Tuesday, April 24, 2012

የኤልያስ ሽሽት



           መጽሐፍ ቅዱስ ስለ በረቱ ሰዎች ብቻ የሚናገር መጽሐፍ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የተጠቀመባቸውንም ሰዎች ድካም ያለመሸሸግ የሚያስነብበን ሚዛናዊ መጽሐፍ ነው፡፡ ስለ በረቱት ጉብዝና ስናነብ መዛል መድከም አለና አንታበይም፡፡ ስለተፍገመገሙት ስለወደቁት ስናነብ ደግሞ መቆም አለና ተስፋ አንቆርጥም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሀብታም ነኝና ባለ ጠጋ ሆኛለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም ለሚሉ ነገር ግን ጎስቋላና ምስኪን፣ ደሀና እውር የተራቆቱም መሆናቸውን ለማያውቁ የሕይወት ተላሎች ብርቱ ተግሳጽ ነው፡፡ ለመከራ የተፈጠሩ፣ ለፈተና የተበጁ፣ በመጨረሻው የውርደት ስፍራ ላይ የተጣሉ ለሚመስላቸው፣ ከችግር ወደበለጠ ችግር ለሚገላበጡ፣ የመሸ እንደማይነጋ፣ የመረረ እንደማይጥም፣ የጠመመ እንደማይቀና፣ ያጣ እንደማያገኝ የገዛ ልባቸው ለሚሰብክላቸው ደግሞ ቃሉ መጽናናት ነው፡፡

(In the very same revelation that shows us God, then, we see also His dealings with us- how He loves us, desires the best for us, sets forth His plan for us.)1

         በዚህ የሕይወት መጽሐፍ ታሪካቸው በማይዋሸው መንፈስ ቅዱስ ከተፃፈላቸው የእግዚአብሔር ሰዎች መካከል ካነሣነው ርእስ ጋር ሊሄድ የሚችለውን የኤልያስ ኑሮ እንዳስሳለን፡፡ (1ነገ. 18÷1) በእስራኤል ምድር ላይ ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ዝናብ ከተከለከለ በኋላ የእግዚአብሔር ድምጽ ወደ ኤልያስ “ ሂድ ለአክዓብ ተገለጥ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ” ሲል መጣ፡፡ ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው እንደተባለ የእስራኤል ልጆች በሁለት አሳብ ያነክሱ ስለነበር ነቢዩ ኤልያስ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር አምላክነትና ከበኣል አምላክነት የሚበጃቸውን አስተውለው እንዲከተሉ አማረጣቸው፡፡ የእስራኤል ልጆች በኤልዛቤል ማዕድ የሚበሉ 450 የበኣል ነቢያት፣ ንጉሡ አክዓብ፣ 400 የማምለኪያው ዐጸድ ነቢያት፣ ራሱ ኤልያስን ጨምሮ ሁሉም በቀርሜሎስ (ፍሬያማ ቦታ) ተራራ ላይ ተሰበሰቡ፡፡ ኤልያስም በእነዚያ ሁሉ የበዓል አምላኪዎችና ነቢያት መሐል ለብቻው በእግዚአብሔር ስም ተገለጠ፡፡ ከበኣል የሆኑትም ሁሉ ለጣዖታቸው ወይፈኑን አሰናድተው ከማለዳ እስከ ቀትር ድረስ በአል ሆይ ስማን እያሉ ስሙን ይጠሩ ነበር፡፡ በታላቅ ቃል እየጮኹ ትንቢት እየተናገሩ ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ገላቸውን በካራና በቀጭኔ ይብዋጭሩ ነበር፡፡ ነገር ግን የሚመልስ፣ የሚያደምጥም አልነበረም፡፡

          ኤልያስ ከመስዋዕተ ሠርክ በኋላ ማፈርን በተሞሉት የበኣል አምላኪዎች ፊት ሕዝቡን ሰብስቦ የእግዚአብሔርን መሠዊያ አበጀ፡፡ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቆርጦ በእንጨቱ ርብራብ ላይ አኖረው፡፡ ከጣዖታቸው የእሳት ምላሽ ባጡት ሁሉ ፊት እንዲህ ሲል ጸለየ “አቤቱ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ፡፡” ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር እሳት ወደቀች መሥዋዕቱንም በላች፡፡ ሕዝቡም ሁሉ በግንባራቸው ተደፍተው እርሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው አሉ፡፡ ኤልያስም የበኣልን ነቢያት ሁሉ በቂሶን ወንዝ ወስዶ አሳረዳቸው፡፡ እግዚአብሔርም የሰው እጅ ከምታህል ጥቂት ደመና ብዙ ዝናብን ለምድሪቱ ሰጠ፡፡ ኤልያስም በአክዓብ ሠረገላ ፊት ወገቡን አሸንፍጦ ይሮጥ ነበረ የእግዚአብሔርም እጅ በእርሱ ላይ ነበረች፡፡

