ኑሮ ከሚጠይቃቸው ነገሮች አንዱ ስርዓት ነው፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ያሉ ዕቃዎች በስርዓትና በአግባብ አልተቀመጡም እንበል መኝታ ቤት ውስጥ የሳሎን ዕቃ፣ እልፍኝ ውስጥ ደግሞ የማዕድ ቤት ዕቃዎች ቢቀመጡ፣ መጸዳጃው የእንግዳ ማረፊያ እንዲሆን ቢደረግ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ስርዓት ለአንድ ቤት ሰላም እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ አጥርን ስናስብ ለአንድ ቤት ሕልውና ያለውን ትልቅ ድርሻ እናስተውላለን፡፡ አበው “አጥር የሌለውን ቤት ዶሮም ትደፍረዋለች” ይላሉ፡፡
አስተውላችሁ ከሆነ አንዳንድ ቤቶችን ለማንኳኳት ፈራ ተባ የምንልበት፣ ከኃይላችን ቆጥበን በጥቂቱ የምናኳኳበት ጊዜ አለ፡፡ ይህም የሚሆነው በስተውስጥ ያለው ሰው ሰብእና እየታወሰን ነው፡፡ ፍቅሩ፣ ደግነቱ፣ አክብሮቱ፣ ትህትናው፣ ቅንነቱ፣ ይቅርታና ትዕግስቱ . . . . እነዚህ ሁሉ ልባችንን ከመግዛት አልፈው የእጃችንንም ይቆጣጠሩታል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ እጅ ይበዛበታል ተብሎ በእግር የሚንኳኳ ቤትም አለ፡፡ ይህ ደግሞ የነዋሪው ሞልቶ የተረፈ ክፋት፣ ለባልንጀራዬ የማይል ስስት፣ አይንን በጨው ያጠበ ድፍረት እየታወሰን የምናደርገው ነው፡፡ ምንም እንኳን ሁለቱም ጠባያት በውስጥ ያለውን ሰው ማንነት የሚጠቁሙ ብቻ ናቸው ማለት ባንችልም በአብዛኛው ግን ከሚያንኳኳው ይልቅ የሚከፍተውን ሰው ሁኔታ ይገልፃሉ፡፡
እኛ ራሳችንን የምንደፍረውን ያህል ሌሎች ሰብእናችንን አይደፍሩትም፡፡ የሰዎች እኛን ማክበር የሚመጣው እኛ ለራሳችን ከሚኖረን ከፍተኛ አክብሮት ነው፡፡ ሕይወት ስጦታ እንደሆነች ካመንን ሰጭውን የምናከብረው ስጦታው ያለውን ዋጋ በሰጭው መጠን በመረዳትና በመንከባከብ ተገቢውን አክብሮት በመስጠትም ጭምር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በመጠን መኖር እንዳለብን ይመክራል፡፡ (1ጴጥ. 1÷13) ከኃጢአት የምንርቅበት ማስተዋል በመጠን መኖራችን ነው፡፡ የኃጢአት አንዱ ትርጉም ትርፍ ነገርን መፈለግ የሚል ነው፡፡ ያልተመጠነ ኑሮ ይቅርና ያልተመጠነ ቅመም እንኳን ያለውን ጉዳት እናውቀዋለን፡፡ ንግግር ካልተመጠነ በአፍ መበደልን፣ ተግባር ካልተመጠነ በኑሮ ኪሳራን ማስከተሉ እሙን ነው፡፡ ያልተመጠነ ግንኙነት ለዝሙት፣ ያልተመጠነ ጨዋታ ለሀዘን፣ ያልተመጠነ ጥረት ለሞት ይዳርጋል፡፡ ሰው ለአኗኗሩ ለአረማመዱ አጥር ሊበጅለት ይገባል፡፡ ዛሬ በወጣትነታችን ላይ የሚስተዋለው ገደብ የለሽ ፍላጎት ነው፡፡ ያየሁት ሁሉ አይለፈኝ፣ ከሁሉ ካልቀመስኩ አይሆንም፣ ካልሞከርኩ አልማርም የዘመናችን ተግዳሮት ነው፡፡ የሚቆምበት ቦታ ከተራመድን፣ የሚሠራበት ቦታ ከተኛን፣ ዝም ማለት ባለብን ቦታ ከለፈለፍን ኑሮ ስርዓት አልበኝነት የሰፈነበት ትንሽ ዓለም ይሆናል፡፡ እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤት ነን፡፡ (1ቆሮ. 3÷9) ቤት ደግሞ የማያስደፍር አጥር ያስፈልገዋል፡፡
አስተውለን ከሆነ ወደ ቤታችን የመጣ ሰው ወንበር ስቦ ቢቀመጥ፣ ውኃ ቀድቶ ቢጠጣ፣ ሞቆት መስኮት ቢከፍት ማንም የሚገረም ደግሞም ቅር የሚለው የለም፡፡ ነገር ግን አልጋ ላይ ሄዶ ቢቀመጥ ይህ እንደ ነውር ነው፡፡ ይህንን ያደረገው ወንድ ቢሆን ምን አስቦ ነው፡፡ ሴት ብትሆን ደግሞ ምን አስባ ነው ያስብላል፡፡ ስለዚህ በቤታችን ካሉት ዕቃዎች እንደ አልጋ ክብርና መፈራት የሚቸረው የለም፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በእያንዳንዳችን ሕሊና ውስጥ ከተተከለው አጥር የተነሳ ነው፡፡ በልክ መኖር እኛ ወደ ክፋት እንዳንሄድ ብቻ ሳይሆን ክፉም ወደ እኛ እንዳይመጣ አጥር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወት መሰረት፣ የማዕዘን ድንጋይና ራስ ነው፡፡ ቤትን ስናስብ እነዚህ ነገሮች ወሳኝ ናቸው፡፡ ያለ መሰረት መጽናት፣ ያለ ማዕዘን መቆም፣ ያለ ራስም ፍፃሜ አይታሰብም፡፡ በቀጣይ ለአንድ ክርስቲያን የማያስደፍሩ አጥሮች ምን ምንድናቸው የሚለውን ለማየት እንሞክራለን፡፡ ጥበብ ይብዛላችሁ!!
ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment