(ውዴ ይህ ነው÷ ባልንጀራዬም ይህ
ነው)
መኃ. 5÷16
አንድ
ሕግ አዋቂ ወደ ኢየሱስ መጥቶ መምህር ሆይ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው፡፡ (ሉቃ. 10÷25) ጌታም ሕግ
አዋቂው በሕይወት ይኖር ዘንድ የሚችልበትን ትምህርትና ሊተገብረው የሚገባውን ነገረው፡፡ ዳሩ ግን ሕግ አዋቂው የመጣበት አላማ ጌታን
መፈተን እንጂ የሚረባውን አስተውሎ መመለስ ባለመሆኑ ሌላ ተጨማሪ ጥያቄ ጠየቀው፡፡ ሁሉን በሚችል አምላክ ፊት በፈታኝ ልብ መቆም
ምን ያህል አስፈሪ ነው? እርሱ ሁሉን ይመረምራል በማንም ግን አይመረመርም፡፡ እርሱ ሁሉን ይፈትናል በማንም ግን አይፈተንም፡፡
አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ለመስማት ስንሰበሰብ እንዲህ ያለውን
ልብ ይዘን እንቀርባለን፡፡ ከዚህም የተነሣ ለነፍሳችን ሊቀርላት የሚገባውን
ከማር ወለላ ይልቅ ለጉሮሮ ጣፋጭ የሆነው ትምህርት ሬት ሆኖብን፤ ለአገልጋዩም ፈተና ሆነን የምንመለስበት ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡
ከእባብ ልባምነትን እንድንማር የታዘዝን ሰዎች ከሰው ጥቂት መልካም ነገር መማር ያንንም በዚያው በተነገረበት መንፈስ መረዳት ካልቻልን
የእባብን ያህል እንኳን ልባምነት የለንም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚለን ቅን ተናገሩ ብቻ ሳይሆን በቅንነትም ስሙ ነው፡፡ በጎ
እየተናገርን በበጎ ካልሰማን፤ በፍቅር እየሰማን መልካሙን ካልተናገርን ሁለቱም በአንድ ጆሮ ሰምቶ በሌላው እንደማፍሰስ ነው፡፡
ሕግ አዋቂው ይህንን ከሚያህል እውቀቱ ማስተዋልን አለማትረፉ ምንኛ
ያሳዝናል? በእርግጥ እውነተኛ ማስተዋል የጥበብና የእውቀት ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር እውቀት ሁሉ እንጀራ እንጂ
ሕይወት አይሆንም፡፡ በሌላ ስፍራም ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነውን ኒቆዲሞስ ጌታ “አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን
ይህን አታውቅምን? (ዮሐ. 3÷10)” ብሎታል፡፡ ኒቆዲሞስ ሕግ አዋቂና ሳንሄድሪን የሚባለው የአይሁድ ሸንጎ አባል ነው፡፡ ነገር
ግን ጥልቅ የሆነውን የጌታ አሳብ መረዳት አልተቻለውም፡፡ በየትኛውም የሰው ሁኔታ ውስጥ ጌታ ትሁት ነው፡፡ ሕግ አዋቂው ለመፈተን
ቢመጣም ጌታ አዋርዶ አልሸኘውም፡፡ ይልቁንም እንዲህ ላለው ልቡ ርኅራኄ በማሳየት፣ ራሱን ያጸድቅ ዘንድ “ባልንጀራዬስ ማን ነው?”
በማለት ላቀረበው ጥያቄም ተጨማሪ ምሳሌ በመስጠት አሰናበተው፡፡ ማን ምን እያሰበ እንደሆነ እያወቀ የሚታገስ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
መልካሙን
አመል የሚያጠፋ ክፉ ባልንጀራ በበዛበት ዘመን ባልንጀራዬ ማን ነው? የሚለው ጥያቄ አስፈላጊ ነው፡፡ አብዛኛው ጥፋት የሚፈጸመው
በባልንጀራ ምክር ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ” (መዝ. 1÷1) ይላል፡፡ በክፉ ባልንጀራ ምክንያት
ብዙ ጎጆ ፈርሶአል፡፡ ጓደኞች ተቆራርጠዋል፡፡ የቆሙ ሰዎች ወድቀዋል፡፡ ለክፉዎች ምክር አለመሸነፍ ብፅዕና ነው፡፡ ስለ ምክር ከተነሣ የኢዮብን ሚስት እናስባታለን፡፡ እግዚአብሔርን
ስደብና ሙት ስለ ምን ፍጹምነትህን ትጠብቃለህ በማለት መከረችው፡፡ (ኢዮ. 2÷9) የሴቲት ምክር ምን ያህል አስገራሚ ነው? ምክር
የእርሷ ሲሆን ሞቱ ግን የእርሱ ነው፡፡
ሱሰኝነትን ለባልንጀራቸው ያስተማሩ ሰዎች ትምህርቱ የሚያመጣው
ኪሳራ ላይ የሉም፡፡ ስካርና ዝሙትን ያስተማሩ ሰዎችም ውጤቱ የሚያመጣው ስብራትና በሽታ ላይ የሉም፡፡ ተንኮልን፣ ክፋትን አቀብሎ
ሸሽ አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ የምንቸራውን ይሰጡናል አብረውን ሊያጭዱ ግን አይኖሩም፡፡ ኢዮብ ለገዛ
ሚስቱ ክፉ ምክር የሰጠው ምላሽ የእርሱን ጥንካሬ ያሰየ፣ የመካሪዋን ፍላጎት ያሳፈረ፣ ጌታ እግዚአብሔርን ደግሞ ያከበረ ነበር፡፡
የምንመከረውንም የምንመክረውንም የምናስተውልበትን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያድለን፡፡ እውነተኛ ባልንጀራ ትርጉሙ ከወንድምም ይበልጣል፡፡
ጌታ ሕግ አዋቂው ራሱን ለማጽደቅ ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ ለተሻለ
ትምህርት ተጠቀመበት፡፡ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ስለ ወረደ በዚያም ወንበዴዎች አግኝተው ስለ ደበደቡት በሞትና በሕይወት መካከልም
ሲሆን ትተውት ስለሄዱ አንድ ሰው ተረከለት፡፡ በዚያም መንገድ አንድ ካህን ሲያልፍ ምንም ሳይረዳው ገለል ብሎ አለፈ፤ ደግሞ አንድ
ሌዋዊ በዚያ ሲያልፍ እንደ ካህኑ ሁሉ ምንም ሳይረዳው ትቶት ሄደ፡፡ አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፡፡
ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው እስኪድንም ድረስ የሚያስፈልገውን ሁሉ ዋጋ ከፈለ፡፡ (ሉቃ.