         ከዚህ ሁሉ የእግዚአብሔር ሰው ድል በኋላ አክዓብ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመለስ ለሚስቱ ለኤልዛቤል የሆነውን ሁሉ ነገራት፡፡ ኤልዛቤልም፡-ነገ በዚህ ጊዜ ነፍስህን ከእነዚህ እንደ አንዲቱ ባላደርጋት አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህንም ይጨምሩብኝ ብላ ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች፡፡ ኤልያስም ነፍሱን ሊያድን አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና፡-ይበቃኛል አሁንም አቤቱ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ (1ነገ. 19÷1-4)፡፡

         ከላይ ለማየት የሞከርነው የኤልያስ ታሪክ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት የሚሆን ብዙ ቁም ነገሮችን የያዘ ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ የምናልፍባቸው ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ለልባችን የሚሰጡት የተለያየ ትርጉም አለ፡፡ አንዳንዶቻችን ከመከራችን እንኳን መታዘዝን ስንማር ሌሎች ደግሞ እንኳን ከፈተናቸው ከምቾታቸውም ትርፋቸው አመጽ ይሆናል፡፡ አዳንዶች ከሕይወት ውጣ ውረድ ኑሮዬ ይበቃኛል ማለትን ሲማሩ ሌሎች ደግሞ ስለ ሥጋ በማሰብ እጣቸው ሞት ይሆናል፡፡ ከመከራችን ውስጥ ለሌሎች የሚተርፍ በረከት፣ ከሀዘናችን ውስጥ ለሌሎች የሚተርፍ ደስታ፣ ከመገፋታችን ውስጥ ለሌሎች የሚተርፍ ዕረፍት ይኖር ይሆን? በኑሮ ለሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች የምንሰጠው ምላሽስ ምንድነው?  

        ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ከእምነት በሆነ ድፍረት ከእርሱ መንፈሳዊ አቋም ፍጹም ተቃራኒ በሆኑ ሰዎች ፊት በእግዚአብሔር ስም ቆመ ድልም ነሣ፡፡ ከኤልዛቤል ማስፈራሪያ በኋላ ግን ክትክታ (ፍሬ አልባ ጨፈቃ) ዛፍ ስር ተኝቶ ሞትን ለመነ፡፡ ነቢዩ በርሃብ ዘመን እግዚአብሔር በዮርዳኖስ ትይዩ በሚገኘው በኮራት ፈፋ ዋሻ ውስጥ ሸሽጎ ጠዋትና ማታ እንጀራና ሥጋ በቁራ እየላከ መግቦታል፣ ከማድጋ እፍኝ ዱቄት፣ ከማሰሮ ጥቂት ዘይት፣ ከመበለት ተስፋ መቁረጥ ውስጥ በልቶ መጥገብን፣ ቆርሶ ማትረፍን አሳይቶታል፡፡ በቀርሜሎስ ተራራ ላይም ለመሥዋዕቱ በእሳት በመመለስ በበቅሎና በፈረስ ለሞት በፈለጉት ንጉስና የበኣል ነቢያት ፊት አክብሮታል በዚያ ያለውንም ሕዝብ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶአል፡፡ አሁን ግን ከሰማው የዛቻ ድምጽ የተነሣ ሞትን መፍትሔ አድርጓል፡፡ ሁላችንም ብንሆን ከዚህ የተለየን አይደለንም፡፡ ከእግዚአብሔር ብዙ ተውሎልን እንዳልተቀበልን በብዙ አውሎና ወጀብ ውስጥ መንገድ ሰጥቶ እንዳልተደረገልን ወደ ራሳችን መፍትሔና ተስፋ መቁረጥ መምጣታችን የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡ ተስፋ መቁረጥ ሞትን መመኘት በአቋራጭ የመገላገል ፍላጎት የእኛ የግል ስሜት ብቻ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ኑሮአቸውንም ሞታቸውንም ለክብሩ የተጠቀመበት ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎችም ይህንን የሸለቆና የምድረ በዳ ኑሮ ተለማምደዋል፡፡


የኤልያስ መፍትሔ፡-

1. ከሞት ወደ ሞት፡ - አስተውለነው ከሆነ ወደ ሕይወታችን ፈተና ሀዘን ጭንቀት ሲመጣ የእኛ መፍትሔ ከምንሸሸው የተሻለ አይደለም፡፡ ኤልያስ የኤልዛቤልን እገድልሃለው ሸሽቶ እግዚአብሔር ግደለኝ ወደሚል ስንፍና ነው የመጣው፡፡ እግዚአብሔር በኮራት ፈፋ ያደረገለት፣ በሲዶና አጠገብ በሰራፕታ ያዘጋጀለት፣ ቀርሜሎስ ላይ በእሳት የመለሰለት እንዲህ ባለው ፍርሃት ውስጥ ላለመውደቅ ከበቂ በላይ ነው፡፡ ነገር ግን ኤልያስ እንደ እኛው ሰው ነበር፡፡ (ያዕ. 5÷17)

