Friday, April 27, 2012

ድል የመንሣት መርኅ


         

         ሕይወት ብርቱ ሠልፍ በሆነችባት ዓለም ውስጥ በኑሮ ላይ ድል የማንግኘት ፍላጎት የሁሉም ነው፡፡ ከክርስቲያን ማብራሪያዎች አንዱም ወታደር የሚለው ነው፡፡ (2 ጢሞ. 2÷3) ወታደርን ስናስብ ለመንግስቱ ሕግ መከበር የቆመ በማንኛውም ውጊያ ውስጥ ቆርጦ የሚሠለፍ ድሉንም ሽንፈቱንም በጋራ የሚያጣጥም፣ በአጠቃላይ ፈቃዱ ሁሉ ወደ መንግስቱ የሆነ ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡ በክርስትና ውስጥ ውጊያው እንደ ሰው ልማድ አይደለም፡፡ መጋደላችንም ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው፡፡ (ኤፌ. 6÷12) ስለዚህ በማንኛውም ሠልፍ ውስጥ ባለ ድል ለመሆን የምንከተላቸው መርሆዎች ሽንፈታችንንም ድላችንንም የመወሰን አቅም አላቸው፡፡

        ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የፊልጵስዩስን መልእክት ሲጽፍ የነበረበት ሁኔታና በመልእክቱ ውስጥ የተላለፈው የእግዚአብሔር አሳብ ለአንድ ክርስቲያን ድል መንሣት “መርኅ” የሚሆን ትምህርትን የሚያስተላልፍ ነው፡፡ መልእክቱ የተፃፈው በሮም እስር ቤት ውስጥ ሲሆን የመልእክቱ ጥቅል አሳብ “በጌታ ደስ ይበላችሁ” የሚል ነው፡፡ (ፊል. 4÷4) ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መካከል ስለ ደስታ አብዝቶ የሚናገር ክፍል ሲሆን ኑሮ የምሬት አደባባይ ለሆነባቸው፣ ዛሬን በሥጋት ለሚያሳልፉ ነገንም በፍርሃት ለሚጠባበቁ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል መፍትሔን የያዘ ነው፡፡ መልእክቱ አራት ምእራፎችና አንድ መቶ አራት ቁጥሮች ሲኖሩት በዋናነት የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታ ከአፍሮዲጡ ስለመቀበሉ የፊልጵስዩስን ቤተ ክርስቲያን ለማመስገን የተፃፈ ነው፡፡


         ሐዋርያው ያሳየውን ጥንካሬ ስንዳስሰው ሊታሰብለት በሚገባ ቦታ ላይ ሆኖ ለሌሎች ያስባል፣ ሊጠየቅ በሚገባ ቦታ ላይ ሆኖ ስለ ሌሎች ደኅንነት ይጠይቃል፣ እርሱ መጽናናት በሚገባው ስፍራ ላይ ሆኖ ሌሎችን ያጽናና ነበር፡፡ እኛ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በወኅኒ እንደተጣልን እናስብና ምን አይነት መልእክት ልንጽፍ እንደምንችል ገምቱ? መኝታው ይቆረቁራል፣ ምግቡ አይመችም፣ እገሌን የእኔ ቀን ደግሞ ሲመጣ ያገናኘን በሉልኝ፣ የምወጣበት ቀን ናፍቆኛል፣ የመሳሰሉትን ከዚህ ዓለም ፈቀቅ ያላሉ አሳቦች ልንጽፍ እንችል ይሆናል፡፡ መሄድ ከክርስቶስ ጋር ለመኖር መናፈቅ፣ እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል ለማወቅ መጓጓት፣ ኑሮዬ ይበቃኛል ማለትን መማር፣ ሁሉን ከሁሉ ስለሚበልጥ ጌታ እንደ ጉዳት መቁጠር፣ ወደ ሙታን ትንሣኤ ለመድረስ መመኘት፣ አገሬ በሰማይ ነው ብሎ መመካት፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ ማሰብ፣ በተቃዋሚዎች አገልግሎት ደስ መሰኘት እነዚህ ሁሉ ከሥጋ እስራት ውስጥ የተፃፉ የመንፈስ አርነቶች ናቸው፡፡ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች ከመከራቸው ለሌሎች ትመምህርትና መጽናናት የሚሆን ነገርን ትተዋል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ልጅም“ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ” (ዕብ. 5÷8) ተብሎለታል፡፡ እኛስ ከፈተናዎቻችንና ከችግሮቻችን የተማርነው ምንድነው?

