Tuesday, May 29, 2012

ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም



 
         ዓይናችሁ በተነሣንበት ርእስ ላይ እንዳረፈ አንድ ነገር ለማስተካከል እንደምትሞክሩ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ለማየት የምንሞክረው ስለምንታገለው እንጂ ስለምንታደለው ነገር ስላልሆነ “ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” የሚለውን የተለመደ ብሒል ከላይ በአነበብነው መልኩ ተክተነዋል፡፡

         ሰዎችን ለሕይወት እንዳላቸው አመለካከት በዕድል አልያም በሥራ የሚያምኑ ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ ስኬትን የእድል ተጽእኖ ውጤት አድርገው የሚመለከቱ ወገኖች ሁሉንም ነገር ከዐርባና ከሰማንያ ቀን ዕጣ ፈንታ ጋር አያይዘው የሚመለከቱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ስኬታማነትን የታታሪነት ውጤት አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች መመሪያቸው “ጥረህ ግረህ ብላ” የሚለው ቅዱስ ትእዛዝ ነው፡፡ እድልና ጥረት አብዛኛውን ጊዜ አከራካሪ እንዲሁም ለተለያዩ አሳቦች መንሸራሸር ምክንያቶች እንደመሆናቸው ብዙ ምንጮችን ባጣቀሰና አሳበ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ልናብራራቸው አሳማኝ ምክንያት አይፈቅድልንም፡፡

         ቆም ብለን ለማገናዘብ ፋታ ካገኘን ለምንድ ነው ሰዎች “ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” የሚለውን አባባል የሚጠቀሙት? ደግሞ ሌላ ጥያቄ እናክልና ለዚህ አባባል በሰዎች ልቡና ውስጥ ያለው መነሻና መድረሻስ ምን ሊሆን ይችላል? እናንተ የቻላችሁትን ያህል ለመጠየቅ ሞክሩ፡፡ እኔ ግን ለጊዜው የታየኝን ልግለጽ “ምሬትና ተስፋ መቁረጥ” እንደ መነሻ፤ እድል የሚያመጣውን መጠበቅና በስንፍና መርካት ደግሞ እንደ መድረሻ (የመነሻው ውጤት) ሆነው አግኝቼአቸዋለሁ፡፡ ብዙ ሞክረን አልሳካ ሲለን፣ ያዝነው ያልነው ነፋስን የመከተል ያህል ሲሆንብን አወይ እድሌ! እንላለን፡፡ ታዲያ ይህ ወደ በለጠ ትጋት ሳይሆን ወደባሰ ውሳኔ የምንደርስበት ሆኖ ይስተዋላል፡፡ ጊዜው ለእኔ ጥሩ አይደለም፤ እድሌም ጠማማ ነው በማለት ለስንፍና እንዳረጋለን፡፡  

         የመታደል እንጂ ያለመታገል አመለካከት ለብዙዎች እምነታቸውም ጭምር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የተበላሸው እንዲስተካከል፣ የጠመመው እንዲቀና፣ የሳተው እንዲመለስ፣ የዛለው እንዲበረታ ከመሥራት ይልቅ “ስላልታደልኩ ነው እንጂ ይህና ያ አይሆንብኝም ነበር” በማለት አለመታደላቸውን የሚነግሩን ብዙ ናቸው፡፡ ይህ አባባል እኔ አልችልም ጌታ ግን ይችላል፣ እኔ አልዋጋም እርሱ ግን ይታገልልኛል፣ ጌታ በአሸነፈው ውጊያ ድሉ ለእኔ ይቆጠርልኛል (መታደል)፣ የሚሰማኝ ይሰማዋል በሚል እምነት የምንናገረው ከሆነ ጠንካራ ጎኑ ያይላል፡፡ ነገር ግን ይህንን ማለት መቻል በራሱ ሌላ ትግል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ብዙ ሰው ማመንን እንደ ቀላል፣ መሥራትን ግን እንደ ተራራ ሲመለከት ነው የኖረው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማወቅ (መጽሐፍትን መመርመር) እንደ ክህደት አለማስተዋል ደግሞ እንደ እምነት እየተቆጠረ የኖርንበት ዘመን የትየለሌ ነው፡፡ የታመነው ምስክር ግን  “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ተራራን ማንፏቀቅ፣ ግንድንም ወደ ባህር ልብ ማስጠም ትችላለች” ብሎናል፡፡ አቅሙ ስላለን እንሠራ ይሆናል አቅም ስላለን ግን አናምንም፡፡ ብዙ የሚረዱ አሕዛብ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ይህ ግን ወደ እውነት አላደረሳቸውም፡፡

                          ይታደለዋል እንጂ ከጌታ ደጅ ጠንቶ፤

                          አሁን ምን ያደርጋል አንዱ በአንዱ ቀንቶ፡፡

         ክርስትና ሩጫውን (መልካሙን ገድል) ለመጨረስ የምንተጋበት ሜዳ እንደመሆኑ በእምነት ሆኖ መታገል ግድ ይላል፡፡ (2 ጢሞ. 4÷7) ክርስቲያን ወታደር እንደመሆኑ በጦሩ ሜዳ ላይ ድልን ለመቀዳጀት ጸጋውን ትምክህት በማድረግ መታገሉ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን በመንፈሳዊው አኗኗር ረገድ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ከመልበስና በመንፈስ ሠይፍ ክፉውን ከመቃወም፣ የጠላትን አሠራር ከመታገል ይልቅ የእግዚአብሔርን መንጋ እረኛ ለሚመስሉ የግብር ተኩላዎች፣ አሳቢ ለሚመስሉ የጥቅም ባሪያዎች፣ እኔ የጎደለኝ ምንድነው? ከማለት ይልቅ ወንድሜ ለምን ተቀባይነት አገኘ ለሚሉ ቃየሎች፣ እውነትን በተራበ ሕዝብ ላይ ተረት ለሚያጋሱ ባልቴቶች አለመታደላችንን እየለፈፍን እጅና እግራችንን አጣጥፈን ብንቀመጥ ባለ ዕዳ ከመሆን አናመልጥም፡፡

        እግዚአብሔር የልቡን አሳብ ያካፈላቸው፣ የቃሉ ደጅ የተከፈተላቸው፣ የሰማዩን በማስተዋል የተባረኩ ብዙ አዋቂዎች እንዳልተረዳ ፈርተው ኖረው ፈርተው ሞተዋል፡፡ እውነትን እስከ መጋደል ባንመሰክር የማወቃችን ትርፉ ምንድነው? ያወቅነውን ለሌሎች ለማካፈል ከመታገል ይልቅ በአልታደልኩም መደለያ ለራሳችን እየሞቅን ብቻ መኖር ደስታው ምን ጋር ነው?

        እውነት ሰማይና ምድር የጸኑበት ነው፡፡ ነቢያትና ሐዋርያት ሸንጎ ለሸንጎ የተንከራተቱለት፣ በአደባባይ እስከ ደም መፍሰስ የመሰከሩለት ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ የንስሐን አዋጅ የሰበከው የእግዚአብሔርን በግ ያስተዋወቀው አንበጣ እየበላ የግመል ጠጉር እየለበሰ ነበር፡፡ ከአመጸኛው ዓለም የተለየውም ላመነበት እውነት በመሞት ነው፡፡ እኛ የላመ የጣመ እየበላን፣ ያማረ የተዋበ እየለበስን ለእውነት ባንመሰክር ደግሞም ለዚህ ባንታገል ምንኛ ምስኪኖች ነን፡፡ አንድ ጉባኤ ላይ መምህሩ አስተምሮ ከጨረሰ በኋላ አንድ አባት ቀረብ ብለው “በጌታ የተነገረውን የሰሙትም ለእኛ ያጸኑትን እግዚአብሔርም እንደ ራሱ ፈቃድ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም መንፈስ ቅዱስንም በማከፋፈል አብሮ የመሰከረለትን እውነት ትተህ አንድ ሰዓት ሙሉ በአሳብህ ልክ የሰፋኸውን ውሸት የጋትከን ማን አስጨንቆህ ነው” ያሉትን አስታውሳለሁ፡፡

        የእግዚአብሔር ቃል የሚያዘን ከትግልም ከፍ ያለ ነገር ነው፡፡ ይህም ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድንጋደል የሚመክር ነው፡፡ (ይሁዳ 3) ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የእግዚአብሔርን ምሥጢር እርሱንም ክርስቶስን እንዲያውቁ እጋደላለሁ የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና ይለናል፡፡ (ቆላ. 2÷1) በዚህ መሠረት የምንታገልለት ብቻ ሳይሆን የምንጋደልለት ሃይማኖት ክርስቶስ ነው፡፡

       ጌታ የይሁዳ አንበሳ ነውና በዙሪያችን የሚውጠውን ፈልጎ እንደ አንበሳ የሚያደባ የጨለማ ኃይል ሁሉ አያስፈራንም፡፡ እርሱ የሕይወት ውኃ ምንጭ ነውና ሰባት እጥፍ የሚነደው እሳታቸው ላቆሙት ስህተት አያንበረክከንም፡፡ ሁሉን ያያልና በምናየው አናማርርም፡፡ ሁሉን ይሰማልና በምንሰማው አንሸበርም፡፡ ሁሉን ያውቃልና ባልደረስንበት ነገር ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ሰው እንዲህ ካለው የጥበብና የእውቀት መዝገብ ካልቀዳ የአረም መጫወቻ መሆኑ እሙን ነው፡፡

       የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በድቅድቅ ጨለማ ላሉት የሚደነቀውን የወንጌል ብርሃን  ያደረሱት በብዙ ትግልና መጋደል ነው፡፡ እዚህ አልታገልኩም እንጂ አልታደልኩም የሚል ምክንያት የለም፡፡ በዚህ ዓለም ባለው ኑሮአችንም እንዲሁ ነው፡፡ ዛሬ ላለንበት የኑሮ ደረጃ (ድህነት) ያበቃን አለመታደል ነው ወይስ አለመታገል? የትዳራችሁ መፈታት፣ የጎጆአችሁ መፍረስ አለመታደል ነው ወይስ አለመታገል? የልጆች ስነ ምግባር መጉደል፣ የወላጆች መወስለት አለመታገል ወይስ አለመታደል? በመስሪያ ቤት፣ በቤተ እምነት ያለው የከፋና የተበላሸ አስተዳደር አብሮን ያለው ስላልታገል ወይስ ስላልታደልን? ጊዜያችንን ሰውተን ብዙ ተግባራችንን ትተን መጥተን በየመድረኩ የሥጋና የደም አሳብ፣ ጸብና ክርክር፣ በብልሃት የተፈጠረ ተረትና መጨረሻ የሌለው የትውልዶች ታሪክ የምንሰማው ስላልታደልን ነው ወይንስ ስላልታገልን? ፈተና የወደቅነው፣ ሰው የደረሰበት ያልደረስነው ስላልታደልን ወይንስ ስላልታገልን?

       ተወዳጆች ሆይ መኖር ብርቱ ሠልፍ ነውና ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም፡፡ ሕይወት በአልታደልኩም ፍልስፍና ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕቡአዊነት ትግል የምትፈታ እንቆቅልሽ ናት፡፡ መንፈሳዊ ዓለም ሩጫውን ጨርሻለሁ ለማለት በፊታችን ያለውን ጉዞ በድል ለማጠናቀቅ የምንጋደልበት ነውና እንታገላለን እንጂ አንታደለውም፡፡ ለወዳጅነታችሁ መጽናት፣ ለትዳራችሁ መዝለቅ፣ ለፍቅራችሁ ማበብ፣ ለሥራችሁ ስኬት፣ እንዲመጣ ለምትሹት ለውጥ በሚያስፈልጋችሁ ሁሉ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት በመቅረብ በሙሉ አቅማችሁ ታገሉ፡፡ ምክንያቱም ድልን ትግል ይቀድመዋል፡፡ በእርግጥም ኑሮን ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም!!

