Wednesday, May 15, 2013

የሰው ልጅ እንጀራ



                                 እሮብ ግንቦት 7/2005 የምሕረት ዓመት

         አገልግሎት አንድ አካል ብቻውን የሚያደርገው ነገር ሳይሆን ሁሉም ምዕመን ተገናዝቦና ተባብሮ የሚያከናውነው ተግባር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደ ክርስቶስ አካል በምትተረጎምበት ሁኔታ እኛ ሁላችን የክርስቶስ አካል ብልቶች ነን (ሮሜ. 12÷5)፡፡ ሁላችንም በአንዱ ክርስቶስ አንድ ልብ አለን (1 ቆሮ. 2÷16) አንዲሁም አንዱን ምግብ (የእግዚአብሔር ቃል) ሁላችን እየተመገብን በህብረት እናድጋለን፡፡ ነገር ግን ጤነኛ ምግብ መመገባችንን እርግጠኛ ልንሆን ይገባል፡፡ መመገብ ውድቀትን ተከትሎ የመጣ እርግማን አይደለም፡፡ ከሰው ተፈጥሮ ጋር የተያያዘ የእለት ከእለት ተግባር እንጂ፡፡ በውኑ ምንድነው የምንመገበው? ክርስቶስ በምድር  ላይ ሲመላለስ በአንድ ወቅት በሰማርያ ደክሞት አረፍ ብሎ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ ሊገዙ ሄደው ነበር መጥተውም ብላ ብለው ይለምኑት ጀመር፡፡ እርሱም የበላ መሆኑን ሲገልጽላቸው ሰው አምጥቶለት ይሆንን ተባባሉ እርሱ ግን የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው አላቸው (ዮሐ. 4÷34)፡፡

         እንግዲህ ክርስቶስ ሊያገለግል እንጂ ሊገለገል አልመጣም (ማቴ. 20÷8) እንደተባለው እርሱ በምድር በተመላለሰበት የሥጋው ወራት ሁሉ የአባቱን ፈቃድ ማድረግ ቋሚ ትጋቱ ነበረ፡፡ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን እውነተኛ ዓላማ እስኪፈጽም ድረስም እረፍት አልነበረውም፡፡ መብሉ የአብን ፈቃድ መፈጸም ነበርና መንፈሳዊ ርሀብ አልነበረበትም፡፡ ጌታ በቃልና በኑሮ አባቱን ደስ ያሰኘ ልጅ ነበር፡፡ በሙላት የተመገበ ሰው ለአባቱ ደስታ ነው፡፡ እኛም ይሄ ነው! የተጠራንለት ዓላማ ሁሌም ፈቃዱን መፈጸም ሁሌም ቃሉን መመገብና በቃሉ መሞላት፡፡


         በዚህ ዘመን የምናየው ግን ከዚህ በተለየ መልኩ አንድ በላተኛ ብዙ ተመልካች ነው፡፡ አንድ አገልጋይ ቆሞ ይሰብካል ሌላው ተቀምጦ ያዳምጣል፤ እድገት የለም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የበይ ተመልካች ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ሁሉም አማኝ አገልጋይ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም አካል ነውና እግርም፣ እጅም የየራሳቸው ሥራ አላቸው፡፡ እግር ከተያዘ መራመድ የለም፡፡ እጅ ከተያዘች መጉረስ የለም፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ሁሉም እንደተሰጠው ጸጋ እርስበርስ ተያይዞ የሚያድግበት ስፍራ እንጂ አንዱ አፍጥጦ ሌላው የሚቀለብበት የባሪያና አሳዳሪ ኑሮ አይደለም፡፡ አገልግሎት የሕይወት ምስክርነት ጭምር ነው፡፡ የተለወጠው ሕይወታችን የሚገለጥበት ስፍራ፣ የሚታይበት መድረክ አገልግሎት ነው፡፡ ያመነውን ጌታ በሰው ሁሉ ፊት የምናሳይበት ቦታ ነው፡፡

         በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን እለት እለት መጨመርና መብዛት የነበረው ሁሉም በተለወጠና በአዲሱ ሰው ማንነት ይንቀሳቀሱ ስለ ነበረ ነው፡፡ ስናገለግል ሁሌም እናድጋለን፡፡ የሰማርያዋ ሴት ከነበረችበት ከንቱ ኑሮና የሕይወት እንቆቅልሽ አላቆ በአዲስ ሕይወት ዓይኗን ከፍቶ፣ እንስራዋን አስጥሎ፣ አለማመኗን ገፎ፣ በአገልጋይ ሥልጣን የወጣችው፤ |ያዳነኝን ኑና እዩ እስክትል ድረስ መንፈሳዊ ድፍረት ያገኘችው የአባቱን ፈቃድ ሊፈጽም በመጣው (መብል) በክርስቶስ ነበር፡፡ ከሕይወት ውሀ ወንዝ የሰዎችን በርሃ ኑሮ ማርካት፣ የሰውና የእግዚአብሔርን ግንኙነት እንደ ገና ማደስ፣ በእውነትና በመንፈስ የሆነውን አምልኮ መግለጥ፣ የዓለም ቤዛ እርሱ የሚመጣው መሲሁ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማሳመን፣ ልዩነትን ማስወገድ(የአይሁድና የሳምራውያንን በጊዜው)፣ ሁሉን በፍቅር ማየት፣ ራስን ዝቅ ማድረግ፣ ከአንዲት ውሃ ልትቀዳ ከመጣች ሴት ጋር ማውራት የእርሱ መብል ይህን ነበር፡፡ጌታ ደቀ መዛሙርቱን የጠበቃቸው እንግዲህ ባለ አገልግሎት ነው፡፡ ትህትና፣ ፍቅር፣ የዋህንት፣ ምስክርነት ነው፡፡

          አገልግሎት እንጀራ መግዛት ሳይሆን ቁጭ ብሎ መብላት ነው፡፡  አንድ አገልጋይም በጌታ አግር ስር ያረፈና ቃሉን ያጣጣመ መሆን አለበት፡፡ በአንድ ወቅት ጌታ በአላዛር ቤት በተገኘ ጊዜ ማርታ በብዙ ትደክም ነበር፡፡ ማርያም ግን ከእግሩ ስር ተቀምጣ ቃሉን ታደምጥ ነበር፡፡ ጌታም ማርታ በብዙ አትድከሚ ነበር ያላት፡፡ ማርያምን ግን በጎ እድልን መረጥሽ ነው ያላት፡፡ የዚህ ዓለም እንጀራ ድካም ብቻ መሆኑን ነው የሚያስተምረን፡፡ ማረፍ ቃሉንም መመገብ በውበትም ሳይጠወልጉ ጌታን መስበክ እንዴት ነፍስን በሀሴት ይሞላል? እንደዛ እንደ ኤማሁስ መንገደኞች እየጠወለግን አይደለም በመንገድ ስለ ጌታ መመስከር ያለብን፡፡ እንደጌታ አረፍ ብለን በፍቅር እንጂ፡፡ አገልግሎታችን ከጌታ ፍቅር የተነሣ ከሆነ ዘመን ይሻገራል፡፡ ምክንያቱም ጌታ ፍቀር ነውና!!

2 comments:

  1. Tebarek tsegaw abezeto yebezaleh Amennnnnnn

    ReplyDelete
  2. hulachinm endeteseten tsega meten befikir endinagelegil Egziabher mastewalun yabzalin! enantenim Egziabher yibarkachihu!

    ReplyDelete