Wednesday, May 22, 2013

እየሆነ ያለው . . . (ክፍል አንድ)


                             እሮብ ግንቦት 14/2005 የምሕረት ዓመት

         የእግዚአብሔር ጸጋና ሰላም፤ ምሕረትና ፍቅር የበዛላችሁ፤ መኖራችሁ ከዚህ የተነሣ እንደ ሆነ የአፍና የልብ ምስክርነት ያላችሁ ተወዳጆች ሆይ ሕይወት እንዴት ነው? መቼም ሰው ሁሉ እንደ አንድ የሚጠላው ጥያቄ ይህ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ጥያቄው ከተሸከመው ቁም ነገር የተነሣ ቢከብደን የሚገርም አይሆንም፡፡ በዚህ ምድር ከሕይወት በላይ የበለጠ ምን ርዕስ ሊኖር ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ራሱን ያብራራበት ትልቁ መንገድ “ሕይወት ነኝ” የሚል ነው (ዮሐ. 14÷6)፡፡ የየትኛውም ቤተ እምነት አስተምህሮ ለሕይወት ዋጋ ይሰጣል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ልክ እንደ መጽሐፉ “ወልድ የሌለው ሕይወት የለውም” (1 ዮሐ. 5÷2) በማለት ዕለት ዕለት ትመሰክራለች፡፡

         በእድሜያችሁ ከሰዎች ጋር በብዙ ዓይነት ርዕስ እንዳወራችሁ እገምታለሁ፡፡ ዳሩ ግን ምን ያህሉ ሕይወት ነበረበት? አልያም ምን ያህሉ የሕይወትን ያህል ዋጋ ነበረው? የእግዚአብሔር ቃል “አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር” (ቲቶ. 2÷1) በማለት ያስጠነቅቀናል፡፡ ይህ ቃል ተናጋሪውን ብቻ እንደሚመለከት ልታስቡ ትችላላችሁ፡፡ ዳሩ ግን ለሰሚውም የዚያኑ ያህል መልእክት አለው፡፡ የስንቶች ጆሮ ስለ ሕይወት ለመስማት ወኔው አለው? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ምላሳችን ላይ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ጥያቄ ለራሳችን ባቀረብንባቸው ጊዜያቶች ሁሉ ከውስጠታችን ጋር ተዛዝበናል፡፡

       አሁን በዚህ ሰዓት በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በአንድም በሌላም ምክንያት ተገናኝቶ በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያወራል፡፡ መረጃ ይለዋወጣል፡፡ ይከራከራል፡፡ ደግሞም ይካሰሳል፡፡ እባካችሁ በሁላችንም ሞት ይሁንባችሁና አሁን በዚህ ቅጽበት በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ እያወራችሁ እንደ ሆነ ቆም ብላችሁ አስተውሉ፡፡ የማታወሩ ደግሞ ካላስቸገርኳችሁ በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ እያሰባችሁ እንደ ሆነ አስተውሉ፡፡ በዚያ በምታስቡት አልያም በምታወሩት ውስጥ ሕይወት የሆነው ነገር ምን ያህል ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ሚዛን ላይ ይቅርና እናንተ ሚዛን ላይ እንኳ ክብደቱ ስንት ነው? ብዙ ዜናዎችን የምትከታተሉ ከሆነ የሰዎች ቀልብ የሚሰለብበት፣ ዓይን ፈጦ ጆሮ የሚቆምበት ምን ዓይነቱ የወሬ ርዕስ ነው? መርዶ መርዶው አይደለምን? ሰውን እንዲህ ካለው የሞት ወሬ ጋር ያያዘው ጉዳይ ምን ይሆን? ድህነት ነውን? አለመሰልጠን ነውን? ወይስ አማራጭ ማጣት ይሆን? ወይስ . . . . !


       ሰዎች ሕይወትን ገፍተው ስለ ምን ሞትን ያሻትታሉ? ወገኖቼ ስለ መለያየትና ጥላቻ ተጨንቀው ሳይቀር የሚያወሩት የፍቅር ወሬ አልቆባቸው ይሆን? ሰዎች ለጸብና ክርክር ዓይናቸው የሚፈዘው ደግና በጎው ተነቦ አልቆ ነውን? እንጃ! እነሱና እግዚአብሔር ያውቃሉ፡፡ የለም! አንዳንዶች ግን የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ እኔም የምጽፈው “ሳያውቁ በስህተት” የሚለው ለሚመለከታቸው ነው፡፡ ግን አውቀው በድፍረት ለሚያደርጉስ ያው አይደለምን? የምጽፈው ሁሉን እንዲያስብ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እስቲ ወዲህ ተመለሱና ጥቂት አሳቦችን እንነጋገር፡፡ መቼም እኛና ጠባያችን የዓመትና የወር፤ የሳምንትና የቀን ትንግርት ነው፡፡ ተማሮም አማሮም፣ ነፍጎም ለግሶም፣ አጥቶም አግኝቶም፣ ለብሶም ታርዞም፣ ስቆም ተከፍቶም ተስፋ መቁረጥ የጋራ ትግላችን ነው፡፡ ሰው የማጣት ጫፍ ላይ ሆኖ ሞቱን እንደሚመኝ ሰምተን አንደቅ ይሆናል፡፡ ሰው የማግኘት  ጠርዝ ላይ ደርሶም የዚያኛውን ጫፍ ያህል በጥያቄዎች የተሞላ መሆኑ ግን አግራሞት ይጭራል፡፡ እንደ እውነታው ግን የሰው ኑሮ ይኸው ነው፡፡

