Friday, July 6, 2012

የመንደር ፍም



“የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት በላዩም ዕጣን አኖሩበት በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ፡፡ እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ፡፡ (ዘሌዋ. 10÷1)”
         በዘፍጥረት መጽሐፍ እግዚአብሔር በመልኩ (ጽድቅ፣ ቅድስና፣ እውቀት) እንደ ምሳሌው (ወኪል ገዥነት) የፈጠረውን የሰው ልጅ የታሪክ ጅማሬ (ልደት) እናስተውላለን፡፡ ሰው የመጨረሻው ቀን ፍጥረት እንደመሆኑ ለሰው የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ አስቀድመው ተፈጥረዋል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር አሳቢነትና ፍቅር ይስተዋላል፡፡ አንድ የስነ መለኮት አጥኒ “እግዚአብሔር ሰውን አስቀድሞ ፈጥሮት ቢሆን ኖሮ ሌሎቹ ፍጥረታት እስከ ዛሬ አይፈጠሩም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰው አስተያየት ሲሰጥና አሳቡን ሲቀያይር እንቅፋት ይሆናል፡፡” በማለት ሰው መጨረሻ የተፈጠረበትን ምክንያት ተናግረዋል፡፡ እግዚአብሔር ግን በዚህ ሁሉ አዋቂ ነው፡፡ እርሱ የሚያውቀውን መላእክቱና ቅዱሳኑ እንኳን አያውቁም፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፍጹም ጽድቅ ያለው ካለ እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፍጹም ቅድስና ያለው ካለም እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
        በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሰው ከተፈጠረ በኋላ ለተፈጠረበት ዓላማ ሲታዘዝ የምናየው አንድ ምዕራፍ ነው፡፡ በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ሰው ከእግዚአብሔር አሳብ ባለመታዘዝ ጠንቅ ሲለያይና ውድቀትን ሲያስተናግድ እንመለከታለን፡፡ ደግሞም እግዚአብሔር መንግስት ነውና በበደለው ሰው ላይ ቅጣትን ሲያስተላልፍ እናነባለን፡፡ አዳም ከበደል በኋላ በመልኩ እንደ ምሳሌው ልጅን እየወለደ (ዘፍ. 5÷1) በአንድ ሰው ምክንያት በደለኝነት ለሁሉ ደረሰ፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ እግዚአብሔር አብርሃምን እንደጠራ፣ በልጁ በይስሐቅ አንድያ ልጁን ክርስቶስን እንዳብራራ፣ በያዕቆብ የራሱን ሕዝብ እንደለየና የእስራኤል አምላክ እንደተባለ እናስተውላለን፡፡ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ከተሸጠ በኋላ የያዕቆብ ቤት ዕጣ ባርነት ሆነ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ በግብጽ ልክ እንደ አንድ ሰው በባርነት የአብራካቸውን ክፋይ ከጡብ ጋር እየረገጡ ተገዙ፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ላደረገው ሕዝብ የኃጢአቱ ደመወዝ ነበር፡፡
       በቀጣይ የምናገኘው መጽሐፍ ኦሪት ዘፀአት ሲሆን ይህም የመውጣት መጽሐፍ ይባላል፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ በባርነት ቀንበር ስር እንደወደቀ ያየነው የእስራኤል ሕዝብ ነፃነቱ የታወጀው በዚህ መጽሐት ውስጥ ነው፡፡ የፋሲካውን በግ ደም በመቃንና በጉበናቸው ላይ ቀብተው ግብጽን የለቀቁበትን አስደናቂ መዳን እናስተውላለን፡፡ እግዚአብሔር በጸናችና በተዘረጋች እጅ ሕዝቡን ከጨቋኝ ገዥአቸው አላቆ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ ጉልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው! በሚል ምስጋና አፋቸውን በእልልታ ሞላው፡፡
