ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን 2006 የምሕረት
ዓመት
ልጄ ሆይ፤ በነገርህ ሁሉ የታመንህ ሁሉ፡፡ በአነጋገርህም ደማም ሁን፡፡
ሰውን የሚያስፈራና የሚያሳዝን ነገር ለመናገር አትድፈር፡፡ በልዝብ ምላስ ሰውን አታታል፡፡ ሰውንም ከሚያሙ ሰዎች ጋር አትደባለቅ፡፡
ልጄ ሆይ፤ ንብረትህ በልክ ይሁን፡፡ ቤተ ሰዎችም አታብዛ የቀንድ ከብትና የጋማ ከብትም በብዙ አታርባ፡፡ ላንተ የማይገባውን ነገር
ከማንም ቢሆን አትቀበል፡፡ አንተም ለማንም ቢሆን የማይገባውን ነገር አትስጥ፡፡ የማታገኘውንም ነገር አትመኝ፡፡ በዓይንህ ካላየህና
እርግጥ መሆኑን ካልተረዳኸው በቀር በማንም ሰው ላይ የሚወራውን ወሬ እውነት ነው ብለህ አትቀበል፡፡ ለሰውነትህ የሚያስፈልገውን
ነገር ለማግኘት አስብ እንጂ ሰው የሚጠፋበትን ሰው የሚጨነቅበትን ነገር አታስብ፡፡
ልጄ ሆይ፤ ሮጠህ ለማታመልጠው ነገር አትሽሽ፡፡ እርሱም ሞት ነው፡፡
ደጋ ብትወጣ፤ ቆላ ብትወርድ፤ ወንዝ ተሻግረህ ብትሔድ፤ በዋሻ ብትደበቅ፤ ጠመንጃና መድፍ ይዘህ ብትሰለፍ ምንም ቢሆን ከሞት ለማምለጥ
አትችልም፡፡ እግዚአብሔርንም ፍራ በሥጋና በነፍስ ላይ ሥልጣን አለውና፡፡ ንጉሥንም አክብር እግዚአብሔር ሠይፍን አስታጥቆታልና፡፡
በአንተም ላይ የሹመት ሥልጣን ያላቸውን አገረ ገዢዎችን ሁሉ አክብራቸው፤ ታዘዝላቸው፡፡ አባትና እናትህን፤ የእግዚአብሔርን ቃል
የሚያስተምሩህን መምህሮችህን፤ የሀገር ሽማግሌዎችንና ባልቴቶችን ሁሉ በሚቻልህ ነገር እርዳቸው፡፡
ልጄ ሆይ፤ ካረጀህ በኋላ እንደ ገና ተመልሼ ምነው ልጅ በሆንኩ ብለህ
አትመኝ፡፡ ምንም ቢሆን አታገኘውምና፡፡ ወደፊትም ምነው በሞትኩ ብለህ አትመኝ፤ ምንም ቢሆን አይቀርልህምና፡፡
ልጄ ሆይ፤ እገሌ ቸር ነው ይበሉኝ ብለህ ገንዘብህን ለማንም አትስጥ፡፡
ለወዳጅ ከመስጠት ለዘመድ መስጠት ይሻላል፡፡ ለጠላት ከመስጠት ለወዳጅ መስጠት ይሻላል፡፡ ከሁሉ ይልቅ ለተቸገሩ ድሆች መስጠት ይበልጣል፡፡
ለድሆች የሰጠ ሰው ብድሩን በሰማይ ያገኛል፡፡
ልጄ ሆይ፤ ማናቸውንም ነገር ቢሆን ለመስማት እንጂ ለመናገር አትቸኩል፡፡
ከወዳጅህም ጋር በተጣላህ ጊዜ ቀድሞ በወዳጅነታችሁ ጊዜ የነገረህን ምስጢር አታውጣበት፡፡ ከወዳጅህም ጋራ አንድ ጊዜ ጠብ ከጀመርክ
በኋላ፤ ምንም ብትታረቅ ሁለተኛ ምስጢርህን ለእርሱ ለመናገር አትድፈር፡፡ ቂምህንም አትርሳ፡፡ ቂምህን አትርሳ ማለቴ ከታረቅህ በኋላ
ክፉ አድርግበት ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን እርሱ ሞትንና ኩነኔን የማያስብ ክፉ ሰው የሆነ እንደ ሆነ እርቅ አፍርሶ እንዳያጠፋህ
ሳትዘናጋ ተጠንቅቀህ ተቀመጥ ማለቴ ነው፡፡