Thursday, December 1, 2011

የተወደደ መስዋዕት


ከንጹሕ ልብ በላይ ይበልጥ የሚያከብር ነገር የለም፡፡ የዚህ ልብ አስደሳቹ ተግባር ደግሞ አመስጋኝነት ነው፡፡ ምስጋናችንን በገለጥንበት በእያንዳንዱ ጊዜ ስብእናችንን ይበልጥ እናጠነክረዋለን፡፡
እውነተኛ ታታሪዎችና የሚከበሩ ሰዎች ሁልጊዜም መልካምን ነገር መናገር የተናገሩትንም ከፊሉን እንኳን በተግባር መቀየር ልምድ ያደረጉ እንደሆኑ ልብ ብለነው እናውቅ ይሆን? አለዚያ ሊሠሩ አይችሉም፡፡ ይህም በእግዚአብሔርና በወዳጆቻቸው ዘንድ ያላቸውን ስፍራ ዋጋ የሚወስን ይሆናል፡፡ ሌሎች ለእኛ የሚያደርጉትን መልካም ነገር መመልከትና ተመሳሳዩን ማድረግ ፤ ደስታን የሚፈጥሩ፣ ሰላምን የተሞሉ፣ ማስተዋልን የተላበሱ ከአመስጋኝ ልብ የሚወጡ ቃላቶችን መናገር የዘወትር መርህ ማድረግ ለሙሉ ሕይወት ዕረፍት፣ በወጀብና በአውሎ ለሚያልፉ ብርታት፣ ዙፋኑ እምነት ለሆነ ልብ ጽናት ነው፡፡
        ልባችንን ለሌሎች በመክፈታችን የሚመጣብን ስቃይ እንኳን ቢኖር ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ ሕይወት ብዙ የተደበቁ ሀዘኖች (ውጣ ውረድ) እንዳሉባትም ማስተዋል ግድ ይለናል፡፡ በእያንዳንዱ ጽጌሬዳ ውስጥ ብዙ እሾሆችን አስከብባለችና በእንክርዳዱ ሳይሆን በስንዴው ደስ መሰኘት አለብን፡፡ በየዕለቱ ለምን ያህል ጊዜ ስጣዊና ውጫው ሕይወታችን በሌሎች ሰዎች ጥረት ኑሮና ሥራ ላይ የተመሰረተ መሆኑንስ እናስተውላለን? ይህንን ማሰብ እኛ እንደተቀበልነውና እየተቀበልንም እንዳለነው ልክ ለመስጠት ከበረታንም አብልጠን ለመለገስ ራሳችንን ተግባር ላይ ልናውል እንደሚገባን መረዳት ያስችለናል፡፡
        የወርቃማው ሕግ ተግባራዊነት በዚህ ውስጥ ነውና ሌሎች ሊያደርጉልን የምንወደውን እኛ ደግሞ ለሌሎች ልናደርግላቸው ሕያው አግባብ ነው፡፡ ለሌሎች ያለን እውነተኛ አሳቢነት ራሳችንን ማራኪ ሆነን እንድናገኘው የነፍሳችንም መዓዛ የጥላቻን ጠረን እንዲያሸንፈው ይረዳናል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት፣ እውነትን ምንጩ ያደረገ መልካምነት፣ መጥላት አማራጩ ያይደለ ወዳጅነት፣ ለሌሎች ፍላጎትና ችግር የርኅራኄ ስሜት ማሳየት፣ የራስን ድካም ያለማቋረጥ አለመውቀስና ይቅር ባይነት ከሁሉም በላይ በሁሉ አመስጋኝነት እነዚህ ብርታትና ቆራጥነትን የሚጠይቁ ጥሩ ልምዶች ናቸው፡፡ መልካም ልምዶች ደግሞ ቋሚ የሆነ ጥንቃቄና መሰጠትን ይሻሉ፡፡ ስንጠነቀቅላቸው ደግሞ ብርሃን ታግሎ ሊጥለው በማይቻለውና በጣም በሚያምር መልኩ ያንጸባርቃሉ፡፡
        ለሁሉም ነገር ባይሆንም በሁሉም ነገር ግን አመስጋኝ መሆን እንችላለን፡፡ አመስጋኝ ልንሆን የማንችልባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ግን ጠለቅ ብለን ብንመረምር አመስጋኝ ለመሆን ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች በሁሉም አጋጣሚዎች ውስጥ ልናይ እንችላለን፡፡ ንጋት ስለሚያመጣው ብርቅ ብርሃን፣ በጨረቃና በከዋክብት ደምቆ ስለሚያልፈው ሌሊት፣ ምድርን ስለሚያረሰርሰው የበረከት ዝናም፣ ያለመዛነፍ ስለሚያገለግሉን ወቅቶች፣ ለእኛና ለሌሎች ስለሆኑ ብዙ ነገሮች አመስጋኝ መሆን ይጠበቅብናል፡፡
(ይቀጥላል)

1 comment:

  1. BETAM LEB YENEKAL EGZIABHER TSEGAWN YABZALACHEHU

    ReplyDelete