ከሁለተኛው አስተያየት የቀጠለ፡ -
መጋባትን በአግባቡ የፈጸሙ ሰዎች ትዳር ውስጥ ልዩነትን ወደ አንድነት፣
መራራቅን ወደ ቅርበት ሲያመጡት እንመለከታለን፡፡ ምክንያቱም አንዱ በሌላው ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሌላውም በአንዱ ውስጥ ስፍራን አግኝቶአል፡፡
ሳይጋቡ የገቡ የልብ ጥምረት፣ የአሳብ መስማማት አይስተዋልባቸውም፡፡ አካላዊ ሕብረት ጎልቶ ቢታይም የመንፈሳዊ ውስጠታቸው ነፀብራቅ
መሆን ግን አይችልም፡፡
ከሙሽራው ክርስቶስ ጋር ያለንን ጥምረት ቅዱስ መጽሐፍ ሲነግረን
“እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን” ይላል፡፡ በእርሱ ብንኖር እርሱ ደግሞ በእኛ ለመኖሩ መሠረቱ የጌታን ልብ መያዛችን ነው፡፡ የሙሽራይቱ
ለሙሽራዋ የሚኖራት ትልቁ ክብር እንደ ልብዋ ሳይሆን እንደ ልቡ አሳብ መኖሯ ነው፡፡ የክርስቶስ አካል (ቤ/ን) ብልቶች እንደመሆናችን
መንፈስ ቅዱስ ለክርስቶስ ለማጨት ሕይወታችንን በሚጎበኝበት ሁኔታ ውስጥ ትልቁ ጥያቄ ማን ያግባሽ? የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር
ፈቃዳችንን ተጠቅሞ በሕይወታችን ውስጥ በፍቅርና በኃይል ይሠራል እንጂ ነፃ ፈቃዳችንን ለመጣስ አንዳች ነገር አያደርግም፡፡ ጌታ ከገዛ እውነቱ ይጣላ ዘንድ አመፀኛ አይደለም!
ስለ መታጨት ስናስብ ከመጽሐፍ ቅዱስ የዘፍጥረት ምእራፍ ሃያ አራት
ታሪክ ተጠቃሽ ነው፡፡ አብርሐም ለልጁ ለይስሐቅ ሙሽሪትን ለመፈለግ ሎሌውን እንደላከ የምናስተውልበትን ክፍል እናነባለን፡፡ አብርሐም
ልጁን በሞሪያም ለመሥዋዕትነት ካቀረበ (በአባቱ ሕሊና ከተሠዋ) በኋላ በምሳሌነቱ የልጁን ትንሣኤ ከተመለከተ ከዚያም ሚስቱን ከቀበረ
በኋላ እንደ ተስፋው ቃል እውነተኛ ወራሽ ለሚሆነው ብቸኛ ልጁ ይስሐቅ ሚስትን ያጋባው ዘንድ ሎሌውን ላከ፡፡
ሎሌው የናኮር ከተማ ወደምትገኝበት መስጴጦምያ ተጓዘ፡፡ በዚያም
ርብቃ ውኃ ልትቀዳ ስትመጣ በመንገድ አገኛት፡፡ ሎሌውም ውኃ አጠጪኝ በሚል የመግባቢያ ቃል ስለ ውኃ አጣጯ ይስሐቅ ነገራት፡፡ አባቱ
አብርሃም ለልጁ ያልሠጠው አንዳችም ነገር እንደሌለ ከእርሱም ጋር ብትጋባ የእዚህ ሁሉ ክብርና ባለ ጠግነት ተካፋይ እንደሆነች አወጋት፡፡
አባት ለልጁ መልካም ሚስትን ለማዘጋጀት ሎሌውን እንደላከ ሎሌውም ለይስሐቅ መልካሚቱን እንደወሰደ የታጨችይቱም ያላየችውን ነገር
ግን የሰማችለትን፣ ያላገኘችውን ነገር ግን ተስፋ የተሰጣትን ቃል አምና አዎንታዊ ምላሽ ስትሰጥ እናስተውላለን፡፡
ለጸጋው
ቃል አደራ የተሰጠን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ እንደ አባት ፈቃድና መመሪያ ለአንድ ልጁ ለክርስቶስ ታጭተናል፡፡ ሎሌው ከአብርሃም እንደወጣ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሠርፆአል (ዮሐ.
