Tuesday, March 13, 2012

ሠግቶ መኝታ



      ሰው ጥርስ ስላለው ብቻ ማኘክ ምላስ ስላለው ብቻ ማላመጥ እንቅልፍ ስላለውም ብቻ መተኛት አይችልም፡፡ እያንዳንዱ የሰውነታችን ብልት እርስ በእርሱ የተያያዘ በመሆኑ የአንዱ ጉዳት በሌላው ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል፡፡ ከፍተኛ ራስ ምታት በያዘን ጊዜ ለመሳቅ እንቸገራለን፡፡ በዚህም የያዝነው ሰብእና ምን ያህል የተባበረ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በማህበራዊ ኑሮም ያለው ግንኙነት ከዚህ የሸሸ አይሆንም፡፡ ከባንቱ ፍልስፍና የተገኘ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፡- “ኑሮ የጋራ ነው፡፡ መኖርም ደስታውንም ችግሩንም አብሮ ለመካፈል ነው፡፡ በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ የግል የሆነ ነገር የለም፡፡ አንዱን የሚመለከተው ሌላውንም ይመለከታል፡፡ የጥቂቶች ኃይል የሁሉም ኃይል ነው፡፡ የጥቂቶችም ድካም የሁሉም ድካም ነው፡፡ ከሠራተኞችና ከታታሪዎች ጋር በኖርን ቁጥር ትጉህና ጠንካራ እንሆናለን፡፡ የእነርሱ ኃይል እኛንም ያነሣናል፡፡ ከሰነፎችና ከደካሞች ጋር ከኖርንም የእነርሱ ስንፍና ተጽእኖ ያደርግብናል፡፡ እናም ከከፍታ ይልቅ ቁልቁል ያወርደናል፡፡”

       ምድር ላይ ያለው ትልቁ ሀብት ሰው እንደመሆኑ አንዳችን ከሌላው ጋር የምንፈጥረው ሕብረት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ መጠቃቀም እንዳለ ሁሉ ማስታመም የሚከብዱ ጉዳቶችንም ማስተናገዳችን አይቀሬ ነው፡፡ የምንኖረው ምርጫችን ሁሉ ተግባራዊ በሚሆንበት ዓለም አይደለም፡፡ ሌሎችም የራሳቸው ዓላማ የሕይወት ዘይቤ የአስተሳሰብ ደረጃ የግል መረዳት አላቸው፡፡ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ለጉዳት ከሚዳርገን ነገር ውስጥ አንዱ ይህንን የተብራራ ሀቅ አለመረዳትና አለመቀበል ነው፡፡ በትዳር ውስጥ እንኳን አንዱ ለሌላው አሳብ ካልተሸነፈ በቀር አንድ ሥጋ ናቸውና በአንድ ጊዜ በአንድ ነገር ላይ ተመሳሳይ አመለካከት ይኖራቸዋል ማለት አንችልም፡፡

       በጣም አምሽቶ የሚተኛ ወዳጄ ሲያጫውተኝ “እኔ ከመተኛቴ በፊት የማስተኛቸው ብዙ ነገሮች አሉ” በማለት ለምን እንደሚያመሽ ነገረኝ፡፡ ሕሊናዬ “በላጤነት የማውቀው ይህ ባልንጀራዬ ዛሬ የሚያስተኛቸው ከየት አገኘ?” በማለት ይበልጥ ለመስማት ያለኝ ጉጉት ጨመረ፡፡ እርሱም “ሙቀጫና ዘነዘና  ቴፕና ሲኒ የአቶ እገሌ ሚስትና የወይዘሮ እገሊት ባለቤት የፊት አውራሪ ልጆች እነዚህን ሁሉ ካላስተኛሁ አልተኛም፤  ዝም ብዬ ልተኛ ብሞክር እንኳን ፈቃዴ በማይጠየቅበት መንገድ ምንም አይነት መዳፍ በላዬ ላይ ሳያርፍ እቀሰቀሳለሁ፡፡ ስለዚህ የእኔ እንቅልፍ ሠግቶ መኝታ ነው” አለኝ፡፡ እኔም “አትጸልይም እንዴ?” አልኩት፡፡ “እጸልያለሁ! የምጸልየው ግን እንቅልፍ ስጠኝ ብዬ ሳይሆን ጎረቤቶቼን እና ንብረቶቻቸውን አስተኛልኝ ብዬ ነው” አለ፡፡ ባልና ሚስት በተጣሉት እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ላጤዎች ጎረቤት እስከ ስድስተኛ በሚፈላ ቡና አፍጠው የሚያመሹ ወገኖች ወዳጅነትን ጠብቆ መኖር ብዙ ዋጋ መክፈልን እንደሚጠይቅ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

       ከሀገር ወጥተው በስደት አገር የሚኖሩ ሰዎች ከገዛ ወገናቸው ጋር በቀላሉ መግባባትና አብሮ መኖር ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ይልቅ በቋንቋም በዜግነትም ልዩ ከሆነ ወገን ጋር መተባበር ሲቀላቸው ይታያል፡፡ ይህም በሕሊናችን ውስጥ አንድ ጩኸት ይፈጥራል “እኛ ለእኛ የምንሆነው መቼ ነው?”፡፡ ማኅበራዊ ኑሮ እኛ ቤት ማስተኛ የሆነው ነገር ጎረቤት ጋር መቀስቀሻ ከሆነ ቢቀርስ? ማለትን ይጠይቃል፡፡ በክርስትና ውስጥ ደግሞ እንዲህ ያለው ውሳኔ ራስን ብቻ ወዳድ መሆንን መኮነን ነው፡፡ ለሌሎች እንቅልፍ ሥጋት ለኑሮአቸው ፍርሃት ለልባቸው ሁከት ላለመሆን መጠንቀቅ ማስተዋል ነው፡፡ በፍጥረት መጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር ከጠየቃቸው ጥያቄዎች አንዱ “ወንድምህ ወዴት ነው?” የሚል ነበር፡፡ (ዘፍ. 4÷9) ለራሳችን ከምናሳየው ፍቅር ባልተናነሰ መልኩ ለሌሎች ፍቅር ማሳየት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለው ነው፡፡

        በፊት በፊት መንገድ ላይ አስተውላችሁ ከሆነ ልጆች “እስካልነካሁህ ድረስ እንደፈለኩ መሆን እችላለሁ፤ ስምህንም እስካልጠራሁም ድረስ መሳደብ መብቴ ነው” ይላሉ፡፡ ትልልቆቹ ጋር ስትመጡ ደግሞ ስክር ብሎ “እኔ ብሰክርም አልረብሽም” ይላሉ፡፡ ራሳችንን የማንችልባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች እንኳን ሰው ላለማስቸገር ብለው ጉድጓዳቸውን ቆፍረው ቢሞቱ አፈር አልባሽ ድንጋይ አጋዥ ያስፈልጋል፡፡ ተወዳጆች ሆይ ከሰው ጋር ላላችሁ ወዳጅነት ዋጋ ስጡ፡፡ የእገሌ ጠቡ እንኳን ናፈቀኝ እየተቆጣኝም ቢሆን አጠገቤ በሆነ ብላችሁ አታውቁም? የያዝነውን ነገር ዋጋና ጥቅም ካጣነው በኋላ የምናስተውል ተላላ መሆን የለብንም፡፡ ሁላችንም የአንድ አካል አባሎች ነን፡፡ ተፈጥሮ በእኛ ውስጥ የእርስ በእርስ መፈቃቀርንና መፈላለግን ዘር ተክላለች፡፡ አብረን ለመኖርም የምንችል አድርጋ ቀርፃናለች፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የተፈጠርነው ለሁላችንም የጋራ ደኅንነት መሆኑን ማመን ይገባናል፡፡

        በማኅበራዊ ኑሮ ለምትቸገሩ ሁሉ በሥጋ ለባሹ ሰው አልጎዳም ሊል የሚችል ማንም የለምና በዚህ አትደነቁ፡፡ ቁም ነገሩም ይህ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር በዚህ ውስጥ ምን ተማርን? ምን አተረፍን? ለሌሎች የሚረባ ምን ነገር ያዝን? የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሰዎች ከሚያደርሱብን ጉዳት ከሚዘረጋብን ወጥመድ ለማምለጥ በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ የሚረዳንንም ኃይል ለማግኘት ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት መቅረብ ይኖርብናል፡፡ ሠግቶ ላለማንቀላፋት ከማኅበራዊ ኑሮ አንፃር ጥቂት መፍትሔ በቀጣይ እንመለከታለን፡፡ ፍቅር ይብዛላችሁ!

                                                                   ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment