ሐይቅ
እስጢፋኖስ (ኢየሱስ ሞዓ) አካባቢ ከገዳሙ ትንሽ ራቅ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ነው፡፡ ለብዙዎቻችሁም አዲስ ሊሆን እንደሚችል
እገምታለሁ፡፡ አገራችን የመፈቃቀር፣ አብሮ የመብላት፣ እንግዳ የመቀበል ታሪክ ብቻ ያላት አይደለችም፡፡ ደም የመቃባት፣ የገዛ ወገንን
ገሎ የመሸለል፣ አቂሞ ለበቀል ዱር የመሸፈትም ታሪክ የተሸከመች ናት፡፡ ስለ ፍቅር አብዝቶ በሚነገርበት፣ አብሮ መኖርና መደጋገፍ
እንደ ስልጣኔ በሚቆጠርበት ዓለም ዛሬም ድረስ በሞት የሚፈላለ፣ጉ ለጥፋት የተሰማሩ መኖራቸውን ማስተዋል እጅጉን ለልብ ሀዘን ነው፡፡
አካባቢው
ላይ በተገኘንበት ወቅት አንድ ሰው ተገድሎ ፀጥታ አስከባሪዎች ስፍራውን በብርቱ ይጠብቃሉ፡፡ ከመጠየቅ እንደተረዳነው ምክንያቱ የሟች
ቤተሰቦች የገዳይን ወገን እንዳይገሉ ለመጠበቅ መሆኑን ተረዳን፡፡ በአንድ ሰው ስህተት ሙሉ ቤተሰብ መጨነቁ፣ ነፃነት አጥቶ የቤት
ውስጥ እስረኛ መሆኑ፣ በሞትኩ አልሞትኩ ሥጋት መሸበሩ እንኳን ለባለቤቶቹ ለታዛቢውም የሚጨንቅ ነበር፡፡ ማኅበረሰቡ ግን አብሮት
እንዳደገ የቤት እንስሳ በጉዳዩ አለመገረሙ ያስገርም ነበር፡፡ እኛም ያለበደሉ ሞት በደጁ የሚያደባበትን ቤተሰብ ሊታደግ የሚችለው
መፍትሔ ምንድነው? በማለት ጠየቅን፡፡ የተሰጠን መልስ ግን ለሌላ ጥያቄ የሚጋብዝ ነበር “የሰነፍ እርቅ”፡፡ እንደተነገረን ከሆነ
የሰነፍ እርቅ ማለት ገዳይ በሕግ ጥላ ስር ከሆነ በኋላ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ በዚህ መሐል የገዳይ ቤተሰቦች በሟች ወገን ጥቃት
(ግድያ) እንዳይደርስባቸው ለጊዜው የሚደረግ መገላገያ ነው፡፡ ስለ ዋስትናው የጠየቅናቸው አባት እንደነገሩን “በሰነፍ እርቅ አስገደለኝ”
የሚባል አባባል እንዳለ ጠቅሰው የሟች ቤተሰብ እርቁን ሊያፈርስ፣ የገዳይን ቤተሰብ ሊገድል እንደሚችልና በብዛት እንዲህ ያለው ነገር
ሲከሰት እንደሚስተዋል አስረድተውናል፡፡ በማከልም የሟች ቤተሰብ ውሉን አፍርሶ ቢገኝ በሕብረተሰቡ ዘንድ ነውር እንደሆነ ነግረውናል፡፡
ከዚህም ጋር አያይዘው ልብን የሚነካ ታሪክ ማለትም የሰነፍ እርቅ ከተደረገ በኋላ ስለሞተ ሰው አጫውተውናል፡፡ ብዙ ጊዜ የሰነፍ
እርቅ ሲከናወን ካሳ ስለማይካስና ሽምግልናው ገዳይ ተገኝቶ መጸጸቱን የማያሳይበት በመሆኑ ዘላቂነቱ አጠራጣሪ እንደሆነም መረዳት
ችለናል፡፡
ደም በደም፣ ወንጀል በበለጠ ወንጀል፣ ቅያሜ በከፋ በቀል የሚመለስበት አገር
ላይ እየኖርን መሆኑን ማወቃችን ምን ያህል በጸሎት መትጋት እንዳለብን የሚጠቁም ይመስለኛል፡፡ አንዱ በዘራው ሌላው እያጨደ፣ አንዱ
በበደለ ሌላው እየካሰ፣ አንዱ ባጠፋ በጅምላ እየተላለቅን መኖራችን እውነት በልባችን ላይ ስፍራ እንደተነፈገ የሚያስረዳ ነው፡፡
እንዲህ ያለውን ነገር ለመቀየር የተለያዩ ቤተ እምነቶች በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ለይቅርታ ያለንን አመለካከት
