Friday, June 8, 2012

ጅቡም ይበላል (ክፍል ሦስት)


       
       በዚህ ክፍል ካለፈው የቀጠለ አስተያየት እናቀርባለን፡፡ እስካሁን የልባችሁን አሳብ ላካፈላችሁን ደግሞም አስተያየት ለላካችሁልን ሁሉ የእውነት እናመሰግናለን፡፡ በመጀመሪያ ባለፈው ክፍል ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ አንፃር እንየው በማለት ወደጋበዘን ወንድም አስተያየት በማስከተልም ሌላ ሁለት አስተያየቶችን እንመለከታለን፡፡
       ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ሰላም፣ እኩልነት እነዚህ ሁሉ በምንም የማንደልላቸው ርሀቦች ናቸው፡፡ የእነዚህን መጓደል እንጀራ አይተካውም፡፡ ራሳችን ለራሳችን የምንነግረው ማንኛውም ሽንገላም ከብዝነት አያሳርፈውም፡፡ ሰዎች እነዚህ ካልተከበሩላቸው የአሳብና የአካል ትግላቸው አይቋረጥም፡፡ ሰው አማራጭ ካጣ ቀይ መስመር፣ ነጭ መስመር የሚባል ወሰን አይወስነውም፡፡ ለእርሱ ልኬቱና ድንበሩ እውነትና ፍትሕ ነው!
       መሪዎች ጠንቅቀው ሊያውቁት ደግሞም በጥበብ ሊመላለሱበት አግባብ የሆነው ነገር ቢኖር የሕዝቦች ሕሊናዊና አካላዊ ፍላጎት በቅጡ ምላሽ ካላገኘ ብሶት እንደ ፍግ እሳት ውስጥ ውስጡን እየነደደ፤ አይነካም ያሉት እንደሚነካ፣ አይደፈርም ያሉት እንደሚደፈር፣ አይሻርም ያሉት እንደሚንኮታኮት ነው፡፡ ምክንያቱም የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውምና ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነገር አገርን በመምራት ደረጃም ብቻ ሳይሆን ቤተሰብን በመምራት ውስጥም ይሠራል፡፡ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባልቻሉ አባቶቻቸው ስም ላለመጠራት ጥረት የሚያደርጉ ልጆችን አስተውለናል፡፡ ከከፋ ጅቡም ይበላል!
      ዛሬ ብዙዎች የደከሙበትና የሚሟገቱለትን ፖለቲካ የኢኮኖሚው አለመረጋጋትና የዋጋ መናር እያበላሸው ነው፡፡ ምክንያቱም የራበው ሰው የሚሰማህ ከልቡ በጆሮው ሳይሆን ከአንገት በሆዱ ነው እንዲሉ ልብ ያለው ልብ ይበል በማለት ልለፈው፡፡ ክብረት ይስጥልኝ!
                                                                                           ፈታሒ
4. ቤተ ፍቅር ስለ አማራጭ፣ አመራጭ ስለማጣትና አማራጭ ካልተገኘ እንኳን በጅብ የተነከሰው በግ ቀርቶ ጅቡም ሊበላ ይችላል… ለምን ሲባል ደግሞ ‹‹ወገኔ እዬዬም ሲደላ ነው›› ሲባል አልሰማህም እንዴ የሚለው በማኅበረሰባችን የእለት ተእለት ኑሮ ውስጥ የሚንጸባረቀው የቆየው ብሂል በአያ ጅቦና በበጊቱ ተረክ የቀረበውን ታሪክ የሚያጠናክር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ቤተ ፍቅር በታሪክ አሰደግፋ ያቀረበችው ጽሑፍ ብዙ ሊያነጋግረንና ሊያወያየን እንደሚችል ባምንም ግን አማራጭ በራሱ ፍጹም ያልሆነ ማጠፊያው ሲያጥረን ከእንግዲህስ የመጣው ይምጣ በሚል የምንወድቅበት የቢቸግር ምርጫ እንደሆነ ሊያሳዩ የሚያስችሉ መከራከሪያ አሳቦችን በመደርደር የውይይቱን ድንበር፣ ወሰን ማስፋት ይቻል ይመስለኛል፡፡ እናም በዚሁ መንፈስ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድሁ፡፡
        መቼም እኛ ኢትዮጵያውያን የተረት ድኃ አይደለንምና ከተነሳው ታሪክ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ሌላ ተረት ልጥቀስ ግን በሀገራችን እንደ ጅብ በተረትና በብሂል የተንበሸበሸ ሌላ የዱር አውሬ ይኖር ይሆን እንዴ አንባቢዎቼ፣ እናም ተረታችን አሁንም ከጅቦች ሰፈር የወጣ ወይም የራቀ አይደለም፤ ተረቱ እነሆ፡- ‹‹ጅብ ከሚበላኝ ጅብ በልቼ ልቀደስ፡፡››  ይህ እንግዲህ በጅብ ከመበላትና ጅብን ከመብላት የትኛው ነው የተሻለው አማራጭ በሚል ተጠየቅ የቀረበ ተረት መሆኑን አንባቢ ልብ ይላል፡፡ በመሠረቱ የተረቱ አብይ አሳብ መቼም በቁሜ እያለሁ ጅብ ከሚበላኝ ምንም ጸያፍና የረከሰ ፍጡር ቢሆንም ጅቡን በልቼ ብቀደስ አሊያም የሚወሰንብኝን ቀኖናዬን ብቀበል ሳይሻላል አይቀርም የሚል ስሜት ያለው ነው የሚመስለው፡፡
