Friday, May 11, 2012

ልበ ሰፊ (ካለፈው የቀጠለ)



“ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገቡ እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፡-ነገሩ እንዲሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” (የሐዋ. 17÷10)፡፡

          የቤርያ ከተማ በምስራቹ ወንጌል እንድትጎበኝ ምክንያት የሆነው በተሰሎንቄ ከተማ በጳውሎስና በሲላስ ላይ የደረሰው መገፋት ነበር፡፡ በእኛ መሰደድ ውስጥ ለሌሎች ሕይወት ማግኘት ሲሆንላቸው ማየት ድካማችንን እንዳናስብ የሚያደርግ በቂ ምክንያታችን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የተሰሎንቄን ከተማ በዋስ ለቆ ከወጣ በኋላ የተሰደደባት ቤርያ በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊ የሆኑ ሰዎች የነበሩባት ከተማ ናት፡፡ ዮሴፍ ወንድሞቹ ከአባቱ ቤት ቢያሳድዱት እግዚአብሔር ለግብፅ ምድር እንጀራ አድርጎታል፡፡ እንደ እግዚአብሔር አሳብ ለተጠሩና ጌታን ለሚወዱ ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡ (ሮሜ. 8÷28) እግዚአብሔር በሌሊትም ድምፁን በመስማት የሚያምኑ አሉት፡፡ ቃሉ በሚነገርበት ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት ተተርጉመው ሰዎች በቀላሉ እንዲደርሳቸው በተመቻቸበት በዚህ ዘመን እግዚአብሔርን በቀን መፈለግ ጭንቅ ሆኖአል፡፡ የቤርያ ሰዎች የሚደነቀውን ብርሃን የተገናኙት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ጳውሎስና ሲላስም የከበረውን የምስራች የተናገሩት በወጀብና በአውሎ መሐል ሆነው ነው፡፡

          የቤርያን ሰዎች ልበ ሰፊ ስላስባላቸው ነገር ማወቅ  ለእኛ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን፡፡

ሀ. ማመዛዘን፡-

          “ነገሩ እንዲሁ ይሆንን?” የሚለው አገላለጽ ችኩልነት ለሚያጠቃው ኑሮአችን ጠንከር ያለ ትምህርት አለው፡፡ ከምንፈተንባቸው ነገሮች መካከል ለሌሎች አሳብ ትኩረት አለመስጠትና ሊሆን የሚችልበትን የበዛ ጎን አለማጤን በተደጋጋሚ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን በመንፈሳዊው መንገድ ብቻ ሳይሆን የምድር በሆነው ኑሮአችንም ማመዛዘን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በጊዜው ባለማመዛዘናችን አልፎ የቆጨን ነገር ምን ያህል የበዛ ነው? የቤርያ ሰዎች ጳውሎስ ስለ ሰበከ ሲላስ ስለተናገረ ሳይሆን ከእነርሱ ስለወጣው ቃል ትኩረት ሰጥተው ነበር፡፡

          ለብዙ ጊዜ በጉባኤ ላይ ሲሰበክ ፊቷን በነጠላ ተሸፋፍና ትሰማ የነበረች እህት ከብዙ ጊዜ በኋላ ይህንን ለምን እንደምታደርግ ስትናገር “ለማሳት እንዳልገለጥና ለመሳት እንዳልጋለጥ ይልቁንም በልቤ ጆሮ ማድመጥን ማመዛዘንን ከዚያም መቀበልን እንድችል ነው” በማለት የተናገረችው ልብን ይነካ ነበር፡፡ የሰባኪ መልክና የዘማሪ ድምጽ ገምግመው ስለሚመለሱ ወገኖች እንደነቃለን፡፡ አጭር ተናገረ ረዥም፣ ቀጭን ተናገረ ወፍራም፣ ቀይ ተናገረ ጥቁር የቤርያ ሰዎች መስማታቸው በማመዛዘን ነበር፡፡

         የእግዚአብሔርን ቃል በምንሰማበት ጊዜ እውነት ይሆንን? በማለት የሰውን አሳብ ከእግዚአብሔር አሳብ፣ የሥጋና የደም ምክርን ከመንፈሳዊው ቃል፣ የምድር የሆነውን ዘላለማዊ ከሆነው መለየት አለብን፡፡
    

ለ. መጻሕፍትን መመርመር፡-

        ሌላው የቤርያን ሰዎች ልበ ሰፊ ያስባላቸው ጉዳይ ዕለት ዕለት መጻሕፍትን መመርመራቸው ነው፡፡ ትላንት በልቻለሁ ብለን ዛሬ ከመብላት አልተከለከልንም፡፡ ምክንያቱም በሥጋ ልንቆም የምንችልበት ኃይል ያለው ዕለት ዕለት ለሰውነታችን ባሕርይ ተስማሚ የሆነውን ምግብ በመመገብ ነው፡፡ እንዲሁ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ዕለት ዕለት የሚኖረን የጠበቀ ግንኙነት ነፍሳችን ልትቆም የምትችልበትን ሁኔታ ይወስናል፡፡ የቤርያ ሰዎች በሚዛናዊነት የሰሙትን ቃል ከመጻሕፍት ጋር ያመሳክሩ ነበር፡፡ ስለ ሂደቱም ወንጌላዊው ሉቃስ ሲነግረም “እየመረመሩ” ይለናል፡፡ መመርመር ከማንበብ የዘለለ ትርጉም አለው፡፡ ማንበብ ፊደል ሲሆን መመርመር ግን ትርጉም ነው፡፡