Friday, May 25, 2012

መልክአ እናት



ሰላም ለኪ እናታችን
ባለሽበት እንዳለሽ
አንቺ የተባረክሽ ነሽ
ሰላም ለዓይኖችሽ
ከጭስ ጋራ ለሚማጎቱ
ከእንቅልፍ ጋር ለተፋቱ
ተቅበዝባዥ ፍጡር ሆኜ ኑሮዬን ከምገፋ
ምነው እንባሽን በሆንኩ
ከዓይኖችሽ ስር እንዳልጠፋ፡፡
ሰላም ለከንፈሮችሽ ትላንት ለማውቃቸው
ዛሬ ለምናፍቃቸው
ውዳሴ ክብር ምርቃት
ጭብጨባ ሙገሳ ሽልማት በተረፈበት ቀዬ
ምነው ያ'ንቺን እርግማን - ይናፍቃል ጆሮዬ
ከሌሎች ውዳሴና ክብር እልፍ ጊዜ የተሻለ
ለካ በ'ርግማንሽ ውስጥ እናትነትሽ አለ፡፡
ሰላም ለጣቶችሽ
ለሰዎች የቀረቡ፣ከራስሽ ግን የራቁ
መስጠት መለገስ እንጂ መቀበልን ለማያውቁ
ሰላም ለኪ!
ባለሽበት እንዳለሽ፡፡
(በዕውቀቱ ስዩም፣ የግጥም ስብስብ፣ 2001 ዓ.ም)

Wednesday, May 23, 2012

እውነት ማለት የኔ ልጅ



ሰስተው እንደቁዋጠሩት ጥሪት፣ ከአባት ከእናት አትወርሺው፤
እንደቁዋንቁዋ ሃይማኖትሽ፣ በአደባባይ አታነግሺው፤
እውነት የነፍስሽ ነው ልጄ፣ የማንነትሽ ክታብ፤
የድብቅ ገመናሽ ንባብ፡፡
የእኔ ልጅ፣
ከየአደባባዩ ቡዋልት፣ ከየሸንጎው እንቶ-ፈንቶ፣
                                 እውነት ፍለጋ ስትባዝኚ፤
ማስተዋልሽን አታባክኚ፡፡
ፈጣሪ በራሱ አምሳል፣ ኑሮ ብሎ እንደፈጠረው፤
እያንዳንዱ ምስለ-ፍጡር፣ በእለት-ተእለት ማህደሩ፤
እውነት የራስ ነው ልጄ፣
የነፍስሽ ሳቅና ለቅሶ፤
የሕሊናሽ ሙግት ቅኝት፤
የራስሽ ለራስሽ ግኝት፡፡
የሕሊናሽ ነው ልጅ፣ ነቅተሽ እርሱን አድምጪ፤
ሲስቅ ዳንኪራ እርገጪ፤
ሲያለቅስ መርዶ ተቀመጪ፡፡
እንጂማ ልጄ፣
ሳቅ ጥርስ እንዳይመስልሽ፣ ያነባስ መች አልቅሶ፤
በሕይወት ስንክሳር ቅኝት፣ ደስታ ሀዘኑ ተመሳቅሎ፤
የክት እውነቱን በብብቱ፣ ያደባባዩን በገጹ አዝሎ፤
ነው ልጄ የሰው ውሎ፡፡
እና ልጄ፣
ብልጭ ካለ ጥርስ ላይ፣ ከሚፈሰው እንባ፣ እውነት ፍለጋ ስትባዝኚ፤
ማስተዋልሽን አታባክኚ፡፡
       (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ የግጥም ስብስብ፣ 2004 ዓ.ም)

Tuesday, May 22, 2012

ማን ይናገር? (ካለፈው የቀጠለ)



        የክርስቶስን ትንሣኤ ለማፈን ገንዘብ ጥቅም ላይ ውሎ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ (ማቴ. 28÷15) ወንጌል እንዳይሰበክ የእግዚአብሔር ክብር እንዳይገለጥ ሕዝቡ ወደ ማስተዋል እንዳይመጣ ዛሬ ድረስ ገንዘብ ትልቅ ድርሻ ያበረክታል፡፡ ነገር ግን ቃሉ አይታሠርምና የሰው አቅም ሊያቆመው አይችልም፡፡ የሰውም ማንኮራፋት ሊያውከው ከቶ አይችልም፡፡

       አገልጋዩ ማን ይናገር? ተገልጋዩ ደግሞ ማን ይናገረኝ? ማለት ይኖርበታል፡፡ ከእኛ የምንናገር ከሆነ እውነትን ወደ ጎን እየተውን ለራሳችን ነገር እየተሸነፍን እንሄዳለን፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ሀብታችን ክብራችን ጉልበታችን በአጠቃላይ የሥጋ አቅም ሊወድቅ እንዲሁም በመንፈስ ድሆች በልባችን ንጹሆች በመሆን ጽድቅን በሚራብ ማንነት መቅረብ ይኖርብናል፡፡ የእርሱ ባለ ጠግነት ተዘንግቶ በእኛ ባለ ጠግነት የምንመካ ከሆነ መፈለግንም ማድረግንም በእኛ የሚሠራ ጌታ ተትቶ እኔነታችን የሚተጋ ከሆነ መንፈስ ለእኛ ለሚናገረው ጆሮ የለንም ማለት ነው፡፡

        ተወዳጆች ሆይ ማን ይናገር? ሰው ወይስ እግዚአብሔር፣ ሐብት ወይስ ጸጋ፣ ሥጋ ወይስ መንፈስ? ምድራችን የምትናጠው ሁሉም የራሱን የሚናገርባት የአምላካችን አሳብ ወደ ጎን የተተወባት በመሆኗ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለልባችን፣ ለኑሮአችን፣ ለሙሉ ሕይወታችን እንዲናገር ስንፈቅድለት፡-

ሀ. ምሪት እናገኛለን፡- አብዛኞቹ ተንቀሳቃሽ ነገሮች መሪ አላቸው፡፡ መሪ ወደምንፈልግበት ቦታ በአግባቡ እንድንደርስ የሚያስችለን ነገር ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን መሪ ሌሎቹን ክፍሎች የሚመራ ነው፡፡ እግዚአብሔር የምንፈልገውን እንደ ፈቃዱ እየመዘነ ወደሚፈልገው የሚመራን አምላክ ነው፡፡ ሰው ምሪት ከሌለው መረን እንደሚሆን ሁሉ የእግዚአብሔር ምሪት ከሌለን ቃልም ተግባርም ብልሹ ይሆናል፡፡ አብዛኞቻችን የሁኔታን፣ የሰውን፣ የዓለምን ምሪት በአግባቡ ተለማምደናል፡፡ ዳሩ ግን የቸገረን የእግዚአብሔርን ምሪት ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ጌታ ያስችላል! እርሱ እንዲናገረን ስንፈቅድ ደግሞ ምሪቱና ትእዛዙን የምንፈጽምበት ኃይል አብሮ ወደ ኑሮአችን ይመጣል፡፡

ለ. ሰላማችን ይበዛል፡- ይህንን ጽሑፍ በመጻፍ ላይ እያለሁ አንድ ሰው የተናገረኝ ንግግር ደጋግሞ ወደ አእምሮዬ ይመጣ ነበር፡፡ ይህም “ቃልህ የሰበረውን በመረቅ አትጠግነውም” የሚለውን አባባል አስታወሰኝ፡፡ ሰው ከራሱ የሚነግረን ምርጡ እንኳን ችግር አለበት፡፡ ይህም ዓለም እንደሚሰጥ ያለ ሰላም ያስገኝልን ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን ነፍሳችን የምትናፍቀው መንፈሳችን የሚጠማው ሰላም ያለው እግዚአብሔር በሚናገረው ውስጥ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን እውነት መረዳታችን በራሱ በሰው ነገር እንዳንደነቅ ከእግዚአብሔር የሆነውንም ነገር ወደ መጠባበቅ እንድናዘነብል ያስችለናል፡፡ በእርግጥስ ሰላማችን የሚበዛው እግዚአብሔር በሚናገረን ውስጥ አይደለምን? “ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፤ አቤቱ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች” (መዝ. 41÷1)፡፡

Friday, May 18, 2012

ማን ይናገር?


 “አንድ ስለሰማሁት የቤተ መቅደስ ታሪክ ላውጋችሁ፡፡ ሰባኪው በእጅጉ ተቸግሮአል፡፡ መንስኤው በእድሜና በሀብት አንጋፋ የሆኑት ምእመን በስብከት ወቅት ማንቀላፋት ብቻ ሳይሆን ክፉኛ ማንኮራፋታቸው ነው፡፡ አዛውንቱ ከመድረኩ የመጀመሪያው መስመር ላይ ከፊት ለፊት ስለሚቀመጡ ሰባኪው በሁኔታው እጅግ ታውኳል፡፡ በመጨረሻ ግን ሰባኪው አንድ ብልሃት ውል አለው፡፡ አዛውንቱ ሁሌም ከልጃቸው ልጅ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጡ ነበር፡፡ ስለዚህ ሰባኪው ያንን ብላቴና ጠራና ወደ አንድ ጥግ ወስዶ “አንድ ነገር ታደርግልኛለህ? በየሳምንቱ እሁድ ሃምሳ ሳንቲም እሰጥሃለሁ” አለው፡፡

“ተስማምቻለሁ፡፡ ፍላጎትዎ ምንድነው?” አለ ልጁ - በችኮላ፡፡
“ከባድ ነገር አይደለም፡፡ አያትህ ማንኳረፍ ሲጀምሩ ቆንጠጥ ታደርጋቸውና ታነቃቸዋለህ፡፡ የአዛውንቱ እንቅልፍ አይደልም እኔን የረበሸኝ፡፡ ችግሩ ሰውየው ሲያንኳርፉ በአዳራሹ የተሰበሰበውን ምእመን በሙሉ ከእንቅልፍ ያነቁብኛል፡፡ የእኔ ደግሞ ብዙ የስብከት ርዕስ የለኝም፡፡ እናም ሕዝቡ ከእንቅልፉ እንዲነቃ አልፈልግም፡፡ አለበለዚያ ምእመናኑ በስብከቴ ሊሰላቹ ይችላሉ”
“ሂሳቡን ይመድቡ!” አለ ልጁ - እጁን እየዘረጋ፡፡
“በቅድሚያ? አታምነኝም እንዴ?” አለ ሰባኪው በድንጋጤ፡፡
“ሥራ - ሥራ ነው (ቢዝነስ ኢዝ ቢዝነስ)፡፡ ይህ የእምነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሃይማኖትም አይደለም፡፡ ሃምሳውን ሳንቲም ያስረክቡኝና ግዳጄን ልፈጽም” ልጁ ኮስተር በማለት መለሰ፡፡ በዚያች እለት ልጁ ተግባሩን ቀጠለ፡፡ አዛውንቱን እየጎሰመ እንቅልፍ ነሳቸው፡፡ አዛውንቱ ልጁን እየተመለከቱ “ምን ነካህ?” ቢሉትም ምላሽ መስጠት ቀርቶ ፊታቸውን እንኳን ማየቱንም አቆመ፡፡ ጆሮውንም ወደ ሰባኪው ቀሰረ፡፡
ከስብከቱ በኋላ አዛውንቱ “አንተ ተንኮለኛ! ምን አግብቶህ ትቀሰቅሰኛለህ? በእርጅና ሳቢያ በምሽት መተኛት አልችልም፡፡ ከሳምንቱ ቀናት አንዲት እሁድን ተመቻችቼ በምተኛበት ወቅት ለምን ገዳፋ ትሆነኛለህ? ምን ነካህ? ምን ተፈጠረ? ደግሞ ለስብከቱ ያለህ ትኩረት . . . አንዲት ቃል ተረድተህ ቢሆን እንኳ ጥሩ . . . ” አሉት፡፡
“አባቴ . . . ይህ የሃይማኖት ጉዳይ አይደለም” አለ ልጁ “ለአድራጎቴ በቅድሚያ ሃምሳ ሳንቲም ይከፈለኛል፡፡ በሚቀጥለው እሁድም ሥራዬን እቀጥላለሁ”
“ቆይ! እኔ አንድ ብር እሰጥሃለሁ፡፡ አትረብሸኝ!”
“ጥሩ! ሂሳብ በቅድሚያ” ልጁ ፈነጠዘ፡፡
በተከታዩ እሁድ ሰባኪው ግራ ተጋባ፡፡ አዛውንቱ ያንኳርፋሉ፡፡ ልጁ ደግሞ ወደ ሰባኪው አልመለከት አለ፡፡ “ልጁ ምን ነካው? ዛሬ ሂሳቡን በቅድሚያ ስላልከፈልኩት ይሆን?” በማለት ሰባኪው አሳብ ገባው፡፡
ከስብከቱ ፍጻሜ በኋላ ልጁና ሰባኪው ተገናኙ፡፡ “ምን ነካህ? ለሃምሳ ሳንቲም አታምነኝም? ይኸውልህ!” አለ ሰባኪው፡፡
“ጥያቄው የዱቤ ጉዳይ አይደለም፡፡ አያቴ እንዳልረብሻቸው አንድ ብር መድበውልኛል፡፡ ስለዚህ እርስዎን እንዳገለግል ከፈለጉ . . . እንግዲህ ምርጫው የእርስዎ ነው” አለ ልጁ ፀጉሩን እያከከ፡፡
“እኔ እኮ ምስኪን ሰባኪ ነኝ፡፡ በዚህ አይነት ከሀብታሙ አያትህ ጋር መፎካከር አልችልም
“ሥራ - ሥራ ነው፡፡ ሂሳቤን ከፍ ካላደረጉ አያቴ ብቻ ሳይሆኑ እኔም ማንኮራፋት እጀምራለሁ፡፡ ከዚያም አዳራሹ ይታወካል፡፡ የአያቴን ብቻ ሳይሆን የእኔንም ሂሳብ ሊኖርብኝ ነው፡፡ ለጊዜው በሳምንት ሁለት ብር ሂሳብ እንስማማ፡፡ ከዚያ የገበያው ሁኔታ እየታየ እንደራደራለን” አለ ልጁ - በድፍረት፡፡”