       እግዚአብሔር ሕዝቡን አዳነ ስንል መጀመሪያ የሚፈጠርብን ጥያቄ ከምን? የሚል ነው፡፡ የእስራኤል ሕዝብ በኃጢአታቸው ምክንያት ለኃጢአት ውጤት ባርነት ተዳርገዋል፡፡ ስለዚህም ከዚህ የባርነት ኑሮ የሚያድናቸው ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ በእነርሱ የፍላጎት ጊዜ ውስጥ አልተከናወነም፡፡ የሰው አቅም ሲሟጠጥና የሰው ብቸኛ አዳኝ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ሕዝቡ ሲረዳ እግዚአብሔር ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ ራሱን ምክንያት አድርጎ እርሱ በወደደውና በላከው ሙሴ ባርነት ታሪክ ሆነላቸው፡፡
       እስራኤል በበጉ ደም ዳኑ በማለት ስለዳነ ሰው ስናወራ ሌላው የምንጠይቀው ጥያቄ ሊሆን የሚችለው  መዳን ለምን? የሚለው ነው፡፡ የዘሌዋውያን መጽሐፍም የሚመልስልን ይህኑ ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ ስለ አምስቱ መሥዋእቶች ማለትም የሚቃጠል፣ የእህል፣ የደኅንነት፣ የኃጢአት እና የበደል መሥዋእት ስናነብ ከግብጽ ባርነት እግዚአብሔር ሕዝቡን ነፃ ያወጣበት ዓላማ እንዲያገለግሉትና እንዲያመልኩት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይህ አሳብ ግን እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያደረገውን እንደ መደራደሪያነት አቅርቦታል የሚል ትርጉም አይሰጥም፡፡ ምንያቱም በማምለክ ውስጥ ያለው ጥቅምና በረከት ለሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን በየትኛውም መንገድ ማለትም በመመለክ ቢሆን ባለመመለክ፣ በመገልገል ቢሆን ባለመገልገል ሁሉ ከእርሱ በእርሱ ለእርሱ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር ሊመለክና ሊገለገል እንዴት እንደሚገባው ለሕዝቡ መመሪያን ሲሰጥ እንመለከታለን፡፡
        አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ደስታ ከእኛ ደስታ፣ የእግዚአብሔርን ፍላጎት ከእኛ ፍላጎት አንፃር ለመዳኘት ስንሞክር ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ማንኛውም እንቅስቃሴአችን በተለይ አምልኮ ከእግዚአብሔር አሳብና ፈቃድ አንፃር ይመዘናል እንጂ እግዚአብሔርን በእኛ ልምምድ ላይ እንዲደገፍ ማድረግ አንችልም፡፡ ምክንያቱም መንፈስ የሆነውን እግዚአብሔር በመንፈስ ሆነን ካላደመጥነው በቀር አሳቡ ከአሳባችን መንገዱም ከመንገዳችን በእጅጉ የራቀ ነው፡፡
        በነቢዩ በሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር የእስራኤል ንጉሥ ያደረገውን ሳኦልን የናቀበት መንገድ የሰውና የእግዚአብሔር አተያየት ምን ያህል የተራራቀ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ እስራኤል ከግብጽ ወጥተው በምድረ በዳ በሚያደርጉት ጉዞ ብርቱ ተቃዋሚዎቻቸው አማሌቃውያን ነበሩ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሊበቀልለት ሳኦልን ላከው፤ ፈጽሞም እንዲያጠፋቸው እንዳይምራቸውም በማስጠንቀቂያ ጭምር አዘዘው፡፡ ሳኦል ግን የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን ማርኮ፣ ለእግዚአብሔር ሕዝቡ ይሠዉአቸው ዘንድ መልካሞቹን በጎችና በሬዎች ይዞ ተመለሰ፡፡ በሰው ሰውኛው ስናስበው ሳኦል ለእግዚአብሔር የቀና መልከ መልካሙን ያደረገ ይመስላል፡፡ ዳሩ ግን አለመታዘዝ በየትኛውም ያማረና የተዋበ ነገር ውስጥ ቢሸሸግ ሁሉን ከሚችል አምላክ ፍርድ ሊሰወርና ሊሰውር አይችልም፡፡ (1 ሳሙ. 15) እግዚአብሔር ለጨከነበት ብንራራ፤ እግዚአብሔር በራራለት ላይ ደግሞ ብንጨክን ሁለቱም ራስን በእግዚአብሔር ፊት ለማጽደቅ መሞከር ነው፡፡ የሰው ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ዋጋ ኢዮብ እንዳለው ራስን የመናቅ ያህል ነው፡፡ (ኢዮ. 42÷5) ስለዚህ እግዚአብሔር በጨከነበት ነገር ላይ መጨከን ለእውነት ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን የትኛውም ግንኙነት “እርሱ እንዳለ” የሚል መሆን አለበት፡፡
          በርእሳችን ላይ ያነሣነው ክፍል የሚነግረንም ይህንን ነው፡፡ የአሮን ልጆች በየራሳቸው ጥናውን ወስደው በእግዚአብሔር ፊት እሳት አደረጉበት በላዩም ላይ እጣን ጨመሩበት፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለው ስህተት ምንድነው? የሚለው ጥያቄ የምንነጋገርበት ማእከል ነው፡፡ ናዳብና አብዩድ ያደረጉት የተለመደውን ተግባር ቢሆንም በዚህ ውስጥ ግን የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚቀሰቅስ ሌላ ድርጊት እናስተውላለን፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ያላዘዘው “ሌላ እሳት” ነው፡፡ ልብ የምንላቸው ብዙ ነገሮች በዚህ ትምህርት ውስጥ እንደተካተቱ ማስተዋል ከእግዚአብሔር ፍርድ ያስመልጣል፡፡ ሌላ ጥና አልያም ሌላ እጣን እንደወሰዱ አልተነገረንም፡፡ ነገር ግን ሌላ እሳት (እንግዳ እሳት) እንዳቀረቡ ተጠቅሷል፡፡ እንግዲህ የአሮን ልጆች የከፋ ኃጢአት ሌላ እሳት እንደሆነ እንረዳለን፡፡
        የዘሌዋውያን መጽሐፍ ከፍጥረቱ የቁጣ ልጅ የሆነው የሰው ልጅ በበደሉና በኃጢአቱ የሞት ባርያ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለሆነ በእውነትና በመንፈስ ያመልክ ዘንድ በልጁ በክርስቶስ ያዳነውን ክርስቲያ የምናይበትን ትምህርት የሚሰጠን ክፍል እንደመሆኑ ከዚሁ አንፃር ሕይወታችንን መፈተሽ ይጠበቅብናል፡፡
         የአሮን ልጆች እሳት ከእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ መውሰድ እንዳለባቸውና አምልኮም በዚህ መንገድ መሆን እንደሚገባ በግልጥ የተቀመጠላቸው መመሪያ እያለ ከመገናኛው ድንኳን ውጪ የመንደር ፍም ያቀረቡበት ምክንያት ከመገመት የከበደ አይሆንም፡፡ በድፍረትም (ምን ይመጣል) ይሁን በቸልተኝነት (ምን አለበት) ጉዳዩ አለመታዘዝ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ቤት በሌላ እሳት የማርከስ እንዲሁም ክብሩን የማቃለል ሂደት ነው፡፡ ሰው ከራሱ ካለው ወስዶ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኘው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእኛ የሚሠራ እግዚአብሔር ነው፡፡ (ፊል. 2÷13) ጌታ እንኳን ስለ እውነት መንፈስ ሲናገር “ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል” (ዮሐ. 15÷13) ብሏል፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው ከእርሱ በእርሱ ለእርሱ በማድረግ ነው፡፡ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ ቸልተኝነትና ዓመጽ ቢታይም እግዚአብሔር ግን በናዳብና አብዩድ ላይ የነበረው አይን ዛሬም በዙሪያችን ነው፡፡ በኃይለኛው በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ምንኛ አስፈሪ ነው?
