የፈለከውን ነገር ሁልጊዜ ላታገኝ ትችላለህ፡፡ ያገኘኸውን ነገር
መውደድን ግን ተለማመድ፡፡ መሻትህ ሁሉ ላይኖርህ ይችላል ያለህን መንከባከብ ግን አትርሳ፡፡ ኑሮዬ ይበቃኛል ማለት ስለ ግብህ ማሰብ አቆምክ ማለት አይደለም፡፡ በዚህ
ውሳኔ ማረፍ ቅሬታን ያርቅልሃል እምነት ማጣትን ያስወግድልሃል ተስፋ መቁረጥንና የተዛባ አመለካከትህንም ያስተካክልልሃል፡፡
አሳብህም ልብህም ሰፊ ይሁን አመለካከቶችህ ሁሉ ሕያው እግዚአብሔርን
በመተማመን ቅዱሱን መንፈስ ክንድ በማድረግ ላይ የተመሰረቱ ይሁኑ፡፡ ሥራህንና ቃልህን ለማዛመድ ትጋ፡፡ የልብህና የእጅህ እርስ በእርሳቸው እንዳይጣረሱ ጥረት አድርግ፡፡ ምድራችን ስለፍትህ በሚያወሩ
ግን ደግሞ ለሕግ በማይገዙ ፍቅርን በሚሰብኩ ግን በፍቅር ለመኖር ምንም ጥረት በማያደርጉ የጌታን ቃል በሚያደምጡ ግን ደግሞ ቃሉን በማይኖሩ ሰዎች የተሞላች ናት፡፡
ልብ
በል ወሳኙ ነገር የምትኖርበት ቦታ ሳይሆን አኗኗርህ ነው፡፡ ከምታምንበት
ነገርም በላይ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባው ባመንክበት ነገር እንዴት ትኖራለህ የሚለው ነው፡፡ ሁላችንም በሕይወት ያለነው ደስተኞች እንድንሆን
ነው፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔርን ድምጽ አድምጥ ለኑሮህ ብልጥግና ፍቃዱን ተከተል ስኬታማ ለመሆንም በእውነት ላይ ቁም፡፡ እኛ ቀብረን የምናዝነውን ሀዘን ቆመው፣ እኛ ርቦን የምንሰቃየውን ስቃይ ጠግበው፣
እኛ አጥተን የምናነባውን እንባ አግኝተው የሚያነቡት ብዙ ናቸው፡፡ ልዩነቱ እኛ ሁሉን ለእርሱ ክብር ማድረጋችን ነውና ሁኔታዎችህን
ሁሉ ለእርሱ ክብር ማድረግን መልመድ ይገባሃል፡፡
ማንም ሰው ከጠባቡ ግለኝነት ሕይወት ወደ ሰፊው ጠቅላላው የሰው ልጅ
ምልከታ ከፍ እስኪል ድረስ መኖርን ተማረ አይባልም፡፡ ማለዳ ማለዳ አዲስ ትርጉም ባለው መንገድ ለመኖር ራስን መመልከታችን ወደ
ፊት ከመመልከት ጋር ሊዋሐድ ይገባዋል፡፡ ያለህን ስትሰጥ ጥቂት ሰጥተሃል ራስህን ስትሰጥ ግን ያኔ በእውነት ሰጥተሃል እንደሚባለው
የእኛን ብቻ ሳይሆን እኛንም ለሌሎች ማካፈል አለብን፡፡ ለምሳሌ ማየት ለተሳነው ሰው መመልከት ቢችል ኖሮ ሊያከናውን የሚችለውን
እኛ ብናከናውንለት፣ መራመድ ለማይችል ቢራመድ ኖሮ ሊሠራው የሚችለውን እኛ በመራመድ ብንሠራት፣ መናገር ለማይችለው መናገር ቢችል
ኖሮ የሚያስረዳውን አፍ ሆነን ብንናገርለት ይህ ራስን ማካፈል ነው፡፡ በፍቅር መግዛት በጥላቻ ከመግዛት፣ ብቸኝነትን ከመንከባከብ
ሕይወትን ማጋራት አብዝቶ የተሻለ ነው፡፡ በትህትና ልንሠራው የምንችለውን መልካም ነገር በሸካራ ቃላቶች ልናውከው፣ በግለኝነት ልናፍነው
አይገባም፡፡
እርግጠኝነት ያለው ፍቅር የሕፃናት ነውና ለእነርሱ በእርጋታ ንገራቸው፡፡
እንክብካቤን የሚፈልግ ፍቅር ያለው በአዛውንቶች ዘንድ ነውና በእድሜ ለገፉ በእርጋታ ንገራቸው፡፡ ርኅራኄን የሚፈልግ ፍቅር ያለው
በድሆች ዘንድ ነውና ለእነርሱ በእርጋታ ንገራቸው፡፡ በከንቱ የሚተጋ ፍቅር ያለው በኃጢአተኞች ዘንድ ነውና ለስሁታን በእርጋታ ንገራቸው፡፡
ሕያውና ዘላለማዊ ፍቅር ያለው በጌታ ዘንድ ነውና የሰውን ዓመጽ ለማሸነፍ ሕይወቱን ለሰጠው ለእርሱ በእርጋታ ተናገር፡፡ የጉብዝና
ወራት ፍቅር ያለው በወጣቶች ዘንድ ነውና ለእነርሱም በጥበብ ተናገር፡፡ ጌታ የማያየው የለምና በምታየው ተስፋ አትቁረጥ፣ እርሱ
የማይሰማው የለምና በምትሰማው አትመረር፣ እርሱ የማይደርስበት የለምና ባልያስከው ነገር አትቆጭ፣ ጌታ ከምናየው ከምንሰማው ራሳችን
ለራሳችን ከምንነግረው በላይ ነውና ልብህ በዚህ ይጽና፡፡ መዋደድ ይብዛላችሁ!!
Amen libachin be Egziabher yitsina! Mikirun hulu le hiwot ena le dihnet yadrgilin. Tsega yibzalachu!
ReplyDeleteYagegnenewin mewded balenim mamesgen endinchil Egziabher yirdan!
ReplyDeleteጌታ ከምናየው ከምንሰማው ራሳችን ለራሳችን ከምንነግረው በላይ ነውና ልብህ በዚህ ይጽና፡፡
ReplyDeleteእምነትህ በእግዚያብሔር ላይ ይሁን ሁሉን ነገር ከእርሱ ዘንድ ታገኛለህ በአምላክህ ብቻ ታመን ሁሉ ያደርግልሃል ከጠበከዉ በላይ ጌታ ለሚታመኑት ሁሉ ቸር ነዉ፡፡
ReplyDelete