        ከላይ ያነበብነውን ወግ ያወጋን ኦሾ የተባለው ጸሐፊ ነው፡፡(ትርጉም፡- ዳዲሞስ፣ ርዕስ፡- የልብ ቋንቋ፣ ዓመተ ምሕረት፡- 1998፣ ገጽ 61-64) ከላይ የተነሣንበትን ርዕስ ዋና ጭብጥ ለማብራራት በእጅጉ ስለሚረዳ ለመንደርደር ተጠቅመንበታል (ከእባብ እንኳ ልባምነትን እንድንማር ታዘን የለምን?)፡፡ በዚህ ወግ ውስጥ በዋናነት ሁለት ነገሮችን እንመለከታለን፡፡

1. የሕዝቡን መንቃት የማይሻ አገልጋይ

          የተኛ መንቃት እንዳለበት፣ ክርስቶስ ደግሞ ለንቃት የሚሆን አብርሆት እንደሆነ መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ (ኤፌ. 5÷14) መፍዘዝንና አለማወቅን ልክ እንደ ትክክለኛ የእምነት አንዱ ክፍል አድርገን የምናይ ከሆነ ምስኪኖች ነን፡፡ ሰው የሚጠፋው ከእውቀት ማነስ ስለሆነ ልማት የሚኖረው እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን በማወቅ ነው፡፡ (ሆሴ. 4÷6) ተቀመጥ በወንበሬ፣ ተናገር በከንፈሬ እንደሚባል አፈ ንጉሥ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሕዝቡን የጥበብና የማስተዋል ሁሉ መዝገብ ወደሆነው ጌታ የማድረስ ኃላፊነት አለበት፡፡ (ቆላ. 2÷1) ከላይ ያየነው ሰባኪ ግን ቃሉ በሙላት ስለሌለው ከሕዝቡ መንቃት ይልቅ ማንቀላፋታቸውን ናፋቂ ነበር፡፡

        እግዚአብሔር ለእኛ ላለው ፈቃድ ልኬቱ የራሱ የእግዚአብሔር አሳብ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ፍላጎትና ምሪት ከቃሉ ውጪ በሰው አሳብና ምክር ልንመዝነው አንችልም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ንቃት የዝግጅት ከፍተኛው አካል እንደሆነ ተገልፆልናል፡፡ (ማቴ. 24÷42) ያልነቃ ሰው በቀላሉ ለጠላት ኢላማ ይሆናል፡፡ ከእውነትም ከውሸትም የቀላቀለ መሐል ሰፋሪ ነው፡፡ ሊመጣ ያለውን ሳያውቅና ሳይገምት በድንገት ይደርስበታል፡፡ እንቅስቃሴው ሁሉ ወደነፈሰው ነው፡፡ ከወንጌል ጠባይ አንዱ በሥጋ አሳብ የዛሉትን በመንፈስ ማንቃት፣ በዚህ ዓለም ነገር ያንቀላፉትን በእውነት ቃል መቀስቀስ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያገለግሉ ሁሉ ቃሉን ያለ መጨመርና ያለመቀነስ በሕዝቡ ልብና ጆሮ ማድረስ ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን የምናስተውለው ከዚህ የተለየ ነው፡፡

        ከላይ ባነበብነው የሰባኪው ንግግር ውስጥ በዋናነት የምናስተውለው የሕዝቡን መንቃት እንደማይሻና ለዚህም ምክንያቱ ብዙ የስብከት ርዕስ (በእግዚአብሔር ቃል ላይ የጠለቀ መረዳት) አለማወቁ እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ የሚከፋም ደግሞ አለ፡፡ እውነቱን እያወቁና እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን መልእክት እየተረዱ ሐቁን በኃይል ማፈን! በዚያም በዚህም ውስጥ ያለው ስውር ዓላማ ግን ሰው እንዲነቃ አለመፈለግ ነው፡፡ ለዚህስ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል?

ሀ. መብትና ኃላፊነትን ማወቅ፡- የእግዚአብሔር ቃል በእግዚአብሔር መንግስት ያለንን ስፍራና መወጣት ያለብንን ተግባር በግልጥ የሚያሳይ ነው፡፡ በእርሱ መንግስት ያለንን መብት በአግባቡ ስንረዳ ከአጉል ወቀሳ፣ ግብዝነት ከተጠናወተው ኑሮ፣ ግምታዊ ከሆነ እንቅስቃሴ፣ አፍአዊ ከሆነ ማስመሰል እንላቀቃለን፡፡ መቼ መናገር፣ የት መናገር፣ ለምን መናገር እንዳለብን ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ሰው መብትና ኃላፊነቱን በትክክልና በአግባቡ ሲረዳ የሚቆጣጠረው እውነት፣ የሚገዛውም ሐቅ ይሆናል፡፡ ሰው ምን ይላል ከሚል መመሪያ እግዚአብሔር ምን ይላል ወደሚል መገዛት ይሸጋገራል፡፡ ነገር ግን የሰዉ መንቃት እንደልብ ስለማያገላብጥ አይፈለግም፡፡ ከዚህ የተነሣ ላለማንቃት ይሠራል፡፡

ለ. ምክንያታዊ መሆን፡- እግዚአብሔርን ለመረዳት እምነት እንጂ ምክንያት አያሻንም፡፡ የተረዳነውን እግዚአብሔር ለመውደድ፣ ለመከተል፣ ለማምለክ ግን ከበቂ በላይ ምክንያት አለን፡፡ ይህም ስለ እርሱ ያወቅነው የእውቀት መጠን ነው፡፡ ከቃሉ ጋር ያለን ተዛምዶ እያሽቆለቆለ በመጣ ቁጥር እምነት ከመስማት መስማት ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ስለሆነ ለምናደርገው ነገር ሁሉ ምክንያት እያጣን በዘፈቀደ የምንወጣና የምንገባ አይነት ሰዎች እንሆናለን፡፡ ሰው ለሚያደርገው ማንኛውም ነገር ሕያው የሆነውን ቃል ምክንያቱ በዚያም ውስጥ የተገለጠውን መመሪያ መሰረቱ ሲያደርግ ለሥጋና ደም (ለሰው አሳብ) መታዘዝን ያቆማል፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ልብ ለመዝረፍና በሰው ኪስ ለማዘዝ አይመችም፡፡ ሰው ወዶ በፍቅርና በመረዳት ከሚያደርገው ፈርቶና ደንቁሮ ቢያደርገው ስለሚመረጥ የሰው መንቃት አይፈለግም፡፡ ፍንጭ ለመስጠት ያህል ስለሆነ ለጊዜው እነዚህ ይበቁናል፡፡

2. ስለ ሐብቱ የሚያንኮራፋ ተገልጋይ

      የምንሰበሰበው በስሙ፣ የምናመልከው ስለ ክብሩ፣ የተከተልነው ስለ ፍቅሩ፣ የምንታገሰው ስለ ተስፋ ቃሉ ከሆነ በእግዚአብሔር ነገር ላይ የሥጋ አቅማችንን ለማሳየት ዓለማዊ መፍትሔ ለመፈለግ የምናደርገው ምንም ዓይነት ጥረት አይኖርም፡፡ ስለ እግዚአብሔር የሰማነውን የአንዲት ደቂቃ አሳብ ሰማይና ምድር እንኳን አይተኩትም፡፡ እግዚአብሔር በአንድ ልጁ በኩል ያደረገውን የተቀበልነው በጸጋ (የማይገባ ስጦታ) ነው፡፡ (ኤፌ. 2÷ 4-8) በሚያስፈልገንም ሁሉ የሚረዳንን ኃይል የምንቀበለው ከጸጋው ዙፋን ነው፡፡ (ዕብ. 4÷16) የሕይወት ራስና የእግዚአብሔር ሙላት ወደሆነው ክርስቶስ የምናድገውም በዚሁ ጸጋ ነው፡፡ (2ጴጥ. 3÷18)

          የእግዚአብሔር ቤት ያለንን የምናሳይበት ሳይሆን ባለ ጠጋ የሆነውን ጌታ የምናወድስበት፣ ያደረግነውን የምንዘረዝርበት ሳይሆን ያደረገልንን ዘወትር እየዘከርን ልባችንን ከእጃችን ጋር በማንሣት የምናመሰግንበት ነው፡፡ ሐብትና ንዋይ የሚናገርበት ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ የሚያዝበት የእውነት ዓምድና መሠረት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የምንቆመው ጸጋው በሰጠን እድል ፈንታ እንጂ እኛ ለእግዚአብሔር እንደሰጠነው በሚሰማን ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰው በራሱ ነገር እንዳይመካ እግዚአብሔር ትንሹንም ትልቁንም ሐብታሙንም ደሀውንም የሚቀበልበት መንገድ አንድ ሆኖአል፡፡
                                                                       ይቀጥላል

Tuesday, May 15, 2012

“እናታችን ሆይ”


                     
         ትምህርት ቤት ሳለሁ የማማከር ስነ ልቡና (Counseling Psychology) መምህራችን የነገረንን ታሪክ አስታውሳለሁ፡፡ ልጅቷ መንፈሳዊ አማካሪዋ ወደሚሆኑ አባት መጥታ ስለ ጸሎት ሕይወቷ ጥያቄ ሲያቀርቡላት “አባታችን ሆይ” ብላ እንደማትጸልይ ይልቁንም በዚህ ፈንታ “እናታችን ሆይ” በማለት እንደምትጸልይ ነገረቻቸው፡፡ በምላሿ የተገረሙት አባት ከፊት ይልቅ ትኩረታቸውን በመስጠት እንዲህ ለመጸለይዋ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ጠየቋት፡፡ እርሷም በልጅነቷ አባቷ እንደደፈራትና ለእናቷ የከፋ ጥላቻ እንደነበረው በዚህም ምክንያት ለአባቷ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለአባት ያላት አመለካከት እንደተበላሸ በአባቷ ላይ ያላትም ጥላቻ እግዚአብሔርን አባት ብላ እንዳትጠራው በልጅነት መንፈስም በፊቱ እንዳትቆም እንዳደረጋት ነገረቻቸው፡፡