       በመንደር ፍም እግዚአብሔር ፊት ለመቆምና ደስ ለማሰኘት መትጋት በዘመናችን በእጅጉ የሚስተዋል ሐቅ ነው፡፡ ሰዎች በድፍረት የእግዚአብሔርን አሳብ ሲያጣምሙ፣ መንፈስ ቅዱስን ተክተው መለኮታዊ በሆነው መመሪያ ላይ የሥጋና የደም ምክራቸውን ሲያቆሙ፣ እውነትን ገፍተው ፊደላዊ ለሆነው የሞት አገልግሎት ሲፋጠኑ እየተመለከትን ነው፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር እሳት በመሠዊያው ላይ ያለውን መሥዋእትና ስብ እንደምትበላ ሁሉ በመሠዊያው ላይ የሚዘብቱትንም ዘባቾች ትበላለች፡፡ እስቲ የመንደር ፍሞችን (እንግዳ እሳት) ወደ ሕሊናችሁ በማምጣ ጥቂት አስቡ፡፡ በቤቱ ላይ ማዘዝ የራስ ሙሉ መብት አይደለምን? ከገዛ ቤቱ በስተውጪ ተጥሎ ማንኳኳ ይገባዋልን? ሀብታም ነኝ ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም ማለት፤ ጎስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም መራቆትንም አለማወቅስ ከፍርድ ያድናልን?
     የአሮጌው ሰው ማንነት ሁለቱም እሳት አይደለምን? ችግሩ ምኑ ላይ ነው? እንዲህና እንደዚያ? በማለት ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ካለ ሰው ከአሳቡ ጋር ይታገል ዘንድ አግባብ አይደለም፡፡ አምልኮ በእግዚአብሔር እሳት እንጂ በመንደር ፍም (ስሜት፣ የሰው የበላይነት፣ ተረት፣ እኔነት፣ የሰው ብልሃት፣ ለዚህ ዓለም የሚመች አካሄድ፣ ማስመሰል) ጌታን አያከብርም፡፡ የአክዓብ ሚስት ኤልዛቤል እግዚአብሔር ፍርዱን ነቢይ በሆነው በኢዩ አማካኝነት በገለጠ ጊዜ ውድ በሆነ ጌጣ ጌጥ ራስዋን አስጊጣ ደግሞም ዓይኖቿን ተኳኩላ ጠበቀችው፡፡ (2 ነገ. 9÷30) የቱንም ያህል ብትዋብ ግን ከእግዚአብሔር ቁጣ መዳን አልቻለችም፡፡ ምክንያቱም ጌጧ የዚህ ዓለም፤ ኩሏም የሰው ኩል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ዝርግፍ ጌጥ የሆነላቸው (ኤር. 2÷32) በእርሱም ኩል የደመቁ (ራዕ. 3÷18) ሁሉ ከፍርድ አምልጠዋል፡፡ አንተስ?
    ተወዳጆች ሆይ ቤተ ክርስቲያን እየታመሰች ያለችው በመንደር ፍም ነው፡፡ ለእውነት ሳይሆን ለጥቅም ባደሩ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ለልባቸው አሳብ በተሸነፉ፣ ለክብሩ ሳይሆን ለክብራቸው ዘብ በቆሙ ወገኖች ምክንያት የሥጋ አቅም እየገነነ የመለኮት ፈቃድ ደግሞ ወደ ጎን እየተተወ ነው፡፡ ለአንድ እውነተኛ ክርስቲያን ደግሞ ይህንን መለየትና ከዚህ ዓመጽ ራስን መለየት የተገባ ነው፡፡ ልባቸው በእውነት መንፈስ ሳይሆን በመንደር ፍም በተሞላ አስመሳዮች ብዙዎች እየተቃጠሉ ነው፡፡ ቅን ፈራጅ የሆነው ጌታ ግን በዙፋኑ አለ፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሕያው በሆነው በእርሱ ፊት በመንደር ፍም ፊቱ እንዳንቆም ለዘላለም ይጠብቀን፡፡ 

2 comments:

  1. It's very interesting issue. Let God keeps us from looking other way zan z way he gives 4us!

    ReplyDelete
  2. Amen! It touchs ma heart nd rly it's contemporary issue. God bless u!

    ReplyDelete