        ያው የዚህ ውሳኔ መነሻ ደግሞ በእውቀቱ ስዩም የተባሉ ጸሐፊ በአንድ ወቅት ስለ ራብ ባተቱበት መጣጥፋቸው እንደጠቀሱት፡- ‹‹ከሙሴ ሕግ ይልቅ የጨጓራ ሕግ ያይላልና›› ራቤን በማስታገስ ነፍሴን ላቆያት፣ ሕይወትም ትቀጥልና ከዛ በኋላ በጅብ የተነከሰን በግ መብላት ትክክል ነው ወይስ አይደለም፣ ያረክሳል ወይስ አያረክስም… ወደሚለው ክርክር ለማምራት እንችላለን የሚል ይመስለኛል፤ የዚህ ክርክር ጫፍ ደግሞ ከተቸገርን፣ አማራጭ ከሌለንማ እንኳን በጅብ የተነከሰችው በጊቱ ቀርታ ጅቡስ ሌላው ሌላውስ ይበላል እንጂ በክፉ ቀንማ ነፍስን ለማቆየት ክቡር የሆነ የሰው ልጅስ ተበልቶ የለ እንዴ ወደሚለው የሚጎረብጥ አማራጭ ሐቅ የሚያደርሰን ይመስለኛል፡፡
         መቼም በአዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ሆነን ‹‹በይበላልና በአይበላም›› ‹‹በያረክሳልና በአያረክስም›› ኦሪት ሕግ እንደ አንዳንዶች ወገኖቻችን ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ ለመዶል የሚሻ ሰው ካለ የነገራችን ጭብጥ ‹‹ከይበላልና አይበላም›› ‹‹ከያረክሳልና ከአያረክስም›› እሳቤ በእጅጉ እልፍ ስለሚል አልተገናኝተንም ከማለት ውጭ የምኖረው አይኖረኝምና አሳብ ሳላንዛዛ በዚሁ ወደተነሳሁበት ቁምነገር ማጠናከሪያ አሳቦች አብረን በአንድነት እናዝግም፡፡
        መቼም ሰው በሕይወት ትግል፣ ሰልፍና ግብግብ ውስጥ ከሚገጥሙት ውጣ ውረዶችና አጣብቂኝ ለመውጣትና ለማምለጥ የተሻለውን አማራጭ መጠቀሙ ሐቅ ነው፤ ግን በራሱ ያ አማራጭ ፍጹም ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም ባይ ነኝ ምክንያቱም እውነታውን ስንመረምር ያን አማራጭ እንደ አማራጭ አድርገን የወሰድነው ቢያንስ ይሻላል በሚል ማነጻጸሪያ ስለሆነ ነው የሚለው እሳቤ ደግሞ የውይይታችን ማሾሪያና ማጠንጠኛ ዋና እሳቤ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በሀገራችን የቆየ እንዲህ የሚል ብሂል አለ፡- ‹‹ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት … ምንትስ ያሻላል፡፡›› በተረቶቻችን ውስጥ ለዘመናት በማኅበረሰባችን ውስጥ የቆየውን የሕይወት ፍልስፍና፣ የኑሮ ዘይቤ የሚገልጹ፣ ታሪካችን፣ ባሕላችን፣ ማንነታችንና ማኅበረሳበዊ አስተሳሰባችን የቆመበትን መደላድል የሚያሳዩ እውነታዎች የታጨቁበት ለመሆኑ ምስክር መቁጠር የሚያሻን አይመስለኝም፡፡ እናም ተረት ማብዛቴ ለዚያ ነው እንጂ አንባቢያንን ለማታከት አይደለም፡፡
       እናም ከላይ የጠቀስነው ተረትም ሊገልጽልን የፈለገው እሳቤ አረረም መረረም፣ ከፋም ለማም፣ ተመቸንም አልተመቸንም… እየተቋሰልንም ቢሆን እየተዳማን ከለመዱት ጋር መኖር ይሻላል እንጂ ምን ሲደረግ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ሥልጣኔ፣ አዲስ የኑሮ ዘይቤ/ፍልስፍና… እሹሩሩ የምንልበት ጫንቃ ሊኖረን ይችላል በሚል ግትር አቋም ላይ የተደላደለ እሳቤን የሚያንጸባርቅ ይመስላል የተረቱ ጭብጥ እናም በታሪካችን ውስጥ አዲስ አስተሳሰብን፣ አዲስ የኑሮ ስልትን፣ አዲስ የስልጣኔ ጎዳናን አማራጭ ለማስተዋወቅ የሞከሩ ሁሉ ከመወገዝና ከመረገም ጦስ እንዳላመለጡ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንም ምስክር ነው፡፡
        በዚህ ረገድ መቼም እንደ እምዬ ምኒሊክ ክፉኛ የተቸገረ ንጉሥ ኖሮን የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ለአብነት ያህል አፄ ምኒልክን በስልክ መነጋገር ያዩ የዘመኑ መኳንትና ካህናት ጃንሆይ ከእርኩስ መንፈስ ጋር እየተነጋገሩ ነው በማለት ክፉኛ እንዳሟቸው፣ እንዳብጠለጠሏቸውና በቤታቸው ስልክ የገባ አንድ መኳንትም ስልኩን ጠበል አስረጭተው በላዩ ላይ እሳት መልቀቃቸውን ታሪካችን ይነግረናል፡፡
       ከተነሳንበት ርእስ ብዙም እንዳንርቅ ስለ አማራጭ ሲነሳ ብዙዎቻችን በሕይወታችን ያልሞከርነውን አማራጭ ከማሰብና አዲስ ነገረን ከመቀበል ይልቅ ከለመድነው ነገር ጋር ተስማምተን እየመረረንም ቢሆን እየተሳቀቅን መኖርን መምረጥ ምንፈልግ ይመስለኛል፡፡ ያልተሞከረና አዲስ ነገርን አማራጭ አድርጎ ለመቀበል የሚተናነቀን እንደሆንን ራሳችንን ብንፈትሽ መልሰን ራሳችንን ሳንታዘበው እንቀራለን ብዬ እገምታለሁ፡፡ ስለዚህም እየመረረንም ሆነ እያለቀሰንና እየተራገምንም ቢሆን ‹‹ከማናውቀው መልአክ ከምናውቀውና ከሚያውቀን እንትና ጋር መኖር…›› የተሻለ አማራጭ መስሎ ስለሚሰማን ያልተሞከሩ አዳዲስ አማራጮችን ለመውሰድ ገና ስናስበው የጥርጣሬ መንፈስ የሚወረን ይመስለኛል፤ ይህ ደግሞ ምክንያት የለሽ ፍርሃት የሚወልደው ተልካሻ አስተሳሰብ ከመሆን ባለፈ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፡፡
        በሌላ በኩል ደግሞ መራጭ ወይም አማራጭን ፈላጊ ሰው ማለት ይላሉ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ከብዙ መጥፎዎች መካከል የተሻለውን መጥፎ የሚመርጥ ነው፡፡›› በእርግጥ ከብዙ መጥፎዎች መካከል የተሻለውን መምረጥም በራሱ ብልህነት ቢሆንም ፍጹምና ሁሌም ግን ትክክልና ውጤታማ ይሆናል ብዬ ግን አላስብም፡፡ በይበልጥ ይህ እውነታ የሚጎላው በመንፈሳዊ ሕይወታችን ወይም ኑሮአችን ውስጥ ስለ ምርጫዎቻችን ስናስብ ከላይ በጠየቅነው ጥያቄ ውስጥ ያለው እውነታ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡
        እናም በእኛ ዘንድ የተሻለ አማራጭ ነው የምንለው የትኛው ነው… ለአላፊና ለጠፊ ደስታ ስንል ከኃጢአት ጋር ተስማምቶና ተመቻችቶ መኖር ወይስ እንደ ሎጥ ነፍሳችን እያስጨነቀንም ቢሆን የጽድቅን ሕይወት መምረጥ፣ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲባል ሀገርንና ወገንን በሚጎዳ ስራ ውስጥ መዘፈቅ ወይስ ከእውነት ጋር በመቆም በሐቅ መኖር፣ ከአንድ ሰው ጋር በቅዱስ ትዳር መወሰን ወይስ ከዚያችም ከዚህችም ጋር ለምን ይቅርብኝ በሚል ዕድሜን መፍጀት፣ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ወይስ ሰውን የትኛው ነው የተሻለውና የሚበልጠው አማራጭ፣ የመስቀሉ የእውነትና የሕይወት መንገድ ነው ወይስ ሰፊውና ብዙዎች የሚመርጡትና የሚጓዙበት የሞት ጎዳና . . .፡፡
        እንደ ንጉሥ ዳዊት ‹‹ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፡፡›› የሚል ውሳኔ የተሻለ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ወደሚበልጥ አማራጭ መጠጋት ግን በብዙ እንድናተርፍ ይረዳናልና የዕድሜያችን ጀንበር ሳያዘቀዝቅ የተሻለውን ብቻ ሳይሆን ከሁሉ የሚበልጠውን አማራጭ የሙጥኝ ማለቱ ብልህነት ብቻ ሳይሆን በእጅጉ የሚጠቅመንም ነው፡፡ በጹሑፌ ማጠቃለያ ለራሴና ይህን ጽሑፍ ለሚያነቡ ለአንባቢዎቼ ሁሉ ግን አንድ ጥያቄ በመጠይቅ ጹሑፌን ልቋጭ፡- የእኔና የእናንተ ወይም የእኛ የመጀመሪያችንም ሆነ የመጨረሻች አማራጫችን ወይም ምርጫችን ምንና ማን ይሆን . . .??? ቤተ ፍቅር ስለ መጀመሪያውና ስለ መጨረሻው ደግሞም ከሁሉም ስለሚበልጠው አማራጭ ወይም ምርጫ የምትለን ነገር ይኖራት ይሆን… በተስፋ እንጠብቃለን… የእኔን አበቃሁ!!!
                                                           ሰላም! ሻሎም!
                                                             በፍቅር ለይኩን ነኝ፡፡
5. የእኔ እይታ ከፍርድ ጋር በሚያያዝበት መንገድ ነው፡፡ ለቆሎ ተማሪው ምላሽ የሰጡትን መምህር ጌታ ያብዛልን ባይ ነኝ፡፡ ፍርድን ሁሉን ለሚችል እግዚአብሔር መስጠት ካልሆነ ደግሞ ቅን ፈራጅ መሆን የእውነት ዳኛ የሆነውን ጌታ የምንመስልበት አንዱና ዋናው ሂደት ይመስለኛል፡፡ ክርስቶስ ራሱ አምላክ ሆና ሳለ ነገር ግን በማንም ሊፈርድ እንዳልመጣ ተናግሮአል፡፡ እኛማ ታዲያ እንዴታ!
      አገራችን ፍርድ አዛቢዎች እንደ ሊባኖስ ዝግባ ከፍ ከፍ ያሉባት ናት፡፡ ከዚህም የተነሣ እየተቀባበሉ ማልቀስ የአብዛኛዎቻችን ሆቢ ነው፡፡ ፍርድ ከፍተኛ ማመዛዘንን ይጠይቃል፡፡ ከባሕል፣ ከሥርዓት፣ ከልማድና ከእኔነት (ወገናዊነት) በላይ ለእውነት ማድላትን፣ ለፍትሕ መሞገትን ይጠይቃል፡፡ ከተማሪው የሱታ ለእኛ የሚሆን ጥቂት ነገር ላካፍላችሁ፡፡ መምህሩ፡-