ማስተካከልና ማሳደግ አለብን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል “ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ” (ቆላ. 3÷13)
ይላል፡፡ የይቅርታችን መሠረት እግዚአብሔር በልጁ በኩል ለእኛ ያሳየን (የሚወደውን አንድያ ልጁን በመስጠት) ይቅርታ ሲሆን እኛ
ለሌሎች ይቅርታ እንድናደርግ የሚያስችለን ኃይል (ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና) ደግሞ በመስቀል ላይ ሆኖ ለወጉት
ምሕረትን የለመነው ጌታ ነው፡፡ ያንን የመስቀል ላይ ምሕረት በደም የሆነ ይቅርታና ስርየት ዕለት ዕለት የሚያስታውሰን ደግሞ ቅዱሱ
የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡
ክርስቶስ እኛን ይቅር ያለን በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን፣ ከፍጥረታችንም
የቁጣ ልጆች ሳለን ነው፡፡ የኃጢአት ደመወዝ ሞት እንደመሆኑ የዘራነውን ማጨድ ፍትሃዊነት ሆኖ ሳለ ክርስቶስ ግን የማይገባንን ሕይወት
ሰጥቶ የሚገባንን ሞት እርሱ ሞተልን፡፡ (ኤፌ. 2÷1-6) ዛሬ በእኛ ላይ የሚሆንብን ነገር እኛ በእግዚአብሔር ላይ ከሠራነው በደል
አይበልጥም፡፡ ብዙው ተትቶልን ጥቂቱን ይቅር ማለት ካልቻልን ግን እጀ ነካሽ፣ ወጪት ሰባሪዎች ነን፡፡ እግዚአብሔር ሰነፍ እርቅ
የለውም ይቅርታና ምሕረቱ ለዘላለም ነው፡፡ በዚህም ይጸጸት ዘንድ እግዚአብሔር ሰውን አይደለም፡፡
ይህንን
ርዕስ ያነሣሁበት ምክንያት ለምክርና ለተግሳጽ የሚሆን ጥቂት ቁም ነገር ስላገኘሁበት ነው፡፡ በእኛስ ሕይወት ሰነፍ እርቅ አይስተዋል
ይሆንን? ፆም እስኪፈታ የይምሰል ታርቀን በነገር የምንፈስክ ስንቶቻችን ነን? ካንጀት ሳይሆን ካንገት፣ የልብ ሳይሆን የአፍ እርቅም
ሰነፍ እርቅ ነው፡፡ ከፊል ቂም ከፊል ይቅርታ፣ ከፊል ኩርፊያ ከፊል ሰላምታ፣ ከፊል መንፈግ ከፊል መቸር ባጠቃላይ ይግደልሽ እያሉ
ይማርሽ እንደሚባለው ያለ አይነት ነው፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑትን፣ በእውነትና በመንፈስ የሚያመልኩትን እንዲህ ይላል “እንግዲህ
መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ
አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ፡፡ (ማቴ. 5÷23-24) ክርስቶስ ለእኛ ያሳየውን ይቅርታ ስንረዳ እኛም ሌሎችን ይቅር የማለት ጉልበት
እናገኛለን፡፡ ይቅር ማለት ይብዛላችሁ!!
Egziabher be'anid liju bekul yasayewn yikrta endinreda ena egnam yikr bay lib endinoren Egziabher yirdan!
ReplyDelete