Friday, March 16, 2012

ሠግቶ መኝታ (ካለፈው የቀጠለ)


1. እግዚአብሔር አለ፡- ለብዙዎቻችን የእግዚአብሔር መኖር የሚሰበከው ለእግዚአብሔር የለሾች ብቻ እንደሆነ እናስባለን፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር የሚኖረው ለማያምኑት ብቻ ሳይሆን ለሚያምኑትም ሕልውናውን እያብራራ ነው፡፡ ምክንያቱም በሕይወት ውጣ ውረድ ለሚፈጠሩብን ማናቸውም ዓይነት ጥያቄዎች የእርሱ ሕልውና ብርቱ መልስ ነው፡፡

      በአንድ የፍልስፍና ትምህርት ቤት ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ሕልውና ርዕስ ተነስቶ ፕሮፌሰሩ እንዲህ በማለት የእግዚአብሔርን አለመኖር ለማስረዳት ሞከረ “ እግዚአብሔርን በዚህ ክፍል ውስጥ ካላችሁት የሰማው አንድ ሰው አለ?” በማለት ጠየቀ፡፡ ከሚሰሙት ተማሪዎች መሐል የሚመልስ ጠፋ፡፡ መምህሩ በማስከተልም “በዚህ ካላችሁት መሐል እግዚአብሔርን የነካው ሰው አለን?” ሲል ጠየቀ፡፡ አሁንም በድጋሚ መልስ ጠፋ፡፡ ፕሮፌሰሩ ለመጨረሻ ጊዜ ጠየቀ “ከእናንተ መካከል እግዚአብሔርን ያየው ሰው አለ?” አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ከተማሪዎቹ መልስ ጠፋ፡፡ መምህሩም “በቀላሉ ከዚህ ተነስተን በእግዚአብሔር አለመኖር መስማማት እንችላለን” በማለት ደመደመ፡፡

        ተማሪዎቹ ግን እንዲህ ባለው ንግግር ደስተኖች አልሆኑም፡፡ ስለዚህ ሁሉም እድል እንዲሰጣቸው በመጠየቅ በአንድነት ቆመው “በዚህ ካለነው መሐል የፕሮፌሰራችንን አእምሮ (አንጎል) ያደመጠው አለ?” ክፍሉን ፀጥታ ዋጠው፡፡ አሁንም ሌላ ጥያቄ ተደመጠ “የፕሮፌሰራችንን አእምሮ የነካው ሰው አለ?” አሁንም ምላሽ ጠፋ፡፡ በማስከተልም “የፕሮፌሰራችንን አእምሮ የዳሰሰውስ በዚህ ክፍል ካለነው መሐል አለ?” ክፍሉ ከፊት ይልቅ ዝምታ ሰፈነበት፡፡ ተማሪቆቹም “በፕሮፌሰራችን ሎጂክ (ምክንያታዊነት) መሰረት በእርግጠኝነት ፕሮፌሰራችን አእምሮ የላቸውም” በማለት ሁሉም በጭብጨባ ተበተኑ፡፡  

        የሰይጣን የዘመናት ውጊያ በእግዚአብሔር ሕልውናና ፍቅር ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች የሚከብዱብንም ልባችን ከዚህ ሀቅ ሲሸፍት ነው፡፡ በእያንዳንዱ የኑሮ ተግዳሮት ፊት የእግዚአብሔርን ሕልውና ብናብራራበት በማኅበራዊም ሆነ በግል ኑሮአችን እጅግ አትራፊ በሆን ነበር፡፡ እግዚአብሔር በፊቱ ለምናቀርበው ጸሎት ቀዳሚ ምላሹ “አለሁ” የሚል ነው፡፡ ይህ ለምናምን ለእኛ ትልቁ ዕረፍ ነው፡፡ ማግኘት ቢሆን ማጣት መክበር ቢሆን ውርደት መወደድ ቢሆን መከዳት መራብ ቢሆን መጠማት ተወዳጆች ሆይ እግዚአብሔር አለ፡፡ በዚህ ምድር ላይ ያለን ግንኙነት ከሰው ጋር ብቻ ቢሆን ሕይወት ምንኛ በመረረች ነበር፡፡ ዳሩ ግን ሁሉን ከሚችልና ከሚያስችል እግዚአብሔር ጋር ሕብረት ስላለን ሕልውናው ጉልበታችን ነው፡፡ የትምና ከማንም ጋር ትኖሩ ይሆናል፡፡ በዚያም ግን ጌታ ያለከልካይ አለ፡፡ በዚህ ሕያውና ቻይ አምላክ ታመኑ!

2. ሁሉን በልኩ እዩት፡- ኑሮን ከሚያከብዱብን ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ከሚጎዱብን ነገሮች መሐል ሁሉን በልኩ አለማየት ተጠቃሽ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ችግር ከራሳችን ጋር ላለን ሰላማዊ ትስስር ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ማኅበራዊ ኑሮ ነገሮችን በአግባቡ ማስተዋልን ይጠይቃል፡፡

       ማንኛውም ሰው የራሱ የሆነ ውስጣዊና ውጫዊ ጊዜያዊና ዘላቂ የሕይወት ሠልፍ አለበት፡፡ ከዚህም የተነሣ ከሰውም ሆነ ከራሳችን የምንጠብቀው ልከኛ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ሁሉን በልኩ ማየት ማለት ከሰው ትንሽ ከራስ ብዙ መጠበቅ ነው፡፡ በዚህም ከምንቀበለው ይልቅ የምንሰጠው የበዛ ይሆናል፡፡ የማንም ሰው ጉዳት ወደ እኛ ደርሶ ከመጎዳታችን በፊት የሚጎዳው ራሱ ባለቤቱ ነው፡፡ አንበሳ ሌላውን ከመጉዳቱ በፊት አስቀድሞ ራሱን ማስቆጣት አለበት፡፡ እኛ ጋር የሚደርሰው ጉዳት ከጎጂው የተረፈ ነው፡፡

3. ለዓላማችሁ ትኩረት ስጡ፡- ዓላማ የምንኖርለት ትልቁ ምክንያታችን ነው፡፡ ሰው ለመኖር የሚጓጓው ለመሥራት የሚተጋው በፊቱ የተቀመጠ ዓላማ ሲኖር ነው፡፡ በተለይ በስደት ሀገር በተለያየ ምክንያት የምትኖሩና በማኅበራዊ ኑሮ ለምትቸገሩ ከሁኔታው በላይ በዚያ ለምትኖሩበት ዓላማ ትኩረት መስጠቱ መቸገራችሁን ይቀንሰዋል፡፡ በእንቅፋቶቻችን ማንም አይደነቅም፡፡ በዚያ ውስጥ የምናገኘው ድልና የምናሳየው ስኬት ግን ለምድራችን ድንቅ ነው፡፡

4. እግዚአብሔር ያስችላል፡- ከድካም ሁሉ ትልቁ ድካም አቅምን አለማወቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዘመናችንን ሁሉ የሚተጋው አቅማችንን እንድንረዳና የእርሱን ኃይል እንድናምን ነው፡፡ እግዚአብሔር ድካማችንን የሚያስንቅ ብርታት የሰውን ጥላቻ የሚሽር መውደድ ልብን የሚያሰፋ ቃል አለው፡፡ ትላንትን ያሻገረን ዛሬን ሊያሳልፈን ትላንት ያበረታን ዛሬንም ሊደግፈን የበረታች ክንዱ ተዘርግታለች፡፡ ምን ተስኖት ጌታ ነውና ስሙ ይባረክ፡፡ ፍቅር ይብዛላችሁ!

No comments:

Post a Comment