Tuesday, April 3, 2012

ስመ አበሮች



          ሰው ማኅበራዊ እንደመሆኑ ከግለኝነት ይልቅ እርስ በእርስ የሚገናኝባቸው ጉዳዮች የበዙ ናቸው፡፡ ከሁሉም የበረታው ግን የዓላማ ዝምድናና ግንኙነት ነው፡፡ ክርስትና በሥጋ ካለው ዝምድና እንዲሁም ከማኅበራዊ መስተጋብር የጠነከረና ስር የሰደደ ነው፡፡ የሥጋ ዝምድና በሞት የሚፈታ መቃብርን የማያልፍ ሲሆን መንፈሳዊው ቤተሰባዊነት ግን በሞት ላይ ሕያው ከመቃብርም አልፎ ለዘላለም ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ግብረ አበር ሲባል እንሰማለን ይህ ከወሬ፣ ከምክር፣ አቅጣጫም ከመጠቆም ባለፈ ራስን ደምሮ በተግባሩ መሳተፍን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ የአንዱ ተጠያቂነት ሌላውንም ተጠያቂ ያደርጋል፣ የአንዱ ኪሳራ ሌላውንም ይነካል፣ የአንዱ እንባ ሌላውንም ያስነባል፡፡ እዚህ ላይ አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል ነው፡፡ የአንዱ ሞት ለሌላውም የሞት ያህል ነው፡፡ በደስታውም እንዲሁ ነው፡፡ የእገሌ ሳቅ ለእገሊትም ደስታ ነው፡፡ የአንዱ ማትረፍ ለሌላውም ትርፍ ነው፡፡ በጋራ ትግል የጋራ ድል በጋራ ድካም የጋራ ሽንፈት መቀበል የግብረ አበርነት ጠባይ ነው፡፡

           የስም አበርነትን ስንመለከት አለሁ ግን አልተሳተፍኩም፣ አባል ነኝ ግን አልተባበርኩም፣ ይመለከተኛል ግን አልተመለከትኩም የሚል ዓይነት ነው፡፡ በተደከመበት ላይ ንግግር፣ በተለፋበት ላይ ድርድር፣ ባለቀ ነገር ላይ መሸለል አይነተኛ ጠባያቸው ነው፡፡ ስም አበሮች አቀብሎ ሸሽ ዓይነት ናቸው፡፡ ዋጋ መክፈሉ ላይ የሉም ዋጋ ሲሰጥ ግን ማልዶ ሰልፈኛ ናቸው፡፡ ሥራውን ስትሠሩ፣ ድካሙን ስትደክሙ፣ ተግዳሮቱን ስትጋፈጡ አጠገባችሁ የሉም፡፡ ነገር ግን የድመት አፍንጫ የንስር ዓይን አላቸው፡፡ ከተግባሩ በኋላ ሲወራ አብሮ ይወራላቸዋል እንደውም የእነርሱ ሊልቅ ይችላል፡፡ በክርስትናውም ዓለም የስም ተሳትፎአቸው ያየለ ሥራውና ተግባሩ ላይ ግን ደካሞች የሆኑ፣ ብዙ የሚወራላቸው ጥቂቱም የሚበዛባቸው አሉ፡፡ ባለቀ ሥራ ላይ መራቂዎች፣ በግንባታው ላይ ግን የሩቅ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው፡፡

         ተወዳጆች ሆይ ከስመ አበሮች ወይስ የግብረ አበሮች ናችሁ? መልካም ነገር በስም ሳይሆን በግብር ሲተባበሩት፣ በሩቅ ሳይሆን ቀርበው ሲኖሩት ጣዕም፣ ውበትና ለሌላው የሚተርፍ በረከት አለው፡፡ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚሉት ሁሉ መንግስቱን እንደማይወርሱ፣ በቃልና በአንደበት ብቻ የሚዋደዱም ፍቅር የሆነውን ጌታ እንደማያከብሩ፣ ሕጉን የሚሰሙ ዳሩ ግን የማይፈጽሙ እንደማይባረኩ ባለቤቱ ተናግሯልና ለጽድቅ ስመ አበር ከመሆን ግብረ አበር መሆን ያስፈልገናል፡፡

          ክርስትና ነኝ ሲሉትና ሲሆኑት አንድ አይደለም፡፡ ዛሬ የሚፋንኑት የግብር ሳይሆን የስም አበሮች ናቸው፡፡ ስለ ፍቅር የሚያወሩ ግን ፍቅርን ከስም ባለፈ በግብር የማያውቁት ደግሞም የማይገልጡት፣ ለመውደድ አይደለም ለመወደድ እንኳን ልባቸው የማይታዘዝላቸው፣ ርኅራኄን በስም ብቻ የሚያውቁት ነፍሳቸው ለባልንጀራ የማይራራላቸው ላማጡት የጨከኑ፣ ይቅርታን በርቀት ያውም በስም የተግባቡት የስም አበሮች የግብር ባይተዋሮች፣ ስለ መሆን ብዙ የሚያብራሩ ጥቂት የማይኖሩ የሕይወት ተላሎች ቤት ይቁጠራቸው፡፡ በስም ባልና ሚስት በተግባር የጧሪና ተጧሪ ኑሮ የሚኖሩ የዘወትር ርእሳቸውና ጭቅጭቃቸው በጀት የሆነ የግብረ አበር ያለህ ይላሉ፡፡ መንፈሳዊውም ዓለም የስም ሳይሆን የተግባር ጥያቄው እያየለ መጥቷል፡፡ ተወዳጆች ሆይ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ የምንገልጠው በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ነውና እውነትን በስም ብቻ ሳይሆን በግብርም እንድንተባበር ጸጋው ይብዛልን!!!  

1 comment:

  1. Amen! Bekal ena be andebet bicha sayhon be sira ena be'ewnet endintebaber Egziabher yirdan....fikrachinm yalegibzinet yihun!

    ReplyDelete