Friday, May 4, 2012

በእጁ ፊት (ካለፈው የቀጠለ)


                        
        ስለ እግዚአብሔር ቃል መገኘትና የተገኘውን ቃል ስለ መብላት ነቢዩ ኤርምያስ ከዋዘኞችና ኃጢአትን ምንጭ ባደረገ ደስታ ካረፉ ሕዝቦች መሐል ተለይቶ ብቻውን በእግዚአብሔር እጅ ፊት በመሆን የወሰዳቸውን መንፈሳዊ እርምጃዎች በመዘርዘር ሁለቱን በመጠኑ ለማየት ሞክረናል፡፡ ቀሪዎቹንም በእግዚአብሔር እርዳታ በመንፈሱም ኃይል እንመለከታለን፡፡

3. በስምህ ተጠርቻለሁ

          በስሙ መጠራት ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖር የሚችለውን የጠበቀ ኅብረት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤል አባት እንደሆነም ይገልፃል፡፡ ነቢዩ ሕይወቱ ለእግዚአብሔር የተሰጠ እንደመሆኑ የዘላለም አምባ በሆነው ጌታ ላይ የታመነ አገልጋይ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ነቢዩ የአንተ ገንዘብ ነኝ ለማለት የተጠቀመበት ንግግር ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ላለነው ክርስቲያኖች ደግሞ በስሙ መጠራት የከበረና ከፍ ያለ ትርጉም አለው፡፡ እግዚአብሔርን አባት ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ የተቀበልነው በእግዚአብሔርም ልጆቼ ተብለን የተጠራነው በክርስቶስ ኢየሱስ የከበረ ደም ፈሳሽነት ነው፡፡ የተጠራንበት ስም ከስም ሁሉ በላይ ነው፡፡ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ስም ነው፡፡ ከምድርም በታች ሁሉ ይንበረከኩበት ዘንድ የተሰጠን ስም ክርስቶስ ኢየሱስ የሚለው ነው፡፡ (ፊል. 2÷9-11)

        በክርስቶስ ክርስቲያን መሆናችን እግዚአብሔርን አባት ብለን የምጠራበት መንፈሳዊ መብታችን ነው፡፡ ልጆች ከሆንን መጠሪያችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ተጠሪነታችንም በመልኩ እንደ ምሳሌው ለፈጠረን ከውድቀት በኋላም በአንድ ልጁ የመስቀል ሞት ላዳነን ጌታ ነው፡፡ (ሮሜ. 1÷6) ስሙ ሁለንተናችን ነው፡፡ ቃላችንም ተግባራችንም ክብረት የሚያገኘው በዚህ ስም ስንጠራና ሁሉን በስሙ ስናደርገው ነው፡፡ “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” (ቆላ. 3÷17)፡፡

4. ሐሴትና የልብ ደስታ

       የእግዚአብሔር ቃል መገኘት፣ የተገኘውን ቃል መመገብ እንዲሁም በስሙ መጠራት ሐሴትና የልብ ደስታን ያስከትላል፡፡ የርሀብ ስሜት ያለው ሰው ምግብ ተመግቦ የበላው ሲዋሐደው ደስታ እንደሚሆነው ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ከመንፈስ ርሀባችን ጋር ሲገናኝ መፍትሔውም ከጥያቄያችን ጋር ሲዋሐድ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሐሴትና ሁኔታ ታግሎ የማይጥለው ደስታ ይሆንልናል፡፡ እንደዚሁ ሁሉ አካላዊ ቃል ክርስቶስን ፍጹም ስናምንበት እኛ በእርሱ እርሱም በእኛ በሚኖርበት ሁኔታ አሳባችን ከአሳቡ ፈቃዳችን ከፈቃዱ ጋር መዋሐድ ሲችል በጌታ ደስ መሰኘት ደግሞም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስን ሐሴት መለማመድ እንችላለን፡፡ (ፊል. 4÷4)

         ኤርምያስ ቀኑን ሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖበት ሕዝቡ ሁሉ ልክ እንደ አንድ ሰው ሆነው እያላገጡበት ልብን በሚሰብር ፈተና ውስጥ ሆኖ ሐሴትና የልብ ደስታ ነበረው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም እስር ቤት ሳለ ለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን መልእክት ሲጽፍ ሁል ጊዜ በጌታ ደስተኛ እንደነበረ፣ በተቃዋሚዎችም በአንዳች እንደማይደነግጥ ተናግሮአል፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው ለእርሱ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቆጥሮታል፡፡ ቃሉ በሙላት ሲኖርብን ሁኔታ የማያቆመው፣  መከራ የማያደበዝዘው፣ አእምሮንም የሚያልፍ የክርስቶስ ሰላም ይኖረናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ የእናንተ ሐሴትና የልብ ደስታ ማነው? ዕረፍትና እርካታችሁስ ከማን ዘንድ ነው?

ቃልህ ተገኝቶአል + እኔም በልቼዋለሁ + በስምህ ተጠርቻለሁ = ሐሴትና የልብ ደስታ
 
5. የዋዘኞች ጉባኤ

        ጉባኤ በአንድ ርእስ ለተወሰነ ዓላማ ሰዎች የሚያደርጉት መሰብሰብ ነው፡፡ መልካም ብቻ ሳይሆን ክፋትም ጉባኤ አለው፡፡ የእግዚአብሔር ማኅበር እንዳለ ሁሉ የሰይጣንም ማኅበር አለ፡፡ ከሥጋ አይን አንፃርም የበጎው ተጽእኖ ያሽቆለቆለ እንደሆነ እናያለን፡፡ እንዳለንበት ዘመን ለዋዛ የተመቸ ጊዜ የለም፡፡ ከሕፃን ጀምሮ ሽበት እስከደፉት አዛውንቶች ድረስ ዋዘኝነት ከፍተኛው ተስተናጋጅ ነው፡፡ ቁም ነገር በአስገዳጅ ሁኔታ ካልሆነ በቀር በውዴታ የሚተጋበት እጅግ ጥቂቱ ነው፡፡

        ነቢዩ ኤርሚያስ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ ሆኖ በአገለገለበት ዘመን የገዛ ፍላጎታቸውን የሚያገለግሉ ሐሰተኛ ነቢያት ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ቁጣን እንደሚያመጣ ሕዝቡንም እንደሚቀጣ ሲናገር እነርሱ ደግሞ ሰላም ነው አንዳችም ክፉ የለም በማለት ሕዝቡን በሥጋና በደም አሳብ የሚደልሉ ነበሩ፡፡ ሕዝቡም ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር በንስሐ እንዲመለሱበት የሰጣቸውን ጊዜ በዋዘኝነት ፈጅተውታል፡፡ በአዲስ ኪዳን የቤተክርስቲያን ቋሚ ፈተና የሐሰት ትምህርት አራማጆች ናቸው፡፡ የትምህርታቸውን ጠባይ ቅዱስ ጳውሎስ የእምነት ልጁ ለሚሆን ለጢሞቴዎስ ሲመክር “ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም” (1 ጢሞ. 1÷3) ይላል፡፡  የዋዘኞች ጉባኤ ጠባይ፡-

ሀ. ልዩ ትምህርት፡- የክርስቶስን ወንጌል የማጣመም ሂደት ልዩ ትምህርት ይባላል፡፡ ክርስትና በነቢያትና በሐዋርያት ትምህርት መሠረትነት የቆመ ነው፡፡ ከዚህ የመጣ ሥጋና ደምን ምክር ያደረገ ማንኛውም ትምህርት ልዩ ትምህርት ይባላል፡፡ ሐዋርያው “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” (ገላ. 1÷8) ብሏል፡፡ መልአክት እንኳን ከእግዚአብሔር ቃል መመሪያ ውጪ አንዳች ትምህርትን ቢያመጡ ከእርግማን በታች ናቸው፡፡ ሰው ታዲያ እንዴታ?

ለ. ተረት፡- ሌላው የስህተት ዋዘኛ ትምህርት ጠባይ ተረት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ስላለው ትምህርት ሲናገር “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ” (2 ጴጥ. 1÷16) ብሏል፡፡ እንዲህ ያለው የስህተት ትምህርት አደገኛነቱ በብልሃት የተፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ እኛ ልብስ በልካችን እንደምናሰፋ ሁሉ እውነቱን እንዲመስል ሆን ተብሎ በእውነቱ ልክ የተሰፋ ትምህርት እንደሆነ ዮሐንስ አፈወርቅ ይነግረናል፡፡ ተረት ለአንዳንዶቻችን የልጅ ማባበያና ማስተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ልጆችን በእግዚአብሔር ቃል ማስተኛት ብንችል ብዙ እናተርፍ ነበር፡፡ ብልሃተኛ ተረቶች እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት ተራ ተረቶች አይደሉም፡፡ ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ የማይችሉ ወደ መንፈሳዊ ብስለትና ከፍታ ለመድረስም እንቅፋት የሚሆኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚመስለውን ከሆነው፣ ሐሰቱንም ከመለኮት አሳብ መለየት አለበት፡፡

ሐ. የትውልዶች ታሪክ፡- ኑሮ የመተካካት ሂደት እንደመሆኑ ትውልድ ይመጣል ትውልድ ይሄዳል፡፡ ትላንት ታሪካችን ስለሆነ እንማርበታለን፡፡ እውነት በሚክድና በሚያስተባብል መንገድ ልንጠቀምበት ግን አይገባም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ታሪካቸው ከሰፈረላቸው ሰዎች ጋር የሚያገናኘን ትልቁ ነገር እግዚአብሔር በእነርሱ ሕይወት ለእኛ የገለጠው አሳቡና ፈቃዱ ነው፡፡ አይሁድ ኢየሱስን አባታችን አብርሃም ነው! ባሉት ጊዜ የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር ብሏቸዋል፡፡ (ዮሐ. 8÷39) ቁም ነገሩ ያለው የአብርሃም እምነትና ሥራ ላይ እንጂ ከእርሱ መወለዱ ላይ አልነበረም፡፡ ተወዳጆች ሆይ የክርስቲያን ዘር ነኝ ነው የምትሉት ወይስ ክርስቲያን ነኝ? ከማይጠፋው ዘር የተወለዱ ሁሉ መጨረሻ ወደሌለው የትውልዶች ታሪክ ፈቀቅ ይሉ ዘንድ አመፀኛ አይደሉም፡፡   

