Wednesday, April 18, 2012

ፍቅር ጲላጦሳዊ



       አንዳንድ ሰዎች ፍቅር ልክ እንደ እቅፍ አበባ ለሌላው የሚሰጥ ነገር እንደሆነ ሲያስቡ ሌሎች ደግሞ በላይህ ላይ የተጣለ የማይረባ ግን ደግሞ የጠነከረ ኃይል ነው በማለት ይስማማሉ፡፡ ፍቅር ግን ልንሰጠው የምንችለው ማንኛውም ነገር አይደለም፡፡ ፍቅር ራሱ ሌሎች ነገሮችን እንድንሰጥ የሚያስችለን ከፍተኛ ግፊት ነው፡፡ ጥንካሬን፣ ኃይልን፣ ነፃነትንና ሰላምን ለሌሎች እንድንሰጥ የሚረዳን ጉልበት ነው፡፡ ከዚህ መንፈስ በመነሣት ፍቅር ውጤት ሳይሆን መንስኤ፣ ወራጅ ሳይሆን ምንጭ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በፍቅር የተነሣ የማንሰጥ ከሆነ፣ በፍቅር የተነሣ ይቅር የማንል ከሆነ፣ በፍቅር የተነሣ የማንራራ ከሆነ፣ በፍቅር የተነሣ ለእውነት የማንኖር ከሆነ በእኛ ያለው የፍቅር ኃይል ዋጋ የለውም አሊያም ሞቷል ማለት ነው፡፡

           የሰው ፍቅር ልዩ ልዩ ቢሆንም የእግዚአብሔር ፍቅር አንድ መሆኑ ዘመን የማይሽረው መጽናኛችን ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን እንዴት እንደወደደን መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “እንዲሁም ዓለም አንተ እንደላከኝ በወደድከኝም መጠን እነርሱን እንደወደድካቸው ያውቃሉ” (ዮሐ. 17÷23) ይላል፡፡ እግዚአብሔር እኛን የወደደን ፃድቅ፣ የዋህና ትሁት የሆነውን እስከ መስቀል ሞትም የታዘዘውን አንድ ልጁን በወደደበት ፍቅር ነው፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔር ሲወድ የሰውን ማንነት ታሳቢ አድርጎ አይደለም የምንለው፡፡ መልክና ቁመና ሀብትና ስነ ምግባርን ግምት ውስጥ በማስገባት አልያም ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ሰውን መውደድ የሰው ፍቅር ነው፡፡ አይነቱም ልዩ ልዩና ብዙ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ፍቅር ጲላጦሳዊን በመጠኑም ቢሆን ለማየት እንሞክራለን፡፡ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ወደ መስቀል በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ ከምናስተውላቸው ሰዎች መሐል እንዱ ጲላጦስ ነው፡፡

         ጲላጦስ የጴንጤን አገር ሰው ሲሆን ከ26-36 ዓ.ም የነበረ የይሁዳ ገዥ ነው፡፡ በጭቆና የገዛና ብዙ ሰዎችን ያስገደለ እንደነበር እንዲሁም ከገሊላ ገዥ ከሄሮድስ ጋር እንደተጣላ እናውቃለን፡፡ (ሉቃ. 23÷12) ጲላጦስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዲፈርድ አይሁድ በፊቱ ባቀረቡለት ጊዜ በቅንዓት እንደፈረዱበት ተረድቶ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ የገዛ ሚስቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍርድ እንዳያዛባ ውሳኔውንም እንዲያጤነው አስጠንቅቃዋለች፡፡ (ማቴ. 27÷18-19) ራሱ ጲላጦስ ስለ ክርስቶስ ንጽሕና ሦስት ጊዜ መስክሯል፡፡ (ሉቃ. 23÷4፡15፡22)

         ጲላጦስ የኢየሱስን መንፈሳዊ ሥልጣን ይፈራ ነበር፡፡ በመግረፍም ሊለቀው ሞክሮ ነበር፡፡ ኢየሱስ አንዳች ለሞት የሚያበቃ ወንጀል እንደሌለበትም ተገንዝቧል፡፡ ነገር ግን እጁን ታጥቦ ለሞት አሳልፎ ሰጠው፡፡ ጲላጦስ ላመነበት መጨከን ያቃተው ምስኪን፣  የቄሳር ወዳጅ ለመባል የሰማይና የምድር ንጉስ የሆነውን ጌታ ለነጣቂዎች የተወ ገዥ ነበር፡፡ ፍቅር ጲላጦሳዊ መልኩ እንዲህ ነው፡፡ ይታጠባል ግን የቆሸሸ ተግባር ይፈጽማል፡፡ በአፍ ስለ መልካምነታችሁ ያወራል ግን በወንበዴ መሐል ያሰቅላል፡፡ በአፍ ፍትሐዊ በተግባር ግን ፍትህ አጉዳይ ነው፡፡ ፍትሕ የሰው ልጆች ሁሉ ቋሚ ጥማት ነው፡፡ ለድህነት እንደ መንስኤ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ የፍትህ መጓደል ነው፡፡ ፍትሐዊ ያልሆነ የሐብት ክፍፍል፣ አድሎአዊ የሆነ የጥቅም ማጋራት ሂደት እነዚህን የመሳሰሉት ሁሉ ድህነትን የፍትህ መዛባት ውጤት ያደርጉታል፡፡ የፍቅር ትልቁ ጠባይ ፍትህ ነው፡፡ ፍቅር ጲላጦሳዊ፡-