        መራርነት በደጃችን ሲያደባ፣ አንደበታችንን እሮሮ ሲሞላው፣ ባላሰብነው መንገድ ባልጠበቅነው ሰዓት ችግር ደጃችንን ሲያንኳኳ ሞትን እንመኛለን፡፡ ነገር ግን እየሸሸነው ያለው ፈተና ቢበረታ ያው ራሱ ሞት ነው፡፡ ታዲያ ሰው እግዚአብሔርን ከዚህ ለተሻለ መፍትሔ ባይጋብዘው፣ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ ነህ በሚል መንፈስ በጸሎትና በምልጃ ጉዳዩን ወደ እርሱ ባያቀርብ ምንኛ ምስኪን ነው፡፡ ጸብና ክርክርን ሸሽተው መጠጥ ውስጥ የሚደበቁ፣ ስርቆትን ሸሽቶ ነፍስ የሚያጠፉ፣ ከኪሳራ ፊት ሮጠው ዝሙት ውስጥ የሚደበቁ መፍትሄያቸው እንዴት ያስደምማል፡፡ እግዚአብሔርን የምንጠይቀው በፈተና ውስጥ ስንሆንስ እንዲያደርግልን የምንፈልገው ምንድነው? በእርግጥ የምንለምነው ነገር የእርሱን ክብርና ኃይል የሚገልጥ ነገር ነውን? አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉውን አልፈራውም የሚል ነው? ወይስ ልዑልን መጠጊያው ያደረገ ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል የሚል የዋስትና ቃል አለን? አልያም ደግሞ በአጠገቤ ሺ በቀኜም አስር ሺ ይወድቃሉ ወደ እኔ ግን አይቀርብም የሚል የእምነት አዋጅ ይኖረን ይሆን?ተወዳጆች ሆይ ችግራችሁን ሸሽታችሁ የት ነው ያላችሁት? የባሰ ችግር ውስጥ አልያስ በመጠበቂያችሁ ላይ ናችሁ? በአንዱ ፈተና ተማራችሁ ብዙ ፈተና እያመረታችሁ ይሆን? ከሞት ሸሽታችሁ የት ናችሁ?

2. ከቀርሜሎስ ወደ ክትክታ ስር፡- ሽሽት ከውድቀት በኋላ የታየ የሰው ቀዳሚ መፍትሄ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ባለመታዘዝ ኃጢአትን ከሠሩ በኋላ ያደረጉት ነገር መሸሽ ነው፡፡ ነገር ግን ከመንፈሱ ወዴት እንሄዳለን? ከፊቱስ ወዴት እንሸሻለን? በበረታ ቀትር (ፀሐይ) ሁላችንም ጥላ መፈለጋችን እሙን ነው፡፡ ለእኛ ግን ወደ እግዚአብሐር መቅረብ እንዲሻለን ማወቅ ግን ያስፈልገናል፡፡ ቅጠል ማገልደም፣ ከግንድ ጀርባ መሸሸግ፣ ምክንያት መደርደር እነዚህ ሁሉ የሰው መፍትሔዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ካለው አሳብና መንገዳችን መንገዱ የተለየ አሳቡም የራቀ ነው፡፡  

         ኤልያስ ፍሬያማ ከሆነው ቀርሜሎስ ጨፈቃ ወደሆነው የክትክታ ምድረ በዳ ሸሸ፡፡ ያንን ከሚያህል ከፍታ እንዲህ ወዳለው ዝቅታ ወረደ፡፡ ኤልዛቤል፡-“ነፍስህን ከእነዚህ እንደ አንዲቱ ነፍስ ባላደርጋት”አለችው፡፡ እርሱ ደግሞ እግዚአብሔርን፡-“እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ” ብሎ እንዲሞት ለመነው፡፡ የኤልያስ ልመና የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ እንደነበረው በኋላም በሰዎች ሁሉ ፊት እግዚአብሔር ያዘጋጀውን ማዳን እንዳየውና እንደቃልህ ባሪያህን አሰናብተኝ እንዳለው ስምዖን (ሉቃ.2÷29) አልያም ልሄድ ከክርስቶስ ጋርም ልኖር እናፍቃለሁ እዳለው ቅዱስ ጳውሎስ (ፊል. 1÷23) ያለ አይደለም፡፡ ይህ ዛቻ የወለደው ፍርሃት ያናገረው ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ የእኛስ መፍትሔ ከድጡ ወደ ማጡ አይነት ይሆን? ተራራው ላይ በብርታት ሸለቆ ላይ በዝለት ምን ያህል ጊዜ ተገኝተናል? እግዚአብሔርን ከማዳመጥ ራሳችንን ወደ ማዳመጥ ፈቀቅ ባልንበት ጊዜ ሁሉ የሚሆነው ይኼው ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን አዋቂ ነው፡፡


