አርብ ታኅሣሥ 15 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
(መልእክት ወደ ፊልሞና)
‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)››!
መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ከመክፈታችሁ፤ እንዲሁም የመልእክቱን ክፍል
ከመግለጣችሁ አስቀድሞ አብ፤ ወልድ፤ መንፈስ ቅዱስ፤ አንድ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ማስተዋልን እንዲሰጣችሁ፤ እንዲሁም ከመልእክቱ
ልትረዱ የሚገባችሁን ሁሉ መቀበል እንድትችሉ በቅዱስ መንፈሱ በኩል እንዲረዳችሁ በመንፈስና በእውነት በመገዛት ጸልዩ፡፡ ተወዳጆች
ሆይ፤ ከዚህ በኋላ መልእክቱን ቃል በቃል በጥንቃቄና በእርጋታ አንብቡት፤ ይህንንም በመደጋገም አድርጉት፡፡
የመልእክቱ ዳሰሳ፡-
o
‹‹ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው . . ›› /ቁ. 15/ የመልእክቱ ዋና አሳብ ሲሆን፤ ለመልእክቱ
‹‹የዘላለም መያያዝ›› ብለን ርእስ ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ሐዋርያው ለፊልሞና ‹‹እንደ ባልንጀራ ብትቆጥረኝ እንደ እኔ አድርገህ
ተቀበለው›› /ቁ. 17/ በማለት ይጠይቃል፡፡
o
መልእክቱ ከሐዋርያው ከጳውሎስ መልእክታት በጣም አጭሩ መልእክት ሲሆን፤ ሐዋርያው በእስር ቤት ሆኖ
ከጻፋቸው ከፊልጵስዩስ፤ ከቆላስይስ እና ከኤፌሶን መልእክታት መካከል አንዱ ሲሆን፤ ይዘቱ ግን የተለየ ነው፡፡
o
ሐዋርያው ከጻፋቸው መልእክታት መካከል ለሦስት ሰዎች (ግለሰቦች) የጻፋቸው አራት መልእክታት ተጠቃሽ
ናቸው፡፡ እነዚህም፡- አንደኛ ጢሞቴዎስ፤ ሁለተኛ ጢሞቴዎስ፤ ቲቶ እና አሁን እያጠናነው ያለነው የፊልሞና መልእክት ናቸው፡፡ መልእክቱን
ወደራሳችሁ አቅርባችሁ፤ ለእናንተ እንደተላከ በመቁጠር ብታነቡት በእጅጉ ትጠቀማላችሁ፡፡
o
በመልእክቱ አሳብ ውስጥ ቁልፍ የሆኑ (ትኩረት የሚሰጣቸው) ቃላትን እናገኛለን፡፡ እነዚህም፡- ክብር፤
ቸርነት፤ ጥንቃቄ፤ ወዳጅ፤ ፍቅር፤ ትህትና፤ ጥበብ፤ ግልጽ የሆነ ንጽህና (ቅድስና)፤ ከዚህ በመነሣት የመልእክቱን ይዘት ‹‹ትህትናን
የተላበሰ መልእክት›› እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ በዚህ መልእክት ውስጥ ችግር ፈቺ የሆነውን ክርስትና ለመመልከት
ሞክሩ፡፡
o
መልእክቱ ባለ ሀብት የነበረው የቆላስይስ ክርስቲያን እና የሐዋርያው የጳውሎስ ቅርብ ወዳጅ የፊልሞና
ባሪያ አናሲሞስ (ጠቃሚ፤ ዋጋ ያለው ማለት ነው) ከጌታው ወደ ሮም ኮብልሎ መጥፋቱ፤ በኋላም በክርስቶስ ክርስቲያን ሆኖ ወደ አሳዳሪው
መመለሱን ማእከል ያደረገ ‹‹የእርቅ›› ደብዳቤ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ጥሩ የማይባለውን አጋጣሚ ጌታ አንድን ነፍስ ወደ ክብር
ለማምጣት እንዴት ለበጎ እንደ ተጠቀመበት አስተውሉ፡፡
o
መልእክቱ የ‹‹እርስ በርስ መዋደድን›› /ዮሐ. 13፡34/ አዲስ ትእዛዝ መሰረት ያደረገው የክርስትና
ኑሮ የፍቅር ገጽታ ምን እንደሚመስል በተግባር የሚያስረዳ ሲሆን፤ በዓለም ላይ የሰዎች ባርነት (ስቃይን ጭምር የተሞላ) ተስፋፍቶ
በነበረበት የሐዋርያት ዘመን ባሪያን አስመልክቶ የተጻፈ ብቸኛው መልእክት ነው፡፡ በዚህም ክርስትና የባርነትን ችግር ለመፍታት ያለውን
የላቀ መንገድ የሚያሳይ ጽሑፍ ሆኖ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
o
ሐዋርያው በቆላስይስ መልእክቱ ላይ ‹‹ከእናንተ ከሆነውና ከታመነው ከተወደደውም ወንድም ከአናሲሞስ
. . ›› /ቆላ. 4፡9/ ብሎ እንደጻፈው፤ ፊልሞና በቆላስይስ የሚኖር ባሪያ አሳዳሪና ቤተክርስቲያኒቱም (የምእመናን ስብስብ)
በቤቱ የነበረች እንደሆነ፤ እንዲሁም የፊልሞና መልእክት እና የቆላስይስ መልእክት በተመሳሳይ ጊዜ የተጻፉና የተላኩ መሆኑን እንረዳለን፡፡
በዚህ ክፍል መሰረት መልእክቱ የተላከው ‹‹በአናሲሞስና በቲኪቆስ›› እጅ ነው፡፡