1. ፍትህን ያዛባ ነው፡- ሕሊና ስውር ፍትሃዊ ዳኛ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የምንመስልበት ትልቁ ጠባይ ደግሞ ማስተዋላችን ነው፡፡ ነገር ግን የሰውን ሕሊና ሐሰት ሲጠመዝዘው ፍትህ ይዛባል፣ ፍርድም ይጓደላል፡፡ ገጣሚው፡-
እውነት ቤት ሥትሠራ
ውሸት ላግዝ ካለች
ጭቃ ከለሰነች
ሚስማር ካቀበለች
ቤቱም አልተሠራ
እውነትም አልኖረች፡፡

        ፍቅር ለፍትህ የሚኖርና ለእውነት የሚሞት ነው፡፡ ጲላጦስ ለእውነት ቢፈርድ ወንበሩን ያጣ፣ የቄሳር ወዳጅነት ይቀር፣ የሕዝቡን ጥላቻ ይጋፈጥ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሕሊናውንና ትልቅ ወዳጅ እግዚአብሔርን ያተርፍ ነበር፡፡ ሰው ኖሮ ኖሮ እግዚአብሔርን ካላተረፈ ሁሉስ ምን ይረባዋል? ተወዳጆች ሆይ ፍትሃዊነት እግዚአብሔርን የምንመስልበት መንገድ ስለሆነ ፍቅራችን ለፍትህ የቆመ ደግሞም የቆረጠ ሊሆን ይገባል፡፡ ጲላጦስ ንጹሁን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቶ ወንጀለኛና ኃጢአተኛውን በርባንን የለቀቀ ነው፡፡ ፍቅራችን ፍትህን ያልበደለ፣ እውነትን ያልደለለ ይሁን፡፡

2. ግብዝ ነው፡- ጲላጦስ አደባባይ ላይ እጁን ታጥቦ ከደሙ ንጹሕ ነኝ አለ፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅ ግን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጥቶታል፡፡ ይህ ምንኛ የሚገርም ግብዝነት ነው፡፡ እጁን ቢታጠብም ልቡ ከአመጽ አልጸዳም ነበር፡፡ ቃሉ፡-“ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን” (ሮሜ. 12÷9) ይላል፡፡ ግብዝነት የምናወራውን አለመኖር ነው፡፡ ከደሙ ንጹህ መሆኑን አፍአዊ በሆነ መንገድ ቢናገርም በተግባር የገለጠበት ሁኔታ ግን የሰነፍ ብልሃት ነበር፡፡ በአፍ መርቆ በልብ እንደ መሸርደድ ያለ ነው፡፡

           ለብዙዎቻችን ማስመሰል የመሆን ማካካሻ አልያም ለድካማችን ዋሻ ነው፡፡እግዚአብሔር ግን ካስመሰልነው ብዙ በሆነው ጥቂት ይከብራል፡፡ ሚስቱ ላይ ወንበር ሰባብሮባት፣  ልጁንም እኩለ ሌሊት ከቤት አስወጥቶ ሸምጋይ ፊት ሲቆም “ይህንን ያደረኩት ሚስቴንና ልጄን ስለምወድ ነው” ብሎ ቢናገር አትደነቁምን? ፍቅራችን ያለ ግብዝነት ይሁን፡፡

3. ዋጋ አይከፍልም፡- ለእውነት ዋጋ ሳይከፍሉ እውነተኛ፣ ለፍቅር ዋጋ ሳይከፍሉ አፍቃሪ፣ ለፍትህ ዋጋ ሳይከፍሉ ፍትሃዊ፣ ለወንጌል ዋጋ ሳይከፍሉ አገልጋይ የመባል ፍላጎት በእጁጉ የሚስተዋልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ፍቅር ጲላጦሳዊ የተጠናወታቸው ለእውነት ሳይሆን ለአብላጫ ጩኸት የተሸነፉ ናቸው፡፡ ሞት ባይገባችሁም ለሞት አሳልፈው ይሰጥዋችኋል፡፡ ጲላጦስ ክርስቶስ አንዳች በደል እንደሌለበት እየመሰከረ ክርስቶስን ደግሞ ልሰቅልህ ወይንም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን? ይለው ነበር፡፡

      ሁሉም ሰው ዋጋ የማያስከፍል ኑሮ፣ ወዳጅነት፣ ትዳር፣ አገልግሎት፣ ትምህርት ይፈልጋል፡፡ ሕይወት ደግሞ በዚህ መንገድ ወደ ከፍታን ስኬት፣ ወደ በረከትና ድል መድረስ አታስችልም፡፡ ፍቅር ላይ የጨከኑ፣  እውነት ላይ የቆረጡ እነርሱ አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ላለንበት ሁኔታ ባለፈው ጊዜ፣ ትውልድ፣ ቤተሰብ ምን ያህል ዋጋ ተከፍሏል? ከበደል በኋላ የሰው ሕይወት ዋጋ በመክፈል (በመስዋዕትነት) ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ጲላጦስ ለተረዳው እውነት ያልጨከነ ነበር፡፡ እኛም በክርስቶስ ነገር በወንጌል ጉዳይ ልባችን እንዲጨክን ጌታ ይርዳን፡፡ ክርስቶስ ተነሥቷል መቃብሩም ባዶ ነው!!!
                                                           





1 comment:

  1. Amen ye Egziabher tsega yagizen....motachinin bemotu shiro ye zelalem hiwotin leseten geta kibir yihun!

    ReplyDelete