                     “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ

                     በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ

                     በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ” (መዝ. 1÷1)፡፡

6. በእጁ ፊት

         ነቢዩ ኤርምያስ የነበረበትን ሁኔታ ካስተዋልነው የወሰደው እርምጃ ምን ያህል እምነትን የሚጠይቅ እንደሆነ እንረዳለን፡፡  በአብላጫ አመለካከት ላይ አለመደገፍ የእውነት ባህርይ ነው፡፡ እውነት ተቀባይ ቢያጣ በራሱ መቆም ይችላል፡፡ ነቢዩ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ከመገኘት በእግዚአብሔር እጅ ፊት ለብቻው መቀመጥን መረጠ፡፡ ኅብረትን የሚያስንቅ ብቸኝነት ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ለእግዚአብሔር ብቻችንን ልንቆምለት እንደምንችል አልያም እንደማንችል ራሳችንን መመርመር አንደፍርም፡፡ የእግዚአብሔርን አሳብ ሳይሆን የራስና የሰው ስሜትን እየተከተሉ ጌታን ለማክበር መፍጨርጨር በእምነት ነገር ራስን ያለመቻል ጠባይ ነው፡፡

         ኤርምያስ ከእግዚአብሔር እጅ ጋር የማሳለፍን ጥቅም ጠንቅቆ የተገዳ ነቢይ ነው፡፡ ጌታ መከራ መስቀልን ከመቀበሉ አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱን “አሁን ታምናላችሁን? እነሆ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል አሁንም ደርሶአል ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም” (ዮሐ. 16÷32) በማለት ተናግሮአቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ወደሆነው ጥልቅ አሳብ እየዘለቅን ስንመጣ በሰው የመተው ወደ ጌታ የመጣበቃችን ነገር ያየለ ይሆናል፡፡ ካልተጠራራን አጠገባችን ሰብአዊ ሙቀት ካልተሰማን የሰው መቀስቀሻ ካልሞላን በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም የምንቸገር ጥቂት አይደለንም፡፡ ነገር ግን በተለይ በከፉብን ነገሮች መሐል ስንገኝ በእጁ ፊት መሆንን መልመድ ከዋዘኞች ይለየናል፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ እግዚአብሔርን ክንድህን ከአርያም ላክልን በማለት የለመኑት የእግዚአብሔር ክንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በመኃልየ መኃልይ 5÷4 ላይ ሙሽራይቱ ውዴ እጁን በቀዳዳ ሰደደ አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከ በማለት ትናገራለች፡፡ ይህም ከእጁ ጋር የተያያዘውን ታሪካችንን እንድናስብ ያደርገናል፡፡

       ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሁላችንም በደል በመስቀል ላይ እጅና እግሮቹ ችንካር እንዳለፈባቸው እናውቃለን፡፡ ጌታ ከትንሣኤው በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ያረጋጋው ችንካር ያለፈበትን እጁን በማሳየትና ሰላም ለእናንተ ይሁን በማለት ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ የምንባረክበትም የምንገሰጽበትም እጅ ይህ ነው፡፡ በጎ ስጦታ ፍጹም በረከት ሁሉ ከዚህ እጅ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ስለማይነገር ስጦታው ማመስገን ከፈለጋችሁ እዚህ እጅ ፊት ሁኑ፡፡  ሰላማችንና ዕረፍታችን ስኬታችንና እድገታችን እጁ ውስጥ ነው፡፡ ለጥያቄያችን መልስ፣ ለእንቆቅልሻችን ፍቺ፣ ለሕመማችን ፈውስ፣ ለድካማችን ውርዝውና እጁ ፊት መሆን ነው፡፡ የሰው ቃል የከበዳችሁ፣ የወዳጅ መክዳት ያሳዘናችሁ፣ ኃጢአት ሰላም የነሣችሁ፣ ዕረፍትና ደስታ የሸሻችሁ ኑ እዚህ እጅ ፊት ተቀመጡ፡፡ ቂማችሁ ይታጠባል፣ ሸክማችሁ ይቀላል፣ እርካታችሁ ይታወጃል፡፡ በእጁ ፊት እንደመሆን ያለ መጽናናት፣ መገሠጽ፣ ማረፍ የት ይኖራል?  




2 comments:

  1. Be eju fit yale ereft ena metsinanat beyetim yelem. Shekimachinin hulu be ersu lay tilen endinarf wede tsegaw zufan be eminet enkireb!

    ReplyDelete
  2. Haset ena ye lib destachin behone be geta eji fit be eminet yeminkerbibetin mastewal yadlen!

    ReplyDelete