Thursday, December 1, 2011

የሚዛናዊነት ያለህ (ክፍል ሁለት)



ብርታትና ድካም፣ ውድቀትና ጽናትን ለሚያፈራርቀው የሰው ልጅ ሚዛናዊ የሆነ ቃል በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በጎ ጎኑን የምናደንቅለት ሰው ደካማ ጎን፣ ስለ መጥፎ ጎኑ የምንነቅፈው ሰው መልካም ጎን እንዳለው መረዳትም ብሩክ የሆነ አስተዋይነት ነው፡፡ አንድ አባት ሲመክሩ፡- “ልጄ ብዙ መልካም ነገር እንዳለህ አውቃለሁ፡፡ ግን ይህችን መጥፎ አስተካክል” አሉት፡፡ ሚዛናዊነት በጎደለው አቋም ምንምና ማንንም አንለውጥም፡፡ ዛሬ ለምድራችን መከራ፣ የማያቋርጥ ስቃይ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ሚዛናዊነት የጎደለው አመለካከት፣ ንግግርና ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ሚዛናዊ ሰው አጥርቶ የሚያይ እውነተኛ፣ ለፍርድ የማይቸኩል ትዕግስተኛ፣ ሰውንም በሆነው የሚቀበል ጥበበኛ ነው፡፡
አንድ ዙር እስኪቀርህ ድረስ ሩጫውን እየመራህ ሳለ ያጨበጭብልህ የነበረ ሕዝብ መመራት ስትጀምር ቦታውን እየተወ ቢወጣ ምን ይሰማሃል? በእርግጥ ዓለም ከዚህ የተለየ ምንም ለማድረግ ፍላጎትም ሆነ አቅም የላትም፡፡ ብዙ ሠርተው የነበሩ ምንም እንዳልሠሩ፣ ብዙ ነገር ታግለው ያቀኑ በቦታው እንዳልነበሩ ሲቆጠሩ ልባችን ታዝቧል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን እምነት አለን በሚሉ መካከል ሚዛናዊነት ሲጠፋ ማየት ያሳፍራል፡፡
በአብዛኛው ቢወራልንና ብናወራ የምንወደው በኑሮ የበረታንበን፣ ታግለን የጣልንበትን፣ ተናግረን የረታንበትን ነገር ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ቆመው አይደለም ሞተው እንኳን ስለ ድክመታቸው እንዲወራ በማይፈልጉ ሰዎች ምክንያት በየቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ የሚነበበው የሕይወት ታሪክ የጥቂት እውነትና የብዙ ውሸት ድምር ውጤት የሚሆነው፡፡ የፍቅር ሰው ግን የእውነትና የማመዛዘንን በረከት የተረዳ ነው፡፡
ሕይወት የደስታና ሐዘን፣ የመልካም ዜናና የክፉ ወሬ፣ የሚያረኩ አጋጣሚዎችና ነፍስ የሚያስቱ መሰናክሎች አስደናቂ ቅይጥ ናት፡፡ በመሆኑም አስቀድመን ይህንን እውነታ በተቀበልነው መጠን በተሻለ መልኩ ሕይወትን በጥበብና በማስተዋል መጋጠም እንችላለን፡፡ በመጨነቅ፣ በማዘንና በቅሬታ ለማሳለፍ ሕይወት በጣም አጭር ናትና ጨክነን ከእውነት ጋር መስማማት ይኖርብናል፡፡
ዛሬ ሁሉም ነገር ለመደሰት ሳይሆን ለመማረር፣ ለመቆም ሳይሆን ለመውደቀ፣ ለማረፍ ሳይሆን ለመቅበዝበዝ ብቻ ምክንያት እስኪመስል፤ ኑሮም ከሞት እንጉርጉሮ የከፋ፣ከነፋስ ሽውታ የሳሳ፣ ከማዕበል ሞገድ የጠለቀ፣ ከሕይወት ምሥጢር የረቀቀ እንደሆነ በማሰብ ጥቂት የማይባሉ ወገኖች በውስጣቸው ያለው ደም ተንጠፍጥፎ ያለቀ ያህል ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ይመላለሳሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ ሕመምን ያስከተሉ ነገሮች ያላቸው መልካም ጎን ቢታወቅ ኖሮ ሐሴትን ይፈጥሩ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር መልካምና መጥፎ ጎን ሲኖረው ቁም ነገሩ ያለው ግን ነገሮችን በመልካም ጎናቸው መጠቀሙ ላይ ነው፡፡ የአንድ ነገር ገጽታ እንደ ተመለከትንበት አቅጣጫ ይወሰናል፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በሚዛናዊነት እንመልከታቸው፡፡
     ኑሮ ሚዛናዊ ነዋሪ፣ ሥልጣን ሚዛናዊ መሪ፣ ትዳር ሚዛናዊ አጋር ፣ ልጆች ሚዛናዊ ወላጅ፣ አገልግሎት ሚዛናዊ የሆነ አገልጋይ ይፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ተስፋው የመነመነ፣ ልቡ ጥላቻን ያረገዘ፣ ጭፍን ተመልካች፣ ግድ የለሽ ትውልድ እናተርፋለን፡፡
ኑሮ የማይታኘክ መራራ የሆነባቸውን ለማጽናናት፣ የደፈረሰውን  ሕይወት ለማጥራት፣  በፍቅር እርዛት የተራቆቱትን ለመርዳት፣ በደስታ ጥም በረሃ ውስጥ ያሉትን ለማርካት፣ ያዘመመውንም ተስፋ ለማቅናት ይህ የአገልግሎት መስመር የተወሰነ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ከሚል እሳቤ በመነሣት  የተዘጋጀ ነው፡፡
ስለዚህ የደስታ ጥሙን ለማርካት፣ ከሐዘን ሸለቆ ለመውጣት፣ ከጭንቀት ሕይወት ለመፈታት፣ ከዝለቱም ለመበርታት ጥቂት የመፍትሔ ጠብታዎችን የሚጠብቅ በሚመስል የኑሮ በረሃ ውስጥ እንደተተዋችሁ  ለሚሰማችሁ ሁሉ ምላሽ ብትሹ ሳታመነቱ ጥያቄያችሁን ጻፉልን፡፡ ፍቅርን እንደ ፍቅርነቱ የሚረዳ ልብ ላላችሁ ሁሉ ይህ ብሎግ ቤታችሁ ነው!

4 comments:

  1. እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡ ሚዛናዊ እንድሆን ጽሑፍህ ረድቶኛል፡፡

    ReplyDelete
  2. በጣም ጥሩ እይታ ነው፡፡ ሚዛናዊነት የቤተክርስቲያን መገለጫ መሆን ነበረበት ነገር ግን ምን ያደርጋል በየፍርድ ቤቱ ያጨናነቀው የእኛ ጉዳይ መሆኑ በጣም ያሳፍራል፡፡ ልብ ይስጠና!

    ReplyDelete
  3. SELAM YEZIH BLOG AZGAJOCH FIRST GETA YEBARKACHHU
    BETAM BETAM DES YELAL BERTU BIZU MAWEK YALEBN NEGEROCH ALU.LENAM MIZANAWINET YEHIWOT KEMEM
    MOHONUN ASAWKACHHUGNAL GETA YERDACHEHU.FETENA BINOREM BERTU.

    ReplyDelete
  4. የአንድን ነገር ሙሉ ገጽታ የምናገኘው ከሁሉም አቅጣጫ (በሚዛናዊነት) ስንመለከተው ነው።...
    ተፈጥሮአችን ራሱ ሚዛናዊ እንድንሆን ያስተምረናል። ሁላችንም በተቃራኒ አቅጣጫ የተቀመጡ ሁለት ጆሮዎች አሉን። አእምሮአችን (ሕሊና) እና አንደበታችን (አፍ) ግን አንድ ነው። ስለአንድ ጉዳይ ተቃራኒ የሆኑ ብዙ ነገሮችን ልንሰማ እንችላለን።
    ስለአንድ ነገር በአንደበታችን ከመናገራችን በፊት ነገሮችን በማስተዋል አመዛዝነን ከግራ ከቀኝ መርምረን ቢሆን አድማጭን ከሚያቆስል ንግግር እንጠበቃለን፡ ራሳችንንም ከፍርድ እንጠብቃለን።

    ReplyDelete