እሮብ ሚያዝያ 23/2005 የምሕረት
ዓመት
“. . . በቀን ከሙቀት ለጥላ፤
ከዐውሎ ነፋስና ከዝናብም ለመጠጊያና ለመሸሸጊያ ጎጆ ይሆናል (ኢሳ. 4÷6)”
የእግዚአብሔር ቃል በማይቋረጥ ዋስትናና በማይታጠፍ ቃል ኪዳን የተሞላ ነው፡፡ በሰው ታሪክ ዋስትናና ቃል ኪዳን ሲከተሉን
የሚኖሩ ብርቱ ፍላጎቶቻችን ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት እነዚህን ብርቱ መሻቶች ያሟላ መሆኑ እርሱን የዘላለም
መጠጊያ እናደርገው ዘንድ ያስችለናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ሰው ሆኖ በሰው መካከል በተመላለሰበት
ጊዜ ሕሙማን እንደ ተፈወሱ፣ የተራቡ እንደ ጠገቡ፣ የተናቁ ወደ ክብር እንደ መጡ፣ የተጠሉ ኃጢአተኞች ወዳጅ እንዳገኙ፣ የታወሩ
ዓይኖች እንዳዩ፣ የደነቆሩ ጆሮዎች እንደ ሰሙ፣ የሰለሉ አካሎች እንደ ተዘረጉ በቅዱሱ መጽሐፍ ውስጥ በግልጥ ተጠቅሷል፡፡ ዳሩ ግን
በዚህ ምድር ለማንም መኖሪያ ቤት እንደ ሠራ አልተፃፈም፡፡ ራሱ ጌታ እንኳ ከአእዋፋት ባነሰ ሁኔታ ራሱን የሚያስጠጋበት ቤት የሌለው
ሆኖ ነው የተመላለሰው (ማቴ. 8÷20)፡፡
ሰው ተሰማርቶ መሰብሰብን ሲያስብ ቤትን ያስባል፡፡ ሰው ተከፍቶ ማልቀስ ሲፈልግ ቤቱ ማሳለፍን ይመርጣል፡፡ ደስታውንም
ሀዘኑንም “የሚችለኝ ቤቴ ነው” ብሎ ለማሳለፍ በዚያ መሆን ይቀናዋል፡፡ ሰው ቢጥመውም ቢመረውም ዞሮ ዞሮ ቤቱ ይገባል፡፡ ቤቱ በጎም
ይቆየው ክፉ ተመልሶ ይመጣል፡፡ ምክንያቱም ቤቱ ነው፡፡ አደባባይ ላይ በብዙ ወዳጅ የተከበበ ሰው፣ ባማሩ ሆቴሎች ሲጋበዝ፣ መናፈሻ
ለመናፈሻ ሲዞር፣ አንቱታና ውዳሴ ሲጠግብ የዋለ ሰው ሲመሽ የሚሰበሰበው እንደ አቅሚቲ በሠራት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ተማሪ ቤት እያለሁ
የቅኔ ክፍለ ጊዜ መምህራችን “ይህ ሁሉ አደባባይ ላይ የምትመለከቱት ዘናጭ መሽቶ ቤቱ ሲገባ ተከትላችሁ ብታዩት አብዛኛው ጭቃ ቤት
የሚኖር ነው፡፡ እዚህ “ጦጣ መጀመሪያ የመቀመጫዬን አለች” የሚለው አባባል ስለማይሠራ የአደባባይ ለባሽ፣ የቤት ውስጥ ቀማሽ (ጠግቦ
የማያድር) የበረከተበት ነው፡፡ እናም በምታዩት አትወሰዱ ትምህርታችሁን ጠንክራችሁ ተማሩ፡፡” በማለት የመከሩንን አስታውሳለሁ፡፡
ታዲያ እርሳቸው የነገሩን ምን ያህል ትክክል ነው? በማለት አንዳንድ ጥሩ ለብሰዋል ያልናቸውን ሰዎች ሲመሽ ተከትለን ለማረጋገጥ
በሞከርንባቸው ጊዜዎች መምህሩ የነገሩን እውነት እንደ ሆነ አመሳክረናል፡፡ በእርግጥም ሰው አደባባይ ላይ ቢያጌጥ ቢደምቅ፣ ቢከበር
ቢወደድ መጨረሻው መጠለያው ናት፡፡ ብታዘምም ብትቆምም ቻዩ ያችው ቤቱ ናት፡፡
ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብዙ ነገር አውርቶአል፡፡ እነርሱም የሕይወት ቃል ባለው በእርሱ ነፍሳቸው ሐሴትን አድርጋለች፡፡
ሥጋቸውም በሚፈፀም ተስፋ አድራለች፡፡ አንድ ጊዜ ግን ልባቸውን የሚያውክ ነገር ገጠማቸው (ዮሐ. 14÷1-7)፡፡ እርሱም ጌታ እንደሚሄድ
ሲነግራቸው ነው፡፡ ለሰው ልጅ ከባድ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ስንብት ነው፡፡ በተለይ ቁርጥ ሲሆን መለያየት ይከብዳል፡፡ መለያየትን