        አበው “እናትነት እውነት፣ አባትነት እምነት ነው” ይላሉ፡፡ ምክንያቱም እናት ከእርግዝናዋ ጀምሮ እስከ ምጧ ድረስ ያለው ሂደት ለማንም ግልጥ ነው፡፡ አባትን አባት ብሎ መጥራት ግን ማመንን ይጠይቃል፡፡ ብዙ ማስረጃዎች ጥቅም ላይ የሚውሉት የአባትን አባትነት (ወላጅነት) ለማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህ ከእናት ይልቅ አባት አባትነቱን በተግባር መግለጽ አለበት፡፡ የሙሽራው ክርስቶስና የሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያን ሕብረት ለባልና ለሚስት ጥምረትና የኑሮ ስርዓት ከፍ ያለ ማሳያ እንደሆነ ሁሉ አባት ለልጁ ምን አይነት አባት፣ ልጅም ለአባቱ ምን አይነት ልጅ መሆን እንዳለባቸውም በብርቱ ያስረዳናል፡፡ አንድ አባት ለልጆቹ የሚያደርግላቸው የመጀመሪያው ነገር እናታቸውን መውደድ ሲሆን ለሚስቱ ሊያደርግላት የሚያስፈልገው ቀዳሚ ነገር ደግሞ ልጆቿን መውደድ ነው፡፡ አገራችን ላይ አባትነት ምን ያህል ሚዛን ይደፋል ብለን ብንጠይቅ ምናልባት የቀደመ ታሪክንም መፈተሽ ይኖርብናል፡፡ ዳሩ ግን ለተነሣንበት ርዕስ በሚመጥን መልኩ ዳሰሳ ስናደርግ ብዙ ልጆች እናታቸውንም አባት አድርገው የኖሩበት እንደውም አንዳንድ ልጆች በእናታቸው ስም ሁሉ እንደሚጠሩ መረዳት እንችላለን፡፡ ስለ ቤተሰብ ከሚዘፈኑት ዘፈኖች እንኳ አብላጫው የእናት ነው፡፡

        በአንድ ልጅ እድገት ላይ የቤተሰብ ተጽእኖ ለልጁ መልካም መሆን አልያም መጥፎ መሆን አብላጫውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ በልጆች አስተዳደግ ላይ የአባትና የእናት ሚና ቀላል አይባልም፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ የተነሣሁት ያለፈውን የእናቶችን ቀን አስመልክቶ ነው፡፡ የበሽታ ቀን በሚከበርበት ዓለም ላይ ወደ እዚህ ምድር ስለምንቀላቀልባቸው ሁለተኛ ፈጣሪ እናቶች ቀን መሰየሙ ደግሞም መከበሩ ቢያንስ እንጂ አይበዛም ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለው አጋጣሚ ትልቅ ስፍራ እንደሚኖረው አምናለሁ፡፡ የእኛ አገር እናቶች አባትም ጭምር ሆነው ያሳደጉን ናቸው፡፡ ጠቁረው እንድንቀላ፣ ደክመው እንድንጠግብ፣ ከስተው እንድንፋፋ፣ ኖረው ብቻ ሳይሆን ሞተውም ያኖሩን ናቸው፡፡

          ጆርጅ ዋሽንግተን ስለ እናቱ ሲናገር “እናቴ በሕይወት ዘመኔ ካየኋቸው ሴቶች ሁሉ እጅግ የተዋበች ናት፡፡ መላው እኔነቴ ሁሉ ለእናቴ የተሰጠ ነው፡፡ በሕይወት ዘመኔ ያገኘሁት ስኬት ሁሉ ከእናቴ ከተቀበልኩት ሞራላዊ፣ ስነ ልቦናዊና አካላዊ ትምህርት የተነሣ ነው” በዓለም ላይ እጅግ ተወዳጁ ቃል እናት የሚለው ነው፡፡ ይህም መስማማት ያመጣው ሳይሆን ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ አንድ ወጣት ስለ እናቱ ሲናገር “ከጥቂት ዓመታት በፊት እናቴን በሞት አጥቻለሁ፡፡ በእናቴ ሞት የተነሣ የደረሰብኝ ጥልቅ ሀዘንና ውስጣዊ ሕመም ስር የሰደደ ከመሆኑ የተነሣ አሁንም ድረስ ጠባሳው አልሻረም፡፡ ነገር ግን መለስ እልና በእናቴ ልዩ ፍቅር እንዲሁም እንክብካቤ ያሳለፍኩትን ዘመን በማስታወስ ልጅነቴን እናፍቃለሁ” ብሏል፡፡ አንድ ያልታወቀ ሰው “ብዙ እናቶች እጅግ ደስ የሚሉ ናቸው፡፡ ግን የማንም እናት እንደ እኔ እናት ጽኑ አይደለችም፡፡ ነገሮች እየከበዱ ቢሄዱም፣ ችግሮች ቢከሰቱም እርሷ ግን ተስፋ አትቆርጥም ፈጽሞ አትወድቅም፡፡ በየዕለቱ ለእኔ ያላት ትምህርት ከሚሊዮን ጊዜ የሚበልጥ ማለቂያ የሌለው ነው፡፡ መክፈል የማልችለውን ፍቅርና ምቾት ከእርሷ አግኝቻለሁ፡፡ ለእርሷ ያለኝን ፍቅር ለመግለጽ አልጀምረውም፡፡ ይህ ልክ እንደ መስመር መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ነው፡፡ ግን የማንም እናት እንደ እኔ እናት የተለየች አይደለችም” በማለት ስለ እናቱ ተናግሮአል፡፡

         ሁላችንም ብንሆን ስለ እናት ጥቂት የማለቱን እድል ብናገኘው ማቋረጥ እንደሚሳነን እገምታለሁ፡፡ ስለ እናት የተባሉ ጥቂት የልብ መልእክቶችን እንመልከት፡-
·        የእናት ጥበብ የመኖርን ጥበብ ለልጆች ማስተማር ነው፡፡
·        የእናት ልብ የሕፃናት ትምህርት ቤት ነው፡፡
·        እናት ጉዳታችንን እና ጭንቀታችንን ሁሉ የምንቀብርበት ስፍራ ናት፡፡
·        እናት ምግብ ናት፣ ፍቅር ናት፣ ምድር ናት፡፡ በእርሷ መወደድ ማለት በሕይወት መኖር፣ ስር መስደድና መታነጽ ነው፡፡
·        አንድ ወቄት እናት ከአንድ ፓውንድ ካህናት ይልቅ ትመዝናለች፡፡
·        ከመላው ዓለም እጅግ ውብ የሆነ አንድ ሕፃን አለ፡፡ እያንዳንዷ እናት ደግሞ ይህ ሕፃን አላት፡፡

       ይህ ጽሑፍ የእናቶችን ቀን ምክንያት ያደረገ ቢሆንም በመግቢያው ላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው አባቶች በሕብረተሰቡ ዘንድ ያላቸው ግምት በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ያላቸው ስፍራ ከእናቶች አንፃር ስዕሉ የደበዘዘ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ስለ አባትነት ሲነሣ ከደስታ ይልቅ ፍርሃት የሚነግስባቸው፣  ከደስታ ይልቅ ሀዘን የሚወራቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ አባትነት ያለውን ትርጉም ከምንጩ ስንፈትሸው አባትነት እግዚአብሔር ራሱን ከእኛ ጋር ያስተሳሰረበት ሕብረት መገለጫ ነው፡፡ “በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ” (ኤፌ. 3÷14-15)፡፡ ምድራዊ አባትነት መሰረቱ ሰማያዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመፍጠር፣ ለእስራኤል ዘር፣  በልጁ በክርስቶስ ላመኑ አባት ነው፡፡ ይህም ለልጁ ለክርስቶስ ያለውን የባሕርይ አባትነት ሳይጨምር ነው፡፡ ክርስቶስ እንዴት እንጸልይ ዘንድ ሲያስተምረን “አባታችን ሆይ” በማለት እንድንጸልይ አስተምሮናል፡፡

         ምድራዊ አባትነት ሰማያዊውን የሚያጣቅስ እንደመሆኑ የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ርኅራኄና አሳቢነት ማሳየት አለበት፡፡ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ፊት ስንቀርብ ብዙዎቻችን በአባትና በልጅ መካከል እንዳለ የቤተሰባዊነት መንፈስ መቆም እንፈተናለን፡፡ ይህንን ተጽእኖ ያመጣው ደግሞ በሥጋ ያሉንን አባቶች በምናይበት አይን እግዚአብሔርን ለማየት መሞከራችን ነው፡፡ ነገር ግን ምድራዊው አባትነት በሰማያዊው ይመዘናል እንጂ ሰማያዊው አባትነት በምድሩ አይለካም፡፡ እግዚአብሔር በመልኩ እንደ ምሳሌው ፈጠረን እንጂ እኛ በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እርሱን አላስገኘነውም፡፡ በእንጀራ አባት ብታድጉም እግዚአብሔር የእንጀራ ልጅ የለውም፡፡ እርግጥ ነው! በምድራዊው ስርዓት ዳቦ ለለመነው ልጁ ድንጋይ፣ ዓሣ ለለመነው እባብ የሚሰጥ አባት ይኖር ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ፍቅር ነው! አንኳኩ ያለን ይከፍታል፣ ፈልጉ ያለን ይገኛል፣ ጠይቁ ያለንም ይመልሳል፡፡

        የአባትነት ጸጋ ለተሰጣችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን በሰው ፊት ለማሳየት ትልቁ አገልግሎት ያለው በዚህ ውስጥ ነውና አክብሩት፡፡ አንድን ሴት ልጅ መውለዷ ብቻ እናት እንደማያደርጋት ሁሉ አንድን አባትም ልጅ ማስወለዱ ብቻ አባት አያሰኘውም፡፡ ስለዚህ አባትነት በሚጠይቀው መጠን እንድንኖር መትጋት አለብን፡፡ ጽሑፋችንን አንድ የአሥራ አምስት ዓመት ልጅ ስለ እናቱ በተናገረው እንፈጽም፡፡ “እናቴ ቤታችንን ምድር ላይ ካሉ ቦታዎች ሁሉ ይልቅ ምርጥና የደመቀ ታደርገዋለች፡፡ ምክንያቱም እናቴ እጅግ አዛኝ፣ ቸር፣ የምትረዳ፣ አሳቢና በፍቅር የተሞላች ናት! ካለችኝ እናት የተሻለ እንዲሰጠኝ ጌታን የምለምነው ምንም የለም፡፡ እናቴ ማለት ለእኔ፡-
የምንጣጣም እውነተኛ ጓደኛ
አብረን ልንጓዝ የምንችል ምቹ ወዳጅ
ደስታን የምትፈጥርልኝ አጋር፣ ለመኖር የምታጓጓኝ ልብ ማለት ናት፡፡ ድፍን ዓለም ቢታሰስ የእርሷን ያህል ፍቅርና ርኃራኄ በተሻለ የሚሰጥ አይገኝም፡፡ እርሷ ለእኔ የፈጣሪ ምርጥ ጥረት ናት” እናቶቻችንን ጌታ አብዝቶ ይባርክልን!!!