         በጉድለት ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ሙላትነት፣ በሕመም ውስጥ ስለ ጌታ መድኃኒትነት፣ በርሀብ ውስጥ ስለ እርሱ እንጀራነት፣ በሀዘን ውስጥ ስለ ጌታ ደስታነት ማውራት በጉዳት ውስጥም በሁሉ ማመስገን እንዴት ያለ ዕረፍት ነው፡፡ በአንበሳ ጉድጓድ፣ በወኅኒ ሠንሰለት፣ ሰባት እጥፍ በሚነድ እሳት፣ ፍጥሞ ደሴት ላይ በግዞት፣ ከእግር እስከ ራስ በሚደርስ ቁስል፣ ቀኑን ሁሉ በመገደል ያለፉ የእግዚአብሔር ሰዎች ለጌታ ስንፍናን አልሰጡም፡፡ ይልቁንም በእውነትና በመንፈስ ለሚመለከው ተንበረከኩ፣ እጃቸውን ከልባቸው ጋር አንስተው አመሰገኑ፡፡ ታዲያ ድል የመንሣታቸው ምስጢር ምን ነበር? እስር ቤት ስለ ነፃነታቸው እንዲያወሩ፣ በሚነድ እሳት መሐል ለሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲንበረከኩ፣ በአናብስት ጉድጓድ ውስጥ የይሁዳውን አንበሳ እንዲያመልኩ፣ በወጋሪዎች መሐል የእግዚአብሔርን ክብር እንዲያስተውሉ፣ በታላቋ ሮም ከተማ ውስጥ ሆነው አገራቸው ሰማይን ተቤዢአቸው ክርስቶስን እንዲካፍቁ የሆነበት የሕይወት መመሪያቸው ምን ቢሆን ነው? በችግር፣ በሕመም፣ በስደት፣ በብቸኝነት፣ በሀዘን፣ በመከዳት ሸለቆ ውስጥ ላለን ሁሉ የፊልጵስዩስ መልእክት ድል መንሣትን በመከራ ውስጥ መጽናትን የሚያስተምር ነው፡፡ ከዚህ በታች በአራቱም ምእራፍ ውስጥ የየምእራፉን ዋና ሐሳብ በማንሳት አራት ድል የመንሣት መርሆዎችን እናያለን፡፡

ውሳኔ፡-

ትንንሽ ከምንለው ጀምሮ ትልልቅ እስከምንለው ድረስ በየዕለቱ የምናሳልፈው ውሳኔ በነገዎቻችን ላይ ተጽእኖው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ትክክለኛ ኑሮ የሚጀመረውም በውሳኔ ነው፡፡ መወሰን እንዳለመቻል ኑሮን ዝብርቅርቅ የሚያደርግ ነገር እንደሌለ በዚህ ውስጥ ያለፍን ሁሉ ዘወትር የምናየው ጠባሳ ነው፡፡ የፊልጵስዩስ ምእራፍ አንድ ዋና አሳብ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም ነውና” (ቁ. 21) የሚለው ነው፡፡ ክርስትና እንኳን ኑሮው ሞቱም ጥቅም አለው፡፡ ሰዎች በመኖራችን ውስጥ ከሚያዩት የበለጠ በሞታችን ውስጥ የሚጠብቀን ጥቅም የበለጠ ነው፡፡

           በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ክርስትናን ላላመኑ መመስከር እጅግ ዋጋ የሚያስከፍልበት ዘመን ነበር፡፡ ክርስቲያን መሆን የሚያስወነጅልበት ጊዜም ነበር፡፡ አንድ ክርስቲያን በወታደር ተይዞ ንጉሡ ፊት ሲቀርብ ሁለት ምርጫ ይቀርብለታል “ቄሳር ጌታ ነው” ወይንም “”ኢየሱስ ጌታ ነው” ማለት ከዚህም የተነሣ ክርስቲያኖች ለልዩ ልዩ መከራና ሞት ይሰጡ ነበር፡፡ ክርስቲያኖችም ከሞት በኋላ የሚጠብቃቸው ወዳጅ የተዘጋጀላቸው ስፍራ የዘላለም ቀጠሮ እንዳለ በአስጨናቂዎቻቸው ፊት ከእምነት በሆነ ድፍረት ይመሰክሩ ነበር፡፡ ታዲያ ሰሚዎቻቸው ክርስቲያኖቹ በሚሉት ባያምኑበትም እንኳን አይጠራጠሩትም ነበር፡፡ ስለዚህ ሞታቸውን አውቀው በሥቃይ ያዘገዩት ደግሞም በእንግልታቸው ይዝናኑበት ነበር፡፡ በክርስቶስ መኖር ያለውን ሕይወት በሞቱም መካፈል የሚያስገኘውን ጥቅም እኛ ባንረዳው አንኳን ጠላት አይጠራጠረውም፡፡ ጌታ እኛን ከምን እንዳወጣንና እንዴት ወዳለ ክብር እንዳሸጋገረን ከእኛ በላይ ጠላት ያውቀዋል፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለጠላትም ያብራራል፡፡ ሞታችንን ጥቅም ያደረገው የሁሉ ቤዛ መድኃኔዓለም ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡

          በዚህ ምድር በምናልፍበት ማንኛውም ሁኔታ ድል መንሣትን የምናገኝበት ትልቅ ውሳኔ ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም እንደሆነ ማመን ነው፡፡ ከእርሱ ጋር መኖራችን ትርጉም የሚሰጠውን ያህል በእርሱ መሞታችንም ትጉሙ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህም ሕይወታችን ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኃይል መረዳት ነው፡፡ የሕየወትን ያሕል አስፈላጊ እንደሆነ ያሰብነው ነገር ምንድነው? ለእርሱስ መሸነፍና ራስን መስጠት ሊያስገኝ የሚችለው ጥቅም ምን ሊሆን ይችላል? ለእኛ ሕይወት ሀብት ቢሆን ጥቅሙ ኪሳራ፣ ሕይወት ዝና ቢሆን ትርፉ በሚበልጥ ዝነኛ መረሳት፣ ሕይወት ሥልጣን ቢሆን ትርፉ መሻር አይደለምን?

           ተወዳጆች ሆይ ሁኔታን ድል የምንነሣበት መመሪያ ክርስቶስን ሕይወት ማድረግና ሞትም ጥቅም እንደሆነ መረዳት ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን በጌታ መሞት ጥቅም እንዳለው ከተረዳና በዚህም ላይ እምነቱን ከጣለ ሀዘኑ፣ ጭንቀቱ፣ ሕመሙና ፈተናው ውስጥ እንዴት ለጥቅሙ የሚሆን ነገር አይኖርም? እግዚአብሔር በኑሮአችን ድልን የሚሰጠን እርሱን ለሕይወታችን በተብራራው መጠን ነው፡፡ ጌታ ማንንም ለሽንፈት ወደ ምድር አላመጣም፡፡ እርሱ ለእኛ ያለው ነገር የማያቋርጥ ድል ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በነፍስ በሥጋና በመንፈሱ ላይ ድልን እንዲቀዳጅ ያስቻለው ኑሮውንም ሞቱንም ለጌታ ክብር ለማድረግ መወሰኑ ነው፡፡ ሁሉን ለእርሱ ክብር ማድረግ ቁርጥ ውሳኔና ዓላማችን ሊሆን ይገባል፡፡

አሳብ፡-

የውሳኔዎቻችን መጠበቂያ አሳብ ነው፡፡ በጎ ውሳኔዎቻችንን በክፉ አሳብ ክፉ ውሳኔዎቻችንንም በበጎ አሳብ ለመጠበቅ ብንሞክር ከንቱ ድካም ነው፡፡ መልካም የሆነውን አሳብ የምንጠብቀው በመልካም ልምምድ ነው፡፡ በእግዚአህሔር ፊት እንዳለን በስሙም እንደተሰበሰብን በእውነትና በመንፈስ እንደምናመልክ በሕይወታችንም ሙሉ አዛዥ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ በተሰማን ጊዜ የሥጋን አሳብ የሚቃወሙ ለመንፈሳዊው ነገር ዋጋ የሚሰጡ የምድሩን አናንቀው የሰማዩን የሚያከብሩ ውሳኔዎችን እንወስናለን፡፡ ሕይወቴ ክርስቶስ ሞቴም ጥቅም ነው እንላለን፡፡ ዳሩ ግን ምድረ በዳውን ስንቀላቀል ከፀሐይ በታች ወዳለው ኑሮአችን ስንመለስ የሚጠብቀን አሳብ ለእግዚአብሔር ነገር ክብር የማይሰጥ ከቀመስነው ፍቅር ከተረዳነው እውነት ወደኋላ የሚጎትት ይሆናል፡፡ ስለዚህም ውሳኔያችንን የዓለም አሳብ እየገዘገዘው በአለህበት ሂድ አይነት ይሆንብናል፡፡ በአንድ ሰው ውስጥ ያለው ትልቁ ነገር አሳቡ ነው፡፡ ድርጊቶቻችን የአሳብ ማሳያዎች ናቸው፡፡ መልካም ማሰብ መልካም ለማድረግ አቅም ነው፡፡ መለወጥም በአእምሮ መታደስ ነው፡፡

