Tuesday, June 12, 2012

ጅቡም ይበላል (ክፍል አራት)



  ክቡር ከበደ ሚካኤል ከፃፉት ግጥም መካከል የተወሰነውን ለማጠቃለያ እንደ መግቢያ እንጠቀምበት፡፡
ድንበሬን ማን ገፍቶት አይሉም አይሉም፤
ሚስቴንስ ማን ነክቶአት አይሉም አይሉም፤
አጥሬን ማን ጥሶት አይሉም አይሉም፤
         ጊዜው ከደረሰ ይደረጋል ሁሉም፡፡
         አማራጭ ከሕይወታችን ጋር በብርቱ የተሳሰረ ነገር እንደሆነ በአንድም በሌላም መንገድ መተማመን ላይ እንደደረስን አምናለሁ፡፡ ሰው ነፃ ፈቃድ ያለው ፍጥረት በመሆኑ የመምረጥ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ሰው ነፃ ፈቃድ ባይኖረው ኖሮ ዛሬ ድረስ በገነት የአትክልት ስፍራ አጥሮ በታሰረ ገመድ የሚንገላታ እንስሳ ከመሆን አይለይም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰውና መላእክትን ከሌሎቹ ፍጥረታት የሚለያቸው አንዱ ነገር ነፃ ፈቃድ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ መከራ በምንሰማውና በምናየው ልክ በሆነባት ዓለም ላይ አማራጭ ማጣት ነፃ ፈቃድ ላለው የሰው ልጅ ቢለዋ ተሰጥቶ ሥጋ እንደመከልከል ነው፡፡
         ከላይ ለመንደርደሪያነት ያነሣነው ግጥም የሚነግረን ጊዜው ከጠየቀ ሰው የማይሆነውና የማይከውነው ነገር እንደሌለ ነው፡፡ ስለ ሕይወት የተለያዩ ሰዎች የተለያየ አመለካከትና እይታ እንዳላቸው እናስተውላለን፡፡ ጥቂቶቹን ለመመልከት ያህል “ሕይወት ሽክርክሪት ናት፤ አንዳንዴ ከፍ፤ ሌላ ጊዜ ዝቅ ትላለህ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ዝም ብለህ ትሽከረከራለህ” ሌላ ደግሞ “ሕይወት እጅግ ፈጣንና ኃይሉን ሁሉ ልንጠቀምበት እንደማይቻለን አስር ማርሽ እንዳለው ብስክሌት ናት” በተጨማሪም “ሕይወት በካርታ ጨዋታ ትመሰላለች፤ በእጅህ ላይ ባሉት ካርዶች መጫወት ይኖርብሃል” የሚል የተለያዩ አመለካከቶችን ማስተዋል እንችላለን፡፡
        ከሁላችንም ገሃዳዊ ኑሮ በመነሣት ለሕይወት ማብራሪያ ብንፈልግ ሕይወት ምርጫ እንደሆነች እንረዳለን፡፡ ሰዎች በአደጉ አገሮች ላይ ለመኖር ያላቸውን ጉጉት ከሚያንረው ምክንያት አንዱ የአማራጭ መኖር ነው፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ በታዳጊ አገሮች ላይ ለመኖር ፍላጎት የማጣት ስሜት የሚስተዋለው በአማራጭ ማነስ አልፎም ተርፎ አለመኖር የተነሣ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሰው ከራሱ ጋር ላለመኖር ውሳኔ ላይ የሚደርሰውም በጊዜው ለገጠመው ነገር ልብን የሚሞላ፤ ሚዛን የሚደፋ አማራጭ መፍትሔ አለማግኘቱ ቢኖርም እንኳን አለማስተዋሉ ነው፡፡
           ሕይወት ከግምታችን እንዲሁም ስሜታችን ከሚነግረን ከፍ ያለ ነገር ትፈልጋለች፡፡ ለዚህም ደግሞ ትክክለኛ መሻቷን የሚሞላና ለማንኛውም ነገር ዘላቂ የሆነ አማራጭ ትፈልጋለች፡፡ ሰው ይህንን ከሰው ምላሽ ሊያገኝለት አይችልም፡፡ ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንዲህ ላለው ጥያቄ ከእውቀቱ፣ ከንብረቱ፣ ከሥልጣኑና ከዝናው ዘላቂ መፍትሔ ሊያወጣ አይቻለውም፡፡
          ነቢዩ እንዳለ “እግዚአብሔር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው÷ ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነህ፡፡ ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ ርስቴም ተዋበችልኝ፡፡ (መዝ. 15÷5) እንዳለ አማራጭ ወደሌለው ምርጫችን፣ መፍትሔውን የሚያስንቅ መፍትሔ ወደሌለ የዘላለም መፍትሔያችን፣ መድኃኒትነቱን የሚያህለው ወደሌለ መድኃኒት ዘወር ማለት ግድ ይሆናል፡፡ ከሁከት ለመውጣት የሞከርናቸው አማራጮች ሁሉ የማባባስን ያህል ከሆኑብን እርሱ ጌታ አእምሮን የሚያልፍ ሰላም አለው፡፡ ኑሮ አታካች ሆኖብን ሲነጋ መቼ በመሸ ሲመሽ መቼ በነጋ ለምንል እርሱ የበጎ ስጦታ የፍጹም በረከት ጌታ ነው፡፡ ነውርን መሸከም፣ ኃጢአትን መታገስ ላዛላችሁ እርሱ በምህረቱ ባለጠጋ ነው፡፡ ሀዘን ልባችንን ለሸረሸረው እርሱ ለዘላለም የማንታወክበት ደስታ ነው፡፡
           ወንጌላዊው ማርቆስ አማራጭ ያለችውን ሁሉ አስሳ በመጨረሻ ሞትን ፊት ለፊት መጠበቅ ዕድል ፈንታዋ ስለሆነባት ሴት ታሪክ ያስነብበናል፡፡ (ማር. 5÷25) ጌታ ከምኩራብ አለቆች አንዱ ታናሽቱ ልጁ ታማ እንዲፈውስለት ለመነው፡፡ ጌታም እሺታውን በተግባር ሊፈጽም በመንገድ ሳሉ ስሟ ያልተጠቀሰ አንዲት ሴት ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም ይፈሳት በዚህም በሽታ በብርቱ ትሰቃይ ነበርና የልብሱን ጫፍ ብነካ እድናለሁ በሚል እምነት ቀረበች፡፡ ከታሪኳ እንደምንረዳው ወደ ብዙ  መድኃኒት አዋቂዎች ዘንድ እንደሄደች ነገር ግን ከዕረፍት ይልቅ ስቃይ እንደበዛባት፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ከመሻል ይልቅ እንደባሰባት እንረዳለን፡፡
           በምኩራብ አለቃውና በዚህች ሴት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ እርሱ ባለ ሥልጣን ሲሆን እርሷ ከተራው ሕዝብ መሐል ናት፡፡ እርሱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ግምትና ክብር የሚሰጠው ሰው ሲሆን እርሷ ደግሞ ትኩረት የተነፈገች፣ ለማኅበራዊ ሕይወት እንኳን መጠጊያ ያጣች፣ ችግሯን በማባበል የተጠመደች ናት፡፡ (ዘሌ. 15÷19) ግን ለሁለቱም ያለ ልዩነት ጌታ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ እርሱ ሥልጣኑ የማይፈታው፤ እርሷ ደግሞ ገንዘብዋ የማይፈውሰው ችግር ነበረባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚሆን አማራጭ መፍትሔ በዙሪያቸው አልነበረም፡፡ በሚበልጠው (በሞት) የተፈተነ መሳይ የሌለው አማራጫችን ጌታ ግን ብቸኛ መድኃኒት ሆናቸው፡፡
            ኢያኢሮስ ለአሥራ ሁለት ዓመታት የአይኑ ማረፊያ፣ የቤቱ ድምቀት የሆነች ልጁን ሲያጣ፤ ሴቲቱ ደግሞ ለአሥራ ሁለት ዓመታት ስታንቀላፋ እያባተተ፣ ስትነቃ ልብዋን እያዛለ ያሰቃያት ከነበረው በሽታ የተነሣ ለመኖር ያላት ጉጉት ተሟጦ ተስፋ ቆርጣ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሴቲቱን የግል ጥረት ውጤት “ባሰባት እንጂ አልተሻላትም” በሚል ነው፡፡ ልብ ብለን ካስተዋልን ሴቲቱ ከፍለጋዋ ስትመለስ ዋናዋ ላይ አይደለም የቆመችው ይልቁንም ባሰባት(ኔጌቲቭ) ከምርጫዋ ዕድል ፈንታዋ ይህ ነበረ፡፡ ጉልበት ሳላት፣ ገንዘብ ሳላት ጌታን አላገኘችውም፡፡ አማራጮችዋ ሁሉ ሲሟጠጡ፣ የረገጠችው ደጅ ሁሉ ለመፍትሔ ዝግ ሲሆን፣ እርሷና ሞት ፊት ለፊት ሲፋጠጡ ግን ቀጠሮ የማይሰጥ መድኃኒት አገኛት፡፡ ሄዳ ያንኳኳችው ሲዘጋ የሞት መድኃኒት ወደ ሕይወቷ አንኳኩቶ መጣ፡፡ እርሱ ክርስቶስ ከማንኛውም ሁኔታ ጋር ብንፋጠጥ፣ የትኛውንም አይነት የኑሮ ተግዳሮት በእድሜያችን ብናስተናግድ መቼም የማይታጣ ምርጫችን ነው፡፡
          ገንዘብ እንደሌላችሁ ለሚሰማችሁ ጌታ ብል የማይበላው መዝገብ ነው፡፡ ጤና እንዳጣችሁ ለሚሰማችሁ ክርስቶስ የሞት መድኃኒት ነው፡፡ መጠለያ እንደሌላችሁ ለሚሰማችሁ ሁሉን የሚችል ጌታ አምባ መጠጊያ ነው፡፡  እንደተጠላችሁ እንደተተዋችሁ ለምታስቡ እርሱ በዘላለም ፍቅር የሚወድ ደግ ሳምራዊ ነው፡፡ ፍርሃትና ጭንቀት እንደ አውታር ለወጠራችሁ እርሱ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ ዕረፍት ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ ክርስቶስ ላለው ክርስቲያን አማራጭ ማጣት ጥያቄው አይደለም!

No comments:

Post a Comment