ሀ. እንደሰሙ አይፈርዱም
        አንዳንድ ቃላት ሲጠብቁና ሲላሉ ሁለት ዓይነት ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ ታዲያ አንዳንዴ የሚጠብቀውን አላልተን፣ የሚላላውን አጥብቀን ለመግባባት የተናገርነው የሚያጣላን አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ሲሰማ ንግግሩን አልፎ አሳቡን ለማግኘት ይጥራል፡፡ ሌላው ደግሞ ከአፍ ይውጣ እንጂ ለማድነቅም ሆነ ለመኮነን ይህ ብቻውን በቂ ምክንያቱ ነው፡፡ እነዚያ ጊዜ ስለሚወስዱ እርጋታቸውን ያስተምሩናል፤ እነዚህ ደግሞ ስለሚቸኩሉ ስሜታዊነት እናይባቸዋለን፡፡ ብዙ ወዳጅነት እንደ ሰሙ በሚፈርዱ፣ እንዳዩ በሚወስኑ ሰዎች ምክንያት እንዳልነበር ሆኖአል፡፡ እርጋታ በውሳኔያችን እንዳንፀፀት ይረዳናል፡፡
    
ለ. በፍቅር ደግፈው ይሰማሉ
        አስደናቂው ነገር ደግሞ ይህ ነው፡፡ አንዳንድ ትሁታን ሰዎች እየረዳችሁ ስሙኝ ይላሉ፡፡ እኔን እንደገባኝ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር እኛንም የሚሰማን እየረዳ ነው፡፡ ያጠመምነውን በሚያቀና ጆሮ፣ መኮላተፋችንን በሚያጠራ ልብ እያዳመጠ፡፡ የምንሰማበት ሁኔታ በምንሰማው ነገር ላይ ተጽእኖው ከፍ ያለ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ የሕግ አዋቂ ወደ ክርስቶስ መጥቶ “የዘላለም ሕይወትን እንድወርስ ምን ላድርግ” አለው፡፡ ጌታም ለጥያቄው ምላሽ ከሰጠው በኋላ ሌላ ጥያቄ ጨመረ፡፡ መጽሐፉ እንደሚል ሕግ አዋቂው ጥያቄውን ያቀረበው ሊፈትነው ፈልጎ ስለነበር በመልሱ ሊረካ አልቻለም፡፡ (ሉቃ. 10÷25) አሰማማችን ለእውነት ቅርብ አልያም ሩቅ ሊያደርገን አቅም አለው፡፡ 
        ከመምህሩ የምንማረው ሁለተኛው ነገር በፍቅር መስማትን ነው፡፡ በተለይ ሰዎች ድካማቸውን ሲያካፍሉን በልባዊ ፍቅር ልንሰማቸው ያስፈልገናል፡፡ የሰዎችን ድካም የምናግዝበት የመጀመሪያው ነገር በፍቅር ማዳመጥ ነው፡፡ ትኩረት መስጠት፣ ዓይን ዓይንን እያዩ ማዳመጥ፣ ፊት ለፊት ሆኖ የፈካ ፊት ማሳየት በፍቅር የመስማት ሂደቶች ናቸው፡፡ አገልጋዮች ተገልጋዮቻቸውን በፍቅር ደግፈው ማዳመጥ አለባቸው፡፡ ባል የሚስቱን ድካም በፍቅር ደግፎ ማዳመጥ አለበት፡፡ ግንኙነታችንን የሚያራዝመው፣ ከአጉል ፍርድ የምንጠበቀው በፍቅር ደግፎ በመስማት ነው፡፡

