ጠባይንና ግብረገብነትን፣ ወንድማማችነትንና አብሮ መኖርን የሚያጠቃልል ኃይል ሥነ ምግባር ነው፡፡ ሰው አካባቢውን እንደመምሰሉ አብሮ ከሚውለውና አብሮ ከሚኖረው ጋር መመሳሱሉ አይቀሬ ነው፡፡ አበው “ከበቅሎ ጋር የዋለች ጊደር እርግጫ ተምራ ወደ ጋጧ ገባች” እንደሚሉት ክፉ ባልንጀራ መልካሙን አመል ያጠፋል፡፡ በውጪው ዓለም “የምታነበውን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለው” እንደሚባለው እኛም ጋር “ጓደኛህን ንገረኝና ማን መሆንህን እነግርሃለው” ይባላል፡፡ በዚህም ሰዎች በእኛ ኑሮ ላይ ያላቸው ተጽእኖ ምን ያህል እንደሆነ መረዳት ያስችለናል፡፡ ከሰዎች ጋር ሊኖረን የሚችለውን ግንኙነት መመዘን ያለንንም መተባበር መፈተሽ የዘወትር ተግባራችን ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ መልካም ጠባይ በውጭ ሰውነታችን ብቻ የምናሳየው ሳይሆን በውስጥ ሰውነታችን መለወጥም የሚታይ ነው፡፡ ተኩላ በግን “ምናለ ቤታችንን መጥታችሁ ብታዩልን?” ባላት ጊዜ በግ “ግብዣው መልካም ነው ዳሩ ግን ቤታችሁ ሆዳችሁ ውስጥ ሆነና እንዴት እንምጣ” በማለት እንዳሳፈረችው ለክፉ ባልንጀርነት እኛም ክፍተት መስጠት የለብንም፡፡
ወላጆች ጥሩ ለብሰው፣ የላመ የጣመ ጎርሰው ስላላደጉ ልጆቻቸው ሲቆጩ እናያለን፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃልና በሥነ ምግባር ስላላደጉ ልጆቻቸው ግድ የላቸውም፡፡ የተሻሉ የምንላቸውም በሌላው ልጅ ሥርዓት አልበኝነት፣ የተንጋደደ እድገት ይከፋሉ እንጂ በራሳቸው ልጅ አይቆጩም፡፡ በአገራችን ላይ የምናየው ስልጣኔን ትኩረት ያደረገው ጉዞ ከሰዎች ለውጥና ሥነ ምግባር ይልቅ ቁሳዊ ለሆኑ እንዲሁም ግንባታን መሰረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የተደገፈ ነው፡፡ ነገር ግን ትውልድን ለማትረፍ ሥነ ምግባር ላይ መሰራት አለበት፡፡ እኛ ለፍተን ደክመን በሠራነው የተንጣለለ ቤት ውስጥ ባዶ (ኢ ግብረገባዊ) ሰው ቢገባበት ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ባዶ ቤት ውስጥ በእግዚአብሔር የአሳብ ሙላት ስር ያለ አንድ ሰው ቢገባ ደግሞ ቤቱን ምን ያህል በመልካም ይለውጠዋል? ሁለቱንም ለሕሊናችን ሚዛን እንተወው፡፡
ሥነ ምግባር ከማስመሰል ያለፈ፣ ከግብዝነት የፀዳ ሲሆን ያምራል፡፡ የውጭ አቋማችን የውስጥ ሰብእናችንን የሚያብራራ በመሆኑ እውነትን መሰረት ያደረገ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ዓለም በበኩሉ የራሱ ለውጥና ተሐድሶ አለው፡፡ ይህም የሰዎችን ጠባይና ባህሪ ሲለውጥ እናየዋለን፡፡ አንዳንዶቹን መንፈሳዊነትን ጠልተው ለሥጋ ኃይል ሲያንበረክካቸው፣ ሌሎቹን ደግሞ በክፉ አሳብ ተጠምደው እኔነታቸውን እንዲያከብሩ ይገዛቸዋል፡፡ ይህም ዓለም የሚሰጠው ለውጥ መለያ ጠባይ ነው፡፡ ጌታ ወደዚህ ዓለም የመጣው ሊገለገል ሳይሆን ሰዎችን ሊያገለግል ነው፡፡ (ማቴ. 20÷28) አገልግሎቱም ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ እስከመስጠት ይደርሳል፡፡ እኛም በነገር ሁሉ እርሱን ልንመስል የእርሱንም ልንከተል ተጠርተናል፡፡
አንድ የግሪክ ፈላስፋ ተማሪዎቹን “እኔን ምሰሉ ይህም ልጅ ወላጆቹን በመልክ፣ በቀለም፣ በቁመት መስሎ እንደሚወለደው አይደለም፡፡ ይህ ከዘርና ከደም የሚወረስ የተፈጥሮ ግዴታ በመሆኑ አያስደንቅም፡፡ እኔ ግን ያልኳችሁ ባገኛችሁት ትምህርት እንደ እኔ መምህር፣ አስተዳዳሪ፣ ሐኪም እንድትሆኑም ብቻ አይደለም፡፡ ይህንንም በጥናትና በጥረት ብዛት ማንም ሊያገኘው ይችላል፡፡ እኔን ምሰሉ ያልኳችሁ ግን በቃል፣ በሥራና በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን እንደ መልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠረው ያለው በአፍንጫችን፣ በአይናችን፣ በፀጉራችን እንድንመስለው ሳይሆን በእውቀት፣ በቅድስናና በጽድቅ እንድንተባበር፣ ከእምነት በሆነ ሥነ ምግባር እንድንገልጠውና እንድናገለግለው ነው” አላቸው፡፡ ይህ አገላለጽ በውስጡ ሰውነታችን አምላካችንን እንድንመስል ያብራራል፡፡ ስለዚህ ብዙው ኃጢአትም ሆነ በጎ ተግባር፣ ክፉም ይሁን ቅድስና ማንኛውም ክንዋኔ መነሻው የውስጥ ሕይወታችን ነው፡፡
በቀደመው አሳብ የውጭ ሕይወታችን የሚያንጸባርቀው የውስጥ ሕይወታችንን አቋም እንደሆነ ተነጋግረናል፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እውነተኛ ውስጣዊ ጠባያቸውን አፍአዊ በሆነ ማስመሰል ለመሸፋፈን ቢሞክሩም እውነትና ንጋት እያደር . . . እንደሚባለው መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ወደፊት “የክርስትናው ዓለም ጭንብሎች” በሚል በሰፊው ለማየት እንሞክራለን፡፡ በክርስትና ያለው ስነ ምግባራዊ ሕይወት እንደ ወርቅ የተፈተነ ማስመሰል የሌለበት ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን ጽድቁ ከጸሐፎችና ከፈሪሳዊያን ጽድቅ ካልበለጠ በእግዚአብሔር መንግስት እድል ፈንታ የለውም፡፡ ስለዚህ የቃል ምስክርነት በኑሮ መገለጥና መደገፍ አለበት፡፡ ለሚታየው ሳይሆን ለማይታየው፣ ለውጪው ሳይሆን ለውስጡ፣ ለጊዜያዊው ሳይሆን ለዘላለማዊው፣ ለምድሩ ሳይሆን ለሰማያዊው፣ ለሥጋ ሳይሆን ለመንፈስ ማድላት ለሚበልጠው ማስቀደም ነው፡፡ ማስተዋል ይብዛላችሁ!!