Tuesday, March 27, 2012

ቤት ያለ አጥር (ካለፈው የቀጠለ)



1. የእግዚአብሔር ቃል፡- የምንሰማውን የምናጠልበት፣ የምንናገረውን የምንመርጥበት፣ የምንኖረውን የምናስተውልበት ኃይል የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ሕይወት ለዚህ ስትሰጥ ለነዋሪውም ለተመልካቹም የበዛ ውበት ናት፡፡ ጠላት የሚርቀው፣ ትግል የሚቀለው፣ ዕረፍታችንን ከሚዋጋ ተግዳሮት የምናመልጠው በዚህ የሕይወት ቃል ነው፡፡ ይህንን ቃል አልፎ፣ ተስፋውንም ረግጦ ወደ እኛ የሚሻገር ኃይል የለምና ከቃሉ ጋር ያለንን ሕብረት ማጠናከር አጥራችንን መጠበቅ ነው፡፡

        ቃሉ እርሱን ለማምለክ፣ ለክብሩ ለመገዛት፣ በፈቃዱም ምሪት ስር ለመኖር የሚያስችለን ኃይል ነው፡፡ ጠዋት ስንነሣ አንዲት የአምላክ ቃል ማንበብ ከብዶብን ቀኑን ሙሉ ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነገር እየሰማን እንመረራለን፡፡ የቀኑን ክፋት፣ የሰውን ጥመት፣ የዓለምን እንቶ ፈንቶ የምንቋቋምበት ጉልበት ያለው ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በማሳለፍ ነው፡፡ ሕያውና የሚሠራ፣ ሁለት አፍም ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ፣ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር ይህ ቃል ሕይወት የተስተካከለች አልያም የተንጋደደች ለመሆኗ ወሳኝ ነገር ነውና ለመስማት ጥማትን ለመፈጸም ፈቃደኝነትን ማሳየት ይገባል፡፡ ተወዳጆች ሆይ ቃሉን የኑሮአችሁ መመሪያ፣ የእንቅስቃሴአችሁ ካርታ፣ የማነንነታችሁ መስተዋት አድርጉት እናም ውጤቱን በዘመናችሁ ተመልከቱ፡፡

2. ጸሎት፡- የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ተራራን ፈቀቅ ታደርጋለች፡፡ ትንሽ ጸሎት ደግሞ የእግዚአብሔርን ክንድ ለማዳን ታስነሳለች፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ቤት ከሆንን ማንኛውም ነገር ከቤቱ ጌታ አንፃር መከወን አለበት፡፡ ለእኛ ያለውን ፈቃዱን የምንረዳው ደግሞ በጸሎት ነው፡፡ ንግግርና ተግባር በጸሎት ካልታጠረ የጠላት አሰራር የሚከናወንበት ግዛት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡

         ጥቂት ሳንጸልይ ቀርተን ብዙ የተጎዳንበት፣ ትንሽ ደቂቃ መንበርከክ ተስኖን በብዙ የተፈተንበት ጊዜ አጥር አልባ ለሆነው ኑሮአችን እማኝ ነው፡፡ ከቅርብም ከሩቅም፣ ከውስጥም ከውጭም የሚመጣውን መከራ ለመቋቋም መጸለይ አለብን፡፡ በሕይወታችሁ እግዚአብሔር ካስተማራችሁ እንደ ጸሎት ያለ የማያስደፍር አጥር የለም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ስንነጋገር ከእኛ ሸክም ይሄዳል ከእግዚአብሔር ደግሞ ዕረፍት ይመጣል፡፡ ችግራችንን

3. ቅድስና፡- ላመንነው መለየት ለተለየንለት መኖር ቅድስና ይባላል፡፡ ይህም እምነትና የማመን ፍሬ ነው፡፡ በክርስቶስ ስናምን የምንኖርበት ግዛት በእግዚአብሔር መንግስት ስር ይሆናል፡፡ ግዛቱም የማይደፈር ብርቱ ነው፡፡ የመቀደሳችን ዓላማ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሔር በሕይወት ለመግለጽ እንደመሆኑ የኑሮ ቅድስና ሌላው የማያስደፍር አጥራችን ነው፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ መልካም አባት መኖሩ ብቻ ቤቱን የተፈራ አያደርገውም፡፡ ምክንያቱም በአመለ ክፉ ልጅ ቤቱ ሊደፈር ይችላል፡፡

        መልካሙን እረኛ ወደ ሕይወታችን ወደ ኑሮአችን የሚመጣው ሁሉን ለውጦ ለክብሩ ሊያደርገው ነው፡፡ የለዋጩም ኃይል በተለወጠው ሰው የዕለት ተዕለት ኑሮ መገለጥ አለበት፡፡ ይህም የተቀደሰ የተለየ ሰብእናችንን ያሳያል፡፡ ቅድስና ለአንድ ክርስቲያን የማያስደፍር አጥር ነው፡፡ ሰዎችን በማስረዳት ብዛት ክብርን እንዲያሳዩን ማድረግ አንችልም፡፡ የቅዱሱ እግዚአብሔር ቅድስና በሰብእናችን መንጸባረቅ ሲጀምር ጠላት ፊታችን ደፍሮ ሊቆም፣ የሥጋና የደም ምክር ሊከናወን አይቻለውም፡፡ ይህ አጥር ከፈረሰ ግን ለሁሉም ኢላማ ስለምንመቻች በቀላሉ ለሽንፈት እንጋለጣለን፡፡ ቅድስና ለእግዚአብሔር፡፡ ማስተዋል ይብዛላችሁ!!


1 comment:

  1. Amen! Andit ye geta kal lemanbeb gize atan eyalin ye hiwot mefthe yelelew mezgeb sinagelabit enwilalen. Letselot gize yanesen sewoch rejim sibseba alu lemebal tekemten enasalifalen. Yetun ke yetu maskedem endalebin lemeleyet tesinonal ena Tsegaw yagzen!

    ReplyDelete