የእግዚአብሔር መፍትሔ፡-

1. ከሞት ወደ ሕይወት፡- ከእድሜያችሁ ምን ያህል የቀራችሁ ይመስላችኋል? ከምንኖረው የኖርነው እንደሚበልጥ ባይካድም የፊቱን የሚያይልን ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ኤልያስ ሞትን ሸሽቶ ከሞት የበለጠ ነገር ግን አለመነም፡፡ ከለመነው አብልጦ የሚሰጥ እግዚአብሔር ግን ነቢዩ ግደለኝን ሲያወራው ኑርልኝን ይነግረው ነበር፡፡ ኤልያስ ስላጠናቀቀው ስላከናወነው ነገር በእግዚአብሔር ፊት ሲያወራ እግዚአብሔር ግን ገና ስላልተጨረሰ መፈጸምም ስላለበት ሩቅ መንገድ ይነግረው ነበር፡፡

       ጌታ እንዴት ያለ ወዳጅ ነው፡፡ እስከ ሽምግልና ወደሚሸከመን እንጂ ወደ ሞት አንሸሽም፡፡ ከሸክማችን ወደሚያሳርፍ የዘላለም ሕይወት እንጂ ወደ ባዶ ተስፋ አንጠጋም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ (ልዑል)ሞታችንን ሞቶ መጠጊያ ሆኖናል፡፡ ከበደልና ከኃጢአታችን የተነሣ መተላለፍ ወደ ሞት ሲነዳን ቀራንዮ ላይ ሞታችንን ሞቶ ሕይወትን የሰጠን ጌታ ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡ እግዚአብሔር የሞት መፍትሔ የለውም፡፡ እርሱ የሟቹን ሞት የማይፈልግ ትጉህ እረኛ ነው፡፡

2. ከሸለቆ ወደ ከፍታ፡- ወደ መቃብር እየሄድን በአብ ቀኝ ስፍራ እንደተዘጋጀልን የሰማንበት የምስራች ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ ስለ እኛ ተዋርዶ ወደ ክብር ያሸጋገረን ወዳጅ ይህ ነው፡፡

“እርሱም ወደታች ወርውሩአት አለ ወረወሩአትም ደምዋም በግንቡና በፈረሶቹ ላይ ተረጨ ረገጡአትም” (2ነገ. 9÷33)፡፡ ዝናብ በተከለከለባቸው ዓመታት ሁሉ ኤልያስ በበቅሎና በፈረስ ለሞት ሲታሰስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን የማያስደፍር አጥር ነው፡፡ ጥቅሱ በኢዩ ትዕዛዝ ኤልዛቤል ከመስኮት ወደ መሬት ተወርውራ የሞተችበት ቃል ነው፡፡ ስለ ኤልያስ የተባለውን ደግሞ እንይ፡፡ “ሲሄዱም እያዘገሙም ሲጫወቱ እነሆ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው ኤልያስም በአውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ” (2ነገ. 2÷11)::

          የእግዚአብሔር ቃል የኤልዛቤልን ውድቀት የኤልያስን ከፍታ ይነግረናል፡፡ ነቢዩ ለራሱ ያየው ሞት ነው የፊቱን የሚያውቅ እግዚአብሔር ያየለት ደግሞ ሕይወት ነው፡፡ እርሱ ክትክታ ስር ተኛ እግዚአብሔር ግን ለእርሱ ያዘጋጀው እረፍት ከፍታ ነበር፡፡ ኤልዛቤል ከከፍታው ስትንኮታኮት ኤልያስ ደግሞ ከሸለቆ ወደ ሰማይ ወጣ፡፡ ከቀርሜሎስ ተራራ እስከ ኢይዝራኤል ወገቡን አሸንፍጦ በአክዓብ ሠረገላ ፊት እንዳሮጠ አሁን በእሳት ሠረገላ ተወሰደ፡፡ እግዚአብሔር ባለ ጠጋ አይደለምን? ተወዳጆች ሆይ ጌታ ከሞት የተሻለ መፍትሔ አለው፡፡ ይህ ይታያችኋልን?ማስተዋል ይብዛልን!!

















     
_________________________________________________
1. The Orthodox Study Bible New Testament and Psalms, St. Athanasius Orthodox Academy, 1993, page 823, USA.

4 comments:

  1. ጌታ ፀጋውን ያብዛላችሁ ክብር ሁሉ በክብር ከፍ ላደረገን ለኢየሱስ ይሁን

    ReplyDelete