Monday, March 5, 2012

ቅን



       ኑሮ ሕሊና ውስጥ ነው፡፡ በእዚህ ውስጥ ያለውም ትልቁ የማሸነፍ ኃይል ቅንነት (አዎንታዊ አመለካከት) ነው፡፡ የሕይወትን ሠልፍ በማሸነፍ ሒደት ውስጥ አዎንታዊ አስተሳሰብ ያለው ድርሻ የጎላ ነው፡፡ ካለን ጥበብ ይልቅ ብልሀታችንን የሚመራው አመለካከት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ኖሮን ነገር ግን እውነተኛ አስተሳሰብ ከሌለን ሕይወትን በግርድፉ የምንኖር ምስኪኖች እንሆናለን፡፡ አስተሳሰባችን ለማንኛውም ሁኔታ ምላሽ የምንሰጥበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ልዩነት የሚፈጥረው አንድ ሰው በሕይወት ውስጥ ያገኘው ነገር ሳይሆን ሕይወትን የተቀበለበት መንገድ ነው፡፡

      ጌታ በመስቀል ላይ ሳለ ሁለት ወንበዴዎች አብረው ተሰቅለው እንደነበረ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ለዘመናት ያስተሳሰራቸው ተመሳሳይ አሳብ አንድ ዓይነት ዓላማ ክርስቶስ በመካከላቸው ሲሆን እንደነበረ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ጌታ ለአንዱ ቀይ ለሌላው ጥቁር፣ ለአንዱ ቸር ለሁለተኛው ንፉግ፣ ለአንደኛው ወዳጅ ለሌላው ጠላት፣ ለአንዱ ቅርብ ለሁለተኛው ሩቅ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ለሁለቱም አንድ የሆነው ጌታ በሁለቱ አእምሮ ውስጥ ግን ሁለት ነበረ፡፡ ይህም የሆነው ከአመለካከታቸው የተነሣ ነበር፡፡ አንዱ በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ሲያስተውል አንዱ ግን ምንም አይነት መለኮታዊ መቻል የሌለው ሰው ብቻ (ሩቅ ብእሲ) እንደሆነ አሰበ፡፡ ሁለቱም ግን የአሳባቸውን አጨዱ፡፡  

       ሕይወት ወደ እኛ ቢለዋ ብትወረውር ቢለዋውን ማቆሚያ ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው በስለቱ በኩል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በእጀታው በኩል መያዝ ነው፡፡ እናንተ የትኛውን ትመርጣላችሁ? ያለምንም ጥርጥር የሚያጋጥሙን ነገሮች በሕይወት ላይ ተጽእኖ ማምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከምንም በላይ በሕይወታችን ውስጥ ተጽእኖ መፍጠር የሚችለው ባጋጠሙን ነገሮች ላይ እኛ የሚኖረን አመለካከትና ተግባራዊ የምናደርገው ልምምድ ነው፡፡ ሕይወትህን ለመቀየር እጅግ ጠቃሚው መንገድ ስለ ሕይወት ያለህን አስተሳሰብ መቀየር ነው፡፡ አስታውሱ! በምድርና በገነት መካከል ያለው ርቀት የከፍታ ጉዳይ ሳይሆን የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ፡፡ ቅንነት ይብዛላችሁ!

2 comments:

  1. በጣም አስተማሪና በግል ህይወት ውስጥ ራስህን እንድትመለከት ሚረዱ ጽሁፎች ናቸው
    መምህር እዮብ እግዚአብሄር አምላክ ከዚ በበለጠ ሚስጥሩን ይግለጥለህ,ጸጋውን ያብዛልህ,ክፉ አይንካህ

    ReplyDelete
  2. በጣም አስተማሪና በግል ህይወት ውስጥ ራስህን እንድትመለከት ሚረዱ ጽሁፎች ናቸው
    መምህር እዮብ እግዚአብሄር አምላክ ከዚ በበለጠ ሚስጥሩን ይግለጥለህ,ጸጋውን ያብዛልህ,ክፉ አይንካህ

    ReplyDelete