       በሚታየው ነገር ውስጥ የማይታየውን፣ በሚዳሰስ ነገር ውስጥ የተሰወረውን፣ በጊዜው ውስጥ የዘላለሙን፣ በሚጠፋው ውስጥ የጸናውን  የማደን ጥረት፣ በለስ አልቀናኝም አይነት ከንቱ ድካም ለሰው ከዚህ በቀር ትርፉ ምንድነው? ሐዋርያው “የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው (2 ቆሮ. 4÷17)” በማለት እየሆነ ያለው ነገር ከተደረገልን እንደማይበልጥ ያስረዳናል፡፡ በሰው ውስጥ ከምናየው ነገር አንዱ ማነፃጸር አልያም ማወዳደር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የእግዚአብሔርን አሳብ እየነገረን ያለው ንጽጽራዊ በሆነ መንገድ ነው፡፡ የማይታየው ከሚታየው ጋር፣ የጊዜው ከዘላለም ብዛት ጋር፣ መከራ ከክብር ጋር በግልጥ ተነፃጽረዋል፡፡

     በዚህ ምድር ለሰው የማይለመድ የዘወትር አዲስ ነገር መከራ ነው፡፡ በሰማይ ወደ ፊት ለሰው የማይለመድ አዲስ ነገር ቢኖር ደግሞ ክብር ነው፡፡ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ስቃይ ጋር ሳንላመድ ከፍቶን ኖረን እንደምናልፍ፤ ከዚያኛው ዓለም ክብርና ደስታ ጋርም እንዲሁ ሳንላመድ አርፈን ለዘላለም እንኖራለን፡፡ በሚታየው ዓለም የማይታዩ ብዙ አመፆች አሉ፡፡ በማይታየው ዓለም ደግሞ በመንፈስ የምናስተውላቸው ብዙ በረከቶች አሉ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚታየውን የጊዜው ነው በማለት የማይታየውን አጽንቶ ይነግረናል፡፡ እርሱ ባጸናው ያጽናን!         
                                   
                                       . . . ከሆነልን አይበልጥም፡፡
                                                                          
                                      


2 comments:

  1. ይህን አስተያየት የምጽፈው ከላይ ላለው ጽሁፍ ሳይሆን ስለአጠቃላይ ጽሁፉ ነው። ትላንትና በአጋጣሚ ይህንን ብሎግ ተመልክቼ አንዱን ጽሁፍ ብቻ ማንበብ አልሆንልህ ብሎኝ በጣም ብዙ ጽሁፍ ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ አነበብኩ እጅግ ብዙ የሆኑ ጠቃሚ ምክሮችን ከእያንዳንዱ ጽሁፍ አገኘሁ ።“ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።” ፊል 2.13 እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ አስቀድሜ እግዚአብሔርን አመሰገንኩ ቀጠልኩና ይህን ጽሁፍ ለምትመግበን(ቢን) ወንድም ወይም እህት ላመሰግን ይህችን አስተያየት ጻፍኩኝ። በጣም ከገረመኝ ነገር መካከል ምናልባት እኔ ስለኮምፒተር ብዙ እውቀት ስለሌለኝ ሊሆን ካልቻለ በስተቀር የዚህን ጽሑፍ ጸሐፊ ስም ወይንም ጾታ እንኳን ላውቅ አልቻልኩም። ይህ ሆን ተብሎ ተደርጎ ከሆን ብጽዕና ነውና እግዚአብሔር የዚህን ብሎግ ጸሐፊ በጸጋ ይጠብቅ እላለሁ።ከዚህ በተጨማሪ አሁንም የዚህን ብሎግ ጸሐፊ የምለምነው ፍጻሜው እንዲያምር ነው። አስተውላችሁ ከሆነ ብዙዎች በመንፈሳዊ ስም የተጀመሩ ብሎጎች ፍጻሜ የፖለቲካ መድረክ መሆን ነውና ይህ በዚሁ ይቀጥል የፖለቲካ ብሎጎች በቂ ስላሉን

    ReplyDelete
  2. Amen esu batsenaw yatsinan! bizu yetemarkubet tsihuf new. Egziabher kezihm belay tsegachihun yabzaw!

    ReplyDelete