         የፊልጵስዩስ ምእራፍ ሁለት ዋና አሳብ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን፡፡” (ቁ. 5) የሚል ነው፡፡ ይህ አሳብ መዋረድንም አውቃላሁ መጉደልንም ተምሬአለሁ ወደምንልበት ደረጃ የሚያሸጋግረ አሳብ ነው፡፡ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ የባሪያን መልክ የያዘውን፣ በምስሉ እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን ያዋረደውን፣ እስከ መስቀል ሞትም የታዘዘውን ጌታ የምንመስልበት አሳብ ነው፡፡ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት አልያም በከንቱ ውዳሴ ሳይሆን ባልንጀራችን ከእኛ ይልቅ እንዲሻል የምንቆጥርበት አሳብ ነው፡፡ “በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ ደስ ብሎኛል” የምንልበት ራሳችንን እንደ እንጀራ ለመቆረስ እንደ ውኃም ለመፍሰስ የምናዘጋጅበት አሳብ ነው፡፡ አሳብን ማከም አካልን እንደማከም ቀላል አይሆንም፡፡ ለጌታ ግን ሁሉ ይቻለዋል፡፡ ዛሬ የምናያቸው ትልልቅ ሕንፃዎች በፊት በመሐንዲሱ አእምሮ ውስጥ የነበሩ አሳቦች ናቸው፡፡ እንደውም አንድ ክ/አገር በመሐንዲሱ ስሕተት ፊትና ጀርባው ተቀያይሮ የቆመ ሕንፃ አይቻለሁ፡፡ ሰው አሳቡ ካልተስተካከለ ምድሪቱ ላይ የሚቆመው ሁሉ የተበላሸ ነው፡፡

            በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው አሳብ ትሕትና ነው፡፡ ትሕትና በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆች፣ ያለ ነውር የእግዚአብሔር ልጆች፣ ያለ ማንጎራጎርና ክፋት እንደ ብርሃን የምንታይበት አሳብ ነው፡፡ እርሱን የምንመስለውም በዚህ ነው፡፡ ቅናት፣ ትዕቢት፣ ክርክርና ዓመፀኝነት የሚወገዱት ትሕትና ሲተካቸው ነው፡፡ በእንግድነት ኑሮአችን ትሕትና በማንኛውም ሁኔታ ላይ ድልን እንድናገኝ ያስችለናል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በሸላቾቹ ፊት እንደሚታረድ በግ ዝም ባይል፣ እስከ መስቀል ሞት በትሕትና ባይታዘዝ ስለ ትንሣኤው ልናወራ እንዴት ይቻለን ነበር? ስለ ክብር ለማውራት ውርደትን በትሕትና መቀበል ያስፈልጋል፡፡

          ተወዳጆች ሆይ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው አሳብ ዛሬ እኛ አለን ወይ? በቅናት ወንድምን ማሳደድ፣ ለራስ ጥቅም ሌላውም መግፋት፣ የባልንጀራን ኃጢአት በአደባባይ መግለጥ፣ እውነትን ረግጦ ለራስ ክብር መኖር ይህ በጌታችን የነበረ አሳብ ነውን? ዘረኝነት፣ መለያየት፣ በሐሰት መወነጃጀል ከማን ተማርነው? ለክፋት ትውፊት የለውም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው አሳብ ከቁራሹ ላይ የሚቆርስ፣ ደካማውን ጥሎ ሳይሆን ተሸክሞ የሚያልፍ፣ እጀ ጠባብ ለሚጠይቅ መጎናጸፊያ የሚጨምር፣ ለአሳዳጅን የሚጸልይ ተሳዳቢን የሚመርቅ ነው፡፡ “ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው” (ያዕ. 1÷8) ማስተዋል የድል ምስጢር ነውና እናንተ የምታስቡትን ናችሁ፡፡ ስለዚህ የጌታ አሳብ ይኑርባችሁ፡፡

ግብ፡-

ግብ የምንኖርበት ትልቅ ምክንያት ነው፡፡ አንድ መንገደኛ መንገድ የሚጀምርበት በቂ ምክንያቱ መድረስ የሚፈልግበት ቦታ አልያም ነገር ነው፡፡ መርካት የለጠውን እንድንፈልግ ካላደረገን እንቅፋትነቱ ይጎላል፡፡ ባለን ነገር የምንረካው ከማማረር ኑሮ እንድንድን እንጂ እንዳንተጋ አይደለም፡፡ ከፊቱ ግብ ያለው ሰው የጥረቱ ሁሉ ማብቂያ ያ ነው፡፡ የፊልጵስዩስ ምእራፍ ሦስት ዋና አሳብ “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ” (ቁ. 13) የሚል ነው፡፡

        ክርስትና የዓላማ ኑሮ እንደመሆኑ ማንኛውም እውነተኛ አማኝ የሚፈጥንለት ግብ አለው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ወደወሰነው ግብ የመድረስ ኃላፊነት አለብን፡፡ ትጋታችን እንዴት ዓይነት መሆን እንደሚገባውም በሩጫ ተብራርቷል፡፡ እግዚአብሔር ባቀደልን መንገድ ወደ ግቡ የምንደርስ ከሆነ ሽልማትን እናገኛለን፡፡ ብድራታችንን ትኩር ብለን ማየት ግን የእድሜ ዘመን ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡ (ዕብ. 11÷25) ቅዱስ አውግስጢኖስ “ጌታ ሆይ ነፍሴ አንተን አግኝታ እስካላረፈች አላርፍም” እንዳለ ወደ ምልክቱ መፍጠን ያስፈልጋል፡፡ (ሉቃ. 11÷30) በዚህም ላይ የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ ልብ ልንል ይገባል፡፡ በውሳኔአችን ስንጨክን ውሳኔአችንን የምንጠብቅበት አሳብ ይኖረናል፡፡ ከፊታችን ደግሞ የምንሮጥለት ግብ ይኖረናል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ የሰው አቅም ምን ያህል ነው? ማለት እንችላለን፡፡ በውሳኔአችን በአሳባችንና በግባችን መሐል ለተግባራዊነቱ የሚረዳን ኃይል ከየት እናገኛለን? “የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ” (ዕብ. 12÷1)፡፡

መቻል፡-

ውሳኔ መወሰናችንውሳኔያችንን የምናስጠብቅበት አሳብ መኖሩ ከፊት ለፊታችን የቆመ ግብ ማስቀመጣችን እነዚህ ሁሉ በራሳቸው ውጤት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እነዚህን ወደ ተግባር የምንለውጠው በመቻል (ተግባራዊ በማድረግ) ነው፡፡ የፊልጵስዩስ ምእራፍ አራት ዋና አሳብ ሁሉ ስለምንችልበት ኃይልና ምንጭ ይናገራል፡፡ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ቁ.13)፡፡

           ኃይል አንድን ነገር ሊያንቀሳቅስ የሚችል ጉልበት ነው፡፡ የሰው አቅም ውሱን ነው መቻሉም የፈረቃ ነው፡፡ በክርስቶስ ምንጭነትና ሰጪነት ወደ ሕይወታችን የሚዘልቀው ኃይል ግን ሁሉን የሚያስችል ነው፡፡ ሁሉ ማለት ማንኛውንም ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ይህ ኃይል ብርታቱን በሞት ላይ ገልጧ፡፡ አሁን በሞት የሚደነቅ የለም ሞትን ታግሎ በጣለው ጌታ ግን ገና ቀሪ ዘመናችንንም እንገረማለን፡፡ መቻል በትንሣኤው ኃይል መንቀሳቀስ ነው፡፡ ስላቃታችሁ ነገር አትማረሩ ስለሚችለው ጌታ አውሩ፣ ስለተዘጋባችሁ ደጅ አትበሳጩ የተከፈተውን በር ተመልከቱ፣ ሽንፈትን አታሰላስሉ ድልን ሊሰጥ በሚችለው ጌታ እመኑ፡፡ ሁለንተናችን ሆይ እናመሰግንሃለን!!












3 comments:

  1. Menorum memotum le geta kibir endehone yetereda christian bezemenu hulu fikadun le Egziabher yasgezal. Hasabum sile zelalemawiw hiwot silehone begizeyawi fetena aydenektim.....Egziabreh yibarkachu!

    ReplyDelete
  2. Be Egziabher sim dil; bekalum ereft ale! Kibir hulu le geta yihun!

    ReplyDelete
  3. "be getachin be Eyesus Kirstos bekul dil mensatin lemiseten le Egziabher misgana yihun!"....Egziabher yibarkachu!

    ReplyDelete