15÷26)፣ ስለ ወልድም ወልድ ካለው ወስዶ ይነግረናል (ዮሐ. 16÷12)፡፡ ርብቃ (ቤተ ክርስቲያን) ከስም ሁሉ በላይ የሆነውን
ስም ደግሞም ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሰጠንን ስም የያዘውን፣ ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይ
በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ሊመጣ ባለውም ዓለም ጌታ የሆነውን በአባት ዘንድ እንዳለ ክብር ያለውን ክብር ብታስተውል ደግሞም እሺ ብትል በሠርጉ እራት ላይ እድል ፈንታ ይሆንላታል፡፡
በወርቅና በብር ያይደለ በደሙ የሆነ ጥሎሽ ለእርሷ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶአል፡፡ እንዲህ ባለ ፍቅርና መከራ ለወደደን መታጨት እርሱ
ያግባኝ ብሎ ለአንድ ወንድ ክርስቶስ መለየት ክብሩ በዋጋ የማይተመን ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን የታጨችለትን ልታስተውል ደግሞም ፍቅሩን ልታከብር
ይገባታል፡፡ ከሀብት፣ ከሥልጣን፣ ለዚህ ዓለም ከሚመች ከንቱ መለፍለፍ ተረትና መጨረሻ ከሌለው የትውልዶች ታሪክ፣ በእውነት ላይ
ዓመጽ እነዚህን ከመሳሰል ተጨማሪ ወንዶች (ማመንዘር) ልትርቅ ይገባል፡፡ ለሁሉም የሆነው አንድ ሙሽራ የአንተ የአንቺ ሙሽራ ነው
ወይ? ከነፍሳችን ጋር ሊዋሃዱ የሥጋ ምኞት፣ ዓለምና ዲያቢሎስ በዙሪያችን ያደባሉ ታዲያ ማን ያግባሽ? ማስተዋልን እንድናተርፍ ጌታ
ይርዳን፡፡
ኃይሉ
ወ/ማርያም
3. ቤተ ፍቅር የምታነሷቸው የመወያያ ርዕሶች ተመችተውኛል፡፡ ማን ያግባሽ? የሚለው ጥያቄ በሌላ
ጎኑ ማን ያግባህ? የሚል ጥያቄም እንደሆነ በማመን ያለኝን አመለካከት እገልፃለሁ፡፡ ለመንደርደሪያ ያክል ባለፈው ባስነበባችሁት
አስተያየት ላይ ትህትና የተባለች አልያም የተባለ ሰው የሰጠውን መደምደሚያ ወድጄዋለሁ፤ በአብላጫውም አመለካከት እስማማለሁ፡፡
እንደ እኔ አመለካከት ከሆነ ገንዘብ እንዲሁም አፍ ለትዳር ጣዕም
አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ሀብቱ ልቡ አፉም ልቡ የሚለው እንዳለ ሆኖ መነጣጠል በሌለበት ሁኔታ ቁሳዊና አሳባዊ ነገሮችም ለትዳር
ጤናማነት ወሳኝ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ አዳምን (እንኳን ሔዋንን ረዳት አድርጎ መፍጠር ይቅርና) ከመፍጠሩ በፊት ስለሚኖሩበት፣
ስለሚበሉት፣ ስለሚዝናኑበት፣ ስለሚሠሩት አስቦና አሰናድቶ በአለቀ ነገር ላይ ነው የሞሸራቸው፡፡ ይቅርታ አድርጉልኝና ጎጆ ውስጥ
እንጨርሰዋለን በሚል የጅምር ጋጋታ ላይ ትዳር መመስረት ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙ አይታየኝም፡፡
ሰው
ሥጋና ነፍስ (መንፈስ) እንደመሆኑ ብር ያለው ያግባሽ? የሚለው ከስግብግብነትና ከንዋይ አፍቃሪነት በፀዳ መንገድ መሟላት አለበት፡፡
