Thursday, March 8, 2012

የግልግል ኑሮ



      ለአገልግሎት ወደ አንድ ከተማ ሄደን የተመለከትኩትና የሰማሁት ነገር ብዕሬን እንዳነሣ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው! የታመመ ሰው ልንጠይቅ የገባንበት ክፍል ውስጥ ሰው ከብቦት፣ ፊቱ ተለጣጥፎ በሰመመን ያለ አንድ ሕመምተኛ አስተዋልን፡፡ እኛም የሄድንበት ዓላማ እንዳለ ሆኖ ይህም ወገን ነውና "ምን ሆኖ ነው?" በማለት ጠየቅን፡፡ ከታዛቢዎች መሐል አንዱ "ሚስቱ ደብድባው እስከ አሁን አልነቃም" አለን፡፡ እንደ እኛ ሕመምተኛ ሊጠይቅ የመጣ አንድ ሌላ ሰው ቀበል አደረገና "ማርች ኤይትን አስመልክቶ ነው?" በማለት ለመቀለድ ሞከረ፡፡ አንዳንዶቹ ሴቶች ደግሞ "ምነው እንደ አንቺ ሺ በተወለደ" በሚል መንፈስ በሌለችበት ሙገሳ ቸሯት፡፡ እኛም ጥቂት አይተን ልባችን ግን ብዙ ታዝቦ ተመለስን፡፡

       ዘመናችን የምናየው የምንሰማው ሁሉ ጉድ የሆነበት፤ ሰው ተፋቅሮ ቀርቶ ተቻችሎ፣ ተቀራርቦ ቀርቶ ተራርቆ ለመኖር አቅመቢስ የሆነበት ነው፡፡ ስለ ፍቅር የሚጻፉ መጻሕፍት፣ ስለ ይቅርታ የሚሰበኩ ስብከቶች፣ ስለመቻቻል የሚለፈፉ ንግግሮች፣ ስለ መብት የሚበተኑ ማስገንዘቢያዎች እነዚህ ሁሉ መደለያዎችና ማባበያዎች አልፎም ማስፈራሪያዎች ለምናየው ችግር የማገላገልን ያህል እንኳን መፍትሔ መስጠት ተስኗቸዋል፡፡ እጮኛው ላይ አሲድ ስለደፋ ፍቅረኛ፣ ባሏን ገላው ሬሳው ላይ ምጣድ ስለጣደች ሚስት፣ የባለቤቱን ዓይን ስላወጣ አባወራ፣ የባሏ ሰውነት ላይ የፈላ ውኃ ስለደፋች ሚስት ወዘተ እነዚህ ሁሉ ሰውን የሚያስብ አራዊት፣ አንድ ቤት የሚኖር ጣውንት አስመስለውታል፡፡ ጭካኔ ማስተዋልን፣ ክፋት ትምህርትን፣ ዓመጽም ችሎታን አይጠይቅም፡፡ 

      ወዳጅነትን በመልካም መጠበቅ፣ ከባልንጀራ ጋር በፍቅር መዝለቅ ግን አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፍን፤ ተጎድቶ እንዳልተጎዳ አዝኖ እንዳላዘነ መታገስን፣ የሚበልጥ አሳብ ይዞ የተሻለ ራዕይ ኖሮ ግን ላነሰው መሸነፍን ይጠይቃል፡፡ አልፎም ተርፎ የራስን ለሌሎች ጥቅም አሳልፎ በመስጠት መገለጥን ይጠይቃል፡፡ በፍቅራቸውና በኑሮአቸው የምንቀናባቸው ደግሞም ለሌላው አርዓያ መሆን የቻሉ ሰዎች ቤታቸው ችግር ስለሌለ አለመግባባት ስለማይከሰት አይደለም፤  ለሚበልጠው ስለሚሸነፉ ብቻ ነው፡፡ መብቴ ከማለት ፍቅሬ ማለት የሰውን ከማሰብ የእግዚአብሔርን መመልከት አማራጮችን ከመቁጠር የመረጡትን መንከባከብ ይልቃል፡፡  

      ብዙ ትዳሮች እንዳልሆነ እየሆኑ፣ ብዙ ልጆች ያለ በደላቸው እየተበተኑ፣ በዙሪያችን ያሉ ከልብ እያዘኑ ነው፡፡ ትዳር በፍቅር እንጂ በመብት አይቆምም፡፡  ወዳጅነት ከልብ በሆነ ሕብረት እንጂ በሕግ ወሰን አይጸናም፣ ማኅበራዊ ኑሮም በወንድማማችነት መንፈስ እንጂ በመጠባበቅ አይቆምም፡፡ አሁን አሁን ስናይማ  ያለ ገላጋይ የማይሆኑ ጥምረቶች (ማንኛውም) እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ በእናትና በልጅ መካከል ያለው ግንኙነት እንኳን ገላጋይ አስፈልጎታል፡፡ ገላጋይ ካለ ለድብድብ የሚጋበዙ ሰዎችን አስተውላችሁ፤ አልያም ገላጋይ የሌለበት ቦታ ሄደን ይዋጣልን! ያሉ ልጆችን ተመልክታችሁ ይሆናል፡፡ ገላጋይ ካለ ሁሉም የአቅሙን ይሞክራል፤ ካልሆነለት ደግሞ በገላጋዩ ተተግኖ ይወራጫል፡፡ ስለዚህ ኑሮን ውጥረት የነገሰበት ያደርገዋል፡፡ መቼም ቢሆን በማስፈራሪያዎች መሐል እውነተኛ ፍቅር፤ ልብ የሚያርፍበት ሰላም አይኖርም፡፡  እንደ እኔ የሴቶች ቀን የወንዶች ቀንም ነው! ከሴት ያልተወለደ ብሎም ያልወለደ የለም፡፡ በትዳር ውስጥ ያሉ ደግሞ "አንድ ሥጋ ናቸው" ተብሏል፡፡ ተወዳጆች ሆይ መፍትሔው አንድነትና ፍቅር  ነው፡፡ ስለጭቆና ማውራት ጭቆናን አያስቀረውም፤ መብት አለኝ ማለትም ገፍቶ ከመጣ ሞት አያድንም፡፡ ፍቅር ግን ከሁሉም ይበልጣል፡፡

No comments:

Post a Comment