ሊቃውንቱ በሦስት መንገድ ይከፍሉታል፡፡ የመጀመሪያው በቦታ መለያየት ሲሆን በዚህ ውስጥ የመንፈስ አንድነት አለ፡፡ ሁለተኛው መካካድ
ሲሆን በዚህ ውስጥ ጠንካራ ቅራኔ አለ፡፡ ሦስተኛው ቀብሮ መመለስ ሲሆን በዚህ ውስጥ ደግሞ ብርቱ ሀዘን አለ፡፡ ጌታ ግን ደቀ መዛሙርቱን
“ልባችሁ አይታወክ” በማለት አጽናናቸው፡፡ እርሱ ብቻ ስለ ሰው ልብ ይዞታ ሊናገር ድፍረት አለው፡፡ ሰው ከፊታችንና ከሁኔታችን
ነገሮችን ለመፈረጅ ይቸኩላል፡፡ ጌታ ግን የልብ ነው፡፡ እርሱ ሲናገር ከልብ ይጀምራል፡፡ እርሱ ከጥርሳችን ፈገግታ ባለፈ፣ ከልብሳችን ንጽሕና በዘለቀ የተሰወረውን መታወክ
ያውቃል፡፡ እርሱ ለአፋችን ቅርብ ሰሚ ሳይሆን ለልባችን የቀረበ አዳማጭ ነው፡፡ ለልባችን መታወክ ቅርብ መጽናኛ ኢየሱስ ነው!
ደቀ መዛሙርቱ ስለ ልባቸው መታወክ ጌታን አላስረዱትም፡፡ ሊያስረዱትም አይጠበቅባቸውም፡፡ እርሱ ሁሉን የሚያውቅ ነው፡፡
ከእርሱ ማወቅ የተሰወረ ነገር የለም፡፡ የፀጉራችሁ ቁጥር በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ከዓይኑ እይታ ውጪ ሊሆን ማን አቅም አለው?
ከማወቁስ ሊሰወር ማን ይቻለዋል? ሁሉን በሚችል በእርሱ ፊት ማን በኃይሉ ይበረታል? ልቦችን ሁሉ እርሱ ያውቃል፡፡ ይህንን እያነበባችሁ
በዚህ ሰዓት በልዩ ልዩ ጉዳይ የምትታወኩ ወገኖቼ ሁሉ ጌታ የልባችሁን መታወክ ያርቅላችሁ፡፡ ሰሜን ከምስራቅ እንደሚርቅ ጌታ ጭንቀታችሁን
ያርቅ፡፡ ሌላም ትኩረት ልንሰጠው የሚያስፈልገንን ትምህርት በዚሁ
ክፍል ላይ እናገኛለን፡፡ የአብዛኛው ሰው መታወክ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ጌታ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም
ደግሞ እመኑ” በማለት ለሁከት የምንጋለጥበትን ትልቅ ምክንያት “የአለማመን ጠንቅ” ይነግረናል፡፡ “እነርሱ በእምነት መንግሥታትን
ድል ነሡ፣ ጽድቅን አደረጉ፣ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፣ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፣ የእሳትን ኃይል አጠፉ፣ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፣
ከድካማቸው በረቱ፣ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፣ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ (ዕብ. 11÷33)” ተብሎ እንደ ተፃፈ ዓለምን የምናሸንፍበት
ኃይል ያለው እምነት (ከእግዚአብሔር ለተወለዱ ብቻ) ውስጥ ነው፡፡
1. በእግዚአብሔር እመኑ፡- በእግዚአብሔር ማመን ማለት በአንድነቱና በሦስትነቱ ማመን ነው፡፡
በአካል ሦስትነት በግብር አንድነት የተገለጠ አምላክ እግዚአብሔር እርሱ ብቻ ፈጣሪ እንደ ሆነ በልብ መቀበልና ማመን ነው፡፡ ሁሉን
አዋቂነት፣ በሁሉ መገኘትና ሁሉን መቻል የእርሱ ብቻ እንደ ሆነ መረዳትና ማመንም ይገባል፡፡ ልባችን ለዚህ እውነት በተሸነፈበት
ዘመን ሁሉ እውነተኛ አማኞች ነን፡፡