Monday, March 19, 2012

እመጣለሁ ያለን ይመጣል


         በአንድ መንፈሳዊ የመፍትሔ ፍለጋ ውይይት ላይ  ሰፋ ያለ ርዕስ ተነስቶ ሁሉም አሳብ መስጠት ጀመረ፡፡ አንዳንዱ ጊዜያዊ ያለውን ሌላው ደግሞ ዘላቂ ያለውን ብቻ ሁሉም እንደ አስተሳሰቡ ደረጃ መፍትሔ ይሆናል ያለውን ሰነዘረ፡፡ ከታደምነው መሐል አንዱ ግን ሐሳብ ለመስጠት የመጨረሻ ሰው ስለነበር ሁላችንም የእርሱን ለመስማት ጓጓን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሁላችንም አሳብ ተቀራራቢ መሆንና ልጁ በትምህርት አብሮን ባሳለፈባቸው ያለፉ ዓመታት በተለምዶ “ወጣ ያለ” የሚባል ዓይነት ተማሪ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ የመናገር ዕድሉ ሲሰጠው  “ላነሣነው ችግር ጊዜያዊው መፍትሔ የክርስቶስን ዳግም መምጣት መጠባበቅ ሲሆን ዘላቂው መፍትሔ ደግሞ የጠበቅነው ጌታ በክብር መገለጡ (መምጣቱ) ነው” ብሎ ንግግሩን አጠናቀቀ፡፡ በዚያ ክፍል ውስጥ ከነበርነው አወያያችንን (መምህር) ጨምሮ ያልተደመመ አልነበረም፡፡ መሰብሰባችንም በዚሁ አስተያየት ተደመደመ፡፡

       ክርስቲያን እንደመሆናችን ትልቁ ተስፋችን የክርስቶስ ዳግም መመለስ ነው፡፡ ለሕይወታችንም የተሻለው ዕረፍት ያመነውን ጌታ መገናኘት ነው፡፡ ቅዱስ አውግስጢኖስ “እምነት ማለት ያላየኸውን ማመን ሲሆን የዚህም ሽልማቱ ያመንከውን ማየት ነው” ይላል፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ምንም የለም፡፡ ምድራችን ላይ መፍትሔ የምናገኝላቸው ጊዜያዊ ችግሮች ከፀሐይ በታች በሆኑ ጥበቦች የሚቃለሉ ተግዳሮቶች ይኖራሉ፡፡ ዳሩ ግን እነዚህም እንኳን ፋታ የመስጠትን ያህል ናቸው፡፡ ሌላው ደግሞ የባለቤቱን መምጣት የብርቱ ክንዱን መገለጥ የሚጠብቁ ከሥጋና ከደም ምክር የተላለፉ መከራዎች አሉ፡፡

       ዓለማችን ውሉን እንዳጣ ልቃቂት የተዘበራረቁ ነገሮቿ ይበዛሉ፡፡ ላመነው ለእኛ ደግሞ ናፍቆታችን በጌታ መምጣት መሰብሰብ ነው፡፡ ጌታ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ (ዮሐ. 14÷2)፡፡” እንዳለ በዚህ ተስፋ መጽናት ለመሄድ ከእርሱም ጋር ለመኖር መናፈቅ በጸሎት “ጌታ ሆይ ቶሎ ና” ማለት ይገባናል፡፡

       ከክርስቶስ መምጣት ጋር የብዙዎቻችን ሕይወት ያለው ትስስር ከደስታ ይልቅ በአመዛኙ ከፍርሃት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ስሜት ለመምጣቱ እንደ ቃሉ የሆነ ዝግጅት እንድናደርግ ከረዳን ጥቅሙ የበዛ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን ግብዝነት ነው፡፡ የክርስቶስ መምጣት በፍቅር የምንጠብቀው በማስቸኮል የምንለምነው በደስታም የምናስበው ነው፡፡ መተላለፍና አለመታዘዝ የጽድቅን ብድራት የሚቀበልበት ወገባቸው የታጠቀ መብራታቸው የበራ ትጉህ ባሪያዎች የድል አክሊል የሚቀዳጁበት እውነት ያለ ከልካይ የሚገዛበት የዘላለም ቀጠሮ ከጌታ ጋር ስላላችሁ በዚህ ሐሴት አድርጉ፡፡

        ከማስታመም በላይ በሆነ የሕሊና ቁስል በማያቋርጥ ልባዊ ጸጸት ለምትሰቃዩ በሰው መሐል እየኖራችሁ ብቸኝነት ለሚሰማችሁ ሁለንተናችሁን ሰጥታችሁ በወዳጅ ለተከዳችሁ የፈተና ወጀብ የመከራ ማዕበል ለሚያንገላታችሁ በሀዘንና መከፋት ለቆዘማችሁ የሰው መጠቋቆሚያ የወሬ ርዕስ ለሆናችሁ እመጣለሁ ያለን ይመጣልና በዚህ ደስ ይበላችሁ፡፡ ሚዛን እንደተዛባ ደሀ እንደተበደለ ፍርድ እንደተጓደለ የጌታ የሆኑቱ እንደተገፉ ምድር ግፍን እንደተሞላች እውነት አደባባይ ላይ እንደወደቀ የዓመፀኞች ልብ እንደደነደነ የመለኮት ቃል ወደ ጎን ተትቶ የሰው ወግ እንደፋነነ አይዘልቅም፡፡ አዎ! እመጣለሁ ያለን ጌታ እንደ ቃሉ ይመጣል፡፡



 










No comments:

Post a Comment