እግዚአብሔር ስሙን እንዲቀድስ ክብሩን እንዲወርስ በጽድቅ የፈጠረው ሰው ፈቅዶ
ኃጢአተኛ ቢሆንበት እውነትና ምሕረቱን ጽድቅና ሰላሙን አስማምቶ በማዳን ዳግመኛ የራሱ ሊያደርገን ወደደ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በአርአያውና
በምሳሌው ፈጠረው አዳም ከውድቀት በኋላ በመልኩና በምሳሌው ልጅ ወለደ ኃጢአተኝነትም በዚህ መንገድ ለሰው ሁሉ ደረሰ፡፡ (ዘፍ.
5÷3) እግዚአብሔር አብ ለበደለ ሰው የሚወደውን አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ሰደደ፡፡ እርሱም በሰው መካከል በመገለጥ በሞት ላይ
ስልጣን ያለውን ዲያቢሎስ በሞት እንዲሽር በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነፃ እንዲያወጣ
በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ (ዕብ. 2÷14) መዳን የሚጠይቀውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል አንዱ ስለ ሁሉ ሊሞት ሞትን ዓላማ እኛን
አድራሻ አድርጎ መጣ፡፡
ኃጢአተኛ እንደሆናችሁ ለሚሰማችሁ ሁሉ ጌታን የሚያህል ወዳጅ
አላችሁና ከሞት ጋር የጀመራችሁትን ግብግብ አቁሙ፡፡ በደጃችሁ ቆሞ ለሚያንኳኳውም በመክፈት ምላሽ ስጡ፡፡ ሕሙማንን ሊፈውስ የእግዚአብሔር
ልጅ በውርደት ተገልጧል፡፡ ከተለያየ ክፉ ልማድና ዓለማዊ አሠራር መላቀቅ ያቃታችሁ እናንተን ከዚህ የሚታደግ መድኃኒት ተገልጧልና
በዚህ ደስ ይበላችሁ፡፡ የኑሮ ቀንበር የነውር ሸክም የከበደባችሁ ልባችሁን መሰላቸት የሞላው ሁሉ ነገር የማይታኘክ መራራ የሆነባችሁ
እናንተን ሊያሳርፍ የኃጢአተኞች ወዳጅ የሆነ ጽድቅ ተገኝቷልና በእምነት ቅረቡ፡፡ ጌታ ሆይ ለፍቅርህ ተመን ልኬት የለውምና አንተ
በምታውቀው መጠን ተመስገን!!!
“የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቶአልና፡-
እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ ÷ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት፡፡ (ሉቃ. 7÷34)”
የጉንዳን መንጋ ላይ ቆሞ የሰፈሩበትን ጉንዳኖች እንደሚያራግፍ
ምስኪን ሰው ኃጢአትን በልቡ ሞትንም በጀርባው ተሸክሞ ለዘመናት ከኩነኔ በታች ለተንከራተተው ጽድቁ እንኳ እንደ መርገም ጨርቅ ለተቆጠረቅ
የሰው ዘር በክርስቶስ በምጣት ታላቅ የምስራች ሆነ፡፡ ተገለጠ፡፡ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ለሚያምኑ ሁሉ በእርሱ በማመን የሚገኘው
በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጧል፡፡ በነፍስ በሥጋ በመንፈስም ለታሰሩት መፈታት፣ ለዕውሮች ማየት፣ ለተጠቁት ነፃ
መውጣት፣ ለድሆችም የወንጌል መሰበክ በክርስቶስ ሰው መሆን የሆነ ነው፡፡ በገነት ሰውን የተሸሸገበት ድረስ ሄዶ ወዴት ነህ? በማለት
የሕይወትን ጥሪ ያሰማ አምላክ (የሸሸነው ጽድቅ) ያለንበት ድረስ መጣ፡፡ በበደልና በኃጢአታችን ሙታን የሆንነውን በማይለካ ፍቅሩ
ወደደን፡፡
በመዳፍህ የያዝከው ዕንቁ ከእጅህ ወጥቶ ጭቃ ውስጥ ወደቀ፡፡ ጭቃውን