10÷33)
ኢየሱስ
ክርስቶስ ምሳሌውን ከጨረሰ በኋላ ለሕግ አዋቂው “ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴ እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ነው?”
በማለት ጥያቄ አቀረበለት፡፡ እናንተስ የትኛው ይመስላችኋል? በዚህ ምሳሌ ውስጥ ለመጽናናት የሚሆን ትምህርት እናገኛለን፡፡ በወንበዴ
እጅ ለወደቀው ምስኪን በዚያ መንገድ ካህኑና ሌዋዊው ብቻ የሚያልፉ ቢሆን ኖሮ ምን ተስፋ ነበረው? ወድቆ ከመረሳት፣ ሞቶ ከመቀበር
ከዚህ የተሻለ የሚቀርለት ተስፋስ ምን ይሆን ነበር? እንደ ኢያሪኮ ባለው ስፋራ ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ እርዳታ ማግኘት ቀላል አይሆንም፡፡
ከተማይቱ በዓለም ላይ ከሚገኙ ከተሞች ሁሉ ዝቅተኛ እንደመሆንዋ
ለወንበዴዎች ዓመጽ ምቹ ማስፈጸሚያ በመሆን አገልግላለች፡፡ ካህኑና ሌዋዊው በወንበዴዎች ተደብድቦ መንገድ ላይ የወደቀውን ሰው ያልረዱት
መርዳታቸው ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው አስበው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምሳሌውን አማናዊ ስናደርገው ደግሞ ዋጋ ለመክፈልና የወደቀውን ሰው
ለማዳን የሚያስችል አቅም በእነርሱ ውስጥ አለመኖሩ ነው፡፡ ደጉ ሳምራዊ ግን ይህንን ምስኪን አይቶ አልፎ ይሄድ ዘንድ በእርሱ ያለው
ፍቅር አይችልም፡፡ የወደቀውን ሰው ሳይጸየፍ ይታቀፍ ዘንድ የሚችል የደጉ ሳምራዊ እጅ ብቻ ነው፡፡ የጨረቃ ከተማ ላይ ለወደቀው
ፀሐይ ካልወጣች በቀር መፍትሄ የለም፡፡ ጨረቃ ጨለማውን ተባብራ ታድራለች፡፡ ፀሐይ ግን ጽልመትን ገፋ በሚያስደንቅ ብርሃን ትቆማለች፡፡
በበደሉና በኃጢአቱ ሙት ለሆነው፣ የልቡን ፈቃድና የሥጋውን ምኞት
በመፈፀም ለሚረካው፣ ከፍጥረቱም የቁጣ ልጅ ለሆነው ሰው፣ በወንበዴው ዲያቢሎስ በክፉው እጅ ለወደቀው ሰው ተራ ባልንጀራ ሳይሆን
አዳኝ (ታዳጊ) ባልንጀራ ያስፈልገው ነበር፡፡ በቁስሉ ላይ ዘይት የሚያፈስ፣ የሚሰማ ብቻ ሳይሆን እንደ ችግረኛው የሚሰማው፣ ዲናሩን
አውጥቶ መድኃኒት የሚሆን የሚታደግ፣ የሚምር፣ የሚወድ፣ የሚሸከም ወዳጅ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!!
የአዳኝ ባልንጀራ ከወዴት ይገኛል
ክርስቶስ ላመኑት ከሁሉም ይለያል
ሌዊና ካህኑ ረግጠው ላለፉት
ኢየሱስ ይራራል ሳምራዊ ነው ያሉት፡፡
የአንደበትን ሳይሆን የልብ የሚሰማ
ኃጢአተኛን ወድዶ አብሮ የሚታማ
የጠፋውን ሊያድን ሕይወቱን የሰጠ
ኢየሱስ ብቻ ነው ታሪክ የለወጠ
አሳቡ እንደሚገባ ያልተብራራው ለአንባቢው ፍንጭ የማሳየትና በተሻለ አገላብጦ
ለማየት እንዲረዳ ሲባል ነው፡፡ በመሆኑም ከመነሻው ጀምሮ ያለውን በማመዛዘን ማጥናት ይቻላል፡፡ ማስተዋል ይብዛልን፡፡
'Ersu rasu tefetino mekeran siletekebele yeminfetenewin lireda yichilal' Amen mastewal yibzalin!
ReplyDelete'Eyesus bicha new tarik yelewete'...Tarikachin Eyesus new!
ReplyDeleteHi about Love, this is wonderful,blog. may God bless u.at all every thing that you have on this blog are grat
ReplyDelete