Friday, May 11, 2012

ልበ ሰፊ (ካለፈው የቀጠለ)



“ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገቡ እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፡-ነገሩ እንዲሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” (የሐዋ. 17÷10)፡፡

          የቤርያ ከተማ በምስራቹ ወንጌል እንድትጎበኝ ምክንያት የሆነው በተሰሎንቄ ከተማ በጳውሎስና በሲላስ ላይ የደረሰው መገፋት ነበር፡፡ በእኛ መሰደድ ውስጥ ለሌሎች ሕይወት ማግኘት ሲሆንላቸው ማየት ድካማችንን እንዳናስብ የሚያደርግ በቂ ምክንያታችን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የተሰሎንቄን ከተማ በዋስ ለቆ ከወጣ በኋላ የተሰደደባት ቤርያ በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊ የሆኑ ሰዎች የነበሩባት ከተማ ናት፡፡ ዮሴፍ ወንድሞቹ ከአባቱ ቤት ቢያሳድዱት እግዚአብሔር ለግብፅ ምድር እንጀራ አድርጎታል፡፡ እንደ እግዚአብሔር አሳብ ለተጠሩና ጌታን ለሚወዱ ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡ (ሮሜ. 8÷28) እግዚአብሔር በሌሊትም ድምፁን በመስማት የሚያምኑ አሉት፡፡ ቃሉ በሚነገርበት ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት ተተርጉመው ሰዎች በቀላሉ እንዲደርሳቸው በተመቻቸበት በዚህ ዘመን እግዚአብሔርን በቀን መፈለግ ጭንቅ ሆኖአል፡፡ የቤርያ ሰዎች የሚደነቀውን ብርሃን የተገናኙት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ጳውሎስና ሲላስም የከበረውን የምስራች የተናገሩት በወጀብና በአውሎ መሐል ሆነው ነው፡፡

          የቤርያን ሰዎች ልበ ሰፊ ስላስባላቸው ነገር ማወቅ  ለእኛ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን፡፡

ሀ. ማመዛዘን፡-

          “ነገሩ እንዲሁ ይሆንን?” የሚለው አገላለጽ ችኩልነት ለሚያጠቃው ኑሮአችን ጠንከር ያለ ትምህርት አለው፡፡ ከምንፈተንባቸው ነገሮች መካከል ለሌሎች አሳብ ትኩረት አለመስጠትና ሊሆን የሚችልበትን የበዛ ጎን አለማጤን በተደጋጋሚ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን በመንፈሳዊው መንገድ ብቻ ሳይሆን የምድር በሆነው ኑሮአችንም ማመዛዘን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በጊዜው ባለማመዛዘናችን አልፎ የቆጨን ነገር ምን ያህል የበዛ ነው? የቤርያ ሰዎች ጳውሎስ ስለ ሰበከ ሲላስ ስለተናገረ ሳይሆን ከእነርሱ ስለወጣው ቃል ትኩረት ሰጥተው ነበር፡፡

          ለብዙ ጊዜ በጉባኤ ላይ ሲሰበክ ፊቷን በነጠላ ተሸፋፍና ትሰማ የነበረች እህት ከብዙ ጊዜ በኋላ ይህንን ለምን እንደምታደርግ ስትናገር “ለማሳት እንዳልገለጥና ለመሳት እንዳልጋለጥ ይልቁንም በልቤ ጆሮ ማድመጥን ማመዛዘንን ከዚያም መቀበልን እንድችል ነው” በማለት የተናገረችው ልብን ይነካ ነበር፡፡ የሰባኪ መልክና የዘማሪ ድምጽ ገምግመው ስለሚመለሱ ወገኖች እንደነቃለን፡፡ አጭር ተናገረ ረዥም፣ ቀጭን ተናገረ ወፍራም፣ ቀይ ተናገረ ጥቁር የቤርያ ሰዎች መስማታቸው በማመዛዘን ነበር፡፡

         የእግዚአብሔርን ቃል በምንሰማበት ጊዜ እውነት ይሆንን? በማለት የሰውን አሳብ ከእግዚአብሔር አሳብ፣ የሥጋና የደም ምክርን ከመንፈሳዊው ቃል፣ የምድር የሆነውን ዘላለማዊ ከሆነው መለየት አለብን፡፡
    

ለ. መጻሕፍትን መመርመር፡-

        ሌላው የቤርያን ሰዎች ልበ ሰፊ ያስባላቸው ጉዳይ ዕለት ዕለት መጻሕፍትን መመርመራቸው ነው፡፡ ትላንት በልቻለሁ ብለን ዛሬ ከመብላት አልተከለከልንም፡፡ ምክንያቱም በሥጋ ልንቆም የምንችልበት ኃይል ያለው ዕለት ዕለት ለሰውነታችን ባሕርይ ተስማሚ የሆነውን ምግብ በመመገብ ነው፡፡ እንዲሁ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ዕለት ዕለት የሚኖረን የጠበቀ ግንኙነት ነፍሳችን ልትቆም የምትችልበትን ሁኔታ ይወስናል፡፡ የቤርያ ሰዎች በሚዛናዊነት የሰሙትን ቃል ከመጻሕፍት ጋር ያመሳክሩ ነበር፡፡ ስለ ሂደቱም ወንጌላዊው ሉቃስ ሲነግረም “እየመረመሩ” ይለናል፡፡ መመርመር ከማንበብ የዘለለ ትርጉም አለው፡፡ ማንበብ ፊደል ሲሆን መመርመር ግን ትርጉም ነው፡፡

        በእንግሊዝ አገር የታሪክ አዋቂና ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የነበረው ጆን ሴልደን (1584-1654) በአንባቢነቱና በትምህርቱ የታወቀ ሰው ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ለሞት በሚያጣጥርበት ወቅት “ከፀሐይ በታች የሚገኘውን አብዛኛውን ትምህርት የቻልኩትን ያህል ቀስሜአለሁ፡፡ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተጻፉ አያሌ መጻሕፍትን አንብቤአለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ጥረት ውስጥ ግን ነፍሴን ላሳርፍ የምችልበት ክፍል አላገኘሁም፡፡ ነገር ግን በዚህ ሰዓት ለነፍሴ ዕረፍት ሊሆነኝ የሚችለው ሰዎችን ሁሉ ሊያድን የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተገለጠ የሚመሰክረው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ብቻ ነው” በማለት ተናግሮአል፡፡ የሳይንስና የታሪክ፣ የፍልስፍናና የፖለቲካ ሰዎች ለዚህ ዓለም ጥቅም መጽሐፍ ቅዱስን ሲመረምሩ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፍለናል የምንለው ግን እንደ ባላንጣ ከቃሉ መሸሻችን አስገራሚ ነው፡፡

      ሰው ሊዋሽ ደግሞም ቃሉን እንደ ግል አመለካከቱ ሊናገር ይችላል፡፡ ቅዱስ ቃሉ ምን ይላል ማለት ግን ከእኛ ይጠበቃል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ያለው ቃል እንደመሆኑ የተናገረንን የሚያስፈጽምበት ኃይል አብሮት አለ፡፡ ስለ ፈውስ ከተናገራችሁ ይፈውሳል፣ ስለ ለውጥ ከተናገራችሁም ይለውጣል፣ ስለ ድል ከተናገራችሁም በወደዳችሁ በእርሱ ከአሸናፊዎች ትበልጣላችሁ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው በዚህ የሥልጣን ቃል ማመንና ዕለት ዕለት እግዚአብሔር በእዚህ ውስጥ ለእኛ ያለውን አሳብና ፈቃድ መመርመር ነው፡፡

ሐ. በሙሉ ፈቃድ መቀበል፡-

        የቤርያ ሰዎች ከተነገረው ቃል ጋር የነበራቸውን መስማማት የሚያስረዳን አገላለጽ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ፈቃዳችን ለብዙ ነገር የተከፋፈለ ነው፡፡ ልዩ ልዩ ለሆኑ ነገሮች ፈቃደኝነታችንን እናሳያለን፡፡ ይህም ሕይወታችንን ጉልበት ያሳጣታል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርነው እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን ፈቃዱን ለማድረግ ነው፡፡ (ኤፌ. 2÷10) እግዚአብሔር ሙሉ ትኩረታችንን፣ ሙሉ መውደዳችንን፣ ሙሉ መገዛታችንን ይፈልጋል፡፡ ከእርሱ የሆነውን ነገር ስንቀበልም በሙሉ ፈቃድ መሆን አለበት፡፡ የቤርያ ሰዎች አመዛዝነው የሰሙትና ከመጻሕፍት ጋር ያመሳከሩት ቃል እውነት ባይሆን ኖሮስ? ብለን እናስብ፡፡ በእርግጥም ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቃወሙት ተብሎ ይፃፍልን ነበር፡፡

         ለእግዚአብሔር ሙሉ ነገራችንን መስጠት መለማመድ አለብን፡፡ ከእርሱ የሰሰትነውና ያስቀረነው ነገር የእድሜ ልክ ፈተና ከመሆን አያልፍም፡፡ በሁለት ልብ ማንከስ በሁለት አሳብ መጓዝ ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡ የቤርያ ሰዎች መቀበላቸው የይምሰል አልያም ተራ አልነበረም ይልቁንም በሙሉ ፈቃድ ነበር፡፡ እውነትን በሙሉ ፈቃድ መቀበልን ስንለምድ የተቀበልነው እውነት በሙሉ ኃይሉ ይሠራብናል፡፡ ለጌታ አሳብ ሙሉ መገዛታችንን እናሳይ ዘንድ ጸጋ ይብዛልን፡፡

Tuesday, May 8, 2012

ልበ ሰፊ


ለአንድ ክርስቲያን ልበ ሰፊ መሆን በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ልብ የሰውነትን፣ የአእምሮንና የስነ ልቡናን ክፍሎች የሚያመለክት እንደመሆኑ ሙሉ እኛነታችንን የሚገዛና የሚቆጣጠር ነው፡፡ ስለዚህ የአእምሮና የአሳብ፣ የስሜትና የፈቃድ እንብርት የሆነው ልባችን ሰፊ መሆን ይኖርበታል፡፡ የምንኖርበት ዓለም ለጥላቻ ምክንያት በሌላቸው፣ እንዲሁ ስመለከትህ ክፉ ትመስለኛለህ፣ ሳይህ ታስጠላኛለህ በሚሉ፣ ሰውን በሆነው ማንነቱ ሳይሆን ገና በይሆናል በሚጸየፉ የተከበበች ናት፡፡ የወደደ የሚጠላባት፣ የገፋ የሚያፈቅርባት፣ ያነባ ስቆ የሳቀ የሚያምጥባት፣ ያጣ አግኝቶ የጠገበ የሚራብባት ይችው የምንኖርባት ምድር ናት፡፡ ታዲያ የኑሮ ትግል ሲበረታ፣ እንደ እግዚአብሔር ያልሆነው ነገር ሲያይል፣ ነውር እንደ ክብር ዓመጽ እንደ ጽድቅ ሲቆጠር፣ ከስቃይ ወደ ባሰ ስቃይ መገላበጥ ሲበዛ፣ በጉድ ነግቶ በጉድ ሲመሽ ልበ ሰፊ መሆን በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ኑሮን በአግባቡ ለመኖር፣ በሕይወት ውስጥ አመዛዛኝ ለመሆን፣ ከቅድም አሁን ከትላንት ዛሬ በተሻለ ለማደግ፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች ለመትረፍ፣ በማዕበል ውስጥ ፀጥታን ለመተንፈስ አሳበ ሰፊነት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡  

ዓለም አመጣሽ ለሆነው አዲስ ነገር የማይደነቅ፣ ለጥላቻ የማይበቀል፣ ሁሉን በፍቅር የሚያይ፣ ሰው ተስፋ የቆረጠበትን የሚታገሥ፣ ሁሉን ከሰጪው እግዚአብሔር የሚጠብቅ፣ ለመስማት የፈጠነ ለመናገር የዘገየ፣ ለፍርድ የማይቸኩል ለማቅናት የሚተጋ፣ በሁሉ የሚያመሰግን ልበ ሰፊ የሆነው ማንነት ነው፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳው የጠላት ዲያብሎስ ዘመቻ፣ የኑሮው ፍላፃ ሁሉ የሚያነጣጥረው ልባችን ላይ ነው፡፡(ምሳ. 4÷23) በዓለም ትልቁ መቅደስ ንጹሕ ልብ ነው (2ቆሮ. 6÷16) እንደሚባል የእግዚአብሔርም ናፍቆት፣ የዓይኑም ማረፊያ ልባችን ነው፡፡ ጉዳት የሚጠነክረውም ከልባችን ሲጀምር ነው፡፡ ከልብ የጀመረውን እግዚአብሔር ካልተቆጣጠረው የሥጋና የደም ምክር አይቆጣጠረውም፡፡ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ጥላቻን በአግባቡ ለማስተናገድ ልበ ሰፊነት ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡ ልበ ሰፊ (አሳበ ሰፊ) በሆነ ሰው ሕይወት ውስጥ በዋናነት ሁለት ባሕርያትን እናያለን፡፡
1. የተዘጋጀ ነው
ያለ ዝግጅት ደስታም መርዶ ነው፡፡ በሕይወት ከምናስተናግደው ውጣ ውረድ በላይ ሊመጣ ላለው ነገር አለመዘጋጀታችን ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ክፉውን ለመቋቋም፣ በጎውን ለመፈጸም፣ ሁሉን እንደ እግዚአብሔር ቃል ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት የእምነት አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ክርስትና በራሱ ለዘላለም ሕይወት ለክርስቶስ ዳግም መምጣት  የምናደርገው ዝግጅት ነው፡፡ ታላቅቅ ከሚባሉት ጀምሮ አነስተኛ እስከሆኑት ተግባራት ድረስ ለሚከሰተው የውጤት ብልሽት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የዝግጅት ማነስ ነው፡፡ ክርስቲያን የልቡናውን ወገብ የታጠቀ፣ ኑሮን በመጠን የሚመራ ነው፡፡ “የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው÷ የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” (ምሳ. 16÷1)፡፡ በክርስትና ዝግጅት የሚገለጽባቸውን ጥቂት ነጥቦች በእግዚአብሔር አጋዥነት በመንፈሱም መሪነት ለመመልከት እንሞክራለን፡፡  
ሀ. ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ
ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት አደባባይ፣ የምንግባባበት ቋንቋ፣ ስጦታውንም የምንቀበልበት እጅ እምነት ነው፡፡ ያላየነውን እግዚአብሔር እንዳየነው፣ ያልዳሰስነውን አምላክ እንዳገኘነው፣ ያልደረስንበትን ተስፋ እንደጨበጥነው የሚያስረግጥ ኃይል ነው፡፡ ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ጤናማነት የምንፈትሽበት ሂደት ነው፡፡ ትልቅ እምነት ወደ ትልቅ ነጻነት ያመጣል፡፡ ዓለምን የምናሸንፍበት ኃይል ያለውም እምነት ውስጥ ነው፡፡ (1 ዮሐ. 5÷4)

በነቢዩ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ በምዕራፍ ሦስት ላይ ያለ ማቋረጥ በእግዚአብሔር ላይ ስለ መደገፍ የሚያስረዳንን ታሪክ እናገኛለን፡፡ በባቢሎን ምድር ናቡከደነፆር ይገዛ በነበረበት ዘመን ኢየሩሳሌም ተቃጥላ ሕዝቡ ሲማረክ ሦስት ዕብራውያን ብላቴኖች አብረው እንደተጋዙ እናነባለን፡፡ አገራቸው ሰላም ሳለ በእምነት ያመለኩትን እግዚአብሔር በተሰደዱበት ምድርም ሆነው አመለኩት፡፡ እግዚአብሔር ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ አመፀኛ አይደለምና የእነርሱ ባልሆነው አገር ርስት፣ በማያውቁት ንጉሥ ፊት ሞገስ ሆናቸው፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑትን የትም ያውቃቸዋል፡፡ ያመንበትን ነገር ምቾት የሚያስረሳን፣ መከራ የሚያስጥለን ከሆነ አደጋ ነው፡፡

ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ቢያቃጥል፣ ቤተ መቅደሱን ቢያፈርስ፣ ንዋያቱን ቢያወድም ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ፍቅር፣ ለእምነታቸው የሚያሳዩትን ቅናት፣ እውነተኛ ኑሮአቸውን ግን ከልብ ከአእምሮአቸው ሊፍቅ ደግሞም በእግዚአብሔር ላይ ከመደገፍ ሊለያቸው አልቻለም፡፡ እነርሱ ቢሰደዱም እግዚአብሔር አይሰደድም፡፡ እነርሱ ቢታሰሩም እምነታቸው ግን አይታሰርም፡፡ እነርሱ በጠላት ቢከበቡም ጌታ ግን አይከበብም፡፡ ዕብራውያኑ በባቢሎን ምድር በዱራ ሜዳ ንጉሡ ባስቆመው ምስል (ጣዖት) ፊት በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸውን እምነት ገለጡ፡፡ ከንጉሡ ቁጣ በኋላም ሰባት እጥፍ በሚነደው እሳት ውስጥ “ባያድነን እንኳን” በሚል ፍፁም እምነት የተፈተነ ኑሮአቸውን የማያቋርጥ መታመናቸውን ለእግዚአብሔር አሳዩ፡፡ በእርግጥ ጌታን ያለማቋረጥ እንደገፈው ዘንድ አይገባምን?     

ዓለም ላይ ወደ ሕይወታችን በሚመጣ ማንኛውም አሉታዊ ነገር ሳንሸበር በክርስቶስ ያለን ነፃነት የሚጠበቀው ትልቁ ኃይል እምነት በውስጣችን ሲኖር ነው፡፡ እግዚብሔርን ከተደገፍከው የተደገፍከው እውነተኛ ወዳጅ ነውና ደስ ይበልህ፡፡ (ት. ኢሳ. 26÷4) ተወዳጆች ሆይ እርሱ ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ፣ እውነተኛ ወዳጅ፣ ማረፊያ ጥላ ነውና ለዘላለም እንመነው፡፡ በጉዳት ውስጥ ሆነን የእግዚብሔር እጅ ሲሠራ ማየት እምነት ነውና በወጀብና በአውሎ መንገድ ያለውን ጌታ እንደገፍ፡፡  
“እምነት ማለት ያላየኽውን ማመን ነው፡፡ የዚህም ሽልማቱ ያመንከውን ማየት ነው፡፡”
 /ቅዱስ አውግስጢኖስ/

ለ. በፍቅር መኖር

በዓለም ላይ እጅግ አደገኛው ነገር “ፍቅር አልባ” እምነት ነው፡፡ ክርስትና መሠረቱ ክርስቶስ፣ መገለጫው ፍቅር፣ ግቡም ሰላምና ዕረፍት ነው፡፡ አምነን የምናመልከውን አምላክ የምንገልጥበት አማራጭ የሌለው መንገድ ቢኖር በሥራና በእውነት የተቃኘ ፍቅር ነው፡፡ ቃሉ እንደሚል “በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን፡፡” (1ቆሮ. 16÷14) ፍቅር ከሌለው ብዙ ተግባር ይልቅ መውደድ በተሞላ ንግግር እግዚብሔር ይከብራል፡፡ ሁሉ የምትለው ቃል “ቃልና ተግባር” የሚል ፍቺ ይዛለች፡፡ በዚህ መሰረት ሙሉው አሳብ ቃላችሁም ተግባራችሁም በፍቅር ይሁን ማለት ይሆናል፡፡ ለዓለም የሚታየው ትልቁ ምስክርነት የእምነት አቋማችን ሳይሆን መውደድ የተሞላው ሕይወታችን ነው፡፡ (ዮሐ. 13÷35) በእግዚአብሔር ፊትም የምንጋፈጠው ጥያቄ የፍቅር ነው፡፡ (ማቴ. 25÷31-46)

ተወዳጆች ሆይ፡- የእድሜያችንን ሙሉ ክፍል መውደድ ላይ ካዋልነው የትኛውም ሚዛን ላይ አንቀልም፡፡ የመልካምነት መመዘኛው ፍቅር ነውና፡፡ አንባቢው ልብ ይበል! ልበ ሰፊ ሰው በፍቅር የተሞላ ነው፡፡ ለጥላቻም ያለው ምላሽ መውደድ ብቻ ነው፡፡ (ማቴ. 5÷43)
“ንስጥሮስ ሆይ አንተን እወድሃለሁ ትምህርትህን ግን እጠላዋለሁ”
/ቅዱስ ቄርሎስ/  

 ሐ. በደልን መናዘዝ

        አጥፍቶ በድያለሁ ማለት እውነተኛነት ነው፡፡ (ዮሐ. 1÷8) በደላችንን ስንናዘዝ ደግሞ ንስሐ ይባላል፡፡ በድለን ከእግዚአብሔር ይቅርታ የምናገኝበት ብቸኛው መንገድም ይኸው ነው፡፡ ኃጢአታችንን ብንሰውር ልማት አይሆንልንም፡፡ ብንናዘዝባትና ብንተዋት ግን ከሚምር ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን እናገኛለን፡፡ (ምሳ. 28÷13) እኛ በደለኝነታችንን አምነን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት መንገድ ንስሐ ሲሆን ኑዛዜያችንን ተቀብሎ እግዚአብሔር ለኃጢአታችን መንፃትን የሚሰጥበት መንገድ ደግሞ ደም ነው፡፡ (1 ዮሐ. 1÷7)

ስለዚህ የሚያውቀውን መተላፋችንን እንዲተውልን ደግመንም ወደእዚያ ጥፋት እንዳንመለስ ጸጋውን እንዲያበዛልን ልባዊ ጸጸትና ሸክምን ይዞ መቅረብ ያስፈልጋል፡፡ መቆሸሽ ካለ መታጠብ ግድ ስለሆነ ንጹሕና የተቀደሰ ኑሮ እንድንኖር ዕለት ዕለት በምሕረቱ ባለ ጸጋ ወደሆነው አምላክ በንስሐ ልንቀርብ ይገባል፡፡ “በብዙኃ ምሕረትከ ደምስስ አበሳነ” በምሕረትህ ብዛት ኃጢአታችንን ደምስስ!

መ. የሕይወት ፀጥታ
ሕይወትን በፀጥታ የማትኖራት ከሆነ አይደለም ከእግዚአብሔር ከደህና ሰውም ሳትገናኝ ትሞታለህ፡፡ የሕይወት ቁምነገሯ፣ የኑሮ ትርፍና ኪሳራ የሚገባን፣ ድምፆች በበዙበት ዓለም መለኮታዊውን የእግዚአብሔር ድምጽ የምንለየው፣ የምንናገረውንና እግዚአብሔር የሚመልስልንን የምናስተውለው በፊቱ ፀጥታና ዕረፍት የሰፈነበት ከሁከትና ከጭንቀት የፀዳ የኑሮ ስርዓት ሲኖረን ነው፡፡ ፀጥታ በሌለበት ሁኔታ መደማመጥና መግባባት እደማይቻል ሁሉ ከፀጥታ የራቀችም ነፍስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መረዳትና ከአሳቡ ጋር መስማማት አትችልም፡፡ እግዚአብሔር የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ ስላይደለ በፀጥታ ውስጥ ይናገራል፡፡

ክርስቲያን በፈጠረው ብሎም ባዳነው አምላክ ያረፈ፣ ከጭንቀት የራቀ፣ አሳቡም በዘላለማዊው ሕይወት የተሞላ ነው፡፡ ቃሉ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉ” (1ጴጥ.5÷7) ይላል፡፡ ግን ጥለናል ወይ? በአሳብህ ውጥረትህንና ጭንቀትህን ከሕሊናህ ደጃፍ አውጥተህ ጣላቸው፡፡ የሚቀበልህም እጅ በርህ ላይ ተዘርግቶአል፡፡ ቤትህን በእግዚአብሔር ሰላም፣ ሙቀትና ብርሃን ለመሙላት የተዘጋጀህ ሁን፡፡ በተሳሳተ መንገድ የሮጠ የሚደርሰው የተሳሳተ ቦታ ላይ ነው፡፡ ከጉዞአችን ይልቅ አሳሳቢው ጉዳይ መድረሻችን ው፡፡ የሕይወት ፀጥታ የመጣንበትን፣ ያለንበትንና የምንደርስበትን አጥርተን እንድናይ ይረዳናል፡፡ የሕይወትህ ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን ማስጠንቀቂያ አንብበኸዋልን “ፀጥታ ይከበር” ይላል፡፡

“በልቤ ውስጥ አንድ ትንሽዬ ክፍል አለች፡፡ በሮችዋ ደስታንና ሀዘንን ለመሰብሰብ በሰፊው የተከፈቱ ናቸው፡፡ ፍቅርም ወደ ውስጧ ይገባል”
 / የልበ ሰፊዎች ንግግር/  
እነዚህ ሁሉ ከላይ የተመለከትናቸው ለልበ ሰፊነት የሚያስፈልጉ ነገሮች እንዲሁም መገለጫ ጠባያት ናቸው፡፡ እግዚብሔርን “በዓለም ላይ ትልቁ ሀብት የት ይገኛል” ስል ጠየኩት፡፡ እርሱም “ታላቅ ልብ (የልብ ስፋት) ካለህ አስቀድመህ አግኝተኸዋል” ሲል መለሰልኝ፡፡ አሜን! 