ብትጠላውም ለዕንቁው ያለህ ፍቅር ግን አይቀንስም፡፡ ስለዚህ አንጽተህ ዳግም የራስህ ልታደርገው ንጹሕ ለመሆን የሚጠይቀውን ሁሉ
ዋጋ ትከፍላለህ፡፡ ካሉት መቶ በጎች የባዘነውን አንዱ ፍለጋ ዘጠና ዘጠኙን ትቶ እንደተሰማራ ባገኘውም ጊዜ ካልባዘኑት ይልቅ በአንዱ
መገኘት ደስ እንደሚሰኝ መልካም እረኛ ክርስቶስ በቃል ከሚሰማው ነቀፋ በተግባር እስከሚታየው መከራ ሁሉን ስለ እኛ ሲል ተቀበለ፣
ለመዳንም የሚያስፈልገውን ሁሉ ዋጋ መስቀል ላይ ከፈለ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋና በደም አቋም በዚህ ምድር
በተመላለሰበት ወራት የሞት ቀንበር ለከበደበት፣ የኃጢአት ሸክም ለሚያንገዳግደው የሰው ዘር ባሳየው ርኅራኄ፣ በለገሰው የማይነጥፍ
ፍቅር የኃጢአተኞች ወዳጅ ተብሏል፡፡ ሕሙማን (ኃጢአተኛ) እንደሆኑ ለሚያምኑ ሁሉ ክርስቶስ መድኃኒት ነው፡፡ አይሁድና ፈሪሳውያን ግን ከዘላለም
ሞት ሊያድን የመጣውን ጌታ የኃጢአተኖች
ወዳጅ፣ የግፉአን
ባልንጀራ እያሉ ያሙት ነበር፡፡ መልካም መሆናችን ላለመታማት ዋስትና የለውም፡፡ በጎነታቸው በክፋት እየተመዘነ፣ መውደዳቸው የጥላቻን
ያህል ዋጋ እየጠነፈገ፣
እንደ ማር የጣፈጠ ንግግራቸው ሕይወት የሆነ ምክራቸው እንደ ሬት እየተቆጠረ ኖረው ያለፉ እውነተኞችን ታሪክ ያስታውሰናል፡፡ ጌታም
የጥላቻ ጉልበት ያደቀቃቸውን፣ የገዛ ነውራቸው ያሳፈራቸውን፣ የሰው ፊት የገፋቸውን በልቡ ተቀብሎ በቤታቸው ስለተስተናገደ ክፉዎች በጎውን
ያሙት ነበር፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ
“አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን” (2ቆሮ. 6÷9) ይላል፡፡ የብዙዎቻችን ጥረት ክፉ ላለመሆን ሳይሆን ክፉ ላለመባል ነው፡፡ ስለዚህ
ሌሎች ስላሉን እንጂ ስለሆነው፣ ስለሚወራብን እንጂ ልባችን ስለሚያወራልን ግድ አይለንም፡፡ በመባልና በመሆን መካከል ግን ሰፊ ልዩነት አለ፡፡
ሰዎች እኛን በሚያሙበት ክፉ ነገር ውስጥ አለመገኘት በመልካም መታማት ነው፡፡ መርቆ መረገም፣ ወድዶ መጠላት፣ አቅፎ መገፋት፣ አጉርሶ
መነከስ፣ በጎ ውሎ መሰደድ የክርስቲያን ክብሩ ነው፡፡ ክርስቶስም በመልካምነቱ ታምቶአል፡፡ ሐዋርያው በጊዜው ሰዎች ስለሚሉትና እርሱ
ስለሚኖረው ኑሮ ሲያስረዳ አሳቾች ይሉናል እውነተኞች ነን፣ ያልታወቁ ይሉናል የታወቅን ነን በማለት ኑሮውንና ሐሜታውን ለይቶ ያሳየናል፡፡
ተወዳጆች ሆይ እኛ ስንባል ስንታማ ምን ዓይነት ሰዎች ነን? ንፉግ ስንባል ለጋስ፣ ክፉ ስንባል ደግ፣ ጠላት ስንባል ወዳጅ ነን
ወይ? ሰዎች እኛን በሚያሙበት ነገር ውስጥ ከተገኘን ችግሩ ያለው እነርሱ ጋር ሳይሆን እኛ ጋር ነውና አካሄዳችንን ማስተካከል አለብን፡፡
ከዚህ ውጪ ከሰው ለሚመጣው ማንኛውም ሀሜትና ወቀሳ ይልቅ እግዚአብሔር ስለ እኛ በሚለው ነገር ላይ ማረፍ አለብን፡፡ በሕይወት ትልቁ
ቁም ነገር ሌሎች ስለ እኛ የሚሉት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚለው ነው፡፡
Amen bebedelachin yaltewen ena benitsu demu ladanen geta kibir yihun! Egziabher agelgilotihn yibark!
ReplyDeleteAmeeeeeeeeeeeeen!
Delete