Monday, April 9, 2012

ሰው ለቤቱ



         የመጽሐፍ ቅዱሳችን የመክፈቻ ክፍል በሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ከመለኮት ለሰው የተላለፉ ለትምህርትና ለተግፃጽ ልብንም ለማቅናት የሚያገለግሉ መንፈሳዊ መልእክቶች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ከዚህ ርዕስ ጋር በተያያዘ የምናነሣው ከያዕቆብ ታሪክ የተወሰነውን ክፍል ይሆናል፡፡ ይስሐቅና ርብቃ ያዕቆብና ዔሳው የሚባሉ ልጆች እንደነበሯቸው እነርሱም ገና በማህፀን ሳሉ ይጋፉ እንደነበር ያም መገፋፋት ወደ ማስተዋል ከመጡ በኋላም በኑሮአቸው እንደተገለጠ ዜና መዋዕላቸው ያስረዳናል፡፡

       ይስሐቅ በእድሜው ምሽት፣ በዘመኑ መጨረሻ፣ አይንን በሚይዝ እርጅና ውስጥ ሆኖ በኩሩንና የሚወደውን ልጁን ዔሳውን በመጥራው “ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ ወደ ዱር ሂድ አድነህም ጣዕም ያለውን ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ” አለው፡፡ ርብቃ ይህንን ትሰማ ስለነበር እርሷም በተራዋ የዔሳውን እግር ጠብቃ ለምትወደው ልጇ ለያዕቆብ በወንድሙ ምትክ በረከትን መቀበል እንደሚችል ለዚህም አደን መውጣት እንደማያስፈልገው ይልቁንም በቤት ካሉት ጠቦቶች መካከል የሰቡና የጣሙትን ሁለት እዲያመጣ አዘዘችው፡፡ ያዕቆብ የእናቱ ብልሀት የተቃኘ ማታለል አልዋጥ ቢለው “ወንድሜ ሰውነቱ ጠጉራም ነው የእኔ ገላ ደግሞ ለስላሳ ነው ታዲያ አባቴ ይህንን ባረጋገጠ ጊዜ በበረከት ፈንታ መርገምን አተርፋለሁ” አላት፡፡ ርብቃ ግን መርገሙ በእኔ ላይ ይሁን በማለት ያዘዘችውን እንዲፈጽም ነገረችው፡፡

        በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ከምናስተውለው ነገር አንዱ መለያየትን ነው፡፡ በያዕቆብና በዔሳው መካከል ግፊያ የጀመረው ገና በማኅፀን ሳሉ ቢሆንም ያ ባለማስተዋል የነበረ ነው፡፡ ወደ ማስተዋል ከመጡ በኋላ ግን የምናየው መለያየት የቤተሰብ ተጽእኖ ውጤት ነው፡፡ እናትና አባት ለልጆቻቸው እኩል ፍቅር ባለማሳየታቸው በወንድማማቾቹ መካከል ዛሬ ድረስ ያልጠፋ መለያየትና ጠላትነትን አትርፏል፡፡ በእኛም አገር እንዲህ ያለው የቤተሰብ መሐል መለያየት ጎልቶ የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ አንድ ሰው የአካባቢውና የቤተሰቡ ውጤት እንደመሆኑ ችግሩ ተሸጋጋሪ፣ ጉዳቱ ሁለንተናዊ ነው፡፡ እየሰማን ካደግነው ይትባህል መሐል “ሴት ልጅ አባቷን ወንድ ልጅ እናቱን ይወዳል” የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህም ስር ሰደድ ብሒል የተነሣ በአንድ ቤት ውስጥ ሁለት ዓይነት ጽንፍ፣ በተለይ በእናትና በአባት አለመግባባት ወቅት ይስተዋላል፡፡ ቤተሰብ አርአያነቱ መጀመሪያ ለቤቱ ሰዎች እንደመሆኑ በመልካም ምሳሌ መሆን እንዲሁም  ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ፍቅር ለልጆች ማሳየት አግባብ ነው፡፡