- ይቀጥላል -


Friday, May 4, 2012

በእጁ ፊት (ካለፈው የቀጠለ)


                        
        ስለ እግዚአብሔር ቃል መገኘትና የተገኘውን ቃል ስለ መብላት ነቢዩ ኤርምያስ ከዋዘኞችና ኃጢአትን ምንጭ ባደረገ ደስታ ካረፉ ሕዝቦች መሐል ተለይቶ ብቻውን በእግዚአብሔር እጅ ፊት በመሆን የወሰዳቸውን መንፈሳዊ እርምጃዎች በመዘርዘር ሁለቱን በመጠኑ ለማየት ሞክረናል፡፡ ቀሪዎቹንም በእግዚአብሔር እርዳታ በመንፈሱም ኃይል እንመለከታለን፡፡

3. በስምህ ተጠርቻለሁ

          በስሙ መጠራት ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖር የሚችለውን የጠበቀ ኅብረት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤል አባት እንደሆነም ይገልፃል፡፡ ነቢዩ ሕይወቱ ለእግዚአብሔር የተሰጠ እንደመሆኑ የዘላለም አምባ በሆነው ጌታ ላይ የታመነ አገልጋይ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ነቢዩ የአንተ ገንዘብ ነኝ ለማለት የተጠቀመበት ንግግር ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ላለነው ክርስቲያኖች ደግሞ በስሙ መጠራት የከበረና ከፍ ያለ ትርጉም አለው፡፡ እግዚአብሔርን አባት ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ የተቀበልነው በእግዚአብሔርም ልጆቼ ተብለን የተጠራነው በክርስቶስ ኢየሱስ የከበረ ደም ፈሳሽነት ነው፡፡ የተጠራንበት ስም ከስም ሁሉ በላይ ነው፡፡ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ስም ነው፡፡ ከምድርም በታች ሁሉ ይንበረከኩበት ዘንድ የተሰጠን ስም ክርስቶስ ኢየሱስ የሚለው ነው፡፡ (ፊል. 2÷9-11)

        በክርስቶስ ክርስቲያን መሆናችን እግዚአብሔርን አባት ብለን የምጠራበት መንፈሳዊ መብታችን ነው፡፡ ልጆች ከሆንን መጠሪያችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ተጠሪነታችንም በመልኩ እንደ ምሳሌው ለፈጠረን ከውድቀት በኋላም በአንድ ልጁ የመስቀል ሞት ላዳነን ጌታ ነው፡፡ (ሮሜ. 1÷6) ስሙ ሁለንተናችን ነው፡፡ ቃላችንም ተግባራችንም ክብረት የሚያገኘው በዚህ ስም ስንጠራና ሁሉን በስሙ ስናደርገው ነው፡፡ “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” (ቆላ. 3÷17)፡፡

4. ሐሴትና የልብ ደስታ

       የእግዚአብሔር ቃል መገኘት፣ የተገኘውን ቃል መመገብ እንዲሁም በስሙ መጠራት ሐሴትና የልብ ደስታን ያስከትላል፡፡ የርሀብ ስሜት ያለው ሰው ምግብ ተመግቦ የበላው ሲዋሐደው ደስታ እንደሚሆነው ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ከመንፈስ ርሀባችን ጋር ሲገናኝ መፍትሔውም ከጥያቄያችን ጋር ሲዋሐድ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሐሴትና ሁኔታ ታግሎ የማይጥለው ደስታ ይሆንልናል፡፡ እንደዚሁ ሁሉ አካላዊ ቃል ክርስቶስን ፍጹም ስናምንበት እኛ በእርሱ እርሱም በእኛ በሚኖርበት ሁኔታ አሳባችን ከአሳቡ ፈቃዳችን ከፈቃዱ ጋር መዋሐድ ሲችል በጌታ ደስ መሰኘት ደግሞም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስን ሐሴት መለማመድ እንችላለን፡፡ (ፊል. 4÷4)

         ኤርምያስ ቀኑን ሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖበት ሕዝቡ ሁሉ ልክ እንደ አንድ ሰው ሆነው እያላገጡበት ልብን በሚሰብር ፈተና ውስጥ ሆኖ ሐሴትና የልብ ደስታ ነበረው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም እስር ቤት ሳለ ለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን መልእክት ሲጽፍ ሁል ጊዜ በጌታ ደስተኛ እንደነበረ፣ በተቃዋሚዎችም በአንዳች እንደማይደነግጥ ተናግሮአል፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው ለእርሱ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቆጥሮታል፡፡ ቃሉ በሙላት ሲኖርብን ሁኔታ የማያቆመው፣  መከራ የማያደበዝዘው፣ አእምሮንም የሚያልፍ የክርስቶስ ሰላም ይኖረናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ የእናንተ ሐሴትና የልብ ደስታ ማነው? ዕረፍትና እርካታችሁስ ከማን ዘንድ ነው?

ቃልህ ተገኝቶአል + እኔም በልቼዋለሁ + በስምህ ተጠርቻለሁ = ሐሴትና የልብ ደስታ
 
5. የዋዘኞች ጉባኤ

        ጉባኤ በአንድ ርእስ ለተወሰነ ዓላማ ሰዎች የሚያደርጉት መሰብሰብ ነው፡፡ መልካም ብቻ ሳይሆን ክፋትም ጉባኤ አለው፡፡ የእግዚአብሔር ማኅበር እንዳለ ሁሉ የሰይጣንም ማኅበር አለ፡፡ ከሥጋ አይን አንፃርም የበጎው ተጽእኖ ያሽቆለቆለ እንደሆነ እናያለን፡፡ እንዳለንበት ዘመን ለዋዛ የተመቸ ጊዜ የለም፡፡ ከሕፃን ጀምሮ ሽበት እስከደፉት አዛውንቶች ድረስ ዋዘኝነት ከፍተኛው ተስተናጋጅ ነው፡፡ ቁም ነገር በአስገዳጅ ሁኔታ ካልሆነ በቀር በውዴታ የሚተጋበት እጅግ ጥቂቱ ነው፡፡

        ነቢዩ ኤርሚያስ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ ሆኖ በአገለገለበት ዘመን የገዛ ፍላጎታቸውን የሚያገለግሉ ሐሰተኛ ነቢያት ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ቁጣን እንደሚያመጣ ሕዝቡንም እንደሚቀጣ ሲናገር እነርሱ ደግሞ ሰላም ነው አንዳችም ክፉ የለም በማለት ሕዝቡን በሥጋና በደም አሳብ የሚደልሉ ነበሩ፡፡ ሕዝቡም ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር በንስሐ እንዲመለሱበት የሰጣቸውን ጊዜ በዋዘኝነት ፈጅተውታል፡፡ በአዲስ ኪዳን የቤተክርስቲያን ቋሚ ፈተና የሐሰት ትምህርት አራማጆች ናቸው፡፡ የትምህርታቸውን ጠባይ ቅዱስ ጳውሎስ የእምነት ልጁ ለሚሆን ለጢሞቴዎስ ሲመክር “ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም” (1 ጢሞ. 1÷3) ይላል፡፡  የዋዘኞች ጉባኤ ጠባይ፡-

ሀ. ልዩ ትምህርት፡- የክርስቶስን ወንጌል የማጣመም ሂደት ልዩ ትምህርት ይባላል፡፡ ክርስትና በነቢያትና በሐዋርያት ትምህርት መሠረትነት የቆመ ነው፡፡ ከዚህ የመጣ ሥጋና ደምን ምክር ያደረገ ማንኛውም ትምህርት ልዩ ትምህርት ይባላል፡፡ ሐዋርያው “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” (ገላ. 1÷8) ብሏል፡፡ መልአክት እንኳን ከእግዚአብሔር ቃል መመሪያ ውጪ አንዳች ትምህርትን ቢያመጡ ከእርግማን በታች ናቸው፡፡ ሰው ታዲያ እንዴታ?

ለ. ተረት፡- ሌላው የስህተት ዋዘኛ ትምህርት ጠባይ ተረት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ስላለው ትምህርት ሲናገር “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ” (2 ጴጥ. 1÷16) ብሏል፡፡ እንዲህ ያለው የስህተት ትምህርት አደገኛነቱ በብልሃት የተፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ እኛ ልብስ በልካችን እንደምናሰፋ ሁሉ እውነቱን እንዲመስል ሆን ተብሎ በእውነቱ ልክ የተሰፋ ትምህርት እንደሆነ ዮሐንስ አፈወርቅ ይነግረናል፡፡ ተረት ለአንዳንዶቻችን የልጅ ማባበያና ማስተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ልጆችን በእግዚአብሔር ቃል ማስተኛት ብንችል ብዙ እናተርፍ ነበር፡፡ ብልሃተኛ ተረቶች እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት ተራ ተረቶች አይደሉም፡፡ ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ የማይችሉ ወደ መንፈሳዊ ብስለትና ከፍታ ለመድረስም እንቅፋት የሚሆኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚመስለውን ከሆነው፣ ሐሰቱንም ከመለኮት አሳብ መለየት አለበት፡፡

ሐ. የትውልዶች ታሪክ፡- ኑሮ የመተካካት ሂደት እንደመሆኑ ትውልድ ይመጣል ትውልድ ይሄዳል፡፡ ትላንት ታሪካችን ስለሆነ እንማርበታለን፡፡ እውነት በሚክድና በሚያስተባብል መንገድ ልንጠቀምበት ግን አይገባም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ታሪካቸው ከሰፈረላቸው ሰዎች ጋር የሚያገናኘን ትልቁ ነገር እግዚአብሔር በእነርሱ ሕይወት ለእኛ የገለጠው አሳቡና ፈቃዱ ነው፡፡ አይሁድ ኢየሱስን አባታችን አብርሃም ነው! ባሉት ጊዜ የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር ብሏቸዋል፡፡ (ዮሐ. 8÷39) ቁም ነገሩ ያለው የአብርሃም እምነትና ሥራ ላይ እንጂ ከእርሱ መወለዱ ላይ አልነበረም፡፡ ተወዳጆች ሆይ የክርስቲያን ዘር ነኝ ነው የምትሉት ወይስ ክርስቲያን ነኝ? ከማይጠፋው ዘር የተወለዱ ሁሉ መጨረሻ ወደሌለው የትውልዶች ታሪክ ፈቀቅ ይሉ ዘንድ አመፀኛ አይደሉም፡፡   

                     “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ

                     በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ

                     በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ” (መዝ. 1÷1)፡፡

6. በእጁ ፊት

         ነቢዩ ኤርምያስ የነበረበትን ሁኔታ ካስተዋልነው የወሰደው እርምጃ ምን ያህል እምነትን የሚጠይቅ እንደሆነ እንረዳለን፡፡  በአብላጫ አመለካከት ላይ አለመደገፍ የእውነት ባህርይ ነው፡፡ እውነት ተቀባይ ቢያጣ በራሱ መቆም ይችላል፡፡ ነቢዩ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ከመገኘት በእግዚአብሔር እጅ ፊት ለብቻው መቀመጥን መረጠ፡፡ ኅብረትን የሚያስንቅ ብቸኝነት ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ለእግዚአብሔር ብቻችንን ልንቆምለት እንደምንችል አልያም እንደማንችል ራሳችንን መመርመር አንደፍርም፡፡ የእግዚአብሔርን አሳብ ሳይሆን የራስና የሰው ስሜትን እየተከተሉ ጌታን ለማክበር መፍጨርጨር በእምነት ነገር ራስን ያለመቻል ጠባይ ነው፡፡

         ኤርምያስ ከእግዚአብሔር እጅ ጋር የማሳለፍን ጥቅም ጠንቅቆ የተገዳ ነቢይ ነው፡፡ ጌታ መከራ መስቀልን ከመቀበሉ አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱን “አሁን ታምናላችሁን? እነሆ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል አሁንም ደርሶአል ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም” (ዮሐ. 16÷32) በማለት ተናግሮአቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ወደሆነው ጥልቅ አሳብ እየዘለቅን ስንመጣ በሰው የመተው ወደ ጌታ የመጣበቃችን ነገር ያየለ ይሆናል፡፡ ካልተጠራራን አጠገባችን ሰብአዊ ሙቀት ካልተሰማን የሰው መቀስቀሻ ካልሞላን በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም የምንቸገር ጥቂት አይደለንም፡፡ ነገር ግን በተለይ በከፉብን ነገሮች መሐል ስንገኝ በእጁ ፊት መሆንን መልመድ ከዋዘኞች ይለየናል፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ እግዚአብሔርን ክንድህን ከአርያም ላክልን በማለት የለመኑት የእግዚአብሔር ክንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በመኃልየ መኃልይ 5÷4 ላይ ሙሽራይቱ ውዴ እጁን በቀዳዳ ሰደደ አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከ በማለት ትናገራለች፡፡ ይህም ከእጁ ጋር የተያያዘውን ታሪካችንን እንድናስብ ያደርገናል፡፡

       ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሁላችንም በደል በመስቀል ላይ እጅና እግሮቹ ችንካር እንዳለፈባቸው እናውቃለን፡፡ ጌታ ከትንሣኤው በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ያረጋጋው ችንካር ያለፈበትን እጁን በማሳየትና ሰላም ለእናንተ ይሁን በማለት ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ የምንባረክበትም የምንገሰጽበትም እጅ ይህ ነው፡፡ በጎ ስጦታ ፍጹም በረከት ሁሉ ከዚህ እጅ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ስለማይነገር ስጦታው ማመስገን ከፈለጋችሁ እዚህ እጅ ፊት ሁኑ፡፡  ሰላማችንና ዕረፍታችን ስኬታችንና እድገታችን እጁ ውስጥ ነው፡፡ ለጥያቄያችን መልስ፣ ለእንቆቅልሻችን ፍቺ፣ ለሕመማችን ፈውስ፣ ለድካማችን ውርዝውና እጁ ፊት መሆን ነው፡፡ የሰው ቃል የከበዳችሁ፣ የወዳጅ መክዳት ያሳዘናችሁ፣ ኃጢአት ሰላም የነሣችሁ፣ ዕረፍትና ደስታ የሸሻችሁ ኑ እዚህ እጅ ፊት ተቀመጡ፡፡ ቂማችሁ ይታጠባል፣ ሸክማችሁ ይቀላል፣ እርካታችሁ ይታወጃል፡፡ በእጁ ፊት እንደመሆን ያለ መጽናናት፣ መገሠጽ፣ ማረፍ የት ይኖራል?  




Tuesday, May 1, 2012

በእጁ ፊት



“ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ አቤቱ÷ የሠራዊት አምላክ ሆይ÷ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሴትና የልብ ደስታ ሆነኝ፡፡ በዋዘኞችና በደስተኞች ጉባኤ አልተቀመጥሁም ቁጣን ሞልተህብኛልና በእጅህ ፊት ለብቻዬ ተቀመጥሁ” (ትን. ኤር. 15÷16)፡፡

        በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከተጠቀመባቸው ታላላቅ ነቢያት አንዱ ኤርሚያስ ነው፡፡ እንደ ስሙ ትርጓሜ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ከፍ ከፍ ያደረገው ሰው ነው፡፡ በትንቢቱም ላይ ያለው ጥቅል መልእክት እግዚአብሔር ታላቅና ቅዱስ ነውና ሕዝቡ ከተሳሳተ መንገዳቸው ተመልሰው በእውነት ልብ እንጂ በሐሰት እንዳያመልኩት ማስረዳት ነው፡፡ በፍፁም ልብ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ እንደማያጡትም ይናገራል፡፡ ነቢዩ በዘመኑ የእግዚአብሔርን አሳብ ያገለገለው በብዙ ሠልፍና ተግዳሮት መሐል ነበር፡፡

        የሕዝቡ መቅበዝበዝ ደግሞም ወደ መድኃኒታቸው ዘወር ለማለት ፈቃደኝነት አለማሳየታቸው አልፎም ተርፎ በነቢዩ ሕይወት ላይ መነሣሣታቸው አገልግሎቱን የእንባ አድርጎበት ነበር፡፡ ታዲያ በአደባባይ በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ የእግዚአብሔርን ቃል ሲናገር ደስ አያሰኛቸውም ደግሞም ለስድብ ሆኖባቸው ነበር፡፡ ባል ከሚስቱ ሽማግሌውም ከጎበዙ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው በአንድነት እግዚአብሔርን ተቃውመዋል፡፡ ነቢዩንም የሰላሙ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ እንክሰሰው እናስፈርድበት ይሉ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከይቅርታ እስኪደክም፣ ኤርምያስም እግዚአብሔርን አታለልኸኝ ብሎ ድፍረትን እስኪናገር፣ ኢየሩሳሌም የሚራራላትን ስለ ደኅንነቷም ይጠየቅ ዘንድ ፈቀቅ የሚለውን እስከማታውቅ ድረስ የቆንጆነቷን ጌጥ የሙሽርነቷን ዝርግፍ ጌጥ ረሳች፡፡ (ኤር. 2÷32) እለት እለት በነቢዩ ወደ እነርሱ ለሚመጣው የእውነት ቃል እንቢተኝነታቸውን ገለጹ፡፡ ነቢዩ ቀኑን ሁሉ ግፍና ጥፋት እያለ ይጮኻል ነገር ግን ቃሉ ስድብና ዋዛ ሆኖበት፣  ሕዝቡም ተሳልቆና አላግጦበት በተመለሰ ጊዜ በእጁ ፊት ለብቻው ቁጭ ብሎ የተገኘውን ቃል በላ፡፡ ከላይ የተነሣንበት ክፍል የተጻፈው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡

       በእውነት ሐሴት የማያደርግ ደግሞም ዋዛ ያሳረፈው ሕዝብ ምንኛ ምስኪን ነው? ከእግዚአብሔር ጥበብ ይልቅ የሰውና ምድራዊ ብልሐት የገዛው ወገን እንዴት ተላላ ነው፡፡ ነቢዩ በእጁ ፊት ለብቻው ቁጭ ብሎ ያደረገውን ከአዲስ ኪዳን አሳብ ጋር በማዛመድ በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን፡፡  

1. ቃልህ ተገኝቶአል

       ሰማይና ምድር የጸኑበት ደግሞም የሚያልፉበት የበረታ ቃል የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ የተገኘ ነገር የማይገኝበትም ጊዜ እንዳለ እንረዳለን፡፡  “የእግዚአብሔርን ቃል ለመሻት ይርዋርዋጣሉ አያገኙትምም” (አሞ. 8÷12) የሚለው የነቢዩ ቃል ይህንን ያረጋግጥልናል፡፡ ለተገለጠው የእግዚአብሔር አሳብ ፈቃደኝነታችንን ካላሳየን በተከደነ ሰዓት መንከራተታችን ግልጥ ነው፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ውድቀት በበረከተበት ሰው ሁሉ እንደገዛ ፈቃዱ በሚሄድበት ዘመን የእግዚአብሔር ቃል እንደተገኘ ይነግረናል፡፡ ሕዝቡ በተሳሳተ መንገድ እየሄደ ትክክለኛው ቃል አለመቅረቱ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ጀርባውን ሰጥቶ ሳለ ቃሉ መገኘቱ የእግዚአብሔር ጸጋ ምን ያህል ቻይ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ሕዝቡ ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ለተገለጠው ቃል የነበራቸው ምላሽ የሚያሳዝን ነበር፡፡

         ቃል ሁለት አይነት አተረጓጎም አለው፡፡ የመጀመሪያው ሬማ የሚለው ሲሆን የእግዚአብሔር መንፈስ ፈቃዱን ለመግለጽ ወደ ሕዝቡ የሚያደርሰውን ድምጽና መልእክት የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህም ነቢዩ ኤርምያስ ተገኝቶአል ያለውን ቃል ያስገነዝበናል፡፡ ሁለተኛው ሎጎስ የሚለው ሲሆን ይህም አካላዊ ቃል ክርስቶስን የሚገልጥ ነው፡፡ (ዮሐ. 1÷1) ቃል ሥጋ እንደሆነ በሥጋና በደም እንደተካፈለ በምስሉም እንደ ሰው እንደተገኘ የምንረዳበትም ነው፡፡ ስለዚህ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

2. እኔም በልቼዋለሁ

       ነቢዩ ለተገኘው የእግዚአብሔር ቃል የሰጠውን ፈጣንና ቀጥተኛ ምላሽ የሚገልጽ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ከተብራራባቸው ነገሮች አንዱ ምግብ (እንጀራ) የሚለው ነው፡፡ (ማቴ. 4÷4) ሰው ሥጋው ያለ መብል እንደማይጸና ሁሉ ያለ እግዚአብሔር ቃል እንጀራነትም የሰው መንፈስ ሕያው ሊሆን አይችል፡፡ የሥጋ መብል ሥጋዊ እንደሚያደርግ የመንፈስ እንጀራም መንፈሳዊ ያደርጋል፡፡ በልቼዋለሁ የሚለው አገላለጽ ቃሉን ማጣጣምንና ከራስ ጋራ ማዋሀድን ይገልጣል፡፡

        ኤርምያስ ከእግዚአብሔር አፍ የመጣውን የተገኘውን ቃል በላ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ራሱ እኔ እያለ ከተናገራቸው ሰባት መገለጫዎች አንዱ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁል ጊዜ ከቶ አይጠማም፡፡ ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋሁ” (ዮሐ. 6÷35) የሚለው ነው፡፡ በሰው መካከል ተገኝቶ በሥጋና በደም የተካፈለ አካላዊ ቃል ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ እናምንበትና እናመልከው ዘንድ ኃጢአተኛ እንደሆን ደግሞም መድኃኒት እንደሚያስፈልገን ለምናምን ሁሉ የእግዚአህሔር ልጅ የእንዲሁ ስጦታ ሆና ተገልጧል፡፡ (ዮሐ. 3÷16) ተወዳጆች ሆይ ቃሉ ተገኝቶአል፡፡ እኛ ግን በልተነዋል ወይ?

        በእርሱ የሚያምን የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር የሚወደውን ልጁን አሳልፎ ለሞት ሰጥቶአል፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ጠላቶቹ ሳለን ለወዳጅ ከመስጠት በሚበልጥ ፍቅር እስከ መስቀል ሞት ታዝዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስም የመዳናችንን የምስራች በአመነው ልብ ውጥ በዘላለም ዋስትና አትሞአል፡፡ ነቢዩ ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ እንዳለ በእኛም ዘንድ እንዲሁ እንዲሆን ጌታ ይርዳን፡፡
- ይቀጥላል -