ሐ. ለሕሊና ይፈርዳሉ
        ሰዎች ስሜታቸውን፣ አካባቢያቸውን፣ ጥቅማቸውን፣ ወገናቸውን፣ ልማዳቸውን በመታዘዝ ለእነዚህ ይፈርዳሉ፡፡ መምህሩ ከተማሪው በላይ በዚያ አስተሳሰብና ልማድ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ነገር ግን ልማድ ላወረሳቸው ሳይሆን ሕሊና ለሚላቸው ታዘዋል፡፡ ሰው በሰው፣ ልማድ በሌላ ልማድ፣ ጥቅምም በሚበልጥ ጥቅም ይተካል ሕሊና ግን በምን ይደለላል? መምህሩ የፈረዱት ለልማድና ለተማሪው ሳይሆን ለሕሊናቸው ነው፡፡ እኔም የታየኝን እንዲህ አስፍሬዋለሁ፡፡ ለእውነት ፍረዱ!
                                                                  ስም አልተጠቀሰም

ይቀጥላል

1 comment:

  1. Bete fikir sile ewinet endininor ke betekiristian abatochim hone ke miemenanu min endemitebek tastemirenalech ena bizu kum negerin kesimenibatal. Egziabher betekirstiyanachinin yasibat. Enantem tsegaw yibzalachu!

    ReplyDelete