        በእንግሊዝ አገር የታሪክ አዋቂና ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የነበረው ጆን ሴልደን (1584-1654) በአንባቢነቱና በትምህርቱ የታወቀ ሰው ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ለሞት በሚያጣጥርበት ወቅት “ከፀሐይ በታች የሚገኘውን አብዛኛውን ትምህርት የቻልኩትን ያህል ቀስሜአለሁ፡፡ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተጻፉ አያሌ መጻሕፍትን አንብቤአለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ጥረት ውስጥ ግን ነፍሴን ላሳርፍ የምችልበት ክፍል አላገኘሁም፡፡ ነገር ግን በዚህ ሰዓት ለነፍሴ ዕረፍት ሊሆነኝ የሚችለው ሰዎችን ሁሉ ሊያድን የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተገለጠ የሚመሰክረው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ብቻ ነው” በማለት ተናግሮአል፡፡ የሳይንስና የታሪክ፣ የፍልስፍናና የፖለቲካ ሰዎች ለዚህ ዓለም ጥቅም መጽሐፍ ቅዱስን ሲመረምሩ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፍለናል የምንለው ግን እንደ ባላንጣ ከቃሉ መሸሻችን አስገራሚ ነው፡፡

      ሰው ሊዋሽ ደግሞም ቃሉን እንደ ግል አመለካከቱ ሊናገር ይችላል፡፡ ቅዱስ ቃሉ ምን ይላል ማለት ግን ከእኛ ይጠበቃል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ያለው ቃል እንደመሆኑ የተናገረንን የሚያስፈጽምበት ኃይል አብሮት አለ፡፡ ስለ ፈውስ ከተናገራችሁ ይፈውሳል፣ ስለ ለውጥ ከተናገራችሁም ይለውጣል፣ ስለ ድል ከተናገራችሁም በወደዳችሁ በእርሱ ከአሸናፊዎች ትበልጣላችሁ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው በዚህ የሥልጣን ቃል ማመንና ዕለት ዕለት እግዚአብሔር በእዚህ ውስጥ ለእኛ ያለውን አሳብና ፈቃድ መመርመር ነው፡፡

ሐ. በሙሉ ፈቃድ መቀበል፡-

        የቤርያ ሰዎች ከተነገረው ቃል ጋር የነበራቸውን መስማማት የሚያስረዳን አገላለጽ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ፈቃዳችን ለብዙ ነገር የተከፋፈለ ነው፡፡ ልዩ ልዩ ለሆኑ ነገሮች ፈቃደኝነታችንን እናሳያለን፡፡ ይህም ሕይወታችንን ጉልበት ያሳጣታል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርነው እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን ፈቃዱን ለማድረግ ነው፡፡ (ኤፌ. 2÷10) እግዚአብሔር ሙሉ ትኩረታችንን፣ ሙሉ መውደዳችንን፣ ሙሉ መገዛታችንን ይፈልጋል፡፡ ከእርሱ የሆነውን ነገር ስንቀበልም በሙሉ ፈቃድ መሆን አለበት፡፡ የቤርያ ሰዎች አመዛዝነው የሰሙትና ከመጻሕፍት ጋር ያመሳከሩት ቃል እውነት ባይሆን ኖሮስ? ብለን እናስብ፡፡ በእርግጥም ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቃወሙት ተብሎ ይፃፍልን ነበር፡፡

         ለእግዚአብሔር ሙሉ ነገራችንን መስጠት መለማመድ አለብን፡፡ ከእርሱ የሰሰትነውና ያስቀረነው ነገር የእድሜ ልክ ፈተና ከመሆን አያልፍም፡፡ በሁለት ልብ ማንከስ በሁለት አሳብ መጓዝ ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡ የቤርያ ሰዎች መቀበላቸው የይምሰል አልያም ተራ አልነበረም ይልቁንም በሙሉ ፈቃድ ነበር፡፡ እውነትን በሙሉ ፈቃድ መቀበልን ስንለምድ የተቀበልነው እውነት በሙሉ ኃይሉ ይሠራብናል፡፡ ለጌታ አሳብ ሙሉ መገዛታችንን እናሳይ ዘንድ ጸጋ ይብዛልን፡፡

2 comments:

  1. "Ewinetegna Amlak yehonk anten yelakewinm Eyesus kirstosin yawku zend yihchi yezelalem hiwot nat!".....Amen tsega yibzalin!

    ReplyDelete
  2. Egziabher amlak kidus kalun yeminastewilbetin libona lehulachinm yadlen!

    ReplyDelete