Thursday, December 22, 2011

የወዳጅ ሰንሰለት (ካለፈው የቀጠለ)


     ማስተዋል የጎደለው ሰው ተናግሮት የነበረው ላይ ሲያተኩር፤ አስተዋይ ሰው ግን በሚናገረ ነገር ላይ ያነጣጥራል፡፡ ሰፊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ደግሞ ይቅርታው ላይ ያተኩራል፡፡ መሠረታዊውን ሕግ አስታውስ የወዳጅነት ስሜት ከአንተ ወደ ሌሎች እስካልሄደ ድረስ ወደ አንተ ሊመጣ አይችልም፡፡ በአንተ በኩል ያለን ስህተት ለማስተካከል አሳዛኙን ሁኔታ የፈጠሩትን ምክንያቶች መርምር፡፡ ይህም መንገድ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ተመሳሳይ ግጭቶችን ለመቀነስ ይረዳሃል፡፡ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ልብና አእምሮህን ከፍርሃት፣ ከጥላቻ፣ ከጸጸት፣ ከቅሬታና ከጥፋተኝነት ስሜቶች ነፃ አድርገው፡፡ አሉታዊ አመለካከቶች እንደገና እየተነሡ እንዳይረብሹህ ጤናማና አዎንታዊ በሆኑ አስተሳሰቦች ሕይወትህን ሙላ፡፡
 ይቅር ባይነት፡-

ወዳጅነትን የሚያጸና ነው፡፡
ብዙ ጊዜም የክብር ዕዳ ነው፡፡
መቼም ቢሆን ግን የደካማነት ምልክት አይደለም፡፡
የጥላቻ ማርከሻ ነው፡፡
ከክብር በስተቀር ሌላ ምንም አያስከፍልም፡፡
ምን ጊዜም ከሚጎዳው ይልቅ የሚያተርፈው ይበልጣል፡፡
በእያንዳንዱ ቤትና ሕይወት ሊኖር የሚገባው ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡

ሁሉንም ነገር መልካምነትን በተላበሰ መንፈስ በጨዋ ለዛ አድርገው፡፡ ምንም እንኳን መብቶችህን ብትገድባቸውም ይቅርታ ማድረግ የምንለው ግን በመልካምነት ሰዎችን ለመንከባከብ ፈቃደኛ መሆንንም ጭምር ነው፡፡
ሰዎችን ይቅር ስንል ሥራቸውን እያበረታታን አልያም የሠሩትን ነገር ሁሉ ትክክል ነው እያልን አይደለም፡፡ ነገር ግን ለአብሮነታችን ዋጋ፣  ለይቅርታ ተቀባዩ እድል፤  ለራሳችንም ፍፁም ደስታን እየሰጠን ነው፡፡ ስለዚህ በሕይወት ውስጥ ካለው ተጽእኖ የተነሣ ይቅር ባይነት የበለጠ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡ አንተም አሁኑኑ ይቅር በልና አሁኑኑ ውጤቱን ከሥራው ታያለህ! ነገ የእኛ አይደለም፡፡ ትላንትም እንዲሁ፡፡ የዛሬ በረከቶች ወይም ስጦታዎች ብቻ በቁጥጥራችን ሥር ናቸው፡፡ የአሁኗን ቅጽበት በሚገባ መኖር ሕይወትን አጣጥሞ የመኖር ምሥጢር ነው፡፡ ትላንት የዛሬ ትውስታ ሲሆን  ነገ ደግሞ የዛሬ ሕልም ነው፡፡ ዛሬን በይቅርታ ኑር፡፡ አስቸጋሪው ነገር ይቅር ለማለት ምክንያት እያለን ይቅር ማለቱ ሳይሆን ያለምንም ምክንያት ይቅርታ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ የይቅርባይነት ትልቁ ዋጋ ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ 
ሌሎች ሲያወግዙ ይቅር ማለት
በሚነፍጉበት ጊዜ መስጠት
በሚያማርሩበት ጊዜ መደሰት
ሲያልሙ መሥራት
ሲያቆሙ መጽናት
በተጠራጠሩበት ጊዜ ማመን
ሲነቅፉ ማመስገን
በሚያፈርሱበት ጊዜ ማነጽ
ሲያመነቱ ኃላፊነትን መውሰድ
በሚፈልጉበት ጊዜ ማገልገል፡፡ 
በእርግጥ ይከብዳል ግን ደግሞ ዋጋው እጅግ የበዛ ነው፡፡ የባልንጀራችንን ጥቃቅን ስህተት ይቅር ማለት ካልቻልን እንዴት በጓደኛችን ታላላቅ የሆኑ መልካም ነገሮች መደሰት እንችላለን።

3 comments:

  1. ማስተዋል የጎደለው ሰው ተናግሮት የነበረው ላይ ሲያተኩር፤ አስተዋይ ሰው ግን በሚናገረ ነገር ላይ ያነጣጥራል፡፡ ሰፊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ደግሞ ይቅርታው ላይ ያተኩራል፡፡ I like it.

    ReplyDelete
  2. yekirta yeand christian mgelachaw new beykrta yalew
    destan selasnebebken geta yebarkh

    ReplyDelete
  3. ሙሉዓለም ከዋሽንግተን ዲሲDecember 23, 2011 at 2:21 PM

    ሌሎች ሲያወግዙ ይቅር ማለት በሚያፈርሱበት ጊዜ ማነጽ በሚፈልጉበት ጊዜ ማገልገል፡፡ All are precious words.May God bless you.

    ReplyDelete