ይህንን ቀለል ባለ እገላለጽ ስናስቀምጠው የመተዳደሪያ ጉዳይ በትዳር ውስጥ የመጨቃጨቂያ ርእስ አይሁን ማለት ነው፡፡ አፍ ያለው
ያግባሽ? የሚለውም ጥያቄ ማታለልና ማደናገርን የሚያጣራ ጆሮ ካለን አስፈላጊ ነው፡፡ አሳባቸውን ወደ ውስጥ እንጂ ወደ ውጪ መግለጽ
የማይችሉ መታለላችን ጨዋ በሚል ሽፋን የሚያሞካሻቸው፣ ማስተዋላችን ደግሞ የሚኮንናቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲያውም የሕሊናዋን
የማታወራ፣ የተሰማትን የማትገልጥ ሴት ከገጠመቻችሁ እንዲሁም አይኑ ቁልጭ ቁልጭ አፉ ዝም ጭጭ የሚል ወንድ ከገጠማችሁ እንደነዚህ
ያሉት ከባድ የቤት ሥራ ናቸው፡፡
አሳቤን ስጠቀልል ሔዋን የተሞሸረችው ለእንስሳት መጠሪያቸውን ለሚሰይመው፣ መኖሪያው
ዔደን ገነት ለሆነው፣ ከእግዚአብሔር ጋር የአባትና የልጅ ሕብረት ላለው አዳም ነው፡፡ በእርግጥም ሔዋንን ማን ያግባሽ? ብለን ብንጠይቃት
አዳም ከማለት ውጪ ሌላ ምላሽ አይኖራትም፡፡ ምክንያቱም ያለው አንድ ወንድ ብቻ ነዋ! ምናልባት በዙሪያቸው ከእጽዋት መካከል የወንዴ
ዘር አልያም ከእንስሳቱ ዘንድ ወንድ ካልሆነ በቀር ለአማራጭ ተቀናቃኝ አልነበረም፡፡ ምናልባትም ሲመስለኝ ከሠይጣን የሆነ ነገር
ግን እንደ ሰው ያለውን ምክር የሰማችው ለብቸኛው አዳም ልብዋ አማራጭ ያገኘ መስሎት ይሆናል፡፡ ዛሬ ግን አማራጩ ብዙ ነው፡፡
በአካል
ቀጭን፣ ወፍራም፣ ረዥም፣ አጭር፣ ቀይ፣ ጥቁር እንዳለ ሁሉ በአስተሳሰብ፣ በኑሮ ዘይቤ እንዲህ የሚመደቡ ወንድም ሴትም ባሉበት ዓለም
እንደመኖራችን ማን ያግባሽን አቅልሎ ማየት አይቻልም፡፡ እኔ ግን በመጠን ኑሩ ስለሚል ቃሉ ብር ካላት አፍም ካላት የተመጠነችውን
ማግባት መልካም ነው እላለሁ፡፡ ክብረት ይስጥልኝ!
ሀብተ ወልድ
4. እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛላችሁ፡፡ ርእሱን እንደተመለከትኩ ውስጤ ጥያቄ ስለተፈጠረብኝ ይህንኑ
ለመግለጽና ምላሻችሁን ብታካፍሉኝ በማለት ጥያቄዬን እንደሚከተለው እገልጣለሁ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ፍቅር ጀምሬ ነበር
ይህም ብዙ ሳይቆይ ተለያየን በልቤ ውስጥ አኑሮ ያለፈው ነገር ግን ቀላል አልነበረም፡፡ ዩኒቨርስቲ ከገባሁም በኋላ ከአንድ ልጅ
ጋር ተቀራርበን ተመርቄ እስክንለያይ ድረስ ዘለቅን ከዚያ በኋላ ግን ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ አሁን ታዲያ ከሁለቱም ጋር በነበረኝ የፍቅር
ጊዜ ከሁለቱም የወደድኩላቸውን ጨምቄ አንድ ሰው በልቤ ስያለሁ ማለትም አሁን ማግባት የምፈልገው እንደዚህ አይነት ሰው ሁነ፡፡ ይህም
ሌላ ከማንም ጋር እንዳልቀራረብና የሚመጣልኝንም የፍቅር ግብዣ ትኩረት እንድነፍግ አድርጎኛል፡፡ እድሜዬ እየገፋ ቢሆንም ማስተካከል
ግን አልቻልኩም፡፡ ምን ትመክሩኛላችሁ? በትዳር አጋር ምርጫ ላይ የእግዚአብሔር ፈቃድስ ምን ይመስላል?
ሕሊና
ይቀጥላል