፡
                           ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment