5. ለውይይት ያቀረባችሁት አሳብ የሁሉንም ልብና ጓዳ የሚፈትሽ እንደመሆኑ ያየሁት ተሳትፎ አነስተኛ
መሆን በእጅጉን አስገርሞኛል፡፡ የሆነው ሆኖ ሕሊና የተባለች ተሳታፊ ለጠየቀችው ጥያቄ ምላሼን ለማካፈል እሞክራለሁ፡፡ ማንኛውም
ሰው እንደ አንድ ቀን ሁለት አይነት የሕይወት ገጽታ አለው፡፡ ማለትም ቀን የምንለው ግማሽ ብርሃን እና ግማሽ ጨለማ እንደሆነ ሁሉ
የአንድ ሰው ሙሉ ታሪክም ደካማና ጠንካራ ጎን አለው፡፡ ጨለማውን እያስወገድን ብርሃኑን ብቻ ተቀብለን እንኑር ወደሚል ጽንፈኝነት
ከመጣን ደግሞ የሚኖረው ሙሉ ቀን ሳይሆን ግማሽ ቀን ነው፡፡ እንዲህ
ቢሆን ደግሞ በሰው ልጅ ኑሮ ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡ!
አንድን ሰው ስናስብም ከዚህ የተለየ፤ አልያም የራቀ ሊሆን አይችልም፡፡
ብርቱ ጎን እንዳለ ሁሉ ደካማም ጎን አለ፡፡ ሕይወትን ለመኖርና ሰውን መትጋት እንዲጓጓ የሚያደርገውም ይህ ይመስለኛል፡፡ ማግኘትና
ማጣት፣ መክበርና ውርደት፣ ሀዘንና ደስታ ያሉት ሰው ውስጥ ነው፡፡ መልክዓ ምድሩ ሲያለቅስ አልያም ሲስቅ አናየውም፡፡ እንግዲህ
የዓለም ገጽታ የሚለካውም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ የምንወደው ሰው የቱንም ያህል መልካም ቢሆን የአንድ ቀን እውነት በእርሱ ውስጥ
አለ፡፡ ልዩነቱ ያኛው ተፈጥሮአዊ ስለሆነ መቀየር አልያም ማሻሻል አለመቻሉ ሲሆን ይኼኛውን ግን በትምህርት፣ በፍቅር፣ በተግሳጽ፣
በልምድ ባናጠፋው እንኳን በተወሰኑ ጨለማዎቹ ላይ ማሻሻያና ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ እውነታው ግን ሁሉም ሰው ጨለማዊና ብርሃናዊ
የሕይወት ገጽታ እንዳለው መረዳት ነው፡፡
የእህታችን ሕሊና ጥያቄ አንድን ሰው በአዎንታዊ ገጽታው ብቻ
የመመልከትና ከእርሱ ጋር ብቻ የመኖር ፍላጎት ችግርን ያሳየናል፡፡ እንደዚህ ያለው ፍላጎት የመጀመሪያ ችግር እውነታን አለመቀበል
ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ከራስ ጋር ግጭት፣ የዘወትር ሙግት፣ ከማይለወጠው ጋር ትግል ይመጣል፡፡ እያየለ ሲመጣ ደግሞ እልህ ውስጥ
ይገባል “ያልኩት ይሁን” የሚል የማያባራ ጦርነት ያስከትላል፡፡ ጠያቂ ሕሊና እውነቱ ሌላ እንደሆነ ቢገባትም በውስጧ ስር የሰደደው
መሻት ግን ይህንን እንድታስተውል እድል የሰጣት አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በአንድ ሰው ታሪክ ውስጥ ያለውን ሁለት ዓይነት የኑሮ ገጽታ
መቀበል ይኖርባታል፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዤ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ ያነሣችውን ጥያቄ ለመመለስ ልሞክር፡፡
እግዚአብሔር ለሚያምኑት እውነተኛ ምሪት አለው፡፡ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ምሪት ይረዳዋል ወይ? ለሚለው ግን መልሱ አይረዳውም
የሚል ይሆናል፡፡ የእህታችንን ጥያቄ ያመጣውም ይኼው ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር
ልጆች ናቸው (ሮሜ. 8÷14” ተብሎ እንደ ተጻፈ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ የማያቋርጥ ምሪት ጌታን ለሚያምኑ ሁሉ አላቸው፡፡ ይህንን መረዳት የሚቻለው ደግሞ ከቃሉ ጋር የጠበቀ ሕብረት በማድረግ እንዲሁም በጸሎት
በመትጋት የምንረዳው ነው፡፡ (የሐዋ. 16÷7) በዚህ ጊዜ የእውነት መንፈስ ምስክርነት በልባችን ይኖረናል፡፡ ነገር ግን መንፈስን
ሁሉ በቃሉ በኩል መርምሩ የሚለው መመሪያ ምን ጊዜም ተግባራዊ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
በአጠቃላይ በኑሮሽ ጭምር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመከተል በዋናነት
በቃሉ ውስጥ በግልጥ የተቀመጡትን መመሪያዎች አስተውያቸው፡፡ ለምሳሌ በእምነት ከማይመስልሽ ሰው ጋር ጋብቻን መመስረት ተጨማሪ የእግዚአብሔር
ምሪት ሳያስፈልግ በግልጥ ተከልክሏል፡፡ በክፉ ባልንጀርነት መጠመድም እንዲሁ፡፡ ሌላው ከሕሊናሽ አንፃር መልካም ምስክርነት የሚያገኘውን
እንዲሁም ለወቀሳ የማይሰጥሽን ነገር ልዩ ምሪት ሳትጠብቂ በጸሎት ማድረግ ትቺያለሽ፡፡ በመጨረሻ በእምነት መመላለስን መለማመድ ይኖርብሻል፡፡
ምክንያቱም እግዚአብሔርን ለሚወዱት፣ በስሙም ለሚያምኑት ደግሞም እንደ አሳቡ ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሆነ እናውቃለን፡፡
(ሮሜ. 8÷28) የእግዚአብሔርን ምሪት ባትረጂው እንኳን የጸና እምነት ካለሽ ያመንሽው አምላክ ለክፉ እንዳይሰጥሽ የታመነ ነው፡፡
ከዚህ በተረፈ የሚከብድሽ እንዲሁም አቅምሽን የሚፈትን ነገር ሲመጣ ወደ ጸጋው ዙፋን በጸሎት መቅረብና በብርቱ ልመናና ለቅሶ ለጌታ
ማስታወቅ ትቺያለሽ፡፡
ከላይ እውነታውን አለመቀበል እህታችን ላነሣችው ችግር እንዳጋለጣት
አልያም አብራው ከችግሩ ጋር እንድትቆይ እንዳደረጋት ተመልክተናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እንደ ድክመት የታየኝ ደግሞ ከሰው አቅም በላይ
ከሰው መጠበቅ ነው፡፡ ይህ ማለት በአንድ ሰው ውስጥ የሁለት ሰውን ሁኔታ እንደ መፈለግ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለብዙ ወዳጅነቶች
መሻከር አንዱ ምክንያት የአንዱ አቅምና የሌላው ፍላጎት አለመመጣጠን (የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን) ነው፡፡ ሰውን በሆነው መቀበል ደግሞ ጤናማነት ነው፡፡ ሕሊና ከሁለት ወንዶች ጋር በነበራት ግንኙነት
ወቅት ያገኘችውን በጎ ነገር (እንደ እርሷ አገላለጽ) ከአንድ ሰው ለመፈለግ መሞከሯ ፍትሃዊነት አይመስለኝም፡፡ ባል ሁሉ ወደ ቤቱ
ተመልሶ የሚገባው ሚስት ሁሉ ደግ ስለሆነ አይደለም፡፡ ሚስትም እንደዚሁ ቤቴ የምትለው ባል ሁሉ ቅን ስለሆነ አይደለም፡፡ ነገር
ግን በአንድ ሰው ውስጥ ያለውን ሁለት ክፍል ስለተቀበሉት ነው፡፡ ልክ እንደ አንድ ቀን!
በሦስተኛ ደረጃ የታየኝ ድክመት ዛሬን በትላንት አልያም እንደ
ትላንት ለመኖር መሞከር ነው፡፡ ይኼ አደገኛ ነገር ነው፡፡ ወጣት የምንለው አንድ ሰው እንደ ትላንትና ሕፃንነቱ መኖር ቢያምረው
መጀመሪያ የምንቸገረው በወተት ሒሳብ ይመስለኛል፡፡ በልጆች አስተዳደግ ውስጥ አስተውለን ከሆነ አንዳንድ ልጆች እንቅስቃሴያቸው ከእድሜያቸው
በጣም የራቀ ይሆንና የአንዳንዶቹ ደግሞ ሁኔታቸው እድሜያቸው ከሚጠይቀው በጣም የዘገየ ይሆናል፡፡ ሁለቱም ግን አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡
በይበልጥ ደግሞ ዛሬ ላይ ሆኖ እንዳለፈው መኖርን ለማስታመም የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ እስቲ አስቡት አዳራሽ በሚያህል ቤት ውስጥ
እንኖረው የነበረውን ኑሮ አንገት በምታስገባ ቤት ውስጥ ለመኖር ብንሞክር የፍንዳታ ድምጽ የሚሰማ ይመስለኛል፡፡ ለአሳቤ መነሻ የሆነችኝ
ሕሊናም ባለፈ ኑሮዋ ውስጥ የነበረውን ነገር በአሁኑ የመፈለግ ዝንባሌ ይታይባታል፡፡
ሕይወት ልክ እንደ መጽሐፍ በምዕራፍ በምዕራፍ የተከፋፈለች
ናት፡፡ ሁሉም ምዕራፍ አንድ ሊሆን ደግሞ አይችልም፡፡ ከሆነም ለመሰልቸት በጣም የቀረብን እንሆናለን፡፡ ስለዚህ አንቺም ከሁለቱ
ፍቅረኞችሽ ጋር የነበረሽ ጊዜ ልክ እንደ ሁለት ምዕራፍ የአንድ መጽሐፍ አካል አድርገሽ ውሰጂው እናም ቀጣዩን የሕይወትሽን ምዕራፍ
ሳታባክኚ በአግባቡ ኑሪ፡፡ በአንዱ መልካምነት ሁሉንም መልካም ማለት እንደማንችል ሁሉ ጥቂት ጥሩ ባልሆኑ ሰዎች ሁሉም ወንድ በጎነት
የለበትም ማለት አንችልም፡፡ ይልቅስ የሳልሽውን መልካምነት ስትጠብቂ የበለጠው መልካም እንዳያመልጥሽ በጽሞና አስቢ፡፡ ከበውቀቱ
ስዩም ግጥም ባነበብኩት እንሰነባበት፡፡ ማን ያግባሽ? አስተውላችሁ ግቡ!
አዳም የትላንቱ
የጥንት የጠዋቱ
ሳይለፋ ሳይታክት ተኝቶ ባደረ
ውኃ አጣጭ አቻውን ተጎኑ ተቸረ
ይብላኝ ለአሁኑ አዳም ለታካች ምስኪኑ
ምነው በተኛና በሸሸሁ ተጎኑ
ለምትል ሔዋኑ፡፡
የጌታ ደረጀ
6. የመወያያው ርዕስ ዋና አሳብ ሊሆን የሚገባው ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ ስለመስጠት እንደሆነ
ተረድቻለሁ፡፡ እንደዚህ ካሰብነው ደግሞ ከሁሉም በፊት ቀዳሚውን ስፍራ መያዝ ያለበት ፍቅር ነው፡፡ ፍቅርን ሀብትም አፍም አያመጡትም፡፡
ፍቅር ግን ሁሉንም ሊገዛ የሚችልበት ጉልበት አለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው የእግዚአብሔርን ልጅ ከዙፋኑ የሚያወርድ ፍቅር ባይኖረውም
ጌታን ለመስቀል ሞት ያበቃው ግን እርሱ ለእኛ ያለው ትልቅ ፍቅር እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ፍቅር እንኳን ምድራዊውን ሀብትና
የአፍ ብልሃት ይቅርና የጥበብና የማስተዋል ደግሞም የማይጨረስ ባለጠግነት ባለቤት የሆነውን ጌታ መግዛት (ማሸነፍ) የቻለው ፍቅር
ነው፡፡
ማን ያግባሽ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መሆን ያለበት “እውነተኛ
ፍቅር ያለው” የሚለው ትልቅ መልስ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ለአንድ ቤት መቆም የመሰረቱን ያህል ወሳኝ ነገር የለም፡፡ ፍቅር መሰረታችን
በሚሆንበት የትኛውም ጥምረት ዘላቂነት መከተሉ የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ ለጥያቄው ትክክለኛ መልስ መስጠት ካለብን ስለ ፍቅር መናገር
ብቻ ሳይሆን መኖርም አለብን፡፡
መዓዛ
Ye Egziabher hasab yalebet ginugninet new lemalet askedimen le ersu fikad megezat be'ersum metamen alebin. Mikinyatum neger hulu lebego new yetebalew besimu lemiyaminut ena ende geta hasab leteterut new!
ReplyDelete"Ewinetegna fikir yalew" yemilew letenesaw tiyake tikikilegnaw milash yimeslegnal. Lemanignawim gingnunet meseret mehon yemigebaw fikir newina!
ReplyDelete"Ewinetegna fikir yalew" yemilew letenesaw tiyake tikikilegnaw milash yimeslegnal. Lemanignawim gingnunet meseret mehon yemigebaw fikir newina!
ReplyDelete