          ያዕቆብ የእናቱን ምክር ሰምቶ በድምጽ ራሱን በሰውነቱ ደግሞ ወንድሙ ዔሳውን መስሎ ቆመ፡፡ ይስሐቅ የያዕቆብን ዔሳው አለመሆን ቢጠራጠረውም ከዚህ ያለፈ አቅም አልነበረውም፡፡  ልብንና ኩላሊትን በሚመረምረው እግዚአብሔር ፊት ግን ሰው በሁለት ማንነት ሊቆም  ከመታወቅስ ሊያመልጥ እንዴት ይችላል? ያዕቆብ ሁሉን በእናቱ ምክር ቢያደርገውም አጨዳውን ግን ከእናቱ ጋር አላጨደውም፡፡ እንደውም ያዕቆብ የወንድሙ ቁጣ እስኪበርድ ድረስ ወደ አጎቱ ላባ ዘንድ ከሸሸ በኋላ እናቱ የሞተችው ዳግመኛ ሳይተያዩ ነው፡፡ ያዕቆብ አባቱ ቤት የዘራውን ማታለል አጎቱ ቤት ዐሥራ አራት ዓመት በመታለል እንዲሁም የገዛ ልጆቹ ዮሴፍን ለምድያም ሰዎች ወደ ግብጽ ሸጠውት ልብሱን በደም ነክረው በማምጣት ልጅህ ሞቷል በማለት በእርጅናው አታለሉት፡፡ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል” (ገላ. 6÷7) ተብሎ እንደተፃፈ ያዕቆብ የዘራውን አጨደ፡፡

            ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ሠላሳ ቁጥር ሠላሳን ስናነብ ግን ያዕቆብ ወደ ልቡ እንደተመለሰና “እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው?” በማለት የአጎቱን ቤት ጥሎ እንደሄደ እናስተውላለን፡፡ እግዚአብሔር የቃል ብቻ ሳይሆን የሕይወትም መምህር ነው፡፡ ስለዚህ ሁኔታን መንገር ብቻ ሳይሆን በሁኔታ ውስጥም ያሳልፈናል፡፡ ያዕቆብ ባለፈባቸው የኑሮ ብርቱ ሰልፎች ውስጥ ምን ያህል እንዳጣ አስተውሎ የአጎቱን የተመለስ ልመናና የአደርግልሃለው ማባበያ እንቢ አለ፡፡ ያዕቆብ ዕድሜውን ለራሱ ለመሰብሰብ ቢተጋበትም እኔነቱ ያስገኘለት ነገር ግን የለም፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ጸጋ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ እናገናዝባለን፡፡

          የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ እኛ የመለኮት ቤት እንደሆንን ይናገራል፡፡ (2ቆሮ. 6÷16) ቤትን ስናስብ ደግሞ ብዙ ነገሮች ወደ ሕሊናችን ይመጣሉ፡፡ ዞረን ዞረን የምንሰበሰብበት፣ ክፉውንም ደጉንም የምናሳልፍበት፣ ከፀሐይ ንዳድ ከበረታ ብርድ የምንሸሸግበት፣ ቢከፋን ማኩረፊያ፣ ቢመቸን ማረፊያችን ነው፡፡ ነገር ግን ቤትን ቤት ሊያሰኙ፣ መኖርም ሊያስችሉ፣ መንፈስና ቀልብን ሊስቡ የሚያስችሉ አስፈላጊ ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ንጽሕና ነው፡፡ ሰው የቤት ዕቃ ስለማሟላት ለማሰብ የቤቱን ንጽሕና በቅድሚያ ሊያስተውል ግድ ነው፡፡ ንጹሕ ባልሆነ ቤት ስለተሟላ የቤት ዕቃ ማውራት ግብዝነት ነው፡፡ በቁሙ ቤትን ያለ ንጽሕና ማሰብ አለኝ እያሉ ለመኖር ካልሆነ በቀር ከቤቱ ተጠቃሚ መሆን አይቻልም፡፡

           እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤት መሆናችንን ከተረዳን የቤቱ ንጽሕና እንዲጠበቅ መትጋት አለብን፡፡ ልብሳችን ላይ ቁሻሻ ማየት የሚያስቆጣን ከሆነ ልባች ላይ የሚገላበጠው የኃጢአት ብዛት ምነው አያስከፋንም? መልካምነት የሚጀምረው ከቤት ነው፡፡ ለቤታችን ንጽሕና ሳንቆረቆር ለመንደር ንጽሕና ዘብ መቆም የራስን እያሳረሩ የሰው ማማሰል ነው፡፡ ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን እውነትም በእኛ ዘንድ አይኖርም፡፡ (1 ዮሐ. 1÷8) ኃጢአት ደግሞ ለእግዚአብሔር ጽድቅ ጠላት ነው፡፡ ኃጢአትም ከዘላለም ሞት ፍርድ በታች ማብቂያ ለሌለው ኩነኔ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ሰው ከዚህ ኃጢአት የሚነፃበት ከፍርድም ነፃ የሚሆንበት ኃይል ያስፈልገዋል፡፡ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ እንደሚያነፃ መረዳት ደግሞ እንደቆሸሹ ለሚያምኑ ሁሉ የሚያጠራ ውሃ ነው፡፡ (1ዮሐ. 1÷7) በሰማይና በምድር ፊት እግዚአብሔርን እንደበደልነው ሲሰማን ወደ ምሕረቱ የምንቀርበው በንስሐ ሲሆን እግዚአብሔር ለእኛ ይቅርታን የሚሰጠን ደግሞ አንድ ጊዜ ከፈሰሰው የልጁ ደም የተነሣ ነው፡፡ ስለዚህ የምንነፃበት እያለ ቆሽሸን የምንቀደስበት እያለ ረክሰን የምንድንበት እያለ ተኮንነን የሚቀበለን የምሕረት እጅ እያለ ተቅበዝብዘን መኖር የለብንም፡፡ ኃጢአትን በመሰወር ውስጥ ልማት የለም በመናዘዝና በመተው ግን በረከት አለና ተወዳጆች ሆይ ንጽሕና ይጠበቅ!!

           ሁለተኛው ፀጥታ ነው፡፡ ዛሬ ዓለም ላይ ጮኸው የሚሰሙት በፀጥታ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡ እንደዚህ ዘመን መደማመጥ የጠፋበት አሳብ የተደበላለቀበት የሚመስለውን ከሆነው መለየት ያስቸገረበት ጊዜ የለም፡፡ ሕይወትን ለኪሳራ የሚዳርጋት ትልቁ ነገር ጽሞና የለሽ ትጋት ነው፡፡ ሰው ያገኘውን ካጣው የያዘውን ከበተነው ያተረፈውን ካጎደለው በፀጥታ ካልመረመረና ካለየ እድገት እንዴት ሊኖር ይችላል? ፀጥታ በተሳሳተ መንገድ ሮጦ የተሳሳተ ነገር ከማጨድ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሔር ለሕይወታችን ያለውን አሳብ ልንሰማውና ልንረዳው የምንችለው ፀጥታን መለማመድ ስንችል ነው፡፡ አለዚያ እየሮጡ መታጠቅ እየሮጡ መፈታት ይሆናል፡፡

          ከኃጢአት ቀጥሎ ለሕይወታችን መታወክ ምክንያት የሚሆነው ለኑሮ መጨነቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን ወደዚህ ምድር ያመጣን አስቀድሞ የሚያስፈልገንን በመፍጠር ነው፡፡ ዛሬ ጭንቀት ስናመርት የምንውለውም ከእኛ ቀድመው ለተፈጠሩት ነገሮች ነው፡፡ የሠራን እግዚአብሔር ነው ለኑሮአችንም ከእርሱ በላይ ሊያስብ የሚችል የለም፡፡ መጨነቅ የማያስረዝሙትን ፀጉር ሲጎትቱ መኖር ነው ይህ ደግሞ ለውጥ በማይመጣበት መልኩ ራስን መጉዳት ነው፡፡ ክርስቲያን ወደ መኖር ባመጣው በአንድ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ባዳነው አምላክ ያረፈ አሳቡም በዘላለም ሕይወት የተሞላ ነው፡፡ ቃሉ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉ” ይላል፡፡ ግን ጥለናል ወይ?

        የሕይወት ፀጥታ የመጣንበትን ያለንበትንና መዳረሻችንን አጥርተን እንድናይ ይዳናል፡፡ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ ስላይደለ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት ፀጥታ ብርቱ ነው፡፡ ስለዚህ በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ፡፡ አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል፡፡ (ፊል. 4÷6) ተወዳጆች ሆይ በልባችሁ ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን ማስጠንቀቂያ አንብባችሁታልን? እንዲህ ይላል “ፀጥታ ይከበር”፡፡ ለበረከት ሁኑ!!

1 comment: